የዕለት ተዕለት ስራውን የሚያከናውነው በሰቀቀንና በጣር ነው:፡ ይህ ስሜቱ እንዳይታወቅና አለሁ ለማለት ያህል ግን ዛሬም ምላሱ አልታጠፈም። ይህ ባህሪው ደግሞ ለማስመሰሉ ከእርሱ ጋር ተስተካካይ አለመኖሩን ነው የሚያሳየው። እየቆረቆረውና እየጎረበጠውም ቢሆን ‹‹ሁሉ ደህና›› ለማለት አቻ የለውም። ዛሬም የሞተ በድኑ እጅ ላለመስጠት ይውተረተራል።
አሸባሪው ህወሓት ከትውልድ ዘመኑ ጀምሮ እንዲሁ አንዱን ከአንዱ በማሸበር እስከ ዛሬ ቢደርስም በጠና ታሞ የአልጋ ቁራኛ ከሆነ እነሆ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ዛሬም ቢሆን በማስመሰል ምላሱ የተገራ በመሆኑ ላለፉት ሶስት ዓመታት ትልቁን የመርዛማነት ሚና ተጫውቷል።መርዙን ሲረጭ የነበረው ደግሞ ‹‹እነርሱ የእኔ፤ እኔም የእነርሱ›› እያለ በየደረሰበት በመማልና በመገዘት እንዲሁም ሐቀኛ በመምሰል ለሚያታልለው የትግራይ ህዝብ ነው፡፡
ዛሬ እንኳ ልጡ ርሶና ጉድጓዱ ተምሶ ባለበት በዚህ ሰዓት ‹‹አብረን ካልሞትን እኔ ምን ተዳዬ›› ያለ ይመስላል።እርሱን እስከጠቀመውና እስካኖረው ድረስም የእኔ የሚላቸውን እየገደለና እየሰዋ ራሱን ለማኖር መውተርተርን ይዟል።ለዚህ ማሳያው ደግሞ በቅርቡ በማን አለብኝነት ተነሳስቶ በአማራ እና በአፋር በኩል የተለመደ ተንኳሽነት ሚናውን ለመወጣት በከፈተው ጦርነት እንቦቃቅላዎችን ወደጦር አውድማ መማገዱ ተጠቃሽ ነው።ገና ግራ ቀኛቸውን በቅጡ የማያውቁትን ታዳጊዎች ለእርሱ ህልውና ሲል በመሰዋት እንጥፍጣፊ እድሜውን በለመደው በንጹሃን ሞት በመተካት በዚህች ምድር ለሰዓታትም ቢሆን ለመቆየት እየሞከረ ይገኛል፡፡
በአስተሳሰብ ደክርቶ፤ በሰውነትም ጃጅቶ በተሟ ጠጠ በዚህ ጊዜ እንኳ ትናንት የኢትዮጵያውያንን አንጡራ ሀብት እያነሳ እንዳሻው ሲረጭላቸው የነበሩ ምዕራባውያን ሚዲያዎችና አንዳንድ ተቋማት በበሉበት እንዲጮሁለት ዛሬም ያለውን ፍርፋሪ ገንዘብ በማጉረስ እንዲንተፋተፉለት የመጨረሻ እድሉን በመጠቀም ላይ ነው።
ውሻ በበላበት ይጮሃል እንዲሉ የሚጎረስ እስካልጠፋ ድረስ እነርሱም በጎረሱት ልክ ብቻ ሳይሆን ህልማቸው ኢትዮጵያ ተበታትና ማየት ነውና ከዚያም ከፍ አድርገው ግባቸውን ለማሳካት ሲያላዝኑ ውለው ማደር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።እውነትን ወደጎን በመተው ውሸት መከተል ከጀመሩ ሰንብተዋል። ጁንታው በራሱ ዜጎች ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ግፍ ከመግለጽ ይልቅ እንደ ውሻ ጅራቱን እየቆላ ለብዙ አስርተ ዓመታት ሲታዘዝላቸው ለነበረው ሙትቻው ህወሓት ዛሬም ‹‹ጥፋት የለበትም›› ሲሉ ብዕራቸውን በማንሳት ተባባሪው ሆነዋል።
የእባብ ጉድጓድ በሞኝ ክንድ ይለካል እንዲሉ አሸባሪው ህወሓት የድሃውን ልጅና የአርሶ አደሩን ልጅ በጦርነት ውስጥ እየማገደ ‹‹የእኔ፣ የአብራኬ ከፋይ ናቸው›› የሚላቸውን ግን በበለጸጉ አገራት ለዚያው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ተሽከርካሪዎች እንዲንሸራሸሩ እያደረገና እጅግ ዘመናዊ በሆኑ መኖሪያ ቤቶች አንደላቆ እያስቀመጠ የድሃውን ልጅ ግን እባቡ ይንደፍህ፤ መርዙንም ይርጭብህ ማለቱ የአስተሳሰብ ምክነትና በቁም መሞቱን አመላካች ነው።
እርግጥ ነው ምንም እንኳ ጣረ ሞት እያሳቀየው ለተወሰኑ ጊዜያት የቆየ ቢሆንም አሁን ግን የምር ጁንታው ሞቷል።የመሞቱ ዜና የቱንም ያህል ርቀት ደርሶ ቢሰማም ቀባሪ ማጣቱ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል። በእርግጥ በአገራችን ባህል መሰረት ሰዎች ‹‹ቀባሪ አታሳጣኝ›› ይላሉ።ቀባሪ እንዳያጡ በደህናው ቀን በምድር እያሉ የሚሰሩት መልካም ተግባር ሊኖራቸው ያስፈልጋል፤ ይህንንም በተቻላቸው ሁሉ ለማድረግ ይጥራሉ።በማን አለብኝነት መጓዝ ሊያሳጣ የሚችለው ከሞት በኋላ ስላለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በምድር እያሉ በሥርዓት ቀብር ጊዜ የሚደረጉ ሂደቶችንም ጭምር ነው።
አሸባሪው በህይወት እያለ በምድር የሰራቸው ክፋቶች ወደር የላቸውም። በብሔር ከፋፍሎ ማጋደሉን ወደጎን ልተወውና በእስር እንዲማቅቁ ሲያደርጋቸው የነበሩ ነፍሶች የትየለሌ ናቸው።እርሱ ፈላጭ ቆራጭ ነበር።ለእርሱ የሚመቸውና ለእርሱ የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ከልካይ አልበረውም፤ ይጻረሩኛል ብሎ የፈረጃቸውን በእጅጉ ሲያሰቃያቸው ነበር።ከእርሱ ሐሳብ የሚያፈነግጡትን ለእስር ከመዳረጉም በላይ ያለርህራሄ ሲያሰቃያቸው እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከእርሱ የተሻለ ሐሳብ ይዞ የሚመጣ ሁሉ የሚታየው እንደ እርኩስ ነው። ሰውዬው ‹እርኩስ› ተብሎ ብቻ አይተውም። ጀርባው ይጠናል፤ በመጨረሻም አንድ አጠር ያለች ሰበብ ተበጅታለት ወደ እስር ቤት ይጣላል። ይህ የተለመደ እና ጥርሱን የነቀለበት ባህሪው ነው። ለአገርና ለዜጎች የተሻለ ሐሳብ ይዞ መምጣት ማለት ከእርሱ በተጻራሪ መንገድ እንደመቆም ይቆጥረዋል። ምክንያቱም እርሱ ራሱን ለማኖር የሌሎችን መስዋዕትነት ይጠይቃል።
ምሱ የሰው ህይወት ነው፡፡ ባይሆንማ ኖሮ በቆየባቸው በርካታ ዓመታት የብዙዎቹን ኢትዮጵያውያንን ህይወት አበላሽቶ፣ በአገሩ ሰርቶ መብላት የሚፈልገውን ከአገር አባርሮ፣ የኢትዮ ጵያውያኑን አንጡራ ሀብት ለራሱ መረን ላጣ ፍላጎት አውሎ፣ በየጊዜው ደግሞ አንዱን ብሔር በአንዱ ላይ እንዲነሳና እንዲናከስ የሚያችል ጠንከር ያለ የቤት ስራ ሰጥቶ እያለ እንኳ የለውጡ መንግስት ለሰራቸው ጥፋቶችና ለፈጸምካቸው ወንጀሎች ይቅር እልህ ዘንድ አሁን ያንን ባህሪህን ተወውና ወደሰላማዊ መንገድ ተመለስ ሲለው አሻፈረኝ ባላለ ነበር።
እንዲያውም ደም ካላየ መኖር እንደማይችል ሁሉ ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው መውጋቱ አረጋጋጭ ክስተት ነበር። በዚህ ራሱ በከፈተው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች መገደላቸው እውን ነው።ይኸው ልማደኛ አሸባሪ ከቅርብ ጊዜ አስቀድሞ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረሱንና የጥሞና ጊዜ መስጠቱን የሰማው እያጣጣረ ባለበት ጊዜ ይሁን ከሞተ በኋላ ባይታወቅም ከመንፈራገጡ ግን እስካሁን ሊነቃ አልቻለም። ምናልባትም አልታወቀለትም እንጂ ያሸለበው አስቀድሞ ሊሆን ይችላል።
ጎልማሳው አሸባሪ ለመሞቱ ምልክት የሆነው የጡሩምባ ድምጽ ከተሰማ ቆየት ብሏል፤ እስካሁን ግን ኃዘንተኞች አልመጡም፤ ቀባሪዎችም አልተከሰቱም፤ የእዝን በመያዝ ለማስተዛዘን እንዳይኬድ ደግሞ ግብዓተ መሬቱን የሚፈጽም ጠፍቷል።ካልታዘልኩ አላምን እንዳለችው ሙሽሪት፤ አስከሬኑን ካላየን አናምንም ያሉ የሚመስሉ አንዳንድ ምዕራባውያን ግን ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ይመስላል።እስትንፋስ ሊሆኑት ቢሞክሩም አሸባሪው ህወሓት ግን ሞቷል።እርግጥ ነው በባህላችን የወደቀን ማንሳትና የሞተን መቅበር ያለ ነውና፤ በቁሞ የሰራቸው ወንጀሎች እንዳሉ ሆው ብንቀብረው ምን ትላላችሁ? ሰላም!
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013