ብሔር የአንድ ማህበረሰብ ክፍፍል መገለጫ ሲሆን፤ ብሔርተኝነት ማህበረሰብ እስካለ ድረስ የማይቀር ማህበረሰባዊ ዕውነታ ነው። ይህ ዘመናዊ ብሔርተኝነት በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ እንደተፈጠረ ይነገራል:: በሃያኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ወደ እስያና አፍሪካ የተስፋፋ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ብሔርተኛነት በአብዛኛው መነሻው ከጭቆና ጋር ይያያዛል:: ጭቆናው ሲበረታ የበለጠ ብሔርተኝነቱ ሥር ይሰዳል:: ሆኖም ግን ብሄርተኝነት ጭቆና በሌለበት ለቡድኖች መሳሪያም ሲሆን ይታያል:: በመልካምነት ሊወሰድ የሚችለው ብሔርተኝነት አክራሪነት ታክሎበት ከብሔሩ ውጪ ላለው አካል ከፍተኛ ጥላቻ እንዲኖር ያስገድዳል:: ይህም ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት እንደሚባል መረጃዎች ያመለክታሉ::
ብሔርተኝነት በዓለም ላይ የፖለቲካ ርዕዮት መሆን ከጀመረ ሁለት ክፍለ ዘመናትን ያሳለፈ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥሯል:: መሪ ሐሳቡ የአንድ ግለሰብ ታማኝነት ከሁሉ ዓይነት የግል ወይንም የቡድን ፍላጎት በላይ ለብሔሩ ወይንም ለብሔረ መንግስቱ ነው ይላል። ስለሆነም ብሔርተኝነት የብሔርን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና በተለይ ደግሞ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ለማሳደግ የሚጥር ሥርዓት ነው።
በኢትዮጵያ ያለው የብሔርተኝነት ፉክክር፣ ባለፉት ሶስት ዐሥርት ዓመታት አፈና ለማስቆም ጥሩ መሣሪያ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ቢሆንም፤ ብሔሮች ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የሚያደርጉትን ጥረቶች ከማስተጓጎል ባለፈ ፤ በግንባር ቀደምነት መብታቸውን ለማክበር እና የህልውና አደጋቸውን ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል ብሎ ደፍሮ ለመናገር ያዳግታል። በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት የተተገበረበት መንገድ የአንድ ብሄርን የበላይነት አንግሶ የሌሎችን ብሄር ብሄረሰቦች ጭቆናና ያፋፋመና አብሮ የመኖር ዕሴትን የናደ ነበር::
ኢህአዴግ ህውሓት ለብሔር ነፃነት የሚል ሽፋንን በመስጠት ክልሎችን የከፋፈለበት መንገድ እና ለእያንዳንዱ ብሔር የተሰጠው የተንሻፈፈ ታሪክ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ ጥላቻ እንዲኖረው አድርጓል:: በኢትዮጵያም የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ፖለቲካ እንዲዳብር የራሱን ሚና የተጫወተ ሲሆን፤ የብሔሮች ጥያቄ ለራስ ቡድን ከመወገን በላይ ከሌላ ብሔር ጋር ራስን በማነጻጸር ግጭት ውስጥ እስከመግባት በመደረሱ ተደጋጋሚ ችግሮች ታይተዋል::
አሸባሪው ህውሓት ኢትዮጵያን ለማዳከምና የራሱን ነጻ ሀገር ለመመስረት እንዲያመቸው በማሰብ የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚል አንቀጽ ቢያስቀምጥም እንኳን ሀገር ቀርቶ ክልል ለመሆን በጠየቁ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ መብት ከማፈን ጀምሮ በርካታ ግድያና እስር ፈጽሟል:: በሲዳማና በሶማሌ ብሄሮች ላይ የደረሰውም ግፍና መከራ ለዚሁ አንድ ማሳያ ነው:: በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የደረሱ ግፍና በደሎችም ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም:: በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን በማሰርም አፋን ኦሮሞን የእስር ቤት ቋንቋ አድርጎት ቆይቷል::
እነዚህና መሰል ጥፋቶች በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ካነሳሱ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው:: ለውጡን ተከትሎ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ይዘዋል:: ነውጡ ለውጥን ሲያመጣ በእርሳቸው የሚመራው መንግስት የፖለቲካ እና ሲቪል ምህዳሩን ከማስፋት በተጨማሪ በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወሰደ::
በማህበረሰቦች ወይም ብሔረሰቦች ላይ ተፈጽመዋል ተብለው በሚታሰቡ ጉዳዮች ዙሪያ ማሻሻያዎችን እና የአገሪቱ ሀብት ተመጣጣኝ ተደራሽነት እንዲኖር ዕድሉ ይፈጠራል የሚል ተስፋን በግልጽ የለውጡ መንግስት ለማሳየት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት አሸባሪው ህውሓት በየጎጡ 114 የሚደርሱ ብሄር ነክ ግጭቶችን በማፋፋም ሀገሪቱ በቀውስ ውስጥ እንድትዘፈቅ በርትቶ ሰርቷል::
አሸበባሪው ህውሓት ባቀነባበራቸው ግጭቶች ግድያ እና የአካል ጉዳት፣ በመኖሪያ እና በንግድ ቤቶች ላይ ውድመት እንዲሁም ለቁስለኞች ህክምና የሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች ድረስ ጥቃት መፈጸም እዚህም እዚያም መታየቱን ቀጠለ:: ከሁሉም በላይ በ2011 እና 2012 ሰዎች በብሄራቸው ምክንያት ብቻ ተገድለዋል:: ህወሓት ያነበረው ጽንፍ የወጣ በብሔር የመከፋፈል መንፈስ ምክንያት ትውልዱ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ መግባቱ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ያደበዘዘ እና በብዙዎች ዘንድ የእርስ በእርስ መጠራጠርን የፈጠረ እና ያፋፋመ ነበር:: ሆኖም ግን የህውሓት ጀንበር እየጠለቀች ስትሄድ በብሄርተኝነት በዚያው መጠን እየተዳከመ ሄደ::
ሰሞኑ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኘው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እንዳለው ኢትዮጵያን ለቀውስ የዳረጋት የጎሳ ፖለቲካ ሃሳብ ተወልዶ አድጎ ፤ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን እየሞተ ያለ ይመስላል:: በተለይም አሸባሪው ህወሓት እራሱ ቆስቁሶ እራሱ በጋየበት እና መከላከያ ሰራዊቱን ከኋላ የወጋበት አሳፋሪ ድርጊት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጎሳ ፖለቲካን አደጋነት እንዲረዳ አድርጎታል:: ለዚህም ይመስላል ሁሉም ኢትዮጵያ ለሀገሬ እዘምታለሁ በሚል ስሜት አሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት ከዳር እስከዳር የተንቀሳቀሰው::
ህውሓት የከፈተው ሀገርን የማፈራረስ አካሄድ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የህግ ማስከበር ዘመቻን ከመደገፍ በተጨማሪ አገር ለማፍረስ የትኛውንም አካል እንደማይታገስ ከየብሔሩ የተውጣጣው ለአገሬ ህልውና እዘምታለሁ ያለው ወጣት ምስክር ሆነ:: በእሳቱ ላይ ነዳጅ እያርከፈከፉ ከብሔርተኝነት በላይ ጽንፍ የወጣ አክራሪ ብሔርተኝነትን አስርጸው፤ ይህንን መሳሪያ አድርገው የኖሩት የህውሓት የሽብር ቡድን አባላት በጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዱር በገደሉ እየተቀጡ ይገኛሉ::
ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ብሔር ሳይለይ መላው ህዝብ አረጋውያን እና ህፃናት ሳይቀሩ መከላከያን ለመደገፍ ሰልፍ ከመውጣት ባሻገር በአቅማቸው የስንቅም ሆነ የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አሳዩ:: ጽንፍ በወጣ ብሔርተኝነት ተወጥራ ለመተርተር ጫፍ ደርሳ የጥፍርን ቅንጣት ታህል እንደቀራት በስጋት ሲነገርላት የነበረችው፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ተመለሰች:: ኢትዮጵያ በምንም መልኩ እንደማትበታተን ታየ:: በኢትዮጵያ ጽንፍ የወጣ አክራሪ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያዊነት እና በብሔርተኝነት ብቻ ተተካ::
የተደፈረው አንድ ብሔር አይደለም:: ‹‹አደጋው የአንድ ብሔር ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ነው፤›› ያሉ ዘማቾች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መከላከያ ሠራዊቱን ለሚቀላቀሉ ከሀዲያ ሆሳዕና 1 ሺህ ወጣት፣ ከጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ከ 1ሺ 300 በላይ ወጣቶች ፣ ከሲዳማ ክልል ከ 5 ሺ በላይ ወጣቶች መከላከያን ለመቀላቀል ተሸኝተዋል:: ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌም ሆነ ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ክልሎች እና አካባቢዎች በነቂስ ወጣቶች ዘምተዋል:: ምክንያቱም የኢትዮጵያ ጉዳት የእያንዳንዱ ብሔር ጉዳት ነው:: እናም ኢትዮጵያ ጽንፍ ከወጣ ብሔርተኝነት ወደ ሀገራዊ አንድነት ለመሸጋገር ችላለች:: በዚህም በኢትዮጵያ የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ቀብር የተፈጸመ ይመስላል::
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም