ጥቅምት 30 በህወሓት ጁንታ ቡድን ኢትዮጵያውያን ያለቀሱበት ጥቁር ቀን ነበር:: ማይካድራ የኢትዮጵያውያን የጋራ እንባ..የጋራ ሲቃ ሆኖ በትውልድ ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራል::አሸባሪው ህወሓት የአማራነትን የታሪክ ጫፍ ለማጠልሸት ከፍ ሲልም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የወሰደው አረመኔያዊ የጥላቻ እርምጃ በማይካድራ ምድር ታየ:: በህወሓት የጭካኔ በትር ሞት የተፈረደባቸው ንጹሕ ነፍሶች በማይካድራ ምድር ዝንተ አለም ሲጮህ ይኖራል:: በወንድሙ ቃየል እንደተገደለው እንደ አቤል ደም ንጹሐኑ በእግዚአብሄር መንበር ይጮሀሉ::
ህወሓት ለዘመናት ክብርና ተገን ሆኖ ሲጠብቀው የኖረውን የመከላከያ ሰራዊት በተኛበት ጦርነት መክፈቱ ሳያንስ ምንም የማያውቁ ንጹሐንን በብሔራቸው ብቻ ቤት ለቤት እየዞረ ሲያርድና ሲያሰቃይ ከመኖሩም በላይ ስር የሰደደ ጥላቻው በማይካድራ ታየ :: በመግደልና በማስገደል በሰለጠኑ አረመኔ ቡድኖች በአንድ ጀንበር በርካታ ንጹሐንን ፈጀ:: አይደለም ፖለቲካ፣ አይደለም ብሔር ሬዲዮ ከፍተው እንኳን የማያውቁ ከአብሮነት በቀር ምንም የማያውቁ ንጹሐን ነፍሶች በነፍሰ በላው ቡድን ላይመለሱ ተሰዉ::
አማራነት ላይ ያነጣጠረ በአሸባሪው ህወሓት የሚረዳ ‹ሳምሪ› ተብሎ የሚጠራ ቡድን በማደራጀት እጅግ አሰቃቂ በደሎችን አድርሷል:: በአሸባሪው ህወሓት ብሎም በውጪ አገር ዲያስፖራዎች ሳይቀር የሚረዳው ይህ ሳምሪ ተብሎ የሚጠራው አማራ ጠል ቡድንም በአማራ ብሔር ላይ የዘር ማጽዳት ተልኮውን እንዲፈጽም የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል::
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት ማይካድራ ጭፍጨፋ የተካሄደው ቀደም ብሎ ታስቦበትና ዕቅድ ተይዞበት ነው፡፤የማይካድራ ጭፍጨፋ ከመካሄዱ በፊት የህወሓት ሰዎች በከተማው እየተዘዋወሩ ሰዎችን የመለየት ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል::ስልታዊ በሆነ መንገድ መታወቂያ እየጠየቁ የአማራ ተወላጆችን የመለየት ስራ በስፋት አከናውነዋል::ከዚህም ባለፈ የተለዩት የአማራ ተወላጆች ቤት ቁጥርም ጭምር በአግባቡ ተይዞ ለታቀደው ጭፍጨፋ ዝግጁ ተደርገዋል::
ከጥቅምት 30 በፊትም ይህንን ጭፍጨፋ የሚያካሂድ ሳምሪ የተሰኘ አረመኔ የወጣት ቡድን በቂ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል::ከዘመናዊ መሳሪያ እስከ ባህላዊ መጥረቢያ፤ቢላዋ፤ገጀራና ጩቤ በመታጠቅ ንጹሐንን ለማረድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል::ቡድኑ አረመኔዊ ድርጊቱን በተገቢው ሁኔታ ለመፈጸምም ቀድሞ የተለዩትን የአማራ ተወላጆች ቤትን መሰረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል በመውሰድ ማን ማንን መግደል እንዳለበት የስራ ድርሻ ወስዶ ተንቀሳቅሷል::ምን አልባትም በየቤቱ ከሚደረገው ጭፍጨፋ የሚያመልጡ የአማራ ተወላጆች ካሉም ተከታትሎ የሚገድል የታጠቀ ቡድን በማዘጋጀትም ማንም ከዚህ ጭፍጨፋ እንዳያመልጥ በቂ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል::በተለይም ጥቅምት 30 ከመድረሱ አንድ ቀን በፊት በከተማው በመዘዋወር የጸጥታ ችግር ስለሚኖር ሁሉም ከቤት እንዳይወጣ በማዘዝ የጥፋት ቡድኑ እንቅስቃሴ ገደብ አስቀመጠ::ይህንን አምነው የተቀበሉ ነዋሪዎችም የተደገሰላቸውን ባለማወቅ ቤታቸውን ዘግተው ተቀመጡ::
ይህ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት አረመኔው ሳምሪ የተሰኘው ገዳይ ቡድን አባላት ቤቱ ከቶ በተቀመጠው የማይካድራ ነዋሪ ላይ እሳት አነደዱበት::የግማሹንም ቤቱን ሰብሮ በመግባት በያዙት መሳሪያ እንደ በሬ አረዱት::በተአምር ከጭፍጨፋው የተረፉ የአይን እማኞች እንደተናገሩት በማይካድራ የተደረገው ጭፍጨፋ ፍጹም አረመኔያዊነት የተሞላበት ነው::ሰዎች በቁማቸው አናታቸው በመጥረቢያ ተፈርክሶ ተገድለዋል::ሆዳቸው በጩቤ ተተርትሮና አንጀታቸው ተዘርግፎ ሞተዋል:: በቁማቸው ስጋቸው በቢላዋ እየተተለተለ በስቃይ ህይወታቸው ያለፉ በርካታ ናቸው::አባት በልጆቹ ፊት እየተማጸነ በገጀራና በመጥረቢያ ተጨፍጭፎ ተገድሏል::
በአሸባሪው ህወሓት ስምሪት የተሰጣቸው ሳምሪ የተሰኙት የገዳይ ቡድን አባላት በገደሏቸው ሰዎች ሬሳ ላይ በመቀመጥም ቢራ ሲጠጡ ታይተዋል::በሬሳ ክምር መሃል በመሆንም ጨፍረዋል፤ እምበር ተጋዳላይ ሲሉም ተደምጠዋል::
አማራ ጠሉ ህወሓት የአማራን ታሪክና ህልውና ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያላደረገው ጥረት አልነበረም:: ከትላንት እስከዛሬ በአማራ ሕዝብ ላይ በርካታ በደሎችን ሲፈጽም እንደኖረ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው:: ወጣቱ አገርና ሕዝብ እንዲጠቅም በሥነ ምግባር ከማነጽ ይልቅ በወንድም ሕዝቦቹ ላይ እንዲነሳ የጥላቻ ንግግሮችን በማስረጽ ታሪካዊውን እልቂት ፈጽመዋል::እነዚህ ወጣት የጥፋት ኃይሎችን በአደንዛዥ እጽ በማስከር ትውልድ አይቶት የማያውቀውን ጭፍጨፋ ለመፈጸም ችለዋል:: የጎንደር ዩኒቨርስቲ ባደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው በማይካድራው ጭፍጨፋ ከ1ሺ 644 በላይ ሰዎች ሰለባ ሆነዋል:: አሸባሪው ህወሓት ዛሬም ድረስ ቦርቀው ያልበቃቸውን አንድ ፍሬ ህጻናት በአደንዛዥ እጽ ህሊናቸውን በማሳት ለጦርነት እያሰለፉ በአዲሱ ትውልድ ላይ ሳይቀር መጥፎ አላማቸውን እያስፈጸሙ ይገኛሉ::
የህወሓት የጥፋት ኃይሎች ከናዚው የጥፋት ኃይሎች ጋር የሚያመሳስላቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ:: የናዚው መሪ ሂትለር ሁለተኛውንና በታሪክ ብዙ ንጹሐን ያለቁበትን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለጀርመናውያን ስለ አይሁዳውያን መጥፎ ወሬዎችን ይነዛ ነበር:: ጀርመናውያንም በመሪያቸው የሚነገራቸውን የተሳሳተ ወሬ በመስማት በአይሁዳውያን ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው::በዚህም ምንም የማያውቁ ስድስት ሚሊየን አይሁዳውያን እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል፡፤የናዚ ጦርም ንጹሐንን ያለ ርህራሄ ለመግደል እንዲያመቸው አደንዛዥ ዕጽ በገፍ ይጠቀምም ነበር:: ህወሓትም የጥላቻ ወሬዎችን በመንዛት በትግራይና በአማራ ወንድማማች ሕዝቦች ላይ የለየለትን ደም አፋሳሽ ታሪካዊ ስህተት በመስራት ላይ ይገኛል:: በጣም የሚገርመው ደግሞ ሳምሪ የተባለው ቡድን በክልሉ መንግሥትና አማራ ጠል በሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ጦርና ጎራዴ ታጥቆ ንጹሐንን ከገደለና እኩይ ተልዕኮውን ከተወጣ በኋላ ወደ ሱዳን በመሸሽ ራሱን ከሀጢያትና ከተጠያቂነት ለማሸሽ ሲል ለውጪው ማህበረሰብ ሌላ የክህደት ወሬ ማራገቡም ሌላው የህወሓት ድብቅ ሴራው ማሳያ ነው::
ሌሎች ታሪኮችን ትተን ህወሓት ምን ያክል ለአማራና ለአማራውያን ጥላቻ እንዳለው ማይካድራ በቂ ማስረጃ ነው:: ከሰውነት በራቀና መቼም ይቅር ሊባል በማያስችል ሁኔታ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን ክቡሩን የሰው ልጅ በብሔሩ ብቻ እየለዩ መግደልና ማሰቃየት የአረመኔነት ጥግ ነው::ከዚህም አልፎ የተገደሉትን ሰዎች እንደ ተራ ነገር በመቁጠር ሬሳውን በየመንገዱ በመጣልና በመጎተት አንዳንዶቹንም በማቃጠል ቡድኑ አውሬአዊ ባህሪውን አሳይቷል :: ክብር በሌለው ለእንስሳ እንኳን በማይገባ ሁኔታ ሰዎች በጅምላ ከመቀበራቸውም በላይ አንዳንዶቹን ከነነፍሳቸው በመቅበር የጭካኔ ጥጋቸውን አሳይተውናል::
አርሶ ከመብላት ውጪ ፖለቲካ ምን እንደሆነ የማያውቅን ሰው ለመግደልና ለማሰቃየት ወጣት ከማደራጀት በላይ ጭካኔ አለ ብዬ አላስብም:: ወጣቱን ለልማት ከማደራጀት ይልቅ ብሔርን መሰረት አድርጎ ዘር እንዲያጠፋ ማሰልጠን አሸባሪው ህወሓት የመጣበትን ትላንትናዊ ጎዳና ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው:: ቀድሞ ሰዎችን በብሔራቸው ለይቶ መረጃ በመያዝና ገጀራና መጥረቢያ ጭምር አስታጥቆ ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ አማራ ሆኖ የተገኘን እያረደ፤ጆሮ እና ምላስ እየቆረጠ በስለት ሆድ እየዘረገፈ እና እየቆራረጠ ለአማራ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ በተግባር አሳይቷል::ነፍሰ ጡር እናቶች ሆዳቸው በስለት እየተቀደደ ከሰው ልጅ አእምሮ በላይ የሆነ እጅግ አረመኔአዊ ተግባራትን ፈጽሟል:: ህጻናትን በመድፈር፣ የሰዎችን ቤት በማቃጠል፣ ልጆችን ወላጅ ፊት በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፤አባትን በሚስቱና በልጆቹ ፊት አንበርክኮ በመግደል መጨረሻ የሌለውን አረመኔያዊ ድርጊቱን አሳይቷል::
እንደ ማይካድራ በግልጽ አይውጣ እንጂ በህወሓት የስልጣን ዘመን በኢትዮጵያውያን ላይ በርካታ በደሎች እዛም እዚህም ሲፈጸሙ ነበር:: አገራችን ኢትዮጵያ በህወሓት የስልጣን ዘመን የደረሰባትን ያክል ኪሳራ መቼም አጋጥሟት አያውቅም:: በእያንዳንዳችን ትላንት ውስጥ በህወሓት የተጻፉ በርካታ አዳፋ ታሪኮች አሉ:: ዛሬ ላይ እንደ ወጣት አገርና ሕዝብ ከመጥቀም ይልቅ በማይጠቅመን የብሄር አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቀን የምንኖረው ያለፈው ስርዓት ያሳደረብን ተጽዕኖ ነው:: በሰው ልጅ ላይ ተጀምረው በሰው ልጅ ላይ የሚያበቁ በርካታ ሰዋዊ ግፎች መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው የህወሓት የተንኮል ሴራ ነው:: አገራችን ኢትዮጵያ ለአገርና ሕዝብ ባልቆሙ ራስ ወዳድ ቡድኖች ለሃያ ሰባት አመታት የኋሊት ተጉዛለች:: ከጥፋታቸው ከመማርና ሕዝቡን ይቅርታ ከመጠይቅ ይልቅ ዛሬም በዚህ ጥንታዊ እሳቤአቸው ውስጥ ሆነው የተስፋ ጎህ የቀደደላትን ሀገር ለማጨለም ሌት ተቀን እየሰሩ ነው::
መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የጽሞና ጊዜ ለመስጠትና አርሶ አደሩ በነጻነት ተንቀሳቅሶ የግብርና ስራቸውን እንዲያከናውን የተናጠል የተኩስ ስምምነት ለማድረግ መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል መውጣቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ይሄው አሸባሪ ቡድን ከተደበቀበት ወጥቶ እንደለመደው ሕዝብ በማስጨነቅ ላይ ይገኛል:: የህወሓት የተንኮል ሴራ በዋናነት አማራነት ላይ ያጠንጥን እንጂ ሁሉንም ብሄር የሚነካ ነው:: ለሃያ ሰባት ዓመታት የተሰሩብን የብሔር እሳቤዎች የጋራ ችግሮቻችን ናቸው:: በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የተዘረፉ የአገር ሀብቶቻችን የጋራ ንብረቶቻችን ናቸው:: ይህ ማለት የአሸባሪው ህወሓት ተንኮል በሁላችንም ህልውና ላይ እጁ አለበት ማለት ነው:: የህወሓት እጆች መልካም የሚመስሉ የተንኮል እጆች ናቸው:: እየዳሰሱ የሚሻክሩ:: እየዳበሱ የሚያሙ:: ሊቆጨን ከተገባ በህወሓት የስልጣን ዘመን ያለፉት እነዛ ዘመናት ሊቆጩን ይገባል እላለሁ:: በህወሓት የስልጣን ዘመን ፊተኛይቱ አገር በብሔር ፖለቲካ ግፍ ታሪክን ጽፋለች:: በእኔነት ውስጥ የበቀሉ፣ እኛነትን የገደሉ ብዙ መርዛም አሻራዎችን ከትባለች:: አሁናዊ ሥነ ልቦናችን እንኳን ያለፈው ሥርዓት የፈጠረው አግድም አደግ እሳቤ ነው::
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ከህወሓት ሌላ አገር ለማፍረስ ስልጣን የያዘ መንግስት አላውቅም:: አገር ከሚጠቅም ይልቅ አገር በሚጎዱ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይትን የሚያደርግ፣ ሕዝቦችን በዘርና በብሔር በመለያየት ግላዊ አጀንዳውን ሲያስፈጽም የኖረ መሪ አላውቅም:: አገራችን ኢትዮጵያ ካለቀሰችባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ራዕይ በሌለው የአሸባሪው ህወሓት መንግስት መመራቷ ነው :: ለዚህ ደግሞ ባለፈው የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ የታዩ ክፍተቶችንና አገራዊ ስንክ ሳሮችን እንደ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል:: ሁሉንም ብንተወው እንኳን በማይካድራ በአማራ ንጹሐን ላይ ያደረሰው በደልና ሞት አፍ አውጥቶ የሚናገር ህያው ምስክር ነው:: አሁን ድረስ አገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን አስተማማኝ የለውጥ ጎዳና ለማደናቀፍ የምንግዜም ጠላቶቻችን ከሆኑት ግብጽና ሱዳን ጋር በማበር በሕዝብ ሉዓላዊነት ላይ ቁማር በመጫወት ከሀዲነቱን በድጋሚ በማሳየት ላይ ይገኛል::
በሥልጣን ላይ እያለ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስገደድ በርካታ ግፍና በደልን አድርሷል:: ከመጀመሪያ ከመሰረቱ ህወሓት እንደ ድርጅት ሲመሰረት አላማና እቅዱ በብሔረሰቦች መካከል የለየለት ጠብና መለያየትን በመፍጠር የአንድ ብሔር የበላይነትን ማቀንቀን ነበር:: እንዳሰበውም ለዘመናት ተዋደው የሚኖሩ ሕዝቦችን በመከፋፈልና የጠብ ቁርሾ በመፍጠር የበላይነቱን ሲያስጠብቅ ኖሯል:: ከሶስት ዓመታት ወዲህ ግን በሕዝቦች የበረታ ትግል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህልውናውን አጥቷል:: የህወሓትን አመሰራረት ከመነሻው ጀምሮ ብናየው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የፈየደው አንድም ነገር አልነበረም:: የእኔና የእናንተን ትውልድ ምስክር አድርጌ ብናገር እንኳን ብሔር ተኮር እሳቤአችን የተፈጠረው በዚህ ድርጅት የሥልጣን ዘመን ነበር:: ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ከሚያውቁ አባቶቻችን አብራክ በቅለን እንኳን ህወሓት በጫነብን የዘር እሳቤ በጥርጣሬ የሚተያይ ትውልድ ለመፍጠር ብዙ መንገድ ሄዷል::
በህወሓት ርዕዮተ አለም ውስጥ አገርና ሕዝብ የሉም:: ከተልዕኮው አንዱ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል የአንድን ቡድን የበላይነት ማረጋገጥ ነበር:: ለዚህም አላማው እንዲበጀው ባልነበረ ታሪክና ያልተጻፈ የውሸት ትርክት በመፍጠር ብሔርን ከብሔር በማጋጨት ስውር ዓላማውን ሲያስፈጽም ቆይቷል::
የማይካድራም ጭፍጨፋ አንድ ቀን የስራ ውጤት አይደለም::አሸባሪው ህወሓት አስቦና አልሞ ለ27 ዓመታት የሰራበትና እኩይ ምግባሩን ያሳየበት ወራዳ ስራው ነው::ከጭፍጨፋው በፊትም ቢሆን በማይካድራ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን በማዳከምና ከ700 አባወራዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በመሰወር አማራን የማዳከም ስራ ሲሰራ ቆይቷል::በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት ጭምር መለስተኛ ህክምና ለማድረግ የመጡ ሰዎች አፍኖ በመግደል የአማራን ብሔር የማጽዳት ስራ ሲሰራ መቆየቱን እማኞች ይናገራሉ::
በአጠቃላይ የማይካድራ ጭፍጨፋ የአሸባሪው ህወሓት አረመኔያዊነት የተገለጠበት መድረክ ነው::ሆኖም ግን ይህን አረመኔያዊ ተግባር ለመሸፋፈን በጦርነት ያስፈጃቸውን ሰዎች ሬሳ በመሰብሰብ መንግስት የጅምላ ጭፍጨፋ አካሂዷል የሚል ክስ ለማቅረብ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ይመስላል::የእርሱ ጋሻ ጃግሬ የሆኑ ምእራባውያንና ሚዲያዎቻቸው የተቀነባበረ ዘመቻቸውን ለማድረግ በሟሟቅ ላይ ይገኛሉ::ሆኖም ግን የሐሰት ክምር እውነትን አያጠፋውምና በንጹሐን ላይ የተደረገው የማይካድራ ጭፍጨፋ ትውልድ የሚፋረደው ይሆናል::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013