ጊዜው ለሀገራችን ፈታኝ የሚባልበት ነበር:: እናት ወንድ ልጇን ስለምን ወለድኩት? ብላ የምታዝንበት፤ የት ላግባው? ከምንስ ልደብቀው? ስትል የምትጨነቅበት ክፉ ዘመን:: የዛኔ ወታደራዊው የደርግ መንግስት አፍላ ወጣቶችን በግዴታ ለጦርነት ይመለምል ነበር:: በወቅቱ አጠራር ‹‹አፈሳ›› በሚባለው ሂደትም በርካታ ወጣቶች እንደወጡ ቀርተዋል:: ጥቂት የማይባሉት የጠዋት ህልማቸው መክኖ በአስከፊው ጦርነት ተማግደዋል::
የዛኔ ውትድርና ይሉት ግዳጅ ለእንዲህ አይነቶቹ ወጣቶች መቅሰፍት ነበር:: ወደው ሳይሆን ተገደው በሚገቡበት ህይወትም እነሱን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው፣ ተጎድተዋል:: ታናናሾቻቸው ሳይቀሩ ፣ መጪውን ዕድል እያሰቡ ሲሳቀቁ ሲጨነቁ ኖረዋል::፡
የዛኔ የጦርነት ዘመቻው ‹‹ብሄራዊ ውትድርና›› በሚል ሰበብ የሚከወን ነበር:: በዚህ አይቀሬ ግዳጅም ወጣት የሚባል ሁሉ በሩ እየተንኳኳ፣ ጓዳና ጓሮው እየተፈተሸ ፣ ከየቤቱ ይለቀም ነበር:: ይህ ዘመን ለዛ ዘመን ትውልድ የሞት፣ የሰቆቃና የመከራ ጊዜ ሆኖ አልፏል:: ዛሬ ላይ ቆመው ወቅቱን በ ‹‹ነበር›› የሚያወጉ የዛኔው ትውልድ ከዕድሜው ላይ የቀነሰውን ክፉ ዘመን በዋዛ አይረሱትም:: በአስቸጋሪው መንገድ የተጓዙ ፣ ልጆቻቸውን ለሞት የገበሩ ፣ በዘመኑ ለበቅ የተገረፉ ሁሉ ጠባሳው ዛሬ ድረስ ክፉ ማስታወሻቸው ነው::
የደርግ ሥርዓት ተወግዶ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ የሀገሪቱ ፖሊሲዎች በአብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ ዴሞክራሲ መርሆች ሲመራ ቆይቷል:: በስመ- ዴሞክራሲ ስያሜ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተሸብቦ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብም በርካታ እሾሃማ መንገዶችን እንዲያልፍ ግዳጅ ተጥሎበታል::
በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ያለፈችበት አስከፊ የጦርነት ህይወት ፈጥኖ አልተደገመም:: በግፍ የተበተነው የቀድሞ ሰራዊት በሌላ ሃይል ተተካ:: የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት እስኪቀሰቀስም ለጊዜው ሀገራችን በውጊያ የቆሰለ ጎኗ አገገመ:: በዚህ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ህዝቡ የሰላም አየርን ተነፈሰ:: የጦርነት የዘመቻ ወሬዎች የተረሱ መሰሉ:: ለአዲሱ ሰራዊት ግንባታ ወጣቱ እንዳለፈው ዘመን በገሀድ ከየቤቱ አልተለቀመም:: እናቶችም ቢሆኑ ልጆቻቸውን በግዳጅ ሸኝተው የሞት ደብዳቤን አልጠበቁም::
ይህ እውነታ ብዙ አልቆየም:: የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት ፈነዳ:: ይኸኔ በርካቶች ለድንገቴው ጦርነት ግንባር መሄዳቸው ግድ ሆነ:: በፍላጎት ዘመቻውን የሚቀላቀሉ በሀገር ፍቅር ስሜት ወደ ማሰልጠኛ ነጎዱ:: ለዚህ ጦርነት ዝግጁ ያልሆኑት ግን ከአጥማጆቻቸው መረብ ሊወድቁ ተገደዱ::
ይህ ዘመን ፍላጎትን የተዋዛ በሚመስል የእጅ አዙር አስገዳጅነት ስር የወደቀ እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ:: በማር በተቀባ መርዛማ ስልት ለጦርነት የሚመለመሉት ወጣቶችም የወዳጅ በሚመስል ግዳጅ የተጠለፉ፣ በካድሬዎች ነበሩ::
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የወረዳ አመራሮች በየገጠሩ ቀበሌ የተጣለባቸውን የዘማች ኮታ ሊያሟሉ ግድ ነበር:: አንድ አመራር የተሰጠውን የወጣት ቁጥር ኮታ አሟልቶ መገኘት ስራው ብቻ ሳይሆን አይቀሬ ግዴታው ነበር::
ጦርነቱ እየተፋፋመ የተዋጊ ኃይል ቁጥር ባስፈለገ ጊዜ አመራሮቹ ወጣት ተመልማዮችን ለማደን የራሳቸውን ስልት መጠቀም ያዙ:: በተለይ የገበያ ቀን በሆነ ጊዜ ከህዝቡ መሀል እየተገኙ ወጣቶችን መፈለግና ማሰስ ልምዳቸው ሆነ:: አፈላለጋቸው ቅንነት የተሞላ አልያም ፈቃደኝነትን የተላበሰ አልነበረም:: በስፍራው ሲቆሙ ዓይኖቻቸው አሻግረው ያማትራሉ:: የተጣለባቸውን የኮታ ቁጥር እያሰቡም ግዴታቸው የሚሞላበትን ስልትና ዘዴ ይፈልጋሉ::
የእነሱ የመጀመሪያ ስልት በአስገዳጅነት ወጣቶችን እያሳደዱ መያዝ ይሆናል:: ግዳዮቻቸውን አንቀው በማጎሪያ ሲዘጉባቸውም አገሬው ለራሱ ልጆች ቀለብ እንዲያቀርብ ሌላ ግዴታ በመጣል ነው:: ጊዜው ደርሶ ወጣቶቹን በመኪና እየጫኑ ሲወስዱ የኮታቸው ልክ ከመሙላት አልፎ ገደብ መጣሱ ያስደስታቸዋል:: ለእነሱ የስልጣን ማቆያና መመሰገኛ ሆኖ የቆየው የኮታ ፖለቲካ ለድሃው ገበሬ ልጅ እንደወጣ መቅረት ምክንያት ሆኖ የብዙዎችን ጎጆ አዘግቷል::
የዘመኑ አመራር ተብዬዎች በወቅቱ ለሚዲያ ፍጆታ በሚያቅርቡት ወሬ ወጣቱ በሀገር ፍቅር ስሜት ለሀገር ዳርድንበሩ ከብር ‹‹አዝምቱኝ›› ስለማለቱ ሲዋሹና ሲቀጥፉ ኖረዋል:: ይህ ታሪክ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ዘመን በገጠሩ ክፍል የተፈጸመ እውነት ስለመሆኑ ብዙዎች ያውቁታል::
እነሆ! ዛሬ ደግሞ ከነባር ታሪኮች በተለየ አዲስ ምዕራፍ እውን መሆን ይዟል:: አሁን በርካታ ወጣቶች የማንም አስገዳጅነት ሳይጫናቸው፣ የውትድርናውን ዓለም እየተቀላቀሉ ነው:: ወጣቶቹ ሀገራቸው ለገጠማት የሰላም እጦት ምላሽ ለመስጠት ጎትጓችና ቀስቃሽ አላሻቸውም:: እንደቀድሞ ልማድም ከመንገድ ታፍሰው ፣ አልያም በሽንገላ ታምነው አልወጡም::
የእነሱ ስሜት በሀገር ፍቅር ደምቆ፣ በሰላም ዓላማ ታጥሯል:: የእነሱ እውነት ላይበገር ጠንክሮ፣ በድንቅ ታሪክ ተውቧል:: ወጣቶቹ አሸባሪው የህውሓት ቡድን አገር ለማፍረስ፣ ህዝብ ለመበተን የሸረበውን ሴራ አሳምረው ያውቃሉ:: በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽመው ኢ ሰብዓዊ ድርጊትም ህመም ስቃያቸው ነው::
ኢትዮጵያዊነት ለእነሱ ከፊደልና ከቃል በላይ ሆኗል:: ህግ በማስከበር፣ አገርን ለማዳን በሚደረገው ዘመቻ ጠላታቸውን በግንባር ለመፋለም ተዘጋጅተዋል:: ይህ ጦርነት የህልውና፣ አገርን የማዳን ግዳጅ ነው:: ይህ ግዳጅም የብዘዎችን ስሜት አንቅቶ ራስን ለመስዋዕትነት አዘጋጅቷል::
ወጣት ቃልኪዳን እንየው ከልጅነቷ ጀምሮ ለሀገር ፍቅር ያደረው ስሜቷ እስከወጣትነቷ ዘልቋል:: ቃልኪዳን የጀግና ወታደር ልጅ ነች:: አባቷ የሀገርን ዳርድንበር ለማስከበር ከጦር ሜዳ ውለዋል:: ይህ እውነታ ስለእናት ሀገር ፍቅርና ስለወገን ክብር እየሰማች እንድታድግ እድል ሰጥቷታል::
ቃልኪዳን የመከላከያ ሰራዊትን በፈቃዳቸው ለመቀላቀል ከወደዱ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት:: በቅርቡም በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሽኝት ለዘመቻው ያላትን ቁርጠኝነት በገሀድ አረጋግጣለች::
እንደ ቃልኪዳን እምነት ስለሀገሯ ፍቅር ፣ ስለወገኗ ክብር የማትሆነው የለም:: ትናንት ከወታደር አባቷ የምታውቀውን ጀግንነትና ወገናዊ አደራ ዛሬ ላይ መረከቧ የአገራዊ ኩራቷን ከፍታ አሳድጓል:: አሁን ቃልኪዳን ሰላም በማስከበሩ ዘመቻ ግንባር ቀደሟ ወጣት ሆናለች:: በዚህም ታላቅ ደስታና ክብር ይሰማታል::
በቅርቡ በመስቀል አደባባይ በተደረገው የጀግና አሸኛኘት በአገር ፍቅር ስሜት የነደዱ ፣ በሰንደቅ ዓላማቸው የደመቁ በርካታ ወጣቶች ለወገን ክብር መንበርከካቸውን አረጋግጠዋል:: ወጣቶቹ ያለማንም ጉትጎታና አነሳሽነት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ለመሰለፍ ሲወስኑ በተለየ አገራዊ ኩራት ነው::
የአዲስ አበባ ነዋሪው ወጣት ዳንኤል ደመቀ በእለቱ በነበረው የሽኝት መሰናዶ ሲገኝ በሙሉ የአይበገሬ ስሜት ሆኗል:: ጊዜው ሁሉም ለእናት አገሩ ጥሪ ምላሽ የሚሰጥበት ነው:: ወቅቱ ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጥቃት የበረከተበት ነው:: ዳንኤል ከሰላምና ከአንድነቱ የሚያስበልጠው የለምና የህግ ማስከበሩን ሂደት ሲቀላቀል በተለየ ወኔና ልበ ሙሉነት ሆኗል::
የኢትዮጵያዊነት ንጹህ ፍቅር በተንጸባረቀበት የአሸኛኘት መርሀግብር ላይ በርካቶች የኢትዮጵያ ሰንደቅላማን እንደሸማ ለብሰው ፣ በአገራዊና ስሜት ቀስቃሽ ዜማዎች ታጅበው ወጣቶቹን ሸኝተዋል:: ይህ እውነታ ብዘዎችን ለቀጣዩ የዘመቻ ምዕራፍ አዘጋጅቷል::
በስፍራው የተገኙ ሁሉ ብሄርና ቋንቋ ፣ ዘርና ሃይማኖት ይሏቸው ጉዳዮች አልጠሯቸውም:: የእነሱ ዓላማ የስማቸው መጠሪያ የሆነች አገራቸውን ከአሸባሪው የህውሓት ጥርስና ከምዕራባውያን ጫና ማላቀቅ ነው:: የወጣቶቹ እውነተኛ ስሜት በመስዋዕትነት በሚገኝ ዋጋ ታላቋን ኢትዮጵያ በደማቅ ስሟ ከነክብሯ ማንገስ ነው::
ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን በጀግኖቿ ተጋድሎ አፍራ አታውቅም:: ይህን እውነታም ጠላቶቿ ጭምር አሳምረው ይመሰክራሉ:: ያለሀገር መቆም፣ በክብር መኖርና መተንፈስ ዘበት መሆኑ የገባቸው ድንቅ የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬ በተለየ አገራዊ ስሜት ከየአቅጣጫው እየተመሙ ነው::
አሁን የ‹‹ደብቁኝ›› ዘመን አልፎ የ‹‹አዝምቱኝ›› ምዕራፍ ተጀምሯል:: ወጣቶቹ የጀግኖች አባቶቻቸውን ታሪክ በመድገም ደማቅ አሻራ ለማኖርም በሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ቃል ገብተው ለህልውናው ዘመቻ ዘብ ቆመዋል::
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013