በርካታ አስደናቂና የማይጠበቁ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ የሚገኘው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያውያን አንዴ በድል አንዴ ደግሞ ግራ በሚያጋቡ ውዝግቦች ታጅበው የቶኪዮ ቆይታቸውን በማገባደድ ላይ ናቸው።ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ እንደተለመደው በአትሌቲክስ በርካታ ሜዳሊያዎችን እንደምትሰበስብ የምትጠበቅ ብትሆንም፣ እስካሁን 1 ወርቅ 1 ብር እና 1 ነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት ተወስናለች።
ትናንት ፍጻሜ በተካሄደበት 800 ሜትር ውድድር የተካፈለችው አትሌት ሀብታም ዓለሙ ስድስተኛ በመሆን ውድድሯን ፈጽማለች።የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ አትሌት የሆነችው ሀብታም ሀገሯን ወክላ መሳተፍ የጀመረችው እአአ በ2015 ሲሆን፤ የተሳተፈችባቸው መድረኮችም የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ነበሩ።
በቀጣዩ ዓመትም በተመሳሳይ በፖርትላንድ በተካሄደ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ የዲፕሎማ ተሸላሚ ለመሆን ችላለች።በሪዮ ኦሊምፒክም በዚሁ ርቀት ስትካፈል በዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በቤት ውስጥ ቻምፒዮናም በተደጋጋሚ ሀገሯን በመወከል ልምድ ያላት አትሌት ናት።ሀብታም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በተካፈለችባቸው ውድድሮች ሜዳሊያ ባታስመዘግብም በየጊዜው ሰዓቷን እያሻሻለች መምጣቷ ግን በዚህ ውድድር የተሻለ ግምት አሰጥቷት ነበር።
በማጣሪያ ውድድሮች ላይም የተሻለ ብቃቷን በማሳየት ለፍጻሜው የደረሰች ሲሆን፤ ይህም በርቀቱ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ሆናለች።ሜዳሊያ ለማጥለቅ ብርቱ ተፎካካሪ እንደምትሆን በግልጽ ያመላከተ ነበር።በመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር የሮጠችው በ2:01.20 ሰዓት ሲሆን፤ ከምድቧ
ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ለግማሽ ፍጻሜው ያለፈችው።ከቀናት በፊት በተካፈለችበት የግማሽ ፍፃሜ ውድድርም ኢትዮጵያን በመወከል በብቸኝነት በመሮጥ ከምድቧ 1:58.40 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃ በመያዟ ነበር ለትናንቱ የፍጻሜ ውድድር ማለፍ የቻለችው።
በአጭርና መካከለኛ ርቀት አትሌቷ ሀብታም ብቸኛዋ የኢትዮጵያ እና አፍሪካ ተወካይ በመሆን በውድድሩ ላይ የተካፈለችው።ይሁን እንጂ በተለይ ከአሜሪካ እና እንግሊዝ አትሌቶች በገጠማት ብርቱ ፉክክር ለሜዳሊያ የነበራትን ቦታ አጥታለች።አትሌቷ ከውድድሩ መነሻ አንስቶ በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ በሚያስችላት ሁኔታ ብትሮጥም በመጨረሻ ግን ተፎካካሪዎቿን መርታት ባለመቻሏ ስድስተኛ 1:57.56 በሆነ የራሷ ፈጣን ሰዓት የዲፕሎማ ባለቤት ለመሆን ችላለች።ይህም ሃብታም በዚህ ርቀት ኦሊምፒክ ላይ የዲፕሎማ ደረጃ ያስመዘገበች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መሆን ችላለች።
ኢትዮጵያ በተለይ የምትታወቅበት የ5 ሺ ሜትር የወንዶች የማጣሪያ ውድድር ትናንት ሲካሄድ አንድ አትሌት ብቻ ወደ ፍፃሜ ማለፉ በርካታ ኢትዮጵያውንን አስቆጥቷል።በአንደኛው ምድብ የተካፈለው አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ በ 13፡31፡13 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ የተሻለ ሰዓት በማስመዝገቡ በፍፃሜው ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክል ብቸኛው አትሌት ሆኗል።በሌላኛው ምድብ ሁለት አትሌቶች ሲካፈሉ፤ ከትናንት በስቲያ በ3 ሺ ሜትር መሰናክል የተካፈለው ጌትነት ዋለ 9ኛ ደረጃን በመያዙ ወደ ፍጻሜው ማለፍ አልቻለም።ሌላኛው አትሌት ንብረት መላክም 14 በማጠናቀቅ በተመሳሳይ ማጣሪያውን ሳያልፍ ቀርቷል።ይህም የርቀቱ የዓለም ቻምፒዮን ሙክታር ኢድሪስን ጨምሮ ሰኞ እለት የ10 ሺ ሜትር አሸናፊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ እዚያው ቶኪዮ እያሉ እንዲሳተፉ እድል አለማግኘታቸው ኢትዮጵያን በርቀቱ የተለመደ ውጤት እንዳታስመዘግብ ያደረገ አሳፋሪ ክስተት በመሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል።
ከትናንት በስቲያ ሌሊት በተካሄደው የወንዶች የ 1500 ሜትር ማጣሪያ በምድብ 1 የተወዳደረው እና በ9 ኛነት ያጠናቀቀው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በተሻለ ሰአት ወደቀጣዩ ዙር አልፏል የሚለው መረጃ ቢወጣም መረጃው የወጣው የሶስተኛው ምድብ ወድድር ሳይጠናቀቅ በመሆኑና በምድብ ሶስት በተደረገው የማጣሪያ ውድድር የተሻለ ሰአት የተመዘገበበት በመሆኑ ሳሙኤል ተፈራ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ከየምድቡ ከ1ኛ -6ኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ የሚያልፉበት እና ከየምድቡ የተሻለ ሰአት ያላቸው 6 አትሌቶች ሰአታቸው ታይቶ ወደ ቀጣዩ ዙር በሚያልፉበት የማጣሪያ ውድድር የተሻለ ፉክክር በታየበት በምድብ 3 ውድድር ከ1ኛ -10 ኛ ደረጃ ያሉት አትሌቶች በቀጥታ እና በተሻለ ሰአት ወደቀጣዩ ዙር አልፈዋል። በዚህ መሠረት በ 1500 ሜትር ማጣሪያ የተወዳደሩት ሳሙኤል አባተ በ5ኛነት እና ታደሰ ለሚ በ2ኛነት በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል። የኦሊምፒኩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ዛሬ ከሰዓትም ሲቀጥሉም ኢትዮጵያ የምትካፈልበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል የሴቶች ውድድር ውጤት ሊመዘገብ ይችላል በሚል ይጠበቃል።በዚህ ርቀት ሁለት አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ከ 9 ዓመታት በፊት በለንደን ኦሊምፒክ የተጻፈውን ታሪክ ለመድገም ይሮጣሉ።በማጣሪያው መቅደስ አበበ በ9:23.95 ሶስተኛ ወጥታ ያለፈች ሲሆን፤ ዘርፌ ወንድማገኝ ደግሞ በ9:20.01 ሰዓት አራተኛ በመሆን ነው ፍጻሜውን የተቀላቀለችው።
ለንደን ኦሊምፒክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ርቀት በሴቶች አትሌት ሶፊያ አሰፋ የብር ሜዳሊያ መመዝገቡ የሚታወስ ነው።በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዶሃ ላይ ሀገሯን የወከለችው መቅደስ አበበ፤ በዚያው ዓመት በተካሄደው የአፍሪካ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለች ወጣት አትሌት ናት።በርቀቱ የብሄራዊ ክብረወሰን ባለቤት (9:02.52) የሆነችው አትሌቷ በዳይመንድ ሊግም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።
በተመሳሳይ በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሀገሯን የወከለችው ወጣቷ አትሌት ዘርፌም በዛሬው የፍጻሜ ውድድር አዲስ ነገር ልታሳይ እንደምትችል ይጠበቃል።በሄንግሎ በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር ርቀቱን 9:16.95 የሮጠችው አትሌቷ በሀገር ውስጥ ከ20 ዓመት በታች ምርጥ ሰዓት ነው።በዚህ ርቀት የተሻለ የአሸናፊነት ታሪክ ያላቸው ኬንያውያን አትሌቶች ሲሁኑ በዛሬው ውድድር ግን ኢትዮጵያውያኑ የሜዳሊያ ተፎካካሪ የሚሆኑበት እድልም የሰፋ እንደሚሆን የዓለም አትሌቲክስ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013