በተለያዩ ጊዜያት አገርን ችግር ውስጥ በማስገባት እንድትፈራርስ የሚጥሩ ሀይሎች ይነሳሉ። በእነዚህ ወቅቶች ደግሞ ህዝብ በአንድነትና በትብብር መንፈስ መቆሙ እንደ ብረት መጠንከሩና እንደ አንድ ማሰቡ የመጣውን ሁሉ እንደ አመጣጡ ለመመከት መዘጋጃ መንገዱ ነው።
እራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ያለው አሸባሪው ህወሓት በአሁኑ ወቅት በተለይም ከየጦር ግንባሩ የሚመጡ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ከህጻናት እስከ አዛውንት አባትና እናቶች፣ ከመነኩሴ እስከ ሼህ በግዳጅ ቢያሰልፍም ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት ደረጃ እየተቀጠቀጠ መሆኑን ነው። ይህም ቢሆን ግን አሸባሪው ህወሓት አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ገብቷል። ለዚህ የሞት ሽረት ትግሉ ማሳመሪያ ወይንም ደግሞ ማጣፈጫ ንጹሀንን እያስፈጀ በለመደው መንገድ ድራማ እየሰራ የውጭውን ዓለም እያደናገረ ይገኛል፡፡ በዚህም መንግስትና ህዝብ አጣብቅኝ ውስጥ እንዲገቡ በዚህ ግርግር ደግሞ እርሱ ወደሚናፍቀውና ወደኖረበት የበዝባዥ አገዛዙ ለመመለስ ከፍተኛ የሆነ ስራን እየሰራ መሆኑን ልብ ይሏል።
የጥቅም አጋሮቹ ምዕራባውያንም የእሱን እኩይ ተግባር ብሎም ወንጀል አይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ ከማለፋቸውም በላይ ንጹሀንን ልታደግ ተኩስን አቁሜ ህዝቡን ከርሃብ߹ ከችግር߹ ከስደት ላድን ባለው የፌደራል መንግስት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ላይ ናቸው።
ምዕራባውያኑና አንዳንድ ተቋሞቻቸው ምንም እንኳን በስውር የሳተላይት መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ቢያደርጉም የህወሓት ሃይል በአስደንጋጭ ሁኔታ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ ሆኖ አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ይገኛል። ጁንታው “የአይጥን ያህል ቁመና ይዞ እንደዝሆን ቢንጠራራም” ቅሉ አሁን ላይ ግን ምዕራባውያን ከእርሱ የሚጠብቁት ነገር የሚኖር አይመስልም።
ነገር ግን እነዚህ ጥቅመኛ ጀሌዎቹ በተለይም ባለፉት ጊዜያት የእነሱን ሀሳብ አላስፈጽም ባሉ እንደ የመንና ሶሪያ ባሉ መሪዎችና ህዝቦች ላይ ጡንቻቸውን በማበርታት አፈራርሰዋቸዋል፡፡ ህዝቡንም ለችግርና ለመከራ ዳርገው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ዕጣ እንዲገጥማት የተለያዩ ሴራዎችን እየሸረቡ ነው፡፡ ለዚህ አካሄዳቸው ይጠቅማቸው ዘንድም የውሸት ታሪክ አዘጋጅተው በሌላ ዙር፣ በሌላ መንገድ ለማንበርከክ እየሞከሩ ያሉም ይመስላል ።
ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ደግሞ አሁን ላይ በሱዳን በኩል የመተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፈት ማድረግ አልያም የሚመጣውን ብርቱ ማዕቀብ መቀበልን ለኢትዮጵያ መንግስት እንደ ምርጫ አድርገውም አቅርበዋል።
ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ የተዘጋጀ ወጥመድ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማሸማቀቅ የሚደረግ ሴራ ደግሞ ሁለት መልክ አለው፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” እንደሚባለው ለውሸት ፕሮፖጋንዳቸው ማድመቂያ ከሚያደርጉት ዝግጅት መካከል የጀኖሳይድ ድራማ በተከዜ ወንዝ ላይ መስራት አንዱ ሆኗል። ለዚህም እንዲጠቅማቸውም ከየአውደ ውጊያ የተሰበሰቡትን አስክሬኖች ስክሪፕት ተጽፎላቸው ትወናው ከሚደረግበት ተከዜ ወንዝ እየተወሰዱ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ድራማ ደግሞ በቀጥታ የሚተላለፈው የጥቅም አጋሮች በነበሩትና በሆኑ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃኖች ነው። እነዚህ ከሙያ ስነ ምግባር እንዲሁም ከሰብዓዊነት ውጪ የሆኑ ሆድ አደር ሚዲያዎችም ይህንን ድራማ የገጻቸው ፊት፣ የዜናቸው መግቢያ እንዲያደርጉት የቤት ስራ ተሰጥቷቸው እሱን ለማሳካት ከወዲሁ ጩኸቱን እያቀለጡት ነው።
ምዕራባውያኑ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ካራ ይዘው እንደሚመጡ ቀድሞውኑ እያሳወቁ ነው። በግልጽ እንደተናገሩትም ዓላማቸው የትኛውንም በር ማስከፈት፣ ቀጥሎም መንግስትን ከህወሓት ጋር ድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ትልቅ አደጋ ያላቸው ናቸው።
በቅርቡ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን “የምዕራብያውያኑ ጥያቄ ተንኮል ያለው ወጥመድ ነው። ከዚያም ያለፈ ነው። ሀገር የሚያፈርስ መርዝ የተለወሰበት ጥያቄ ነው” ብለውም ነበር።
እንግዲህ አሁን ላይ ምርጫው በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እጅ ውስጥ ይገኛል። ስለነገው ትውልድ፣ ስለመጪው የኢትዮጵያ ህልውና፣ ክብርና አንድነቷን የተረጋገጠች ሀገር የምንሻ ከሆነ ባለሁለት ስለቱን ካራ ወደ ጎን ገፍተን በቆራጥነት ኢትዮጵያን ማዳን አለብን።
ከዚህ ውጪ ያለው ምርጫ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ እንድትፋቅ ለተዶለተው ሴራ እጅ ሰጥቶ፣ ሀገር አልባ ሆኖ በመቅረት እድሜ ዘመንን በባርነት አንገትን ሰብሮ፣ ከሰው በታች ሆኖ መኖር ብቻ ነው። በእርግጥ ሁለቱም ምርጫዎች ዋጋ ያስከፍላሉ። አንደኛው ጊዜያዊ የሆነ፣ ሆዳችንን አስረን፣ ቀበቶአችንን ጠበቅ ካደረግን የምንሻገረው አደጋ ሲሆን፤ ሁለተኛው ግን ዘላለማዊ የሆነ፣ ሀገር አልባ የሚያደርገን፣ ልጆቻችን ሀገር ብለው የሚኖሩባት ምድር የሚያሳጣችው፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያን የሚያፈራርስ ነው። ምርጫው አሁንም በእጃችን ነው።
ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አንዳንድ ብርቱ አገራት ህዝቦች ከብረት ለበስ ታንክ ፊት ተኝተን߹ ድንጋይ ፈልጠን ጥረን ግረን የአገራችንን ኢኮኖሚ እንታደጋለን ߹እጅ ለእጅ ተያይዘን ችግርንም ረሀብን ችለን ሀገርን ከመፈራረስ በመጠበቅ ሀገራችንን ከምዕራባውያን ሴራ እንታደጋለን ፤ ወይስ እንደ ሶሪያ߹ የመን߹ ኢራቅና ሊቢያ ህዝቦች ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመንደር ሸማቂዎችን አምነን አገራችንን እናፈርሳለን? መልሱ ያለው ከኛው ጋር ነው። ሀገራችንን ከነ ሙሉ ክብሯ ጠብቀን የጠላቶቻንን ህልም አቀጭጨን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከኛ ከልጆቿ የሚጠበቅ ግዴታ ነው!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድም ያሉት ይህንኑ ነው “የውጭ ሃይሎች እንድትረዱት የምፈልገው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም ! ደሃ ነን፤ ከድህነት ፈጥነን ለመውጣት ሰላም፣ ትብብር፣ ድጋፍ ያስፈልገናል። ፈጥነን ከድህነት ለመውጣት ግን ክብራችንን መሸጥ አይጠበቅብንም”።
በእምነት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013