በየትኛውም የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ውድድሮች በውጤታማነታቸው ተጠባቂ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ አገራት እየተገባደደ በሚገኘው የቶኪዮ ኦሊምፒክ እንደወትሮው ድምቀታቸውን ማየት አልተቻለም። በመም ውድድሮች ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሰንጠረዡ የቀዳሚዎቹ ስፍራ ላይ የሚቀመጡት ኢትዮጵያና ኬንያ ቶኪዮ ላይ የለመዱትን በርካታ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም። ከዓለም 38ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ የሆነችው ኬንያ 1የወርቅ 2የብር እና 2የነሃስ በጥቅሉ አምስት ሜዳሊያዎችን ነው ያስመዘገበችው። ከአፍሪካ ሁለተኛዋ በርካታ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፤ ኢትዮጵያ በ3 ሜዳሊያዎች በ1ወርቅ 1 ብር እና 1ነሃስ ከዓለም 46ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። ዩጋንዳም በተመሳሳይ የሜዳሊያ ቁጥር ከኢትዮጵያ በእኩል ደረጃ ላይ የተቀመጠች አገር ሆናለች።
በሩጫው ዓለም ልዩነት ፈጣሪ የሆኑት እነዚህ አገራት ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄዱት ውድድሮች እንደተለመደው ሜዳሊያ የመሰብሰብ እድላቸው የሰፋ እንደሚሆን ይታመናል። ዛሬ አንድ የጎዳና እንዲሁም ሁለት የመም ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ሃገራቱ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ይጠብቃል። ረፋድ ላይ 20 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር ሲካሄድ፤ የኢትዮጵያ ብቸኛዋ ተወካይ የኋልዬ በለጠ በውድድሩ ላይ ትካፈላለች። ከሰዓት በኋላ ደግሞ በታሪክ የምስራቅ አፍሪካውያኑ አትሌቶች ውጤታማ በመሆን የሚጠበቁበት የ5ሺ ሜትር የወንዶች ውድድር ይደረጋል።
በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ ከሞስኮ እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ 3የወርቅ፣ 2የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን ማግኘቷ የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ በቶኪዮ የማጣሪያ ውድድር ሶስት አትሌቶች ቢካፈሉም ለፍጻሜው የበቃው አንድ አትሌት ብቻ መሆኑ ለሜዳሊያ የሚደረገውን ፉክክር ያጠበበው ሆኗል ። የተሻለ ሰዓት በማስመዝገብ በዛሬው ውድድር ላይ የሚካፈለው አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ ለአገሩ ተጨማሪ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ የሚሮጥ ይሆናል። ቀጥሎ በሚካሄደው የዛሬው የሴቶች 1ሺ500 ሜትርም ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ የምትወዳደር ይሆናል።
ነገም አረንጓዴ ጎርፎቹ የሚጠበቁባቸው ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን፤ በተለይ የወርቅ ሜዳሊያ ሊመዘገብበት እንደሚችል የሚታመነው 10ሺ ሜትር የሴቶች ሩጫ ከፍተኛውን ግምት አግኝቷል። በዚህ ውድድር በተለይ የዓለም ቁጥር አንድ የሆኑ አትሌቶች ክብራቸውን ለማስቀጠል የሚፎካከሩበት በመሆኑ አጓጊ አድርጎታል። በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ እና ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሃሰን ከፍተኛ የአሸናፊነት ትንቅንቅ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሳይደፈር የቆየውን የ10ሺ ሜትር ክብረወሰንን በሪዮ ኦሊምፒክ የሰበረችው የርቀቱ ንግስት ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና እንዲሁም ሌላኛዋ የኬንያ አትሌት ቪቪያን ቺሪዮት አለመኖራቸው ደግሞ ሁለቱ አትሌቶች በተለይ እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ በድጋሚ የተሻሻለው የርቀቱ ክብረወሰን የተመዘገበው በሁለቱ አትሌቶች ሲሆን የሁለት ቀናት ልዩነት ያለው መሆኑ ደግሞ የአትሌቶቹ ብቃት ምንያህል ተመጣጣኝና ተቀራራቢ እንደሆነ ያሳያል። የስፖርታዊ ውድድሮች ንጉስ በሆነው በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክም ማን የተሻለ አትሌት እንደሆነ ለማረጋገጥ እንደተዘጋጁም የዓለም አትሌቲክስ ቅድመ ግምት ይጠቁማል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን እኤአ በ2019 በተካሄደው የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ሻምፒዮን መሆን ችላለች። በሻምፒዮናው በ10ሺ ሜትር ተከትላት የገባቸው ለተሰንበት ደግሞ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። ሲፈን ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ በረጅሙ የመም ላይ ሩጫ 10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን ለመጨበጥ በቅታለች።
ይሁን እንጂ ክብረወሰኑ በእጇ ገብቶ 48 ሰዓት ሳይሞላው በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት እጅ ገብቷል። አይናፋሯ ጀግና አትሌት ለተሰንበት በአገሯ ልጅ ተይዞ የነበረውን ሰዓት በድጋሚ ወደአገሩ ከመመለሷም ባለፈ በ5ሺ ሜትርም የዓለም ክብረወሰንን በማሻሻል የወቅቱ ቁጥር አንድ አትሌት መሆኗን አሳይታለች። ሲፈን በአልማዝ ተይዞ የነበረውን 29:17.45 የሆነ ሰዓት በአገሯ በተካሄደ ውድድር 10 ሰከንዶችን በማሻሻል በ29:06.82 ነበር የፈጸመችው። ነገር ግን ደስታዋን በቅጡ ሳታጣጥም የ23 አመቷ ለተሰንበት በ5ሰከንዶች የፈጠነ 29:01.03 ሰዓት በማስመዝገብ የበላይነቱን የግሏ ማድረግ ችላለች። አትሌቷ የመጨረሻውን ዙር በ63 ሰከንዶች መሸፈኗ ደግሞ ያለችበትን የብቃት ጥግ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ተሳትፎ በምታደርግበት በዚህ ውድድርም የራሷን ሰዓት ለማሻሻል አሊያም በአሸናፊነት አገሯ የለመደችውን ወርቅ ለማጥለቅ ተዘጋጅታለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013