አሸባሪው የህወሓት ቡድን በ46 ዓመቱ ጉዞው ተቀጭቷል ። በዚህ ግማሽ ምዕተ ዓመት የተጠጋ እድሜው ታዲያ ከሰራቸው በጎ ስራዎች ይልቅ ያጠፋቸው ጥፋቶች እጅጉን የሰፉ ናቸው ። ቡድኑ በአመጽ ተወልዶ በአመጽ ወደስልጣን የመጣ ነው ። ከዚያ በኋላም ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ በቆየባቸው ወቅቶች ጉልበት እና አፈና ዋነኛ መገለጫዎቹ ነበሩ፤ ከዚያ በኋላም ከስልጣን የተወገደው በሕዝብ እምቢተኝነት ነው ። ነገር ግን አመፅ የኖረበት ህልውናው ነውና ወደተወለደበት ጉድጓድ ተመልሶ ገባ ። እዚያም ሆኖ ግን የማተራመስ ሥራውን ዛሬም ተያይዞታል ። ለመሆኑ ቡድኑ ከውልደቱ ጀምሮ የመጣባቸው የጥፋት መንገዶች ምን መልክ ነበራቸው፤ ይህንን ብዙዎቻችን የምናውቀው ቢሆንም በጥቂቱ በማስታወስ ወደዛሬው የጥፋት ተግባሩ ልመልሳችሁ።
ቡድኑ የተመሰረተው ገና ደርግ ወደሥልጣን በመጣበት ማግስት ነበር ። በወቅቱ ታዲያ ደርግ የሚሄድበትን መንገድ እንኳን በቅጡ ሳይረዳ ቡድኑ ወደአመጽ የገባበትን አካሄድ ስንመለከት ማመፅ ተፈጥሮአዊ ባህርይው መሆኑን እንረዳለን ። ምክንያቱም በወቅቱ ደርግ ገና ወደጥፋት መስመሩ ሳይገባ ደርግን ለመፋለም የሔደበት መንገድ ሲታይ ዓላማው ከደርግ ጋር ተመሳሳይ ባህርይ የነበረው መሆኑን ያሳያል ። ምክንያቱም ሁለቱም በጉልበት ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ነበራቸውና ። በዚህ ሂደት በተከተለው የጦርነት መንገድ በዋናነት ዋጋ ያስከፈለው ግን እታገልለታለሁ ያለውን የትግራይ ሕዝብ ነበር ። በዚህም ለ17 አመታት ከደርግ ጋር ባደረገው ትግል ከ60ሺህ በላይ ለሚሆኑ የትግራይ ዜጎች እልቂት ምክንያት ሆኗል ።
ከዚህም አልፎ በዚህ ጦርነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን እንዲገብሩና አገር እንዳትረጋጋ የራሱን አሉታዊ ሚና ተጫውቷል ። በነዚህ 17 አመታት በተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያ የማደግ ተስፋዋን አጥታለች ። ይህ ጦርነት ባስከተለው ድህነትና ተስፋ መቁረጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ተሰደዋል ። ከዚያም አልፎ በርካታ ቤተሰብ ተበትኗል ። ኢትዮጵያ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በድህነት፣ ቦጦርነትና በኋላቀርነት ስሟ በተደጋጋሚ እንዲነሳና ከነበራት ከፍታ እንድትወርድም የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል ።
የሚያሳዝነው ደግሞ ቡድኑ ይህንን ድርጊት እንደ ጀግንነት በመውሰድ ሕዝብን በተጣመመ አስተሳሰብ ውስጥ እንዲዳክር ያደረገበት የተሳሳተ ትርክት ነው ። በዚህ ዘመን በጦርነትና በውጊያ “ይህ ሕዝብ ጀግና ነው፤ ታግሎ መብቱን ያስከብራል፤ ወዘተ” በሚሉ አጉል የጀብደኝነት ኩራቶች ዜጎች ለማይገባ ጦርነት እንዲማገዱና እርስ በእርስ እንዲጋደሉ በማድረግ በግጭት ወደእድገት ጎዳና እንዳንጓዝ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የኖረ ቡድን ነው ።
ዛሬም ቢሆን ይህ ቡድን በጦርነት ከማመን አለመውጣቱ ሁለተኛው ስህተት ነው ። ቴክኖሎጂ በሚዋጋበት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ጦርነትን እንዴት የመጀመሪያ አማራጭ አድርጎ ይጓዛል ። ይህ ቡድን ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት ለድል የበቃው ዘመኑ ስለፈቀደለትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በነበረው ሥርዓት ደስተኛ ባለመሆኑ በሩን በመክፈቱ እንደሆነስ ሳያውቅ ቀርቶ ነው ወይስ ራሱንም የመካድ አባዜ ተጠናውቶት ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል ።
አሸባሪው ህወሓት ጋሻ ጃግሬዎች ዛሬም ድረስ ደርግን ያሸነፉት በሁሉም ነገር የበላይነትን ይዘውና ጀግኖች በመሆናቸው እንደሆኑ ሲናገሩ ይሰማል ። ይህ ግን አይናችሁን ጨፍኑ፤ ላሞኛችሁ ካልሆነ በስተቀር ደርግን ያሸነፈው ደርግ ራሱ ስለመሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው ።
አሸባሪው ቡድን ታዲያ ዛሬም በተመሳሳይ የኖረበትን ሴራ በመጠቀም ዳግም ድል የሚያገኝ እየመሰለው የተለያዩ የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ሲነዛ ይስተዋላል ። ዛሬም ቆም ብሎ ከማሰብና ለሕዝብ የተሻለ የእድገት አማራጭ እንዲመጣ ወደህሊናው ከመመለስ ይልቅ መልሶ መላልሶ እዛው ላይ በመቆም የጦርነት ነጋሪትን ሲደልቅ ይስተዋላል ። ለዚህም የተለያዩ ማሳያዎች አሉ ። ለአብነት ጥቂቶቹን እናንሳ።
ሰሞኑን አፈቀላጤአቸው ጌታቸው ረዳና የቀድሞ የመከላከያ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፃድቃን ወልደተንሳይ በተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች ብቅ እያሉ የትግራይን ሕዝብ ለጦርት የሚቀሰቅሱበት መንገድ ሲታይ እነዚህ ሰዎች የመጨረሻው ሥርዓተ ቀብራቸው ካልተፈፀመ በስተቀር ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ ያስመሰከሩበት ነው ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ እነሱ አፈር ለብሰው አፈር መስለው በጉድጓድ ውስጥ መውደቃቸው ሳያንስ ሌላውም አብሮኣቸው እንዲሰቃይና እንዲሞት ይፈልጋሉ።
በሌላ በኩል እንደ ፈሪ እናት ራሱ ከባህር ማዶ ሆኖ እዚህ ግፋ በለው በሚል የሚያዋጋው የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምም ልጆቹን በጉያው አቅፎና በሰለጠነ ዓለም ውስጥ አንደላቆ እያኖረ የሌላውን የደሃ ልጅ ሲያስጨርስ ይታያል።
በሌላ በኩል የአሜሪካና የአውሮፓ ወዳጆቻቸውም ከጦርነት የተረፉትን የአሸባሪው ህወሓት ቡድኖች ከየጎሬኣቸው በመለቃቀም ዳግም ነፍስ እንዲዘሩ በማድረግ ቡድኑ እንዳልሞተ ለማስመሰል ሲጥሩ ይስተዋላል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ እና አርሶ አደሩም እርሻውን ተረጋግቶ እንዲያርስ በሚል ያካሄደውን የተናጠል የተኩስ አቁም በመጠቀም ዳግም ነፍስ የዘሩት እነዚህ የአሸባሪ ቡድን አባላት በአንድ በኩል በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ጦርነት ከፍተናል፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት እንደራደር እያለ ነው የሚል የማደናገሪያ ወሬ በመንዛት ላይ ናቸው ። ነገር ግን ቀደም ሲል ሙሉ ትጥቅና የሰው ኃይል ይዘው በሁለት ሳምንት ጊዜ የተፍረከረኩበት ታሪክ የትላንት ነው ። ዛሬ ከዋሻ ወጥተው እንደዚህ የሚደነፉት የውጭውን ደጋፊዎቻቸውን ቀልብ ለማግኘት ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣው ለውጥ የለም ።
አሸባሪው ህወሓትና ሸፍጥ ሁልጊዜ አብረው የሚኖሩ ተመሳሳይ ስብዕናዎች ናቸው ። ያለ ሸፍጥና ሴራ አሸባሪው ህወሓት ለሰከንድም እስትንፋስ የለውም ። ህጻናትን ለጦርነት አሰልፎ ከማስጨረሱም በተጨማሪ የሞቱ ህጻናትን አስከሬን ጭኖ በመውሰድ መንግሥት ጭፍጨፋ እየፈፀመ ነው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ደግሞ ሌላ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ጀምሯል ። በተከዜ ወንዝ ላይ ተፈፀመ ያለውም ጭፍጨፋ የዚህ ሴራ አንዱ አካል ነው ። እነዚህና መሰል ጥረቶች ሲታዩ የውጭ ኃይሎች ይህንን የሞተ ቡድን ከሞተበት ቀስቅሰው ዳግም ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ ወደሥልጣን ለመመለስ ያለመ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው ። ነገር ግን ለሞተ ቡድን እጣ ፈንታው ስርዓተ ቀብር እንጂ ሥልጣን አይደለምና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቡድኑን ማስወገድና ሰላም ማስፈን ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ አሁን የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመደገፍ ለውጤት ማብቃት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ነው ።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013