በኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውስጥና በውጪ ከፍተኛ ጫናዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። በአገሪቱ ውስጥ ያለው ግጭት በመባባሱ ለውጭ ጫና መንገድ ከፍቷል። በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ ድርድር ኢትዮጵያ አቋሟን ባለመቀየሯ ከፍተኛ ለሆነ የውጪ ጫና እንደዳረጋት ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን አቋም ለውጪ አገራት ለማሳወቅ በርካታ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ናቸው። ከዚህም ውስጥ በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት የዲያስፖራ የሰላም ጓድ ጥምረት የሚሰራው ስራ ተጠቃሽ ነው። ስለ ጥምረቱ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ከጥምረቱ የፕሬስ ሴክሬታሪያት እየሩሳሌም ክብረት ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– አገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ይታወቃል። በአገሪቱ ላይ የሚታዩትን የውስጥና የውጪ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል በጥምረቱ የተሰሩ ሥራዎች ምን ምን ናቸው?
ወጣት እየሩሳሌም፡– በአሁን ወቅት ወጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ እራሱን እያነቃቃ ተነስቷል። በውጪ የሚገኙ ወጣቶች የቲዊተር ዘመቻ በስፋት እያካሄዱ ሲሆን የተለያዩ ድርጅቶች እገዛ እያደረጉ ናቸው። በዘመቻዎቹ የውጪ ጫናዎች እንዲቀንሱ ለማድረግ ያለመ ነው። በቲዊተር የሚለቀቁ መልዕክቶች የተጠኑ በመሆናቸው ለሚላክላቸው ድርጅቶች ትክክለኛውን በአገሪቱ የሚገኘውን ሁኔታ ያንፀባርቅ ነበር። በተጨማሪም በውጪ የሚገኙ ድርጅቶች ለሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ መልስ ይሰጥ ነበር። በማህበረሰቡ ውስጥ ስብሰባዎችን በማካሄድ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ገለፃ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡– በሚደረጉት ዘመቻዎች ምን ያህል ወጣቶች ተሳትፎ ያደርጋሉ?
ወጣት እየሩሳሌም፡– በሚደረጉ ዘመቻዎች ብዛት ያላቸው ወጣቶች ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው። በሌላ መልኩ ብንመለከተው በተለያዩ አካውንት ዘመቻውን የሚያደርጉ ወጣቶች አሉ።ሥራዎችን የሚያከናውኑበት አቅም ስላላቸው ዘመቻውን ለማሳደግ ቀላል ሆኖላቸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደዚህ አይነት ስራ ለማከናወን ጥምረቱ እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ምን አይነት ስራዎች ማከናወን ይቻላል የሚለውን ሁኔታ እየታሰበበት ነው። ማህበረሰቡም የራሱን ዘመቻ የሚያከናውንበትን አካውንት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማየት ተችሏል። ምክንያቱም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቲዊተር ላይ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ ነው። በዚህም ላይ ብዙ ጥናት ያከናወኑ ሰዎች ነበሩ።
ወጣቱ ቲዊተር እንዲጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የቲዊተር አካውንት እንዴት ነው የሚጠቀሙትና ቲውተር አካውንት እንዴት ከፍቶ መፃፍ ይቻላል። በምን አይነት መልኩ ነው ትኩረት መሳብ የሚቻለው እንዲሁም እንዴት ሰዎችን ታግ ማድረግ ይቻላል እና አስፈላጊ ለሆኑ ሰዎች ታግ እንዴት እንደሚደረግ ሥራዎች ተሰርተዋል። የዚህንም ውጤት ማየት እየተቻለ ነው። በአሁን ወቅት ሰው እንዴት መጠቀም እንዳለበትና አካውንት መክፈቱ ምን ላይ እንደነበር ማሳየት አስችሏል። የቲዊተር ዘመቻው ሲጀመር አብዛኛው ሰው ምንም ለውጥ ማምጣት አይችልም የሚል አመለካከት ነበራቸው።
ጥምረቱ እያከናወናቸውን ባሉ ሥራዎች ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ የዘመቻውን ጥቅም መረዳት ጀመሩ። የተቃውሞ መረጃ የሚያሰራጩ ዘመቻዎችን ለመፎካከር ጥምረቱ አባላትን ለማብዛትና የቲዊተር አካውንት ለማስከፈት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል። አሁን ህብረተሰቡ ሁኔታውን በመረዳቱ የሚሰጡ ትምህርቶችን በመከታተሉ አካውንት ከፍቶ ዘመቻውን ተቀላቅሏል። በቀጣይ ለህዳሴ ግድቡም በተመሳሳይ ዘመቻዎችን ለማከናወን እቅድ ተይዟል። በተለያዩ አህጉራት የሚኖሩ ወጣቶች በዘመቻው ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው። በዚህ ስራ ወጣቱ ከፍተኛ ተሳትፎ እያረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን እያደረገ ያለውን አገር የማፍረስ ተግባርና በህዳሴ ግድቡ ላይ የግብፅና የሱዳን ጫና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ዲያስፖራው ምን ስራ እያከናወነ ይገኛል?
ወጣት እየሩሳሌም፡– ስራዎችን ለመስራት መጀመሪያ አካባቢ ችግሮች ነበሩ። የመጀመሪያው ችግር የነበረው አንድ ግለሰብ ሲሳተፍ ምን ያክል ተፅዕኖ እፈጥራለሁ የሚለው ነገር ነው። ምክንያቱም የህወሓት ደጋፊዎች ቀድመው የሚያመጡትን ተፅዕኖ ቀድመው አውቀውት ነበር። ይህንን ነገር ለመቀልበስ ትንሽ ጊዜ ፈጅቷል። ትክክለኛውን እውነት ለማውጣት ጠንክሮ መስራትን ጠይቋል። በተቃራኒው እየተሰጠ የነበረውን ዘመቻ ለመቀልበስ ተመሳሳይ ስራዎችን መስራት አስፈልጎ ነበር። የተቀናጀ ስራ ለማከናወን ብዙ ጊዜ በመፍጀቱ የህወሓት ደጋፊዎች የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት በር ከፍቶላቸው ነበር።
የዘመቻው ስራ በተጀመረበት ወቅት የህወሓት ደጋፊዎች ብዙ ሰዎችን ማሳሳት የቻሉበት ወቅት ነበር። ስለዚህ የነበረውን ሁኔታ ለመቀልበስ ጊዜ ወስዷል። አሁን ግን በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየታዩ ናቸው። አሁን የወጣቶች ማህበር እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን ውጪ የሚገኙ ወጣቶችን አገር ውስጥ ካሉት ጋር በማቀናጀት ጠንካራ የሆነ ማህበር ለመመስረት ታስቧል። ይህን ደግሞ ወጣቱ በሚኖርበት አካባቢ እንዴት መረጃዎችን እንደሚለዋወጥና ለኢትዮጵያ ዘብ የሚቆምበት ሁኔታ ለማመቻቸት ታስቧል። ነገር ግን ሥራው እንደ ጅምር ጥሩ ቢሆንም ከዚህ በላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ትምህርት የተወሰደበት ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዝምታን የሚመርጥ በመሆኑና እውነታውን አውቆ ለሌሎች ማሳወቅ ላይ ደካማ ነው። ይህን አስተሳሰብ መቀየር በራሱ ጊዜ የሚፈልግ ነው። ወጣቱ የሚያውቀውን ነገር ለሌሎች እንዲያዳርስ ለማድረግ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው። ማንኛውም ሰው ዝምታን መምረጥ የለበትም፤ ያለውን እውቀት ለሌሎች መስጠት ይኖርበታል። ምክንያቱም እየታገልነው ያለው ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚታገለውን ነው። ይህን በመቃወም ከሕዝቡ ጎን እንቆማለን በማለት ከየትኛውም ብሔር የመጣ ቢሆንም ሁሉም አንድ ነው የሚለውን መልዕክትና እጅ ለእጅ በመያያዝ የአገሪቱን ሉዓላዊነት አሳልፈን አንሰጥም በሚለው መልዕክት ተጠናክሮ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ወጣቱን ለማንቀሳቀስ በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አሉ። ከድርጅቶቹ ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ሁኔታው ምን ይመስላል?
ወጣት እየሩሳሌም፡– እስካሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር ወጣቱ የመገናኘት እድል አግኝቷል። ከዚህ በፊት ኤጀንሲው ትልቅ ስብሰባ አዘጋጅቶ ነበር። በስብሰባውም ኤጀንሲው ወጣት ዲያስፖራዎችን ማግኘትና መርዳት እንደሚፈልጉ ተናግሯል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሰራት ያለበት ስራ አለ። ተቋማቱ ግን በማንኛውም ሁኔታ እንደሚደግፉ ይታወቃል። ከአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኘው ወጣት ጋር በምን አይነት መንገድ መሰራት እንዳለበት በሂደት የሚሰራ ነው። ወጣቱ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች እየሰሩ ነው። የአገራቱን የውሸት ዘመቻ ለመቀልበስ ምን መሰራት አለበት? በጥምረቱስ ምን ስራ ተከናውኗል?
ወጣት እየሩሳሌም፡- ወጣቱን ለማነቃቃት የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ ስራዎች ቀደም ብለው ይሰሩ ነበር። በግብፅና በሱዳን በኩል ያለውን የሚደግፉ ሰዎች ነበሩ። በተለይ የህወሓት ደጋፊዎች የግብፅና የሱዳንን አቋም ሲደግፉ ተስተውለዋል። አብዛኛዎቹ ሰዎች የተሳሳተ አካውንት በመክፈት ስለ ኢትዮጵያ የተሳሳተ መረጃ ሲሰጡ ነበር። አብዛኛዎቹ መረጃዎች ኢትዮጵያ ግብፅን ውሃ ልታስጠማ ነው እንዲሁም ሱዳንን በጎርፍ ልታጥለቀልቅ ነው የሚሉ ናቸው። ኢትዮጵያ በእርስበርስ ግጭት አንድን ብሔር ልታጠፋ ነው የሚሉም መረጃዎች በብዛት ይሰራጩ ነበር። ጥምረቱ በሰራው ሰፊ ስራ ብዙ ወጣቶች ወደ ዘመቻው በመቀላቀላቸው ውጤት እየመጣ ነው። ይህን ስራ በማስፋፋት በማህበራዊ ሚድያ ወጣቱን ማስተማር ይገባል። በተለይ ዲያስፖራ ወጣቶች ስለ አገራቸው ግንዛቤ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ምሁራን የማህበራዊ ሚድያ ትክክለኛ መረጃዎችን በመጠቀም ማስተማር ላይ እየተሰራ አይደለም።
በተወሰነ መልኩ በተሰራው ስራ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ጠንካራ ወጣቶችን ማፍራት ተችሏል። በአውሮፓ የሚገኙ ወጣቶች ስለ ኢትዮጵያ በአግባቡ መረጃ ይዘው የሚከራከሩ ወጣቶች ማፍራት ተችሏል። ስለ ግድቡ የኢትዮጵያ አቋም ምንድነው የሚለውን ብንመለከት ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላት ይታወቃል። በኢትዮጵያ ውስጥ ውሃና መብራት የማያገኝ ህብረተሰብ ያለበት እንደመሆኑ የተፋሰሱ አገራት ወንዙን እንዴት በጋራ መጠቀም እንደሚቻል ውይይት ያስፈልጋል። ለተፋሰሱ አገራት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታና አቋም በተደጋጋሚ በሚደረጉ ዘመቻዎች ማሳወቅ የግድ ይላል።
አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ምንም አይነት መረጃ የላቸውም። ይህ ሁኔታ ለዓለም ህብረተሰብ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ግብፅ በስሜት ውሃ ሊያስጠሙን ነው ብለው መነሳታቸውን በመመልከት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። ለተፋሰሱ አገራት ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በማስረዳት ረገድ ስራ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ወጣቱ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምን መሰራት አለበት?
ወጣት እየሩሳሌም፡– በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ወጣት ከአገሩ ጎን መቆም መቻል አለበት። ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ህብረተሰብ ዝም ያለ ነበር። የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያወሩበትና የሚደመጡበት ወቅት፤ አሁን እያከተመ ይመስላል። በዚህም ሁሉም በአንድነት አገሩን ሊታደግ ይገባል። ይህ ስራ እውቀት ባላቸው ወጣቶች የሚታገዝ ከሆነ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ለችግሮቹ መነሻ የሆኑትን ነገሮች በመለየት ሃይማኖትንና ብሔርን ወደ ጎን በመተው ለአንድ አገር ትብብር ሊደረግ ይገባል። አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ እንዴት መውጣት እንዳለባት ውይይት ማድረግ ይገባል። በአገሪቱ ያለውን የዘረኝነትና የፖለቲካ ሽኩቻ ቀደም ብሎ መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል። ሁሉም ያለውን እውቀት አዋጥቶ ለአገሪቷ አንድነት መቆም አለበት። አንድነትን በመስበክ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለጋራ ነገር መቆም ይገባል።
ወጣቱ ከአገሩ ጎን ቆሞና ለአገሩ ዘብ መቆም እንዳለበት በተደጋጋሚ ሊተላለፍ የሚገባ መልዕክት ነው። ተፅዕኖ ለመፍጠር እንዲቻል ወጣቱ ለሀገሩ በሚጠቅሙ ዘመቻዎች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ አለበት። ኢትዮጵያ በውስጥና በውጪ ባለ ጫና ምንም አትሆንም። ለግል ጥቅማቸው ተሰልፈው የነበሩ ሰዎች ለፖለቲካ ትርፍ ለሚሰሩት ላልተገባ ስራ ግጭቶች እየተፈጠሩ ናቸው። አንዱን ብሔር ከሌላው ለማጋጨት የሚሰሩ ስራዎች መቆም አለባቸው። በተለያዩ ዘመቻዎች ይህን ሁኔታ በመቃወምና አንድነትን የሚሰብኩ ነገሮችን በማሰራጨት ወጣቱ በህብረት መቆም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በጣም እናመሰግናለን።
ወጣት እየሩሳሌም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013