በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚቋቋሙ ማህበራት ግጭቶችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ሚናቸውን እየተወጡ አለመሆኑን አስተያየት የሰጡ ተማሪዎች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተማሪዎች፣ የሰላምና ሌሎችም በርካታ ማህበራት ቢኖሩም ለተቋቋሙለት ዓላማ ጠንክረው እየሰሩ አይደለም።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪው ማሾ ዳሉ ማህበራቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ‘ከብሄርተኝነት ይልቅ አንድነት እንዲጎላ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና መጫዎት ቢችሉም ይህ ሲሆን አይታይም’ ብሏል።
ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ስለ ብሄርተኝነት ሃሳቡ ያልነበረው ተማሪ ይህን ‘ማሰብ ይጀምራል’ ያለው ተማሪ ማሾ ምክንያቱ ደግሞ ‘የነበረው ብሄር ተኮር የፖለቲካ ሂደትና በአንድነት ላይ የሚሰሩ ማህበራት አለመጠናከር ነው’ ብሏል።
የዩኒቨርሲቲው የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ተማሪው አሸናፊ አለማየሁ በበኩሉ ‘የተማሪዎች ማህበራት የሚነዙ የሃሰት መረጃዎች የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ግንዛቤ መፍጠርና የተማሪዎች ጥያቄዎች እንዲፈቱ የማድረግ ሚና ሊኖራቸው ይገባል’ ይላል።
ይሁን እንጂ የሚስተዋለው ሁሉም የራሱን ብሄር የሚያሳይበት ሁኔታ በመሆኑ ተማሪዎችም ከአንድነትና ከአገር በላይ ስለ ብሄር እንዲያስቡ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሟል።
ይህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለፖለቲካ ጥቅማቸው ማስፈፀሚያነት ለሚጠቀሙ አካላት እድል በመፍጠር የግለሰብ ጠብ ወደ ብሄር ግጭት እንዲያድግ መንስኤ እየሆነ በመሆኑ ‘ሊታሰብብት ይገባል’ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሌላው የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ተማሪ አቤል ማቲዮስም ተማሪው እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙት በተረጋጋ ሁኔታ ነገሮችን መመርመርና ወደ ግጭት ከመግባት መቆጠብ ይኖርበታል ብሏል።
በተለይም በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች ግጭቶችን ለማባባስ ታስቦ የሚወጡ በመሆናቸው ተማሪው የመጣበትን ዓላማ ማስቀደምና ከስሜታዊነት ነፃ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።