ከሰላሳ ዓመት በፊት በቆመበት እንደነበረ የሚረግጠው፣ መለወጥ የማያውቀው እና ለመለወጥ ፍላጎት የሌለው እንደ ትህነግ ዓይነት ድርጅት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይገኛል ብሎ ማሰብ ህልም ነው :: አለም ተለዋዋጭ ናት :: ትናንት የተሔደበት መንገድ አላዋጣ ብሎ ይቅርና የትናንትናው አካሄድ አዋጥቶ ማሸነፍ ቢቻል፤ ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ከሆነ ትናንት የነበረውን ልምድ አለም ከደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉ ሃሳቦችን በማምጣት እና መሬት ላይ በመተግባር አቋምን በማስተካከል ከአለም ጋር እኩል ለመራመድ መሞከር የግድ ነው :: ካልሆነ ግን ውድድር በበዛባት አለም ለመኖር ይከብዳል ::
ትህነግ ቆሞ ቀር ድርጅት ነው የሚባለው በግብዝነት ሳይሆን ምክንያቶች በመኖራቸው ነው :: አንደኛ እያንዳንዱን ችግር ለመፍታት የሚሞክረው ከሰላሳ አመት በፊት ይሄድበት በነበረው የወታደራዊ መፍትሄ ነው :: ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ሥልጣን ይዞ ቤተመንግሥት ቢገባም፤ ሥልጣንን በሕዝብ ይሁንታ ከመያዝ ይልቅ ሕዝብን በጠመንጃ አፈሙዝ ለዘመናት በማፈኑ ከቤተመንግሥት መባረሩ ይታወቃል:: ከቤተመንግሥት ከተባረረ በኋላም ችግሮችን በንግግር መፍታት ሲገባው የትጥቅ ትግልን እንደመፍትሄ መጠቀሙና አሁን በሚያደርገው የትጥቅ ትግል የሚጠቀማቸው የውጊያ ስልቶች ከሰላሳ አመት በፊት ይጠቀምበት የነበረው አይነት መሆኑ ትህነግ ቆሞ ቀር ድርጅት ስለመሆኑ ማሳያዎቹ ናቸው ::
ከሰላሳ ዓመት በፊት የተቀመጠውን አንድም ሳይቀይር በመገልበጥ አሁን ላይ ያለውን መንግሥት ለመገርሰስ መከላከያን ወጋ :: አሁን ላይ ወቅቱ የሚጠይቀው የውጊያ ስልት ፈፅሞ ከሰላሳ ዓመት በፊት ካለው የውጊያ ስልት የተለየ በመሆኑ እና በአገሪቱ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ከሰላሳ አመት በፊት ከነበሩት በፍጹም ስለሚለዩ ትህነግ በ15 ቀናት ውስጥ የሚቀበርበት ጉድጓድ ውስጥ አፈር ማላስ ተቻለ ::
ይሁን እና ምዕራባውያን ያሉትን እንዲሁ ሳያኝክ የሚውጠው ትህነግ አሁን ላይ የሕዝብ ማዕበል በመፍጠር ሌላ ስትራቴጂ ተከተለ :: ይህም እንዲሁ ያረጀ እና ያፈጀ ከዘመኑ የጦርነት ስልት ጋር አብሮ የማይሄድ ነው :: የትህነግ ትልቁ ስህተት ይህ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በነበረው ጦርነት ደርግ ሲሸነፍ ደርግን ያሸነፈው በራሱ የቴክኒክ እና የስትራቴጂ ብቃት ያለመሆኑ በበርካታ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል :: በተለይም ከፍጥረቱ ጀምሮ ከምዕራባውያንና ከኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ጠላቶች ጋር ተጣብቆ ያልጠበቀውን ድል ማግኘቱ ዕሙን ነው ::
ምሁራን እንደሚሉት አንድ ሰው ወይም ድርጅት ካሰበው ቦታ እንዲደርስ ከፈለገ ቢያንስ ሶስት ነገሮች ሊገነዘብ ይገባል :: አንደኛ self knowledge (እራስን ማወቅ) ሁለተኛው self respect ; accept Your self as you are (ራስን አምኖ መቀበል ) ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ self esteem: the value that you give for Your self ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ነው ::
ራስን ማወቅ ማለት አንድ ሰው የራሱን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹን ለይቶ ማወቅ ማለት ነው:: ለይቶ ካወቀ ጠንካራውን አጠንክሮ ለማስቀጠል ይሰራል :: ደካማ ጎኑንም እንዲሁ ለማስወገድ ይማራል፤ ሰዎችን ይጠይቃል፤ መጽሐፍ በማንበብ ራሱን ለማብቃት ይሰራል :: ይህ መለወጥ የሚፈልጉ እና ከዓለሙት ግብ ለመድረስ የሚያስችል አንደኛው ለመለወጥ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መገለጫ ነው :: ትህነግ ግን ይህን አያውቅም :: ደካማ ጎኑን እና ጠንካራ ጎኑን የማያውቅ በጉራ መሰረት ላይ የራሱን ማንነት የገነባ ከንቱ ድርጅት መሆኑን እታገልለታለሁ በሚለው የትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ የሚፈፅመውን የግብዝነት ግብሩን አይቶ ማንም ሰው የሚመሰክረው ነው :: የትህነግ ትልቁ ችግር ደካማ እና ጠንካራ ጎኑን ካለማወቅ ባለፈ የራሱን ደካማ እና ጠንካራ ጎን ለይተው በወንድምነት ወይም በእህትነት ሊነግሩት የሚፈልጉትን ደርጅቶች ለማጥፋት ይሮጣል ::
ሌላው እና ሶስተኛው ጠንካራ ሰው ያሰበው አላማ እንዲሳካለት ለራሱ የሚሰጠው ግምት ካለው ብቃት እና ድክመት ጋር የተመጣጠነ መሆን አለበት :: ወያኔ ይህንን ፈፅሞ የዘነጋው እና ሊቀበለው የማይፈልገው የቆሞ ቀርነቱ ማሳያ ነው ::
በአጠቃላይ ወያኔ ሶስት ነገሮችን ስቷል :: በመሆኑም ሲፈጠር ጀምሮ የራሱን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ስለማያውቅ፤ ለራሱም አምኖ ያልተቀበለ እንዲሁም ለራሱ የሚሰጠው ግምት የተጋነነ እና ደካማ ጎኑን በትዕቢቱ የሸፈነ ስብስብ በመሆኑ ደርግን በራሱ ጥረት እንዳሸነፈ በማሰብ አሁን ያለውን መንግሥት በጦርነት ለመጣል የተንቀሳቀሰ በቆመበት የደረቀ የቆሞ ቀሮች ስብስብ ስለመሆኑ ከዚህ በፊት ያደረጋቸውን እና አሁን እያደረጋቸው ያሉትን ተግባራት መመልከቱ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው ::
በፕሮፖጋንዳ ብዛት ራሱን ፈልጎ ማግኘት ያልቻለው ትህነግ ደርግን በራሱ ታግሎ የጣለ ይመስለዋል :: ይህ ፈፅሞ እውነታ የሌለው ትህነግ ራሱን የሚያታልልበት፤ ትህነግን ያጠፋው ራሱ ለራሱ የቀመመው መርዝ ነው :: ለእዚህ አመክንዮችን ማቅረብ ይቻላል :: ደርግን የጣለው ራሱ ደርግ ያራመደው ጸረ ሕዝብ አካሄድ ነው :: በዋነኛነት ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተደረጉ የኢሃፓ፣ መኢሶን፣ ጀብሃ፣ ሻዕብያ እና ኢዲዩን የመሳሰሉ የትጥቅ ትግሎች ናቸው :: በዚህም ደርግ በሕዝብ የነበረውን ድጋፍ ከማጣቱም ባሻገር ወታደሮቹ በጦርነት እንዲሰላቹ አድርጓቸው ነበር :: ለዚህ ማሳያው ሃምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖን ከጓድ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በቤተመንግስት አስጠርተዋቸው ያደረጓቸውን ጥያቄ እና መልስ ማየቱ በቂ ነው ::
ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ በምፅዋው ጦርነት በሻቢያ ተማርከው ወደ ሱዳን ጠፍተው ሄደዋል :: ከሱዳንም በይለፍ ደብዳቤ ታግዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ኮሎኔል ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ሃምሳ አለቃውን ቤተመንግስት አስመጥተው ስለምጽዋው ጦርነት እና ስለተለያዩ ጉዳዮች 24 ጥያቄዎችን ሃምሳ አለቃውን ጠይቀዋቸው ነበር :: ሃምሳ አላቃ የተጠየቁትን ጥያቄዎች እና ሌሎች ጉዳዮች ጨምረው ቅስም የሰበረው እርምጃ በሚል መፅሐፍ በወቅቱ ተፈጥሮ ስለነበረው ነገር ቅልብጭ አድርገው አስቀምጠውታል ::
ኮሎኔል ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሃምሳ አለቃውን ከጠየቋቸው ጥየቄዎች አንዱ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ለምን አስፈለገ ለምንስ መፈንቅለ መንግስቱ ከሸፈ የሚል ነው :: ለዚህ ጥያቄ ሃምሳ አለቃ ታደሰ ሶስት መልሶችን ለኮሎኔል መንግስቱ መለሱ:: አንደኛ «በእርሶ አገር መሪነት ለተከታታይ ዓመታት ጦርነት፣ ስደት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሞት እና እስራት በአገሪቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኛል :: በእርስዎ ዙሪያ ያሉ ባለስልጣኖች ያሻቸውን የሚፈፅሙ በወታደራዊ ኮርስ፣ በአገር ልጅነት፣ በዘር በሃይማኖት፣ በጥቅም የተሳሰሩ መሆናቸው በመካከላቸው ተገብቶ ችግሮችን ማስተካከል ስለማይቻል እና የእርስዎ ባለስልጣናት የሚያቀርቡልዎት ሪፖርት በውሸት ላይ የተመረኮዘ እና የተጋነነ መሆኑ በአጠቃላይ የአገሪቱን ችግር በአስተዋይነት አመዛዝኖ መወሰን እና ለውሳኔዎች ተግባራዊነት ባለሙያዎችን ከመጠቀም ይልቅ ሁሉንም ችግር በባለስልጣኖች ወታደራዊ ኃይል ለመፍታት መሞከርና የመሳሰሉት በእርሶ አመራር የተካተቱ በመሆናቸው ነው ::
ሕግና ሥርዓትን ተቃራኒ በመሆን ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው ፕሬዚዳንቱ ነው ብሎ በቀበሌ ደረጃ መልስ መሰጠት የሚገባው ጉዳይ እየተንዛዛ ማዕከላዊ መንግስት ድረስ መቅረብ አለበት የሚል እና በወታደሩም ውስጥ በአንድ ሻለቃ አዛዥ መመለስ እና ውሳኔ መቅረብ የነበረበት ጉዳይ እየተንገዳገደ ለበላይ አካል ውሳኔ መቅረብ አለበት የሚል እና እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደማምረው የአገሪቷ ስልጣን በሞኖፖል የተያዘ ስለሆነ :: » የሚል ነው ::
ኮሎኔል ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ከጠየቋቸው 24 ጥያቄዎች ውስጥ በጥያቄ ቁጥር 14 ለተጠየቁት ጥያቄዎች ሃምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ ሲያብራሩ ሰራዊቱ አንድ ሰራዊት ሳይሆን የሶስት ኃያላን መንግስት ሰራዊት መሆኑን ጠቁመዋል :: በዚህም መሰረት አንደኛው የሰራዊት ክንፍ የአብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ መንግስት ስር ያለ፤ ሁለተኛው የወታደር ክንፍ በወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ መንግሥት የሚመራ ሲሆን ሶስተኛው የወታደር ክንፍ ደግሞ የአብዮታዊ ሰራዊት ፖለቲካ ኃላፊ መንግስት የሚመራው ነው ::
ሃምሳ አለቃው ወታደሩ በእነዚህ ፈላጭ ቆራጭ የመንግስት ክንፎች ስር የተደራጁ እና ለሶስት የተከፈለ ሰራዊት መሆኑን ገልጸው፤ የወታደራዊ ሹመት የፈለገ በጦር አዛዡ ስር ይሰለፋል:: የመንግስትን ገንዘብ እና ንብረት ለመዝረፍ የፈለገ በደህንነት ቢሮው ስር ፣ የፓርቲ ስልጣን እና አባልነት የፈለገ ደግሞ በፖለቲካ ኃላፊ ስር፣ ይሰለፍ እንደነበረ አመላክተዋል::
ይህ የተከፋፈለው ሰራዊት ደግሞ ተከፋፍሎ በጥርጣሬ በሞት ጥላ ስር የገባች ህይወቱን ይዞ ከዓመት ዓመት የትኛው ይሻላል እያለ በረሃብ፣ በድህነት፣ በበሽታ፣ በጠላቶቹ ጥይት ተሰባበሮ፣ በደሞዝ አከፋፈል፣ በቀለብ አቅርቦት፣ በህክምና አሰጣጥ በማዕረግ እድገት ወዘተ በተለያየ ሊወጣው በማይችለው የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ እንኳን ጠላቱን ተዋግቶ ሊያሸነፍ ይቅርና እርስ በርሱ የሚጠራጠርና በስነልቦናው የማይተማመን ሰራዊት እንደነበር ሃምሳ አለቃው ለደርጉ ሊቀመንበር ኮሎኔል ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያም ፊት ለፊት እንደነገሯቸው በመጽሐፋቸው ገፅ 30 ላይ አመላክተዋል::
ከዚህ በተጨማሪ ደርግን ወያኔ ሳይሆን የጣለው ራሱ ደርግ በፈጠራቸው የአሰራር ክፍተቶች እንደነበሩ ማስረጃዎች ያሳያሉ :: ለምሳሌ በጎንደር እና በትግራይ የነበሩት የ604ኛ እና የ607ኛ ኮሮች የተሸነፉት በወቅቱ ደርግ ጦርነቱን እንዲመሩት የበለጠ አመኔታ ይሰጣቸው የነበሩት የጦር ሳይንስ ለሚያውቁት ጄኔራሎች ሳይሆን ለደርግ የፖለቲካ አመኔታ የነበራቸው የኢሰፓ አባላት ስለነበር ጦሩን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለማዋጋት ብቁ ባለመሆናቸው ጦሩ የፖለቲካ አመራሮች ተመስርቶ በደረሰበት ተደጋጋሚ ሽንፈት ሰራዊቱ የሞራል ውድቀት በተደጋጋሚ እንዳጋጠመው የ604ኛ እና የ607ኛ ኮር አመራር ስር የነበሩ መኮንኖች የጻፏቸውን ትውልድ ያናወጠ ጦርነት እና የደም ዘመን የሚሉትን መጽሐፍቶች አንብቦ መገንዘብ ይቻላል ::
ይህን በብዙ ችግር የተተበተበ ሰራዊት በራሱ እና በሌሎች ብዛት ባላቸው በትጥቅ ትግሉ ባሉ ድርጅቶች የተዳከመ እና የተሸነፈ እንደሆነ ትህነጎች በመካድ እና ራሳቸውንም በማታለል ደርግን ያሸነፈው ወያኔ ከደርግ የተሻለ የወታደራዊ ሳይንስ እውቀት ያለው እና በጦርነቱም ከደርግ የተሻለ ቴክኒክ እና ታክቲክ የተጠቀሙ በማስመሰል ራሱን እና ደጋፊዎችን ሲያታልል ኖሯል ::
ትህነግ ራሱን የመዋሸት አመሉ አሁንም ተነስቶበት በሌለ አቅሙ የኢትዮጵያን መከላከያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከጀርባ ወጋ :: የኢትዮጵያ ሕዝብም በመከላከያ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ዘግንኖት እና አበሳጭቶት ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሰርቼ ጨርሸዋለሁ ያለውን በዘር የመከፋፈል ተግባር በማክሸፍ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከአልማዝ ማዕድን በጠነከረ አኳኋን አንድነታቸውን በማሳየት እና አንድ ላይ በመቆም ህወሓትን በ15 ቀን ውስጥ በሚቀበርበት ጉድጓድ ለማስገባት ተችሏል::
የምዕራባውያን ዕቅድ ሳያላምጥ የሚውጠው ትህነግ ሊቀበር ከተከተተበት ጉድጓድ በመውጣት ያረጃ የጦርነት ስልት ይዞ መጣ :: ይህ ዘመኑን የማይመጥን የውጊያ ስልት ለተመለከተ ህወሓት ከክርስቶስ ልደት እስከ መካከለኛው ዘመን ብቻ እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ድርጅት አያስመስለውም :: የሕዝብ ማዕበል የጦርነት ስልት አድርጎ ሲጠቀምና ህጻናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ ደግሞ ታይቶ በማይታወቅ የአድዋን የክተት አዋጅ በሚያስታውስ መልኩ በኢትዮጵያኖች ከዳር ዳር በአንድ እንዲቆሙ አደረገ :: ይህም ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የቆሙትን የምዕራባውያን መንግሥታት ጭምር ያራደ መሆኑን ለአፍታም የሚያጠራጥር አይደለም ::
ትህነግ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ይዞት በመጣው የጦር ስልት እየተሳተፉ ያሉት ብዙ ተዋጊዎቹ የጦርነቱን አላማ የማያውቁ እና የመዋጋት ፍላጎት የሌላቸው ህጻናት እና አዛውንት ናቸው :: በመሆኑም ቆሞ ቀሩ ትህነግ በግዳጅ ያወጣቸውን ህጻናት እና አዛውንት ተዋጊዎችን የመዋጋት ፍላጎታቸውን ለማነሳሳት አደንዛዥ ዕፅን እንደሁነኛ መሳሪያ እየተጠቀመ ነው :: ይሁን እንጂ በአደንዛዥ እፅ የሰከሩ ተዋጊዎች የጦርነቱ ዓላማ ስላልገባቸው ትህነግ የፈለገውን መሳካት የማይችሉ ስለመሆናቸው የሚያጠራጠር አይደለም ::
ከዚህ ጋር ተያይዞ የጦርነት ጠበብቶች እንደሚሉት አንድ ወታደር ማሸነፍ እንዲችል ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ሊኖሩት ይገባል :: አንደኛ ጦሩ በፍላጎት የሚዋጋ ሊሆን ይገባል :: በዚህም ማንኛውም ወታደር የጦር ሜዳ ድል ለማግኘት ዲስፕሊኑን በጠበቀ መልኩ መሪና ተመሪው ለጦርነቱ የግል እና የጋራ የሆነ አስተዋፅዖ ማድረግ አለባቸው :: ተገዶ የሚዋጋ ግን በመሪዎቹ ላይ እምነት አይኖረውም :: በጦር ሜዳ ላይ የሚያሳየውም የግሉን ፍላጎት እና ስሜት ብቻ ስለሚሆን ለጦርነት ዲስፕሊን ተገዥ መሆን አይችልም :: ጦርነት ደግሞ በቡድን የሚከናወን ስለሆነ የግል ስሜት የሚንጸባረቅበት ከሆነ ጠላትህ በቀላሉ እንዲያሸነፍ ያስችላል ::
ሌላኛው እና ሁለተኛው አንድ ወታደር ጦርነትን ማሸነፍ ከፈለገ ሊኖረው የሚገባው ነገር የመጣበት ሕዝብ የሰጠውን አደራ ከጦርነቱ ዓላማ ጋር ማቆራኘት እንዳለበት የጦርነት ጠበብቶች በስፋት ጽፈዋል :: ህወሓት በሁለተኛው ዙር ይዞት የመጣው ጦር ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች የሚያሟላ አይደለም :: ምክንያቱም ለጦርነት የመለመላቸው ተዋጊ ህጻናት እና አዛውንቶች ከመሆናቸውም ባለፈ ለጦርነቱ የማይሳተፉ ከሆነ ለዕርዳታ የመጣውን ስንዴ እንደማይሰጣቸው የተነገሩ እና በረሃብ ከሚሞቱ በጦርነት መሞትን የመረጡ ነገር ግን ለሚዋጉት ጦርነት ፍላጎት እና ዓላማ የሌላቸውን ነው :: ስለሆነም ህወሓት አሁን የቀመረው የጦር ስልት የራሱን ዕድሜ ከማሳጠር ባሻገር የትግራይን ምድረ ባዶ የሚያስቀር ነው ::
በመጨረሻ ድል ለእውነት እና ለፍትህ እየተዋደቀ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013