የዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት ክፍለ ከተሞች አንዱ ወደ ሆነው የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ይወስደናል።በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የቀበሌ ቤቶች ወይም የመንግስት ቤቶች ይገኛሉ። በእነኚህ ቤቶችም ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርም እጅግ በርካታ ነው።በአንድ ጊቢ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርም በርካታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰዎችም ፍላጎትም የተለያየ እንደሚሆን ይጠበቃል።የሰዎች ፍላጎት መለያየት ደግሞ ብዙ ጊዜ ሰዎችን ወደማይገባ ጸብ እንደንደሚያስገባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
የዛሬው ፍረዱኝ አምዳችንም ከዚህ ጋር የተያያዘ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በፍረዱኝ አምዱ ስለጉዳዩ ከመረመረ በኋላ የዝግጅት ክፍሉ በምርመራ የደረሰበትን እና አቤቱታ አቅራቢዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ያሏቸውን አስተያየቶች እና ውሳኔዎች የያዘ በመሆኑ ዛሬ ስለምንመለከተው አቤቱታ የግራ ቀኙን በማየት ህዝብ መፍረድ ይችል ዘንድ እነሆ ብለናል።
ወይዘሮ ሂሩት መኩሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በመንግስት ቤቶች ስር በሚተደዳረው 952 ቁጥር ቤት ነዋሪ ናቸው።ወ/ሮ ሂሩት መኩሪያ ስለጉዳዩ ያብራሩልኛል ያሏትን ልጃቸውን ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብርሃኑን በመወከል ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር አገናኙን።ተወካይ ልጃቸው ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብርሃኑም ደርሶብናል ያለችውን በደል በዝርዝር ገልጻልናለች።
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የወይዘሮ ሂሩት መኩሪያ ልጅ ናቸው።እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ገለጻ እናታቸው ወይዘሮ ሂሩት መኩሪያ ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ እማሆይ ጥሩወርቅ ይማም ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር።ይሁን እና ከደርግ መንግስት መምጣት ጋር ተያይዞ ትርፍ ቤት ያላቸው ሰዎች ቤታቸው ሲወረስ የእማሆይ ጥሩወርቅ ይማም ቤት ግማሹ በመንግስት ይወረሳል።በመንግስት ከተወረሰው ቤት መካከልም ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ ወይዘሮ ሂሩት መኩሪያ የተከራዩት ቤት ይገኝበታል።በመሆኑንም ከእማሆይ ጥሩወርቅ ቤት ተከራይተው ይኖሩ የነበሩት ወይዘሮ ሂሩት መኩሪያ ቤቱ ከመወረሱ ጋር ተያይዞ ከእማሆይ ጥሩወርቅ ይማም ጋር የተከራይ አከራይ ውል ተቋርጦ በምትኩ የአከራይ ተከራይ ውላቸውን ከመንግስት ጋር አደረጉ።ከእማሆይ ጥሩወርቅ ይማም ጋር የአከራይ ተከራይ ውሉ ይቋረጥ አንጂ የሚኖሩት ግን በአንድ ጊቢ ነበር።በአንድ ጊቢ ሲኖሩም አንች ትብሽ አንች ትብሽ ተባብለው በመልካም የጉርብትና ዓመታትን አሰለፉ።
ነገር ግን በቀን 15 /04/2012 ዓ.ም አንድ ነገር በጊቢው ውስጥ ተፈጠረ።ይህም በጊቢው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በርካታ (127 ሰዎች) ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረው ሽንት ቤት ይሞላ እና በጤናቸው ላይ እክል መፍጠር ይጀምራል።በዚህም የተነሳ በጊቢው ውስጥ የሚኖሩ ከ12 በላይ አባውራዎች እና እማውራዎች ሽንት ቤት ይሰራላቸው ዘንድ ለወረዳ ዘጠኝ አቤት ይላሉ።ወረዳ ዘጠኝም ያለውን ችግር ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አዲስ ሽንት ቤት በጊቢው በሚገኝ የመንግስት ይዞታ ላይ አራት ክፍል ያለው ሽንት ቤት አሰርቶ ለጊቢው ነዋሪዎች ያስረክባል።
በዚህ ጊዜ ለዓመታት ንፋስ ሳይገባበት የኖረው የወይዘሮ ሂሩት እና የእማሆይ ጥሩወርቅ ግንኙነት መሻከር እንደጀመረ የወይዘሮ ሂሩት ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ያስረዳሉ። እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ገለጻ ፤ ለጸባቸው መነሻም የሆነው በፊት ሲጠቀሙበት ከነበረው ሽንት ቤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት ነው።
እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤት ገለጻ በፊት ሲጠቀሙበት የነበረውን ሽንት ቤት እማሆይ ጥሩወርቅ የኔ ነው ይላሉ። ስለሆነም በፊት ሽንት ቤት ለመጠቀም ሁሉም ተከራይ ሲመላለስበት የነበረውን መተላለፊያ መንገድ እማሆይ ጥሩወርቅ ከአሁን በኋላ አዲስ ሽንት ቤት ስለተሰራ በዚህ መንገድ መጠቀም አትችሉም ይላሉ።ይህ መንገድ ለእነ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ የሽንት ቤት መተላለፊያ መንገድ ብቻ አይደለም።ይልቁንም የፈሳሽ ቆሻሻ መስወገጃ እና ቤታቸው በጣም ጠባብ ከመሆኗ የተነሳ ምግብ ለማብሰል የወጠሯትን ሸራ መተላለፊያ መንገድ ናት።ይች የሸራ ማብሰያ ወይዘሮ ሂሩት ከእማሆይ ጥሩወርቅ ጋር ከተዋወቁባት ጊዜ የነበረች እና አንዱ ሸራ ሲያረጅ ሌላ ሸራ እየተኩ ብዙ ያሳለፉባት ብዙ ልጆችን ያሳደገች የማዕድ ቤት ናት።
እንደ ወይዘሮ ኤልሳቤት ገለጻ እና የወረቀት ሰነዶች እንደሚያሳዩት መተላለፊያ መንገዱ በቤት ቁጠር 953 እና በቤት ቁጠር 954 መካከል ያለ ነው።ቤት ቁጥር 954 የእማሆይ ጥሩ ወርቅ የይዞታ ቤታቸው ሲሆን የቤት ቁጥር 953 ደግሞ በመንግስት ስር የሚገኝ እና መንግስት ለተከራዮች አከራይቶ የሚያስተዳድረው ነው።
ነገር ግን እማሆይ ጥሩ ወርቅ 954 እና 953 የተባሉትን ቤቶች በማገናኘት 953 የሚባል ቤት የለም በማለት መተላለፊያ መንገዱን ለመዝጋት ግንባታ እንደጀመሩ ነገር ግን በፍርድ ቤት በመሄድ ሁከት ይወገድል በማለት አቤት እንዳሉ ወይዘሮ ኤልዛቤት ይናገራሉ።
የፍርድ ቤት ሙሉ ክርክር
ወይዘሮ ሂሩት በየካቲት 10/2013 ዓ.ም ለፍርድ ቤት በተጻፈበት የክስ ማመልከቻ አንደኛ ተከሳሽ እማሆይ ጥሩወርቅ ይማምን ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 09 የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤትን መክሰሳቸውን የወረቀት ሰነዶች ያመለክታሉ።
ከሳሽ የካቲት 10/2013 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከሳሽ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የቤት ቁጥር 952 የመንግስት ቤት ላይ ተከራይ መሆናቸውን ነገር ግን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ በመመሳጠር ከሳሽ ላይ የሁከት ተግባር መፈጸማቸውን ይኸውም የከሳሽ የቤት ቁጥር 952፣ የ 1ኛ ተከሳሽ የቤት ቁጥር 954 እንዲሁም ሌላ የከሳሽ አጎራባች የቤት ቁጥር 953 በአንድ ላይ የሚገኝበት ጊቢ ውስጥ ያለ የጋራ መተላለፊያ መንገድ በመዘጋቱ 1ኛ ተከሳሽ በዚህ የመንግስት የጋራ መተላለፊያና መጸዳጃ ቤት ላይ ከየካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሳሽ ክስ እስከ መሰረተበት የካቲት 10/2013 ዓ.ም ድረስ ህገ-ወጥ ግንባታ እየገነቡ እንደተሚገኙ፣ 2ኛ ተከሳሽም የቤቱ አስተዳደር ሆኖ እያለ ህገወጥ ግንባታ ሲደረግ ማስቆም ሲገባው ለ1ኛ ተከሳሽ ግንባታ እንዲያከናውን ፍቃድ መስጠቱ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1149 መሰረት የሁከት ተግባር በመሆኑ ሁከት እንዲወገድላቸው ለፍርድ ቤቱ ክሳቸውን በማቅረብ ስለጉዳዩ ያስረዱልኛል ያሏቸውና የሰነድ እና የሰው ማስረጃ ቆጥረው ማቅረባቸውን ወይዘሮ ኤልሳቤት ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 1ኛ ተከሳሽ የካቲት 22/2013 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የጽሁፍ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበው መቃወሚያው በብይን ውድቅ ተደርጎ ብይኑን ከመዝገቡ ጋር በማያያዝ በፍሬ ጉዳይ ላይ በሰጡት መልስ ተከሳሽ ክርክር የተነሳበት ቤት ባለቤት ሆኖ ሳለ ከሳሽ የሁከት ይወገድልኝ ክስ ለማቅረብ በመጀመሪያ በይዞታውና በንብረቱ ላይ ከተከሳሽ የተሻለ የባለይዞታነት መብት ሊኖራቸው ይገባም እንደነበር፤ ባለቤት የሆነው የመንግስት አካል የባለቤትነት ጥያቄ ባላቀረበበት እና ክርክር ባላነሳበት ሁኔታ ከሳሽ መጸዳጃ ቤቱ የመንግስት ነው በማለት ክስ የሚያቀርቡበት አግባብ አለመኖሩን አንደኛ ተከሳሽ እንዳስረዱ የወረቀት ሰነዶች ያሳያሉ።
ሌላው ከወረቀት ሰነዶች ማየት እንደሚቻለው ይህ ክስ የቀረበበት መፀዳጃ ቤት እና የጋራ መተላለፊያ መንገድ በከሳሽ የተጠቀሰው ይዞታ ተከሳሽ ይዞታ ላይ የሚገኝ መሆኑ ከ 1998 ጂ.አይ.ኤስ ከ 1997 ላይን ማፕ እና ከቀረበው ካርታ ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑን ይህንንም 2ኛ ተከሳሽ በሰጠው ምላሽ ማረጋገጥ እንደሚቻል፣ መጸዳጃ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ በባለቤትነት የያዙት እና ለረጅም ዓመታት ግብር የሚከፍሉበት መሆኑን እና 1ኛ ተከሳሽ በገዛ ፍቃዳቸው የቀበሌ ተከራዮች የሚጠቀሙበት መጸዳጃ ቤት በማጣታቸው ሲያስጠቅሙ መቆየታቸውን፣ ይህን መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ከሳሽ በመተላለፊያነት ሲጠቀሙበት የነበረ መንገድ መኖሩን በኋላ ግን ተከሳሽ ተከራዮች መጸዳጃ ቤቱን መጠቀም እንዲያቆሙ ማድረጉን ተከትሎ በወረዳው ስራ አስፈጻሚ በኩል ለ1 ኛ ተከሳሽ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መንግስት ለከሳሽ እና ለሌሎች የመንግስት ተከራዮች በ1ኛ ተከሳሽ ይዞታ ላይ ጋራ መጸዳጃ ቤት እንዲገነባ ተደርጎ ከሳሽ እና ሌሎች ተከራዮች በአዲሱ መጸዳጃ ቤት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ፣ አዲሱ መጸዳጃ ቤት የሚገኝበት ቦታም ቢሆን ከሳሽ የ1 ኛ ተከሳሽን ይዞታ በመተላለፊያነት ሳይጠቀሙ ለመገልገል የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ቀበሌው ባከራያቸው በየትኛውም አቅጣጫ ትክክለኛ መውጫ እና መግቢያ በመጠቀም መገልገል የሚችሉ መሆኑንና የጋራ መጸዳጃ ቤቱን ለመገልገል የሚያስችል በመሆኑ ክሱ ከቅን ልቦና ውጪ የቀረበ በመሆኑ ከበቂ ወጪ እና ኪሳራ ጋር በነጻ እንዲሰናበቱ አንደኛ ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ መመለሳቸውን እና ከመልሳቸው ጋርም የሰነድ እና የሰው ማስረጃዎችን ቆጥረው ማቅረባቸውን የወረቀት ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሁለተኛ ተከሳሽ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ወረቀት በህጉ አግባብ ተልኮላቸው መልስ በጽሁፍ ባለማቅረባቸው መብታቸው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 199 (1) መሰረት የታለፈ ሲሆን ክስ በሚሰማበት ወቅትም ባለመቅረባቸው ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 70 (ሀ) መሰረት ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱንም የወረቀት መሳረጃዎች ይጠቁማሉ።ውድ አንባቢያን ለፍርድ ይመቻችሁ ዘንድ ሁለተኛ ተከሳሽ (የወረዳ 9 አስተዳደር) የሰጠውን መልስ ከታች ስለምናስቀምጥ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ተከሳሽ መጥሪያ ቢሰጠውም በደብዳቤ እንኳን መልስ ሊሰጠን አልቻለም የሚለውን የፍርድ ቤቱን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በማየት የወረዳ 9 የቤቶች አስተዳደር ደግሞ ለፍርድ ቤት የላከውን ደብዳቤ ማየት የራሳችሁን ፍርድ እንድትፈርዱ ከወዲሁ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ።
ከሳሽ እና አንደኛ ተከሳሽ የክስ አቤቱታ በተሰማበት ወቅት በጽሁፍ ያቀረቡትን በቃል አጠናክረው ፍርድ ቤቱ ተከራክረዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ
ከላይ በከሳሽ እና ተከሳሽ መካከል የነበረውን ክርክር በማዳመጥ ፍርድ ቤት የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።ከሳሽ ክርክር ያነሱበት መጸዳጃ ቤት በአከራይ ተከራይ ውሉ ላይ የጋራ መጸዳጃ ስለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ መጣራትን አድርጓል።በ1 ኛ ተከሳሽ በኩል ይህ ለክርክር መነሻ ስለሆነው መጸዳጃ ቤት ባለመብት መሆናቸውን ያረጋገጥኩበት ነው ያሉትን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 195246 የተሰጠ ውሳኔ አቅርበዋል።
ውድ አንባቢያን በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 195246 ውሳኔ ግልጽ ይሆንላችሁ ዘንድ የተወሰነ ነገር ማለት ተገቢ ነው። ተከሳሽ እማሆይ ጥሩወርቅ በወይዘሮ ሂሩት ከመከሰሳቸው በፊት የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት እና ከበፊቱ ሽንት ቤት ጋር ተያይዞ የይገባኛል ጥያቄ አንስተው የወረዳ ዘጠኝን ቤቶች ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ከሰው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱም ለማሆይ ጥሩወርቅ መወሰኑን ከወረቀት ሰነዶች ማየት ይቻላል።ስለዚህ በመዝገብ ቁጥር 195246 ውሳኔ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዛዝ የሰጠበት መሆኑን ውድ አንባቢያን እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በመዝገብ ቁጥር 195246 ውሳኔ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽ የሆኑበት እና የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 09 ቤቶች ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ተከሳሽ የነበሩበት ሲሆን አሁን በዚህ መዝገብ ለክርክር መነሻ የሆነው መጸዳጃ ቤት በፌዴራል ፍርድ ቤትም ለክርክር መነሻ የነበረ ነው።1ኛ
ተከሳሽን ከሳሽ አላግባብ በመጸዳጃ ቤቱ ላይ የግንባታ ፍቃድ ከልክሎኛል በማለት ክስ ማቅረባቸውንና ፍርድ ሲሰጥም መጸዳጃ ቤቱ በ1988 ዓ.ም በተነሳ የአየር ካርታ እና በ1997 ዓ.ም ማፕ ሲታይ ከቤት ቁጥር 954 ይዞታ ላይ እንደሚታይ እንዲሁም በከሳሽ በአሁን አንደኛ ተከሳሽ ጊቢ ውስጥ ባለ ባዶ ቦታ ላይ የጋራ መፀዳጃ በብሎኬት ተሰርቶ በከሳሽ ጊቢ ውስጥ ላሉ የመንግስት ተከራዮች በጋራ የተሰራ ስለመሆኑ የታመነ መሆኑን፣ ግንባታ ፍቃዱ በተጠቃሚዎች ቅሬታ ስለቀረበበት ብቻ መከልከሉ አግባብ አለመሆኑ፣ መንግስት መጸዳጃ ቤቱ የኔ ነው የሚል ክርክር ሳያቀርብ ለከሳሽ ወይም ለአሁን 1ኛ ተከሳሽ የእድሳት ፍቃድ መከልከል አግባብ አይደለም በማለት ውሳኔ መስጠቱን ማየት ተችሏል።
አሁን በተያዘው ክርክርም ይኸው ውሳኔ የተሰጠበት መጸዳጃ ቤት ህገ-ወጥ ግንባታ ተገንብቶበታል በማለት በከሳሽ ክስ የቀረበበት የወይዘሮ ሂሩትን እና የእማሆይ ጥሩወርቅን የክስ ሂደት የያዘው ፍርድ ቤቱ ያስረዳል። ፍርድ ቤቱም አክሎም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ስለመሻሩ የቀረበ ማስረጃም ሆነ ክርክር እንደሌለ ተመልክቷል፤ ይህ በሆነበት ሁኔታ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት የክርክሩ መነሻ የሆነው መጸዳጃ ቤት 1ኛ ተከሳሽ ይዞታ ስር እንደሚገኝ አረጋግጦ ውሳኔ በሰጠበት እንዲሁም ተከሳሽ የሰጠውን እና ፍርድ ቤት የቤት ቁጥር 952 ቤት አስተዳደር የሆነው አካል የመጸዳጃ ቤቱ ባለቤትነት መብት ባልጠየቀበት ሁኔታ ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ህገ-ወጥ ግንባታ አድርገዋል በማለት ክስ ማቅረባቸውን መረዳት ተችሏል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ይረዳው ዘንድ ለወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት እና ለወረዳው የመሰረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በጋራ` በመሆን በወረዳ 09 የቤት ቁጥር 952 የሚገኝበት ጊቢ ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ እየገነቡት ያለ ግንባታ ይኑር አይኑር ፣ ካለ በማን ይዞታ ላይ እየተገነባ እንደሆነ ግንባታው የጊቢ መተላለፊያ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ካለ በባለሙያ በማጣራት ማብራሪያ እንዲልኩ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የመሰረተ ልማት ቅንጅት፣ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በደ/ቁአ/ክ/ከ/ወ/09/የተመ/ል/ቅ/ግ/ፋ/ቁጥ/ጽ/ቤት/239/2013በቀን10/09/13 በሰጠው ምላሽ ጽህፈት ቤቱ ከባለሙያና አመራር ጋር አንድ ላይ በመሆን ቦታው ላይ በመገኘት እስከ ቀን 09/09/13 ድረስ በተከሳሽ በኩል የተገነባ ምንም አዲስ ግንባታ አለመኖሩን፣ ተከሳሽ በመዝገብ ቁጥር 195246 ባገኙት ፍርድ መሰረት ከጽህፈት ቤታቸው አዲስ ግንባታ ለመገንባት ጠይቀው ቦታው ድረስ በመሄድ ሲለካ ከሳሽ ለማስለካት ፍቃደኛ ባለሆናቸው እንዲሁም በፍርድ ቤት እግድ መሰረት ፍቃድ መስጠት አለመቻላቸውን በመጥቀስ የግንባታ ፍቃድ አለመሰጠቱን፣ ካርታው ፕሮፖርሽናል ካርታ መሆኑን ደርበውም የግል እና የመንግስት በቶች የጋራ ባዶ ቦታ እንደሚገኝ ኮሪደሩ የቤት 954 እና 952 የጋራ መተላለፊያ መሆኑን እና የመኖሪያ ቤታቸውን የጓሮ መግቢያና መውጫ በር አድርገው እንደሚጠቀሙበት ገልጸው አቅርበዋል።
የወረዳው ቤቶች ልማት ጽ/ቤት በደብዳቤ ቁጥር አ/ክ/ከ/አስ/ወ/9/በ./ል/719/13 በቀን 10/09/13ዓ.ም በተፃፈ ምላሽ ጊቢው ውስጥ እየተገነባ ያለ ግንባታ አለመኖሩን ነገር ግን በጊቢው ውስጥ የጋራ መተላለፊያ መንገድ ያለ በመሆኑ ግንባታው ቢፈቀድ በከሳሽ ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ጠቅሰው አቅርበዋል።ፍርድ ቤቱም ከዚህ ሁሉ መረዳት የቻለው ይህ ክርክር ያስነሳው ግንባታ ባለቤትነቱ የ1 ኛ ተከሳሽ መሆኑ በመዝገብ ቁጥር 195246 አረጋግጦ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ግንባታው በከሳሽ ተቃውሞ ምክንያት አለመፈቀዱን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የባለቤትነት ጥያቄ አለማንሳቱን ነው።በዚሁ በፌዴራሉ ፍርድ ቤት የመዝገብ ቁጥር 195246 የፍርድ ሀተታ ላይ ክርክር በተነሳበት ቤት ጊቢ ውስጥ ያሉ የመንግስት ተከራዮች በ1ኛ ተከሳሽ ይዞታ ላይ በብሎኬት መጸዳጃ ቤት ተሰርቶላቸው እየተጠቀሙ እንደሚገኙ መረጋገጡ ሰፍሯል።
ይህ ማለት ከሳሽ በተከራዩት የመንግስት ቤት ውል ላይ የጋራ ተብሎ የተጠቀሰውን መጸዳጃ ቤት የትኛው ነው ለሚለው መልስ የሚሰጥ ነው።ከዚህ በተጨማሪ የጋራ መጸዳጃ ቤት ከከሳሽ ክርክር አንፃር በጊቢ ውስጥ ሁለት መጸዳጃ ሆኖ ሁለቱም ላይ ባለመብት ነኝ ወደሚል ትርጉም የሚወስድ ነው።ነገር ግን ቀደም ሲል በጋራ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው መጸዳጃ የ1 ኛ ተከሳሽ ይዞታ ስለመሆኑ በፍርድ የተረጋገጠ ነው።ስለሆነም በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1149 መንፈስ አንፃር የሁከት ይወገድልኝ ክስ ማቅረብ የሚቻለው ይዞታው የተወሰደበት ወይም በይዞታው ላይ ሁከት የተነሳበት ሰው ሲሆን ከዚህ አንፃር ከሳሽ ባለይዞታ ባልሆኑበት እና የቤት ቁጥር 954 ላይ በሚደረግ ግንባታ ላይ ሁከት ተፈጥሮብኛል ማለታቸው የህግም ሆነ የአመክንዮ መሰረት የሌለው ስለሆነ የከሳሽን ክስ ውድቅ በማድረግ ፍርድ ተሰጥቷል።ውሳኔ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በከሳሽ ላይ የፈጠሩት የሁከት ተግባር የለም ተብሎ ተወስኗል።ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ቻለ ትዕዛዝ ይግባኝ መብት ነው።መዝገቡ ተዘግቷል፤ ይመለስ።የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለው።” የሚል ነው።
የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳር ጽህፈት ቤት ምላሽ
የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቁጥር አ/ክ/ከአስ/ወ/09/ቤ/ል/ 719/2013 እና በቀን 10/09/2013ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 26581 በተከፈተ መዝገብ በቀን 26/08/2013 ዓ.ም ለተላከ ትዕዛዝ ምላሽ በሚል በተጻፈ ደብዳቤ ክሱ በተፈጠረበት ጊቢ ውስጥ ተከሳሽ እየገነቡት ያለ ግንባታ መኖር አለመኖሩ እና ተከሳሽ አደረጉት የተባለው ግንባታው ጊቢ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች መተላለፊያ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ እንዲገለጽ ፍርድ ቤት ባዘዘው መሰረት በጊቢው ውስጥ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የተሰጠበት ደብዳቤ እስከተጻፈበት ድረስ ግንባታ ባይኖርም ከዚህ በኋላ ግን ግንባታ ለመገንባት ቢሞከር በመንግስት ተከራዮች ላይ ከፍተኛ ተጽኖ አንደሚኖረው በደብዳቤ ለፍርድ ቤት መገለጹን የሰነድ ማስረጃዎች ያሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ/ እማሆይ ጥሩወርቅ ከሽንት ቤት ጋር ተያይዞ ወረዳውን ከሰውበት በነበረው ወቅትም የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት የሚከተለውን ጽፎ እንደነበር አቶ ፍቃዱ ይናገራሉ። “ አ/ክ/ከአስ/ወ/09/ቤ/ል/ 546/2013 በሆነ እና በቀን 7/04/2013ዓ.ም ለአራዳ ክፍለ ከተማ የመሰረተ ልማት ቅንጅት፣ ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ እንገለጸው የቤት ቁጥር 954 ጋር ተያይዞ የመንግስት ቤት ተከራዮች ሲጠቀሙበት የነበረው ሽንት ቤት መረጃ እንድንሰጣችሁ በጠየቃችሁን መሰረት በወረዳው ቤቶች ጽህፈት ቤትም የመንግስት ተከራዮች ሲጠቀሙበት የነበረው የጋራ ሽንት ቤት በወይዘሮ ጥሩወርቅ ይማም የተመዘገበ መረጃ በእኛ ጽህፈት ቤት የሌለ መሆኑን እና ይልቁንም የመንግስት ቤት ተከራዮች የሚጠቀሙበት የነበረ እንጅ የወይዘሮ ጥሩወርቅ ነው የሚያስብል ምንም ማስረጃ ስለሌለ የመንግስትን ጥቅም እንዳያሳጣ በእናንተ በኩል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ በእኛ በኩል ያለንን መረጃ በዚህ ደብዳቤ እንገልጻለን።“ የሚል ነው።ይሁን እንጂ ይህ በተባለበት አግባብ በፍርድ ቤቱ ሽንት ቤቱ የወይዘሮ ጥሩወርቅ ይማም ነው ብሎ ፈረደ።እዚህ ላይ ውድ አንባቢን ፍርዱን ለእናንተው ትተናል።
ከዚህ በተጨማሪም የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ማሞ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንዳስረዱት ከእና ወይዘሮ ሂሩት እና ከእነ እማሆይ ጥሩወርቅ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስለጉዳዩ እንድናስረዳ መጥሪያ ልኮ ነበር። የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ የተባለው ሽንት ቤት የወይዘሮ/ እማሆይ ጥሩወርቅ እንዳልሆነ እና መጸዳጃ ቤቱ የጋራ እንደሆነ ብቻ ነው የምናውቀው ብለው ለፍርድ ቤት መላካቸውን ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።
ሌላው የወረዳ 9 አስተዳደር ቤት የቤቶች ልማት አስተዳር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ማሞ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንዳስረዱት ወይሮ ጥሩወርቅ እና ወይዘሮ ሂሩት ክስ ጋር ተያይዞ በነበረው ክርክር ሰነዶችን በሚፈተሽበት ጊዜ የቤት ቁጥር 953 የተባለ ቤት ከጊቢው ጠፍቷል። ይህ ቤት በምን አግባብ ሊጠፋ እንደቻለ እያጣሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አንባቢዎቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎች አሉኝ ወይም ያልተካከቱ ሃሳቦች አሉ የሚል ወገን ካለ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ከወዲሁ ያስታውቃል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013