መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ አንገት ያስደፋ አሳዛኝ ድርጊት በቶኪዮ ኦሊምፒክ እየታየ ይገኛል። ወጣቱና አዲሱ ጀግና አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ10 ሺ ሜትር ከሁለት ኦሊምፒኮች በኋላ ያስመዘገበውን ጣፋጭ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅጡ አጣጥሞ ሳይጨርስ ታሪካዊ ስህተቶች መታየታቸውን ቀጥለዋል።
በግለሰቦች ሽኩቻና መቃቃር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ገና ወደ ቶኪዮ ከማቅናቱ አስቀድሞ ሲሰሩ የነበሩ ስህተቶች በተለያዩ ውድድሮች ላይም አትሌቶችን ከመከፋፈል አልፈው አገር ከውድድሩ ማግኘት የሚገባትን ሜዳሊያዎች አሳጥተዋል። ከአስራ ሶስት በላይ ኦሊምፒኮችን የመሳተፍ ልምድ ላላት አገር እንዲህ አይነት ስህተቶች ተጠባቂ አይደሉም። ግለሰቦች የገቡበት ያልተገባ እልህ በስህተት ላይ ተጨማሪ ስህተቶችን ለመስራት በር ከፋች ሆነው ታይተዋል።
በዚህ ኦሊምፒክ ገና ከጅምሩ የተሰሩትን መርህ አልባና የአገርን ጥቅም ያላስቀደሙ ስህተቶች መዘርዘር አንባቢን ማድከም ነው። በርካቶቹን ስህተቶች አትሌቶቹ ገና ውድድራቸውን ሳይጨርሱ ማንሳት የቡድኑን ስሜትና ስነ ልቦና ይጎዳል በሚል በርካታ ወገኖች ጉዳዩን በዝምታ ማለፍን መርጠዋል። ከትናንት በስቲያ የተካሄደውን የወንዶች አምስት ሺ ሜትር ማጣሪያን በተመለከተ የተፈጸመውን ስህተት በዝምታ ማለፍ ግን የስህተቱ አካል ከመሆን አያድንም።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ከኦሊምፒክ ሜዳሊያ አጥታበት በማታውቀው የ5ሺ ሜትር ወንዶች ውድድር አትሌቶቻችን ማጣሪያውን እንኳን ለማለፍ ሲቸገሩ ማየት ያማል። ወጣት አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ ማጣሪያውን በ6ኛነት አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ዙር በብቸኝነት አልፏል። በምድብ አንድ ማጣሪያውን ያደረጉት አትሌት ጌትነት ዋለና ንብረት መላክ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባልተለመደ መልኩ ዘጠነኛና አስራ አራተኛ ሆነው በማጠናቀቅ ወደ ፍፃሜ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህ ውጤት የተመዘገበው በአትሌቶቹ ድክመት ሳይሆን በግለሰቦች ስሜታዊ ውሳኔ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ርቀት በትልቁ ወርቅ ባይሳካ ብር ካልሆነም በትንሹ የነሐስ ሜዳሊያ የማስመዝገብ አቅሙ ያላቸው በርካታ አትሌቶች እንዳላት ዓለም ይመሰክራል። ያም ሆኖ በርቀቱ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የተደረጉ አትሌቶች አንድም አትሌቶቹ ራሳቸውን እንዲያባክኑ በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ሜዳሊያ እንድታጣ አድርጓል።
ስህተቱ የ5ሺ ሜትር ማጣሪያ ውድድርን የ3ሺ ሜትር መሰናክል ማጣሪያና ፍፃሜ ውድድር ያደረገውን አትሌት ጌትነት ዋለን ሃያ አራት ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲወዳደር ከማድረግ ይጀምራል። የዚህን ውሳኔ ስህተት መሆን ለመናገር የአትሌቲክስ አሰልጣኝ መሆንን አይጠይቅም።
ጌትነት በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት ባላሳየበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል ያውም የተመረጡ አትሌቶች እያሉ እነሱን አስቀርቶ እንዲወዳደር ማድረግ አትሌቱን እንዲባክን ከማድረግ በተጨማሪ በርቀቱ የተዘጋጁትን አትሌቶች ተስፋ ያጨለመና ሞራላቸውን የጎዳ ስህተት ነው።
ይህ ስህተት አትሌቱ ድንቅ ብቃት አሳይቶ ሲዘጋጅበት የቆየውን የ5ሺ ሜትር ተስፋም ገደል ከቷል። ምናልባትም ጌትነት በተዘጋጀበት 5ሺ ሜትር ብቻ ቢሮጥ ወርቁ ቢቀር ብርና ነሐስ ማጥለቅ የሚችል አቅም እንዳለው ማንም መመስከር ይችላል።
ከጌትነት ይልቅ በርቀቱ ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘውና 10ሺ ሜትርን አሸንፎ ለአራት ቀናት በቂ እረፍት ያደረገው ሰለሞን ባረጋ እንዲወዳደር አለመደረጉ ስህተት ነው። ሰለሞን በ10 ሺ ሜትር ያሸነፋቸው በርካቶቹ አትሌቶች በ5 ሺው ማጣሪያ አልፈው የሜዳሊያ ተፎካካሪ ሲሆኑ ሰለሞን አስደናቂ ብቃት ይዞ የምሩፅ ይፍጠርና የቀነኒሳ በቀለን ታሪክ መድገም የሚያስችለውን እድል አጥቷል።
በሌላ በኩል በሄንግሎ የኢትዮጵያውያን ማጣሪያ ውድድር አምስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ተጠባባቂ ተደርጎ የተያዘው አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ቶኪዮ ቢገኝም የመወዳደር እድል አላገኘም። ሙክታር ማጣሪያው ላይ ቀዳሚ ሆኖ ባይመረጥም ታላላቅ ውድድሮች ላይ በመጨረሻ ሰአት መጥቶ የማሸነፍ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ ያሳየ አትሌት ነው። ለዚህም ባለፈው የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና ዓመቱን ሙሉ በሌሎች ውድድሮች ላይ ሳይታይ መጨረሻ ላይ ብቅ ብሎ ማሸነፉን መጥቀስ በቂ ነው።
ይህ አትሌት በርቀቱ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በገነነበት ወቅት እንኳን በለንደን 2017 የዓለም ቻምፒዮና የርቀቱን ድል ወደ ኢትዮጵያ የመለሰ ነው። የሁለት የዓለም ቻምፒዮናዎች አሸናፊው ሙክታር የቱንም ያህል ብቃቱ ጥሩ ባይሆን በማጣሪያ ውድድር ይሰናበታል ብሎ መገመት ከባድ ነው።
ጉዳዩ የመርህ ከሆነ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ለሜቻ ግርማ ለትልቅ ውጤት የበቃው በርቀቱ ቀደም ሲል የተመረጡ አትሌቶች ቀርተው መጨረሻ ሰአት ላይ በመወዳደሩ ነው። ይህ ለሜቻ ላይ የሰራው ውሳኔ ለምን ለሰለሞንና ሙክታር ተግባራዊ መሆን ተሳነው? የበርካቶች ጥያቄ ነው። ይህ ስህተት በርቀቱ ብቸኛ የፍፃሜ ተወዳዳሪ የሆነው አትሌት ሚልኬሳ ግርማ በለስ ቀንቶት ወርቅ ቢያጠልቅ እንኳን ይቅር የማይባል ስህተት ነው። ምክንያቱም ሰለሞንና ሙክታር ቢካተቱ የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻላልና።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013