እየተካሄደ በሚገኘው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ለትልቅ ውጤት በምትጠበቅባቸው ሁለት ርቀቶች ሁለት ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ትናንት ማስመዝገብ ችላለች። በወንዶች ሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር በአትሌት ለሜቻ ግርማ የብር ሜዳሊያ ሲመዘገብ በሴቶች አምስት ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ በአትሌት ጉዳፍ ፀጋይ አማካኝነት ተመዝግቧል።
በወንዶች ሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ የማግኘት ትልቅ እድል የነበራት ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል። ያም ሆኖ አትሌት ለሜቻ ግርማ ያስመዘገበው የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በርቀቱ የመጀመሪያው ትልቅ ውጤት ሆኗል። የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር በሄንግሎ ሲካሄድ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ሳይሳተፍ በመቅረቱ በኦሊምፒክ ቡድኑ ሳይካተት የቀረው አትሌት ለሜቻ በመጨረሻ ሰዓት በርቀቱ ኢትዮጵያን እንዲወክል በመመረጡ የተለያዩ ውዝግቦች ተነስተው የነበረ ቢሆንም አትሌቱ ከህመሙ አገግሞ ባለፈው የሞናኮ ዳይመንድ ሊግ በመሳተፍ የ2021 የዓመቱን ፈጣን ሰዓት 8:07፡ 75 አስመዝግቦ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሩን በኦሊምፒክ መወከል ችሏል ። በዚህም እ.ኤ.አ በ1980 ኦሊምፒክ አንጋፋው አትሌት ሻምበል እሸቱ ቱራ በርቀቱ ለኢትዮጵያ ካስመዘገበው የነሐስ ሜዳሊያ ወዲህ ለሜቻ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ ታሪክ መስራት ችሏል።
ውድድሩ ለኢትዮጵያውያን ፈታኝ ካለመሆኑና የርቀቱ ኮከብና ባህላቸው የሆኑ ኬንያውያን አትሌቶች አለመኖራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ የማግኘት ሰፊ እድል ነበራት። ለሜቻ ባለፈው የዶሃ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ከርቀቱ ኮከብ ኬንያዊው ኮንሲስለስ ኪፕሩቶ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ተቀድሞ በታሪክ የመጀመሪያ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበ አትሌት መሆኑ ይታወሳል። በዚያ ሻምፒዮና ለሜቻን የቀደመው ኬንያዊ አትሌት በዚህ ኦሊምፒክ አለመኖሩና ሌሎቹም ኬንያውያን ቢሆኑ ጥሩ አቋም ላይ ባለመሆናቸው ከርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት አትሌት ጌትነት ዋለ በውድድሩ መሳተፍ ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያውያን ወርቁን እንደሚያጠልቁ ተገምቶ ነበር። በውድድሩም እንደተጠበቀው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሻለ ብቃት ሲያሳዩ ኬንያውያን በአንፃሩ ተዳክመው ታይተዋል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያኑ ኬንያውያኑን አትሌቶች በተጠንቀቅ ሲከታተሉ ሞሮኳዊው ኤል ባካሊ በስተመጨረሻ ሳይታሰብ በ8፡ 08፡90 ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል። አስደናቂ ብቃትና የራስ መተማመን የሚታይበት ለሜቻም በአጨራረስ ተበልጦ 8፡10፡38 በሆነ ሰዓት ታሪካዊውን የብር ሜዳሊያ አጥልቋል። ኬንያዊው ቤንጃሚን ኪገን 8፡11፡45 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያ ወስዷል። ለሜቻ ያጠለቀው የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያና በትልቅ ስኬት የሚጠቀስና የሚፅናና ቢሆንም ወርቅ ያጣበት መንገድ የሚያስቆጭ ነበር። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጌትነት ዋለም በውድድሩ እንዳሳየው ጠንካራ ፉክክር ቢያንስ የነሐስ ሜዳሊያ የማጥለቅ እድል የነበረው ቢሆንም ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት በመደናቀፉ ከሜዳሊያ ውጪ መሆኑ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያን በዚህ ርቀት ትልቅና አዲስ ታሪክ ሰርተዋ ። ኬንያውያን በአንፃሩ የባህል ስፖርታቸው ተደርጎ በሚቆጠረው ርቀት እኤአ ከ1980 ወዲህ የወርቅ ሜዳሊያ ሳያጠልቁ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያውያን ባለፉት ኦሊምፒኮች ከሰሩት ታሪክ አንፃር የሴቶች አምስት ሺ ሜትር ውድድር ላይ ወርቅ ያጠልቃሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በአትሌት ጉዳፍ ፀጋይ አማካኝነት የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ተችሏል። ይህን ውድድር ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሃሰን በአሳማኝ ብቃት 14፡36፡79 በሆነ ሰዓት በማሸነፍ ወርቁን ወስዳለች። ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ የብር ሜዳሊያውን ስታጠልቅ ትልቅ ተጋድሎ ያደረገቸው ጉዳፍ ነሐሱን ወስዳለች። እጅጋየሁ ታዬና ሰንበሬ ተፈሪ አራተኛና አምስተኛ ሆነው በማጠናቀቅ የዲፕሎማ ደረጃ አግኝተዋል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በተለይም ጉዳፍና እጅጋየሁ ወርቁን ለመውሰድ ትልቅ ጥረት ቢያደርጉም እንደ ቡድን ስራ ያሰቡት ነገር አልተሳካላቸውም ። ድንቅ አቋም ላይ ያለችው ሲፈንና የተሻለ አቅም ካላት ኦቢሪ አንፃር ወጣቶቹ ኢትዮጵያውያን የሚያፅናና ብቃትና ውጤት አስመዝግበዋል ።
‹‹የቡድን ጓደኞቼ በዝናቡ የተቸገሩ ይመስለኛል:: የተዘጋጀንበትን ማድረግ ባለመቻላችን እኔም ከዘጠነኛው ዙር በኋላ የታሰበውን ታክቲክ መተግበር ሳልችል ቀረሁ:: በማጣሪያው የእግር ጥፍሬ ላይ ትንሽ ጉዳት ነበረኝ:: ሆኖም እንደ ሰበብ እንዲወሰድልኝ አልፈልግም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእኔ ወርቅ ጠብቆ ነበር ግን አልቻልኩም:: በቀጣይ ግን ከዚህ የበለጠ ጥረት አደርጋለሁ›› በማለት ጉዳፍ ከውድድሩ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየት ሰጥታለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013