በ32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በመሳተፍ ላይ ካሉ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት የበላይነቱን እንደሚይዙ ከሚጠበቁት ሃገራት መካከል ትገኛለች። የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያም ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በወንዶች 10ሺ ሜትር የተመዘገበ ሲሆን፤ ሁለተኛው ወርቅ ደግሞ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ውድድራቸውን በሚያደርጉት ሴት አትሌቶች ሊመዘገብ እንደሚችል ይጠበቃል።
ቀላል ግምት በማይሰጠው በዚህ ውድድር የዓለም ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆኑ አምስት አትሌቶች የኦሊምፒኩን ክብር ለማግኘት የሚፋለሙበት በመሆኑ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል። ሦስቱ ባለፈጣን ሰዓት አትሌቶች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ ኬንያዊያኑ ሄለን ኦቤሪ እና አጄንስ ቲሮፕ ናቸው። የረጅም ርቀት ክብርን ከኢትዮጵያዊያን ለመንጠቅ አብዝታ የምትተጋው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፈን ሃሰንም ከሌሎቹ የዘገየ ሰዓት ቢኖራትም ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምትሆን ግን ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ታሪክ በአጠቃላይ 13 የኦሊምፒክ ተሳትፎዎቿ 54ሜዳሊያዎችን በተለያዩ ርቀቶች ሰብስባለች። ሃገሪቷ የስኬት ታሪክ በማስመዝገብ ከታወቀችባቸው የረጅም ርቀት የመም ውድድሮች መካከል አንዱ ደግሞ 5ሺ ሜትር መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ በዚህ ርቀት በሴቶች ብቻ 3 የወርቅ፣ 1 የብር እና 4 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። በዚህ ርቀት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ መጀመሪያውን የስኬት ተሳትፎ ያስመዘገበችው አትሌት ጌጤ ዋሚ እአአ 2ሺ የሲድኒ ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ነው። ከአራትዓመት በኋላ በተካሄደው የአቴንስ ኦሊምፒክ ሌላኛዋ የርቀቱ ጀግና አትሌት መሰረት ደፋር የወርቅ ሜዳሊያውን ስትወስድ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያው ባለቤት ነበረች።
በቀጣዩ የቤጂንግ ኦሊምፒክ የጥምር ስኬት ባለቤት የነበረችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን፤ እርሷን ተከትላ የገባችው መሰረት ደፋር ደግሞ የብር ሜዳሊያውን ወስዳለች። በለንደን ኦሊምፒክ መሰረት ወደ ወርቅ ባለቤትነቷ ስትመለስ ጥሩነሽ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያውን ከእጇ አስገባቸው። ይኸው ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ የስኬት ታሪክ ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክም ቀጥሎ በአልማዝ አያና የነሐስ ሜዳሊያ ሊመዘገብ ችሏል።
ኢትዮጵያ በርቀቱ ያላት የኋላ ታሪክ ከስኬት ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ብርቱዎቹ አትሌቶች ክብራቸውን አሳልፈው እንደማይሰጡም ይታመናል። የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ሃገሯን በ10ሺ ሜትር በምትወክለው ለተሰንበት ግደይ የተያዘ ሲሆን፤ ሃገሪቷ ቶኪዮ ላይ በምታደርገው 14ኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋም በዚሁ ርቀት በአዳዲሶቹ የኦሊምፒክ አትሌቶች ሜዳሊያ ሊመዘገብ እንደሚችል ከፍተኛ ቅድመ ግምት ተገኝቷል። ቡድኑን የሚወክሉት ሦስት አትሌቶች ሲሆኑ፤ እነርሱም ጉዳፍ ጸጋይ፣ ሰንበሬ ተፈሪና እጅጋየሁ ታዬ የማጣሪያ ውድድራቸውን አልፈዋል።
በማጣሪያ ውድድሩ ምድብ አንድ የሮጡት ሁለት አትሌቶች ሲሆኑ፤ ሰንበሬ ተፈሪ 14፡48.31 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ስትወጣ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ደግሞ 14፡48.52 በሆነ ሰዓት አራተኛ በመሆን ነበር ማጣሪያውን ያለፉት። ምድብ ሁለት የተካፈለችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በበኩሏ 14፡55.74 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ከምድቡ አንደኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው።
በርቀቱ በተለይ ለአሸናፊነት የምትጠበቀው ጉዳፍ ጸጋይ ከወር በፊት ሄንግሎ ላይ በተካሄደው የሰዓት ማሟያ 14:13.32 ያስመዘገበች ሲሆን፤ ይህም ከምድቡ ቀዳሚ ነው። ሰንበሬና እጅጋየሁም በአንድ አንድ ሰከንድ ብቻ የዘገየ ሰዓት ሲኖራቸው በዛሬው ውድድር ከሚሳተፉት አትሌቶች ደግሞ እጅግ የፈጠነ ሰዓት ባለቤቶች ናቸው። ይህም አሸናፊ በመሆን ለሃገራቸው ተጨማሪ ሜዳሊያ እንዲያስመዘግቡ ሊደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚካሄደው ሌላኛው የፍጻሜ ውድድር የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ነው። በዚህ ርቀት ሁለት አትሌቶች የሚሰለፉ ሲሆን፤ በማጣሪያው አንደኛ ሆኖ የገባው ለሜቻ ግርማ 8:09.83 የሆነ ሰዓት ነበር ያስመዘገበው። እርሱን ተከትሎ የገባው ጌትነት ዋለ ደግሞ 8:12.55 በሆነ ሰዓት ሮጧል። በርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት የሆነው ወጣቱ አትሌት ጌትነት እአአ 2017 እና 2019 በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሃገሩን የወከለው አትሌቱ በርቀቱ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ የሜዳሊያ ባለቤት ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013