ኢትዮጵያን የፈተና ማዕበል ከቧታል። አብዛኞቹ ተግዳሮቶቿም ከአሁን ቀደም ካለፈችባቸው ፈተናዎች ጋር ሲነጻጸሩ የተለዩም የተመለመዱም ዓይነቶች ናቸው። ቀደም ባሉት ጽሑፎቼ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት የፈተናዎቹ ወጀቦች የበረቱት ከውስጥና ከውጭ ተደራርበው ስለመጡ ነው። ከውጭው ይልቅ የውስጣዊ ፈተናዎቿ የጠነከሩ ይመስላሉ። ችግሩን ያከፋው ደግሞ ከሀገር ማህጸን ውስጥ የበቀሉ እኩያን “ካላፈራረስንሽ እንቅልፍ አይወስደንም” እያሉ ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር የከፉ ሆነው ለጥፋትና ለውድመት ጨካኞች መሆናቸው ነው።
የውጭ ጠላቶቻችንም ቢሆኑ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” እንዲሉ በአረመኔያዊ ድርጊቱ ሲያብጠለጥሉት ከኖሩት ከዛሬው አሸባሪ ቡድን ጋር ተሰልፈው ሰይፋቸውን እየወዘወዙ ጡንቻችንን ካላሳየን እያሉ ቀረርቶ ላይ ናቸው። ጡንቻቸው የሰብዓዊ እርዳታቸው ዳረጎትና ለልማት እያሉ የሚወረውሩልን መደጎሚያዎች ናቸው። አንዲትን ታላቅ ሀገር ከአንድ ተራ የተደራጀ አሸባሪ ቡድን ትርፍራፊዎች ጋር “ታረቁ! ተደራደሩ!” እያሉ “የመፍትሔ ሃሳብ” ሲያቀርቡ “ነግ በእኔ” ይሉትን ይሉኝታ ለማሰብ እንኳን የቻሉ አይመስልም።
“እስቲ እናንተ አሸባሪ እያላችሁ ከፈረጃችኋቸው ከአልቃይዳና ከመሰል ቡድኖች ጋር ተስማሙና ተደራደሩ?” የሚል መልስ ሲሰጣቸው ፀጉራቸው ይቆማል። “እንዴት ይህን መሰል ሃሳብ ሊሰነዘርልን ቻለ?” በማለትም ሃሳብ አቅራቢዎችን አብረው በመደመር በጠላትነት ያቧድናሉ። “እንኳን አሸባሪዎች ብለው ከፈረጇቸው ቡድኖች ጋር ቀርቶ ሰሜን ኮሪያን ከመሰለ ሉዓላዊ ሀገር መሪ ጋር በልዩነታችሁ ዙሪያ ምከሩና የጋራ መፍትሔ አመንጩ” ተበለው ሲመከሩም “በቀረርቶና በፉከራ” እንዴት ተደፈርን በማለት አየሩን በተቆጣጠሩት “ህሊና ቢስ አፈ ጉባዔ” ሚዲያዎቻቸው አማካይነት ሲያንባርቁ ይውላሉ። በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በሱማሊያ ወዘተ. በፈጸሟቸው ጣልቃ ገብነቶችና የማፈራረስ ተልዕኮዎች ሲገሰጹና ሲተቹ “እኛ ወደ ሀገራቱ የዘመትነው ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊነት መከበር ዘብ ለመቆም ነው” እያሉ በአንደበታቸው እየቀጠፉ በልባቸው ደግሞ “እናንተም ቀናችሁን ጠብቁ” እያሉ ይፎልላሉ።
ለምሳሌነት የምናቀርበው እኛው እራሳችንን ነው። እነርሱ እንደ ሀገር ከመታወቃቸው አስቀድሞ በገናናነቷ ደምቃ የኖረችውን ታላቋን ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ከህወሓት ቡድን ድንክ አስተሳሰብ እኩል ከርክመው ካልተደራደራችሁ እያሉ በዛቻና በማስፈራሪያ በማጀብ “በተመሳሳይ ላባ አብረው ከሚበሩት” ብጤዎቻቸው ጋር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለመሞገት ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው። “የራሷ እያረረባት…” እንዲሉ በእኛ ጉዳይ ለመፍረድና ለመወሰን “ልክ” ናቸው። ጣት ወደ እነርሱ ሲቀሰር ግን ለእብደት አንድ ሐሙስ እስኪቀራቸው ድረስ ኡኡታቸውና ተደፈርን ባይነታቸው ገደቡን ጥሶ ዓለምን ያጥለቀልቃል።
በእነርሱ ዓይን ፊት ሞገስ የተነፈገውን ሁሉ በአመጽና በሽብርተኛነት የሚፈርጁት “ስለ ሰብዓዊ ክብር፣ ስለ ዴሞክራሲና ስለ ፍትሕ” እንደሚሟገቱ ለማሳመን እየሞከሩ መሆኑ በራሱ የተውኔት ያህል የሚያስፈግግ ነው። ለእነርሱ “አሸባሪ” ማለት የእነርሱን አቋም የተጻረረውና ከስህተታቸው እንዲመለሱ የሚመክራቸው ሁሉ ነው። ዳሩ ምክር ቢሰሙ አይደል። የእነርሱ ሥርዓተ መንግሥት ምሉዕ በኩለሄ የሆነ “የጽድቅ መንገድ ነው።” እኛን መሰሉ ሀገር ያለ እነርሱ “ቡራኬ” ለፍትህና ለሰላም መቆም እንደማይችል አምነው ለማሳመን የሚሞክሩት ህሊናቸውንና አስተሳሰባቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ነው። ቢቻላቸው የእነርሱን ሳንባ ተጋርተን አብረን ብንተነፍስ ደስታቸው ወደር የለውም።
ለእነርሱ “የታላቅነት መለኪያው” በጡንቻ ተመክቶ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲው መስክ ዓለምን ተቆጣጥሮ እንዳሻቸው ለመፋነን መወራጨት ነው። ሌሎች ሀገራት እነርሱ ከደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀን ከሌት ላባቸውን ጠብ እያደረጉ ሲሰሩ አይወዱም። ሀገራት ከድህነት ለመላቀቅ ሕዝባቸውን ሲያስተባብሩም ግራ ዓይናቸው ይቀላል፤ የቀኙም ይደፈርሳል። የእነርሱ ብልጽግና አሜን እንዲሰኝለትና እንዲካደምለት የሚፈልጉት በዋነኛነት በእርዳታቸው ስንዴ የመስፈሪያ መጠን ልክ ነው። “በሰብዓዊ ድጋፍና በዴሞክራሲ ግንባታ ስም የበርካታ ሀገራትን በሮች በርግደው ለመግባት ትግል ሲገጥሙም “ማነህ? ለምን ጉዳይ ቤታችን ዘው ብለህ ገባህ?” እንዲባሉ በፍጹም አይፈልጉም። በሰው ጓዳና ገመና እንደፈለጋቸው ሲፈነጩም ሃይ ለመባል እንኳን ለራሳቸው ፋታ አይሰጡም።
ሲያሻቸው “የየትኛውም ሀገር ስደተኛ ኬላችንን ጥሶ እንዳይገባ የድንበራችንን አጥር በግንብ፣ በእሾህና በሽቦ አጠናክረን እንዘጋለን” በማለት ቢሊዮን ዶላሮችን ሆጨጭ አድርገው የሚያፈሱት “ልክ መሆናቸውን” የአዋጅ ያህል በማስተጋባት ነው። በአሸባሪው ቡድን እየተወጋችና እየደማች ያለችው ሀገሬ ግን ለደም አፍሳሹ ሴረኛ ቡድን ድንበሯን አጠናክራ፤ በእርዳታ ቁሳቁስ ስም ለአሸባሪው ቡድን እንዲደርስ የተፈለገውን ሴራ ስታከሽፍ “እንዴት ተደርጎ” እያሉ ይፎክራሉ። አልፎም ተርፎ እጅ በመጠምዘዝ ጭምር አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ቋጥኝ እስከመፈንቀል ይደርሳሉ።
እርግጥ ነው እንደማንም ታዳጊ ሀገር ሀገሬም ችግር ስለገጠማት የሰብዓዊ ድጋፍ መሻቷ ግድ ነው። የልማት አጋሮችን ለማጠናከርም በብርቱ ትናፍቃለች። ነገር ግን እርዳታውም ሆነ የልማት ድጋፍ ለተዋራጅነት የሚዳርጋት ከሆነ “ከዘላለም ባርነት፤ የአንድ ቀን ነፃነት” እንደሚበልጥባት ወደረኞቿ እንደምን ታሪኳን እንዳላማከሩ ይገርማል። አያት ቅድመ አያቶቻችን ኢትዮጵያን ያስረከቡን አፈሯን በደማቸው አላቁጠው፣ ድንበራችንንም በአጥንታቸው ስብርባሪ ማግረው ስለሆነ ይህንን ክብሯን ትቢያ ላይ ረግጣ ተንበርካኪ እንደማትሆንላቸው አያውቁትም፣ አላነበቡም ብሎ ለመደምደም ያዳግታል። አያውቁት ከሆነም ከቤተመጻሕፍታቸውና የጥናት ተቋሞቻቸው ውስጥ ታሪካዊ ሰነዶችን እያመሳከሩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ሊመረምሩ ይችላሉ።
የውስጥ ጠላቶቻችን፣ የጎረቤት ባላንጣዎቻችን፣ የሩቆቹ ተገዳዳሪዎቻችን ምን አጀንዳ ቀርጸው ወደ ምን እየገፉን እንዳለ ለመገንዘብ እጅግም አያዳግትም። እነርሱ በኒውክሌር ኢነርጂ መንጥቀው ዜጎቻቸውን በብርሃን ፀዳል ሲያጥለቀልቁ ለእነርሱ ኩራት ነው። እኛ ግን ፈጣሪ የለገሰንን የዓባይ ወንዝ ገድበን ሌሎቹን ሳንጎዳ ብርሃን እናምርትበት ብለን ስንጨክን በርብርብ ይዘምቱብናል። ተፈጥሮ በለገሰን ምድር ላይ በረከት ለማፈስ ስንተጋና ለልማት መነሳሳታችንን ሲመለከቱም ድንግሉ ኤኮሎጂ ተደፈረ፣ የምንትስ ታሪካዊ ስፍራ ለአደጋ ተጋረጠ፣ “ቅድስት ተፈጥሮ ረከሰች!” ወዘተ. እያሉ ዘምተው ያዘምቱብናል።
ለምሳሌ፤ የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ የጎረቤት ሀገራት ኡኡታ፣ እዮታና ማስፈራራት ቅዠትና መደናበር የፈጠረው ፍርሃት እንጂ ሀገሬ ለራሷ ጥቅም ብቻ አዳልታ እንደማትጎዳቸው ጠፍቷቸው አይደለም። “ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ” እንዲሉ የኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች ግለት ለእነርሱ የተመቻቸ ጊዜ መስሎ ቢታያቸው አይፈረድባቸውም። ያልገባቸውና ከፍ ያለው መሠረታዊ ምሥጢር ግን ሀገራዊ ችግሮቻችን ተጋግለው በፈተኑን ወቅት ሁሉ ኢትዮጵያዊው ልባችን በአንድነት ተሳስሮ እንደሚጀግን ነው። ከግራ ከቀኝ የሚረባረቡብን ኢትዮጵያዊው ሰብእናችን በጊዜ ወለድ ችግሮች አደጋ ላይ የወደቀ መስሏቸው ስለሆነ አይፈረድባቸውም። ያልተረዱት እውነታ ሥነ ልቦናችን የተቀረጸው እነርሱ በሚያስቡት በጠመኔ ቾክ መሰል መጻፊያ ሳይሆን በእሳት ተፈትኖ በተሸለመ የወርቅ ሰሌዳ ላይ መሆኑን ነው።
መከራና ጉም እያደር እንደሚቀል ከታሪካችንና ከተፈጥሮ ዑደት የተገነዘብነው ገና በማለዳ ነው። ሀገሬ ባለፉት ዘመናት ውስጥ እጅግ በርካታ መከራዎችን ተቋቁማ እንደ ብረት እንደጠነከረች ማን በነገራቸው። ወጀብና አውሎ ነፋሱን ተቋቁማ በክብር የቆየችው “ከፉ ጊዜንና ቅዝምዝምን ማሳለፍ ጎንበስ ብሎ ነው” በሚል መርህ እየተመራች ሳይሆን “ጠላቶቿን በሙሉ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣች” አስተምራ በመልቀቅ ጭምር ነው። ግብጾች ይህ ታሪክ ይጠፋቸዋል ተብሎ ይታመን ይሆን? እንጃ! መሃዲስቶቹና ደርቡሾቹ ጎረቤቶቻችን የአባቶቻቸውን ሽንፈት ሳይሰሙ እስከ ዛሬ ይቆያሉ ተብሎ ይገመት ይሆን? እርግጠኛ አይደለሁም። የደቡብ ኮሪያን ጦርነት በማስታወስ “በትልቅ ክብርና ደስታ በኮሪያ ሪፑብሊክ እና በሕዝቡ ስም ኢትዮጵያውያን ለእኛ መብትና ነፃነት ላበረከቱት የላቀ ተጋድሎ ውለታ እንዳለብን እናምናለን” የሚለውን ምስክርነት የዛሬዎቹ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅቶች መሪዎችና ቁንጮ ፖለቲከኞቻቸው አልሰሙ ይሆን? በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለሰላም ማስከበር የከፈልነውንና እየከፈልን ያለነው አስተዋጽኦስ ተረስቷቸው ይሆን?
“ምንጫችን ከምድረ ቀደምቷ አፍሪካ ነው” እያሉ ራሳቸውን “Africane Americans” በማለት የሚያስተዋውቁት “የታላቋ አሜሪካ” ጎምቱ ሴናተሮችና ኮንግረስ ሜን/ውሜን የፖለቲካው ሠፈርተኞችስ ይህ የከበረው የኢትዮጵያ ታሪክ እንዴት ሊሰወርባቸው ቻለ? አላወቁት ከሆነ የታሪክ ድርሳኖቻችንን በየፈርጁ ልናቀርብላቸው እንችላለን።
የትናንት ታሪክ በዛሬ ምስክርነት ሲረጋገጥ፤
አሸባሪው ትህነግ በ27 ዓመታት ውስጥ ዘርቶ ካዘመራቸው መከራዎቻችን መካከል አንዱ ተክሎብን ያለፈው የዘረኝነትና የጎጠኝነት አረም ምን ያህል ነቀርሳ ሆኖብን እንዳስነከሰን ሁሉም ዜጋ በሚገባ ይረዳዋል። በየክልሉ ይስተዋል የነበረውን የአንድ ሰሞን የወንድማማቾች የእርስ በእርስ መቃቃር ዘላለማዊ ጠብ መስሏቸው ጠላቶቻችን በሙሉ ጮቤ በመርገጥ ደስታቸውን እየገለጹ “Cheers! ዋንጫ ኖር!” እያሉ ሲፈነጥዙ መክረማቸውን ስንታዘብ የባጀነው እየገረመንም እየታዘብናቸውም ነበር። ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ስለማያውቁት ቢደነባበሩ አይገርምም።
ብዙ ወደረኞቻችን በዚያም በዚህም አሳበው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለተከፋፈለ ጊዜው ደርሷልና አብረን እንዝመትባቸው!” ብለው ነጋሪት የጎሰሙብን የተሳሳት ግምት አስክሯቸው ነው። እውነታው እነርሱ እንደተመኙት አይደለም። በተለያዩ የቤታችን የውስጥ ገመና ምክንያት ሆድ የባሰውና የተባባሰው ዜጋ እንኳን ሳይቀር ዛሬ ሀገሩ ስትጠቃ እንዴት ሆ! እያለ ለዘመቻ እንደሚሽቀዳደም ሲያስተውሉ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጭነው በጸጸት የሚቀጡ ይመስለናል። ኢትዮጵያዊነት ይሄ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች በውጭ ሀገራት የሚገኙት ዜጎቻችንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው መጠቃት ሲያንገበግባቸው ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በአንዱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸው ስር ተሰባስበው “በአንድ ድምጽ ግፈኞችን የሚሞግቱት” ምሥጢሩ ምንም ሳይሆን የታነጹበት የኢትዮጵያዊነት ክብር ግድ ብሏቸው ነው። ከጊዜያዊ ፈተናዎቻችን ውስጥ እያዘመርን ያለነው እኒህን መሰል በረከቶች መሆናቸውን ጠላቶቻችን እያረሩም ቢሆን ቢሰሙት፣ ወዳጆቻችንም እያሞገሱ ቢያደንቁ አግባብ ነውና በራሳቸው ብሂል “Many Blessings in Disguise!” ብለን የምሳሌያቸውን እውነትነት ብናረጋግጥላቸው ወደ ቀልባቸው ለመመለስ ያግዛቸው ይመስለናል። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013