ኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ትናንት በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ሰባኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን “እኔ የመምህራን ውጤት ነኝ” በሚል መልዕክት አክብሯል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን ከተቋቋሙት ልዩልዩ ማህበራት አንጋፋው የሆነው ይህ ማሕበር በሀገራችን የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ግለጸዋል፡፡
ዶክተር ጥላዬ ባሳለፍናቸው ሃያ አራት ዓመታት ውስጥ የተማሪዎች ተሳትፎ ከሁለት ሚሊዮን ወደ ሃያ ስምንት ሚሊዮን መድረሱን አስታውሰው ለዚህ ስኬት የበቃነውም መምህራን በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማያያዝም መምህራን የትኛውም የአየር ንብረትና መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ሳይበግራቸው በሴቶችና በወንዶች ፣ በከተማና በገጠር ፣ በአርብቶ አደሩና በአርሶ አደሩ መካከል ትምህርት ፍትሀዊነቱን ጠብቆ እንዲስፋፋና የተማሩ ዜጎችን ለማፍራት መምህራን የተጫወቱት ሚና በሀገሪቱ የልማት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
መምህራን
ከማስተማር ሙያቸው ባሻገር በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በአመራርነት በመሥራትም አሁን ለደረስንበት ለውጥ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸውና
በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችም ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆናቸውን በመጥቀስ መምህራን ሁሉንም መሆን እንደሚችሉና የመምህርነት ሙያ ልዩ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ
አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ
መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ዮሀንስ በንቲ በበኩላቸው በመርሀ ግብሩ ላይ የማህበሩ የሰባ ዓመት ጉዞ ያስገኛቸውን ፍሬዎችና
በአንጻሩም የገጠሙትን ውጣ ውረዶች አንስተዋል፡፡
ማሕበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ በየሥርዓተ መንግስቱ የገጠሙትን ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ተቋቁሞ የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ካደረገው ትግል በተጨማሪ በትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ያደረገውን ጥረትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የዓለም አቀፍ መምህራን ማህበር አባል በመሆን ምሥራቅ አፍካን በመወከል በአህጉር ደረጃ የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆኖ እሠራ እናዳለ ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ከሁሉም ከልሎችና ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የማህበሩ አመራሮችና በሙያቸው ከሰላሳ አምስት እስከ አርባ ስድስት ዓመት ያገለገሉ አንጋፋና ሞዴል መምህራን ተገኝተው የምስክርና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የካቲት 14 ቀን 1941 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሰላሳ ሁለት የአንደኛ ደረጃ መምህራን ‹‹ የመምህራን ህብረት›› መበሚል ሥያሜ የተመሰረተው ማህበር በ1957 ዓ.ም ስሙን የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ወደ ሚል 508 ሺህ 502 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡
በቅርቡም የመምህራንን ማህበር ወደ ተሟላ ሰራተኛ ማሕበር ለመለወጥ የሚያስችሉ ጥናቶች መጠናታቸው ተገልጧል፡፡ በዓሉ በፌዴራልና በክልል ደረጃ በሚኖሩ የተለያዩ መርሀ ግብሮች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ. ም ድረስ ይከበራል ተብሏል፡፡
በእያሱ መሰለ