የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ከየካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚያደርገው አምስተኛው የጨፌው የስራ ዘመን አራተኛ ዓመት ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ወደ ህጋዊ መስመር የማስያዙ ስራ የሚቀጥል እንጂ ወደ ኋላ የሚመለስ ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉዳዮ የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን የአገር ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ስድስቱ ትላልቅ ከተሞች አዲስ አበባን በቅርበት አካልለው የሚገኙ በመሆናቸው የሁሉም ሰው ፍላጎት እንዳረፈባቸውም ጠቁመዋል፡፡
በመቶ ሺዎች የሚገመት ሄክታር በህገ ወጥ መንገድ ተይዟል፡፡ የሽግግር ወቅት እንደመሆኑ ህገወጥ የመሬት ወረራና ሌሎች ሰፋፊ ችግሮች ይከሰታሉ፣ ችግሩ አሁንም ይስተዋላል ብለዋል፡፡ ‹‹በህገ ወጥ መንገድ አንዴ ተይዟልና የራሱ ጉዳይ ተብሎ አይተውም ህጋዊ መስመሩን እንዲይዝ ይሰራል›› ብለዋል፡፡
20 እና 30 ዓመታት የተወሰነ ጊዜ የኖረም ህጋዊ የሚያደርገው ነገር ካለ በህግ የሚታይበት አግባብ አንዳለም ጠቁመዋል፡፡ ጉልበት፣ ገንዘብ ስላለውና ከተወሰነ ሰው ጋር በጥቅም በመገናኘት በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን መሬት ህጋዊ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ በሽግግር ወቅት አብዛኛው ህዝብና አመራር ሰላም ለማስጠበቅ በሚሯሯሩጠበት ወቅት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅና ኪሳቸውን ለመሙላት የሚሯሯጡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ዋነኛ የግጭት መንስኤ የነበረው የመሬት ጉዳይ መሆኑን ያስታወሱት አፈ ጉባኤዋ፤ መንግስት ችግሩን ለማስተካከል የተለያዮ ማሻሻያዎች ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ተጠናክሮ የታገለ ባለመኖሩ ሰፋፊ መሬት በተለያየ ሰው ስም ተይዟል በሌላ በኩል ደግሞ ማደሪያ አጥተው የሚቸገሩ ዜጎች አሉ በመሆኑም ይህንን ፈር የማስያዝ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አመራሮችና ፈጻሚዎች ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ ርምጃ እንደተወሰደባቸውም አስታውሰዋል፡፡ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ህጋዊ መስመር በማስያዙ ተግባር የሚፈናቀሉ ዜጎችን ሰላማዊ የመኖሪያ አካባቢ እንዲያገኙ ለማድረግ ጨፌው እንደሚመክርበትም አንስተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው