(ኢትዮጵያን የማፍረስ፣አሸባሪን የማንገስ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ሴራ፤)
ደጋግሜ በዚሁ ጋዜጣ እንደገለጽሁት ሀገራችን በ3ሺህ አመት ጥንታዊ ታሪኳ እንዲህ ያለ ከባድና ውስብስብ ፈተና ፣ ለዛውም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ተናበውና ተልዕኮ ተቀባብለው ሊያጠቋት ተነስተው አያውቅም። በአንድ በኩል ለ30 አመታት በቁሟ የጋጣት የዘረፋት ፣ በታሪኳ እየገዛት አምርሮ የሚጠላት ስሟን ለመጥራት እንኳ የሚጸየፋት ፣ የገዛ ሀገሩን 80 በመቶ ጦር ከድቶ የጨፈጨፈ የጦር መሳሪያ ዘርፎ መልሶ ያጠቃ አረመኔ በታሪኳ ተነስቶባት አያውቅም። ይህ ሳያንስ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ከዚህ ከሀዲና አሸባሪ ጎን ተሰልፈው ጥቃት ከፍተውባታል። ምዕራባውያን እንደ አሁኑ በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ ለማምጣት ፍኖተ ካርታ ቀርጸው ተንቀሳቅሰው አያውቁም። “From Basma to Ethiopia – How C2FC is Using Lethal Journalism to Conduct Information Warfare and Lawfare against Ethiopia” በሚል ርዕስ በጂኦፖለቲክስ ፕሬስ የወጣው ሰነድ ይህን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ሴራ አደባባይ አስጥቶታል። ባዝማ ሶሪያ ናት። ሶሪያን ለማፈራረስ የተቀመረው ሴራ የከሸፈ ቢመስልም ስህተቱን ነቅሶና አርሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዳግም ስራ ላይ ውሏል። በማሳጠሪያ “ፕሮጀክት ባዝማ” የደህንነትና የስለላ ስራዎችን የሰብዓዊ ተቆርቋሪነትና የጋዜጠኝነት ጭምብል ሽፋን የሚሰጥ ህቡዕና አደገኛ የሉዓላዊና ነጻ ሀገርን መንግስት ለመለወጥ በዝግ የተዶለተ ደባና ሴራ ነው ።
Command and Control Fusion Center /C2FC/CCFC/የኢትዮጵያን መንግስት በማዳከም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን በማውረድ እንደ ዩጎዝላቪያው ስሎቦዳን ሚሎሶቪች በጦር ወንጀል መክሰስ ፣ ምዕራባውያን እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩት አሻንጉሊት መንግስት አስቀምጠው “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል፤” የሚለውን አደገኛ አንቀጽ ተግባራዊ ለማድረግ መንገዱን አልጋ በአልጋ የሚያደርግ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጁ የሆነውንና የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆኑትን ህወሓትንና ኦነግ ሸኔን ወደ ስልጣን ለመመለስ ፣ አሸባሪውን ህወሓት አለማቀፍ ሚዲያዎችን እንደ አዲስ ስታንዳርድ ያሉ የአገር ቤት ሚዲያዎች ፣ አክቲቪስቶችን የስለላ ተቋማትን እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን እንደ ማርቲን ፕላውት በአንድ የዕዝ ጠገግ የሚመራውና የሚቆጣጠረው በምህጻረ ቃል“C2FC” የተሰኘው ፕሮጀክት ነው። የዚህ ፕሮጀክት ዋና ግብ ጀግኖች አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው ያቆዩንን ሉዓላዊነቷንና ነጻነቷን ማፍረስ ነው። ይህን እኩይ አላማ ለማሳካት አሸባሪውን ህወሓት ሸኔ ኦነግን የጉምዝ ታጣቂዎችን አልሻባብን በትሮይ ፈረስነት ይጠቀማሉ። ይህን ተከትሎ አዲስ ትርክት ማንበር የረጅም ጊዜ ዕቅዱ ነው። ይህ አደገኛ ሴራ ወደፊት የመጣው አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ትውልድም ሆነ ታሪክ ይቅር የማይለውን ክህደት በመፈጸሙ ሕግን የማስከበርና የሕልውና ዘመቻው ሲጀመር ሲሆን ፤ የብተናና የፍርሰት ፍኖተ ካርታ ሆኖ ወደፊት መጣ። የመረጃ ጦርነትን እንደ ፍላጻ ማንበልበል ይሄን አለማቀፍ ሚዲያዎች ተቀብለው ሳያጣሩና ሚዛናዊነቱን ሳይጠብቁ ይነዙታል ። እነ ማርቲን ፕላውት በቲዊተር ያራግቡታል። ከዚያ ሱዛን ራይስና ጭፈራዋ በባይደን አስተዳደር ፣ በእንግሊዝና በአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ጫና ማሳደር ይጀምራሉ።
ባዝማ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በአውሮፓ ሕብረት ለሚገኙ በጥንቃቄ ለተመረጡ ኃላፊዎች የተሰጠው የህልውና ዘመቻው የተጀመረ ሰሞን መሆኑ ከዚህ ደባ በስተጀርባ የህወሓት ረጅም እጅና ደጋፊ የአውሮፓ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ህወሓት ለዚች ሀገር ያለው የጥላቻ ጥግ፤ ለስልጣን ሲል ምንም ከማድረግ ስለማይመለስ እና ክህደት ጥርሱን የነቀለበት ስለሆነ የዚህ ደባ ጠንሳሽ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዚች ድሀ ሀገር መቀነት ዘርፎ ያሸሸው በአስር ቢሊዮኖች የሚገመት ዶላር በመርጨት ደባውን ይዶልታል። ህወሓት የገዛቸው እነዚህ የሕብረቱ ኃላፊዎች ሰነዱ ቀልብ እንዲገዛ ከቀባቡት በኋላ ለአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ማቅረብ ከተሰጣቸው ተልዕኮ ቀዳሚው ነው። በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግስት የተቀሰቀሰው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጣናውን ወይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ስለሚያዳርስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዲጎርፉ መንስኤ ሊሆን ይችላል የሚለው ማስፈራሪያ የሕብረቱን ትኩረት እንዲያገኝ አስችሎታል። በሶሪያ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ ጦርነቶች ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ስደተኞች የጎረፉባት አውሮፓ ሌላ የስደተኞች ማዕበል ሊነሳብሽ ነው ስትባል በቀላሉ ህወሓትና ጭፍራዎቹ ወደ አዘጋጁላት ወጥመድ እንድትገባ ማድረጉ አይቀርም።
ይሄ መሠሪና አደገኛ ሰነድ ዐብይ ኢሳያስና የሱማሊያው ፎርማጆ አንድነት ፈጥረው ቀጣናውን በበላይነት የመቆጣጠር ዕቅድ እንዳላቸው ያራግባል። በቀጣናው የሚፈጠረው ቀውስ በሳኡዲ አረቢያና በተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ስጋት መደቀኑ እንደማይቀር ይሄው አደገኛ ሰነድ ይለፍፋል። ግጭቱን አለማቀፍ ለማድረግና የኃያላን መንግስታትን ትኩረት በመሳብ በሚፈጠር ግርግር ከተጠያቂነት ማምለጥና ወደ ስልጣን መመለስ የህወሓት የመጨረሻ ግብ መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። የሚያሳዝነው ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ ታሪኳን የተረዱት ህወሓትና ሸኔ በተረኩበት የተሳሳተ ተረክ መሆኑ ነው ። በአውሮፓውያን አረዳድ ኢትዮጵያ ወደለየለት ቀውስና መፍረስ ልትገባ የቀራት አንድ ሀሙስ ነው። የተሳሳተ መነሻ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ያደርሳል እንዲሉ፤ ህወሓትንና መሰሎቹን ወደ ስልጣን ማምጣት በቀላሉ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ በውሳኔ ሕዝብ መመለስ ይቻላል። በእነሱ ግምገማ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ኃይሎች እንዳሉ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ተደርሷል። ይህን የተሳሳተ ግምገማና መደምደሚያ ያስጨበጠው ደግሞ ህወሓት ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ብራስልስና ዋሽንግተን ሆነው የሀገራትን እጣ ፈንታ ለመወሰን ሲንቀሳቀሱ እንደ ማየት ምን የሚያበግን ነገር አለ። ኢትዮጵያ እንደምትበታተን ደምድመው ብትንትኑ ግን እንደ ሶማሌ ላንድ በጅምር እንዳይቀር፤ እንደ ዩጎዝላቪያ ብተና “በስኬት” እንዲጠናቀቅ ህወሓትን ለቅርጫው በአጋፋሪነት ፣ ዐብይን እንደ ሚሎሶቪች በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተፈጸመ ወንጀል በአለማቀፉ የወንጀል ችሎት ማቆምን በጀ ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ዝናብና ቁር ሳይበግራቸው በነቂስ ወጥተው እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተሰልፈው በአንጻራዊነት ነጻ ተአማኒና ፍትሐዊ ምርጫ በማድረግ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት እንዲኖራቸው በወሰኑበት ማግስት፤ በዴሞክራሲ በዜጎች ነጻነት በፍትሕና በዜጎች ሉዓላዊ የስልጣን ምንጭነት እናምናለን የሚሉት ብራስልስና ዋሽንግተን ቃላቸውን አጥፈው በአሸባሪነት ለተፈረጀና ላለፉት 27 አመታት በፈጸመው ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ዘረፋ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋውን ነፍሰ በላ ቡድን ወደስልጣን ለመመለስ በተቃራኒው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠውን ዐብይ ለማግለል መዶለታቸው የፍርደ ገምድልነታቸውን ጥግ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አሸባሪው ህወሓት በጦርነት አሸንፎ አራት ኪሎ መግባት ካልቻለ በሚል ሌላ የጡት አባትነት ዕቅድ/plan b/ ማዘጋጃታቸው ይሄን ያረጋግጣል። ዕቅዱ በኢትዮጵያ ህወሓትን ያሳተፈ ብሔራዊ ምክክር ማድረግና የሽግግር መንግስት መመስረት ነው። የድፍረታቸው ጥግ ደግሞ ዐብይ በዚህ የሽግግር ባሉት መንግስት እንዲኖሮ አይፈልጉም። ይሄ ሰነድ አጎት ሳም /አሜሪካውያን/ በታሪክና ጆግራፊ ሰነፎች ናቸው የሚባል ሀሜት አስታወሰኝ። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያንን አያውቁንም። ነጻነታችንንና ሉዓላዊነታችን ሳናስደፍር ታፍረንና ተከብረን የኖርን ጥንታውያን እንጂ እንደ አሜሪካ ካናዳና አውስትራሊያ ትናንት በስደተኞችና በወንጀለኞች የተመሠረትን ሀገር አለመሆናችንን አለማወቃቸው እውነትም በታሪክ ሰነፎች ናቸው እንድል ተገድጃለሁ።
ምዕራባውያን ይህን አላማቸውን ለማሳካት የመረጃና የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን እንዴት እንደሚመሩት ሳይቀር ስትራቴጂ ነድፈዋል። በአሸባሪው ህወሓትና በኢፌዲሪ መንግስት መካከል የሚካሄደው ጦርነት አስመልክቶ የሚወጡ ዘገባዎች የኢትዮጵያን መንግስት በሚጠቅም መልክ እንዳይዘገቡ ያስጠነቅቃል። በተቃራኒው አሸባሪዎቹን ህወሓትና ኦነግ ሸኔን እንዲጠቅሙ ተደርገው መቀረጽ/frame/እንዳለበት አቅጣጫ ይሰጣል። ይህን አካሄድ የሶሪያን መንግስት ለመገልበጥ እና የቻይናውን ፕሬዚዳንት ዥን ፒንግን ለማጠልሸት ባዝማ እንደተጠቀመበት ጂኦፖለቲክስ ፕሬስ ያስታውሳል። ይህ የባዝማ ህዋስ እንደ ማርቲን ፕላውት ታዋቂ የሚዲያ ሰዎችን ጋዜጠኞችን የዩኒቨርሲቲ ልሒቃን ጠበቃዎችን የዴሞክራሲ ወትዋቾችን የግል የደህንነትና የስለላ ተቋማትን አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ወዘተረፈ ያካተተ ነው። እንግዲህ ይህ ስብስብ ነው ማንኛውንም ዘገባ መጣጥፍ ፕሮግራም እየገመገመ የሚያሳልፈው። ሀገራችን እውነትንና ፍትሕን ታቅፋ የቀረችው ተረኩን የተነጠቀችው እንዲህ ባለ ሴራ ነው። የሁሉንም አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘገባዎች ተመልከቱ ሁሉም ሽብርተኛውን የሚያሞካሹ ሀገራችንን የሚያጠለሹ ናቸው። ይቺን መጣጥፍ እያጠናከርሁ እያለ አሸባሪው ህወሓት በየግንባሩ ውጊያ ላይ የሞቱ ወታደሮቹን አስከሬን አሰባስቦ ተከዜ ወንዝ ላይ በመልቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት ገሎ እንደጣላቸው በማስመሰል የተካነበትን ድራማ እየተወነ ነው። በC2FC ተልዕኮ ተቀብለው የሚጠባበቁት እነ ሮይተርስ አሶሼትድ ፕሬስ ዋሽንግተን ፓስት የአልጀዚራ ቢቢሲ ዘ ኢኮኖሚስት ወዘተረፈ እያራገቡት ይገኛል። ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓወር የሱዳንና የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር ተንሰላስሎ የተለቀቀውን ሀሰተኛ መረጃ ሴትዮዋ እንዳለ በመውሰድ“የሚያሳስብ ጉዳይ ነው” ማለታቸው መሰማቱ ለጊዜውም ቢሆን ማደናገር መቻሉን ያመለክታል።
እንደ መውጫ
አሸባሪው ህወሓት ነፍስ ዘርቶ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት እንዲመለስ መንገድ የሚመራ ታላቅ ሴራ የተሸረበበት ሰነድ ይፋ ሲሆን ያለልዩነት ሚዲያዎች አክቲቪስቶች ልሒቃን መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያወግዙትና ሊቀባበሉት ሲገባ ችላ መባሉ እንደ ዜጋ ክፉኛ አስደንግጦኛል። ምንድን ነው ያደነዘዘን ? ምንድን ነው ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ የከተተን ? ደንታ ቢስ የሆነው ለምንድን ነው ? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አስገድዶኛል። ቢዘገይም አልረፈደምና ዛሬም መንቃትና የሚከተሉትን እርምጃዎች በአስቸኳይ መውሰድ ይገባል።
1ኛ . እንደ አዲስ ወግ ያሉ መድረኮች የሚመለከታቸውን ምሁራን ጋብዘው ሊመክሩበትና አቅጣጫ ሊያስቀምጡበት ፣ ለአለማቀፍ ማህበረሰቡ ቆፍጠን ያለ መልዕክት ሊያስተላልፉበት ይገባል።
2ኛ . ከባይደን አስተዳደርና ከአውሮፓ ሕብረት ይልቅ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕዝቦችን በቀጥታ ኢላማ ያደረገ የተግባቦት ስራ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ አማካኝነት መስራት የግድ ነው። ዜጋው ፖለቲካዊ ልሒቁንና ሚዲያውን ጉሮሮውን አንቆ ወደ ሀቁ የማምጣት የማይገሰሰ አቅም ስላለው፤
3ኛ . የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ በተለይ ዲያስፓራ ዜጎቻችን በየአሉበት ሀገር ያሉ ታዋቂ የኪነ ጥበብ የስፖርት ሰዎችን አክቲቪስቶችንና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ስለሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ስለአሸባሪው ህወሓት ማንነት ደጋግመው ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል።
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013