ጦርነት እንኳን ለሰው ልጅ ለአጠቃላይ ህይወት ላላቸው ፍጡራን ጥቅም የለውም። ለምድርም ሆነ ለነዋሪዎቿ አጥፊያቸው እንጂ፣ አልሚያቸው አይሆንም። ይህን እርባና ቢስነቱን እያወቁ በጦርነት ውስጥና ከውጤቱ በኋላ “እናተርፋለን” ባዮች በረቀቀ ሴራ ጦርነትን ደጋግመው ሲጭሩ፤ ህዝብን ከህዝብ ሲያጫርሱ እናስተውላለን። በተለይም በ<ግሎባላይዜሽን> መርህ የሚመራ፣ በጦር ኃይል ደካማ የሆነውን የአገር ሀብት መቆጣጠር በጉልበት እና በቴክኖሎጂ ተተግኖ መዝረፍ ግቡ ነው።
ይህ በቀማኞች የሚመራ ጦርነት ሰብዓዊ ፍጡርን በሙሉ ለጥቅሙ ሲል እንደሚጨርስ ትናንት በማይጨው ጦርነት ታይቷል። ዛሬ ደግሞ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በሶሪያ፣ በፍሊስጤም ተረጋግጧል። የግሎባላይዜሽኑ ፊታውራሪ የአንድ አገር ዜጋ እርስ በእርሱ ቢጫረስ፣ ሕዝብ ቢፈናቀል ደንታ የለውም። ግቡ እርስ በእርስ አጫርሶ <ጥቁሯ አህጉር> የሚላትን አፍሪካ መዝረፍ ነው።
ታዲያ በግሎባላይዜሽኑ ቁንጮ አሜሪካ ተኮትኩቶና ተደግፎ ከደደቢት በረሃ ተነስቶ ለዙፋን የበቃው ጁንታው ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት የአገርን ጥቅም አሳልፎ ሲሰጥ የኖረ፣ እየሰጠ ያለ እንዲሁም የግሎባላይዜሽኑ ተላላኪ እና ጥቅም አስከባሪ ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ነው። ይህ አሸባሪ ቡድን ዜጎች በከፈሉት መራራ መሰዋዕትነት በ2010 ዓ.ም ከሥልጣኑ እንዲነሳ ሲደረግ አጋጣሚው መብረቃዊና ያልተዘጋጁበት በመሆኑ ሕወሓትን ያስደነገጠውን ያህል፣ ጥቅም አስከባሪያቸው በድንገት በምእበል ሲመታ የምዕራቡ ዓለምም ቀልባቸው ተገፈፈ።
ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ተነቅሎ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ የመሸገው ጁንታው ከጠዋት ከማታ ሳያስበው እጁ ላይ ሸርተት ያለውን ስልጣኑን ለማስመለስ፤ በሀገርና በህዝብ ላይ የተለያዩ ሴራዎችን በማሴር ምድሪቱን አኬል ዳማ ማድረጉን ተያያዘው። መንግሥት ከጦርነት ማንም የሚያተርፍ የለም፣ በመነጋገር ችግሩን እንፍታ በሚል በተደጋጋሚ ለሰላም እጁን ቢዘረጋም፤ የማፊያው ቡድን ጦርነት ባህላዊ ጨዋታየነው በሚል ተሳለቀ። ይባስ ብሎ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንደ ፍርሃት በመቁጠር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባው በመውጋት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የእጅ አዙር ጦርነት ከፍቷል። የአገር ሉዓላዊነትን በውጭ ጠላት አስደፍሯል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለም ጁንታው በአገር መከላከያ ላይ የፈፀመውን የአገር ክህደት ወንጀልና የሽብር እርምጃ አንድም ተቃውሞ አላሰማም ነበር። በማይካድራ ከአንድ ሺ በላይ ንጹሃን ሰዎች ሲጨፈጨፉ ምንም አልተነፈሰም ነበር።
ጁንታው ቀደም ሲል ይህንን በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ የሽብር ወንጀል ሲሰራ አይተው እንዳላዩ በዝምታ ተመልካች የነበሩት ምዕራባዊያን፤ መንግሥት ሳይወድ በግድ በክልሉ ህግን ወደ ማስከበር እርምጃ ሲገባ የምዕራቡ ዓለም ቅጥ ያጣ ማስጠንቀቂያ ማጉረፉን ተያያዙት። ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ ነው። ሰብዓዊ ድጋፍ አልደረሰም በሚል መንግሥትን ከማዋከብ ባለፈ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ገብተው በእጅ አዙር ጦርነት ከፈቱ። በመንግሥት ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን እስከመጣል ደረሱ።
እንዲሁም ዋና ዋና ምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ሙያዊ ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በመዘንጋት የሃሰትና ለአንድ ወገን ያደሉ ዘገባዎችን ሲያስተላልፉ ከርመዋል። አሁንም እያስተላለፉ ነው። የምዕራባዊያን የእጅ ስራ የሆነው የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት (አምነስቲን ኢንተርናሽናል) ሳይቀር በአክሱም በርካታ ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውን አገኘሁት ባለው ለአንድ ወገን ያደላ፤ ያልተረጋገጠ መረጃ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት ሪፖርት ለዓለም ህዝብ አስተጋባ።
ጠዋት ማታ ሳይታክት ለሰላም የሚታትረው መንግሥት ግን የትግራይ አርሶ አደር እርሻውን እንዲያርስና ህዝቡም ስለሰላሙ ቆም ብሎ እንዲያስብበት ለማድረግ ሲባል ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን የተናጠል ተኩስ አቁም ጥያቄ መሰረት በማድረግ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ክልሉን ለቆ ወጥቷል።
በአንጻሩ መንግሥት የወሰደውን ይህን እርምጃ ጁንታው አልተቀበለውም። እንዲያውም እኩይ ተግባሩን ግፋ በለው ለማለት በር ያገኝ ይመስላል። የምዕራብ አገራት መንግሥታትም ጦርነቱ እንዲቆም ሲወተውቱ የቆዩ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው እርምጃን ብዙዎቹ በዝምታ ማለፍ ወሰኑ። ከሰኔ 21 በኋላ በነበረው ጊዜ የአሸባሪው ቡድን እርዝራዦች ያካሂዱ የነበሩትን መጠነ ሰፊ ግድያ፣ ትንኮሳ፣ አፈና፣ የስደተኛ ጣቢያዎች ወረራ …. ወዘተ ባላየ፣ ባልሰማ አለፉት። ከነ አካቴው የህወሓት ኃይል የአማራ ክልልን ሲወር ቡድኑ እንዲታቀብ በመገሰጽ ፈንታ የሚያበረታታ መግለጫ ሰጡ። ይባስ ብለው በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል በመሰናዳት ላይ ናቸው።
በተጨማሪም እንደ ኒዮርክ ታይምስና አሶሼትድ ፕሬስ ያሉ ሚዲያዎቹም አሸባሪው የህወሓት እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሰ እምቦቃቅላ ህጻናትን ሳይቀር በአደንዛዥ እጽ እያሳበደ ለውትድርና መጠቀሙን በማሞካሸት የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል። እንደ አሜሪካ የለየለት ደግሞ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ ማዕቀብ በመጣል ያላቸውን ፍላጎት ምን እንደሆነ በግልጽ አሳይተዋል።
በጥቅሉ መንግሥት ላለፉት ስምንት ወራት ሳይወድ በግድ በክልሉ በቆየበት ህግ የማስከበር ዘመቻ ያለአንዳች አጋዥ ሰላምን ለማምጣት መጣሩና በክልሉ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለሰብዓዊ ድጋፍ ወጪ ማድረጉ “እንደኩነኔ” ሲቆጠር፤ በአንጻሩ የዘር ፍጅት፣ የአገር ክህደት ወንጀል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የጦር ወንጀል …. ወዘተ የፈጸመውን የህወሓት መራሹን ሽብርተኛው ቡድን “እንደጻዲቅ” በመቁጠር ምዕራባዊያን ከዚህ ሽብርተኛ ቡድኑ ጎን ያሰለፋቸው ሚስጥሩ ምንድ ነው? የአሜሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ሲያደርግ የሚስተዋለው ለምን ይሆን? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።
በዓመት 12 ሺህ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት ከታዳጊ አገራት ወደ አደጉ አገራት ወይም ወደ ምዕራባዊያን ይጓጓዛል። ስለዚህ ምዕራባዊያን ከታዳጊ አገራት የሚመዘብሩትን ጥቅም ለማስከበር ድብቅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈው ነው የሚንቀሳቀሱት። ለአብነት የአሜሪካ ግሎባል ዲ ኢንዱስትሪ ላይዜሽን (deindustrialization) ና ዲ ፖፑሌሽን (depopulation) የሚሉ ሁለት ታዳጊ አገራትን መሰረት ያደረጉ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች አሏት። ዲ ኢንዱስትሪያላይዜሽን በሚለው ድብቅ ፖሊሲዋ ታዳጊ አገራት ጠቅላላ ኢንዱስትሪያላይዝ እንዳይሆኑና ኢኮኖሚያቸው እንዳያድግ ሽባ ማድረግ የሚል መርህ ሲሆን፤ ዲ ፖፑሌሽን የሚለው ፖሊሲዋ ደግሞ ለኢንዱስትሪ እድገት ግብዓት የሚሆነውን የሰው ኃይል እንዳያድግ ወይም የህዝብ እድገት እንዳይጨምር መቀነስ መገደብ የሚል አንድምታ ያለው ነው።
ስለዚህ አሜሪካ ብሎም ምዕራባዊያን የታዳጊ አገራት ብልጽግናና እድገት ለድህንነታችንና ለብልጽግናችን ጸር ነው የሚል ጽኑ አቋም አላቸው። በመሆኑም አሜሪካ ብልጽግናቸውና እድገታቸው ያሰጋኛል፣ ኢኮኖሚያቸው ሽባ መሆን አለበት፣ መረገጥ አለባቸው ብላ በድብቅ ፖሊሲዋ በጥብቅ ከምትከታተላቸው በዓለም ዙሪያ ካሉ 13 አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
ከዚህ አኳያ አሜሪካ ይሄንን ድብቅ ፖሊሲዋን በነዚህ አገራት ለማስፈጸም የተለያዩ መንገዶችን የምትከተል ሲሆን፤ አንዱ ባላደጉ አገራት ያሉ እምቅ ሃብትን ለመመዝበር በአገራቱ የሞግዚት አስተዳደር ማስቀመጥ ነው። አይ ለአገር ጥቅም እንቆማለን በሚል የአሜሪካን ጥቅም የማይጠብቁና አሻፈረኝ የሚሉትን ደግሞ አሜሪካ በሴራ ከዙፋናቸው ማስነሳት፣ አል ያም ማስገደል ነው። ለአብነትም አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የቀድሞውን የችሊ ፕሬዚዳንት በአንድ የፍራፍሬ ካንፓኒ ውስጥ ሲአይኤ ገሎታል። ኢንዶኖዢያ ሱካርኖ የሚባል አንድ በጣም አገሩን የሚወድ ሰው አሜሪካ ለሱ ስለማትመች ገላዋለች ፓናማ ኢራን ሳደሙሴን ዓለምን የሚያጠፋ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ሰርቷል። ዓለምን ሳያጠፋ እርምጃ መወሰድ አለበት በሚል በኢራን ላይ ጦርነት ከፍታ ሳዳሙሴንን በስቅላት ገድላ ኢራንን እስካሁን ድረስ የጦር አውድማ አድርጋለች። ነገር ግን ሳዳሙሴንን ከገደለች በኋላ ኢራን ውስጥ ምንም አይነት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አለመገኘቱ ይታወቃል።
ሌላው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር እንዲሁም ዲሞክራሲን በተግባር በማስፈን አገራቸውን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ዜጎች አሜሪካና ምዕራባዊያን ባስቀመጧቸው አሻንጉሊት መንግስታት አገር ጥለው እንዲሰደዱ የማድረግ ስትራቴጂ መከተል ነው። በዚህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር አቅም ያላቸውን ወደ አገራቸው በመውሰድ አገራቸውን ሲያለሙ አፍሪካን ጨለምተኛ አስተሳሰብ ባላቸው መሪዎች የማዳከም ስራ ይሰራሉ። ከዚህ አኳያ ጁንታው ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአሜሪካንና የምዕራባዊያኑን ትልም በማሳካት ወደር የለሽ ነው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ስደት በህወሓት ዘመን በስፋት የታየበት ነበር።
በተጨማሪም አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ1982 እስከ 1989 ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ከተለያዩ ታዳጊ አገር የተውጣጡ ከፍተኛ የደህንነትና የጸጥታ ሃይሎችን አሜሪካ ድረስ ወስዳ በማሰልጠን፤ እርሷ ሳታውቅ አይደለም የጦር መሳሪያ ቀርቶ የህመም ማስታገሻ ክኒን አገራቱ እንዳይገዙ ወይም ከውጭ እንዳያስገቡ አሰልጥና አስቀምጣለች። በዚህም በነዚህ ታዳጊ አገራት አሜሪካ ሳታውቅ ምንም የሚደረግ የልማትም ሆነ የፖለቲካ ስራ የለም።
ስለዚህ ምዕራባዊያንና አሜሪካ የነጭ የበላይነት ቀንበርን ሁሌም በጥቁር ህዝብ ትክሻ ለመጫን የመላ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል የሆነችውን የኢትዮጵያን አከርካሪ ለመስበር ስትራቴጂ ነደፋ እየተንቀሳቀሰች ነው የምትገኘው። አሜሪካ ይህንን ሴራዋን ለማሳከት ደግሞ በበታችነት ስሜት ደደቢት በረሃ የወረደውን የህወሓት አሸባሪ ቡድንን ኮትኩታና ደጋግፋ ለዙፋን አበቃችው። ቡድኑም ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት አገሪቱ በአንድነቷ ጸንታ እንዳትኖር የስታሊኒን ሃሳብ “የራስን አድል በራስ የመወሰን” የሚል ሃሳብ በተላላኪያቸው በጁንታው አማካኝነት አምጥተው በህገ መንግስቱ አስቀመጡ።
በዚህም በአርባ ጉጉ የዘር እልቂት ከተጀመረ ጀምሮ በመላ አገሪቱ እስካሁን ድረስ ለተፈጸመው የዘር ፍጅት አሸባሪው ቡድንን አሜሪካና ምዕራባዊያን በሽብርተኝነት ሊፈርጁትና ማዕቀብ ሊጥሉበት ሲገባ፤ ለምን በዚህ ወቅት በለውጡ ምህዋር ህዝብና መንግሥትን ወደ ብልጽግና ማማ ለማውጣት መንግሥት በሚታትርበት ወቅት አሜሪካ ጫና እያደረገች ትገኛለች ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።
አሜሪካ አሁን ላይ አንዴ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታ አልደረሰም በሚል በመንግሥት ላይ ጫና እያደረሰች ያለችው ለምንድነው ቢባል፤ አንደኛ ከአሜሪካ ድብቅ ፖሊሲ አንጻር ጁንታው ባለፉት 27 ዓመታት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የአገርን ሃብት እየመዘበረ የምዕራቡን ዓለም ጥቅም በማስከበር የተላላኪነት ስራውን በተሳካ መንገድ ሲተገብርና ትውልድን ሲያቀነጭር የኖረ ነበር። ስለዚህ ጥቅማቸው የተነካባቸው አሜሪካና ምዕራባዊያን ይህን ተላላኪ ኃይል ድርድር በሚል ሰበብ አመድ ከለበሰበት አመዱን አራግፈው ወደ ሥልጣን ዙፋን ደጋግፈው ለማምጣት ነው።
ምክንያቱም በጊዜ ሂደት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ አካሄድ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ መሆናቸውን ይፋ እያደረጉ መምጣታቸው፤ ብሄርተኛውን ህወሓትን ሲደግፉ የቆየው ምዕራባዊያኑና አሜሪካ ሃሳብ ገብቷቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያን ሊያስቀድም የሚችል ኃይል የበላይ ሆኖ መውጣቱ በምዕራቡ ዓለም ፖሊሲዎች ላይ ምን ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አርቆ አሰቡ። ስለዚህ መንግሥትን በተለያየ ጫና ከስልጣን በማስወገድ ተላላኪ መንግሥት ለማስቀመጥ የሚደረግ ግብ ግብ ነው።
እንዲሁም መንግሥት ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደሙ ከህወሓት ጋር የሰሩና ምናልባትም ጥቅም ተጋሪ የነበሩ የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት ይህ አዲስ ሁኔታ ሊመቻች እንደማይችል ሲገነዘቡ “ይቺ ባቄላ….” ማለት ጀመሩ። በአሜሪካ ዘንድ እድገት ብሎ የሚናገር መረገጥ አለበት። ስለዚህ መንግሥት ብልጽግና ብልጽግና ማለቱ አንዱ መወጊያው ሆነ ማለት ነው።
ሁለተኛው ዓለም አሁን ላይ ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ገብታለች። ቻይና ያለምንም ጦርነት አፍሪካን በሙሉ በኢኮኖሚ ማርካለች። ይህ ዘግይቶ የገባት አሜሪካ ከቻይና ጋር በአፍሪካ ጉዳይ ሲሎ ለሲሎ ታናንቃለች። ስለዚህ ዝሆኖቹ አሜሪካና ቻይና በሚያደርጉት ፍትጊያ የመጫዎቻ ሜዳ ኢትዮጵያ ሆናለች።
ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ እንደባቡር መስመር፣ የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ስራ ፣ የመንገድ ስራ፣ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወዘተ የመሳሰሉ በቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ፕሮጀክቶች የተገነቡት/የሚገነቡት በቻይና ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ከቻይና በወሰደችው ብድር ብዛት ከጅቡቲ ቀጥላ ሁለተኛ ስትሆን የገንዘቡ መጠንም 16 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። ስለዚህ ይህ የቻይናና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትስስር የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ መንግሥት በአሜሪካ መንግሥት በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረጉት/የሚያደርጉት ጉዳይ ናቸው።
በሦስተኛ ደረጃ ሶማሌ፣ ጅቡቲ፣ኤርትራና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ እናደርጋለን የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ራዕይ ስራ ላይ ከዋለና አሰሪ የጋራ ፖሊሲ መንደፍ ከተቻለ የህዝብ ቁጥሩ ወደ 150 ሚሊዮን የሚጠጋው ይህ አካባቢ ለብልጽግና መሰረት ይሆናል። አካባቢው ትልቅ ገበያ ሊሆን ከመቻሉ በላይ ቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ላይ መገኘቱ ጠቃሚነቱን ያጎላዋል። በየብስ ላይም ሆነ በባህር ላይ በርካታ የልማት ሥራዎች ሊከናወኑ ይችላሉ።
በአንድነት የተሰበሰቡት እነዚህ አገራት ጠንካራ የወታደራዊና የባህር ኃይል ለመመስረትና ለማስተዳደር ጉልበቱም አቅሙም ይኖራቸዋል። ከህዝብ ቁጥር ባለፈ በኢኮኖሚ ሊጎለብቱ ከቻሉ ነጻነታቸውን፣ ልዑላዊነታቸውንና ክብራቸውን ያስከብራሉ ጥቅማቸውን፣ ያስጠብቃሉ። አካባቢውም ወደሰላም ቀጠና ሊቀየር ይችላል። ይህ ደግሞ ለአህጉሩ ተምሳሌት በመሆን ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ስለዚህ ይቺ አገር ለጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን ለነጻነታቸው በር እንደከፈተች ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ከራሷ አልፋ አህጉሩን በማንቃት ታሳምጽብናለች በሚል በኃያላኖቹ ጥርስ ውስጥ ገብታለች።
ሌላው የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በስኬት እየተጠናቀቀ መምጣቱ ፖለቲካልና ኢኮኖሚካል አንድምታ አለው። ይህም የግብጽን የበላይነት ያናጋል። ጂኦፖለቲክሱን በሙሉ ይቀይረዋል። ስለዚህ ምዕራባዊያን አጀንዳቸው ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ዳግማዊ አድዋን በህዳሴ ግድቡ ላይ በመቀናጀቷ፤ ይቺ አገር እንደለመደችው ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን አስተባብራ በነጭ የበላይነት ላይ እንደገና ጥቁሮችን ታስነሳለች የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ግድቡን ከገደበች በኢኮኖሚና በፖለቲካ ትፈረጥማለች። በወታደራዊ ኃይልም ሱፐር ፓወር ትሆናለች የሚል ስጋት ስላለባቸው “እሾህን በሾህ” እንዲሉ አበው በጁንታው አማካኝነት የእጅ አዙር ጦርነት ምዕራባዊያንና አሜሪካ ከፍተዋል።
እንዲሁም ከምስራቁ ዓለም በተለይም ከሩሲያና ከቻይና ጋር ኢትዮጵያ እያጠናከረች የሄደችውን ግንኙነት የምዕራቡ ዓለም በግዴለሽነት አልተመለከተውም። በተለይ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ኒክሊየር የኃይል ማበልጸግ ስምምነት አላቸው። ይሄ ስምምነት አይደለም ግብጽን አሜሪካን እያሰጋት ያለ ትልቅ ችግር ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ያካላት የተፈጥሮ ጸጋ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ጋር ተዳምሮ ነገ ላይ የማይገፋ ሃይል ትፈጥራለች በሚል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
ከዚህ አኳያ ምዕራባዊያንና አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ሁሉም ዜጋ በመረዳት የኢትዮጵያ ህዝብ ምዕራባዊያንና አሜሪካ በጁንታው አማካኝነት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፈቱትን የእጅ አዙር ጦርነት ሁሉም የአገሩን ሉዐላዊነትና ጥቅም ላለማስደፈር ከደቂቅ እስከ ሊቅ አንድነቱን በመጠበቅ ሊፋለመው ይገባል እላለሁ። ቸር እንሰንብት።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013