የዘንድሮው የዓለም ጡት ማጥባት ሳምንት ‹‹ጡት ማጥባትን መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ግዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ግዜ ከሐምሌ 25 አስከ እስከ ነሃሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
የ2013 ዓ.ም የጡት ማጥባት ሳምንት አላማዎችም ጡት ማጥባትን የመደገፍ ጠቀሜታን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማሳወቅ፣ ጡት ማጥባትን በመደገፍ ከማህበረሰብ ጤና ዋና ዋና ኃላፊነቶች ጋር ማያያዝ፣ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከግለሰቦችና ተቋማት ጋር በጋራ መስራትና ጡት ማጥባትን በመጠበቅ የማህበረሰብ ጤናን ለማሻሻል መንቀሳቀስን ያካትታል።
እ.ኤ.አ በ2019 በኢትዮጵያ ያለውን የጡት ማጥባት ሁኔታ በሚመለከት በተሰራ የስነ- ህዝብ ዳሰሳ ጥናት መሰረት 58 ከመቶ ያህሉ ህፃናት እስከ ስደስት ወር ድረስ ጡት እንደጠቡ፣ 12 ከመቶ ያህሉ ከጡት ይልቅ ሌሎች ነገሮች እንደተሰጣቸው፣ 72 ከመቶ ያህሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት የጠቡ መሆናቸው ተረጋግጧል።
የጤና ጠቋማትን ጡት ለማጥባት ምቹ የማድረግ መስፈርትን ያሟሉ 14 ጤና ተቋማት መመረቃቸውንና አንዳንድ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ጡት ማጥባት እንዲያስችላቸው የህፃናት ማቆያ ቢያዘጋጁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡም ታውቋል።
በመንግሥትም ሆነ በግል መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ለሚሰሩ እናቶች የሚሰጠው የወሊድ ፍቃድ በቂ አለመሆን፣ በጡት ማጠባት ላይ ከእናቶች ጀምሮ አስከ ማህበረሰቡ ድረስ የባህሪ ለውጥ አለመኖርና ለጡት ማጥባት ምቹ ሁኔታዎች አለመኖር አሁንም ጡት ማጥባት ይበልጥ ትኩረት እያደረጉ ያሉ ምክንያቶች መሆናቸውም ብዙዎችን ያስማማል።ከሁሉ በላይ ደግሞ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እናቶች ጡት የሚያጠቡ ቢሆንም ትክክለኛውን የጡት ማጥባት ሂደት እንደማይከተሉ ይነገራል።
በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ባለሞያ ዶክተር በላይነሽ ይፍሩ እንደሚገልፁት ዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንገሥታት ህፃናት አድን ድርጅት ህፃናት ከተወለዱ በኋላ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት መጥባት እንዳለባቸውና አስከ ስደስት ወር ድረስም ምንም አይነት ምግብ ሳይወስዱ ጡትን ብቻ መጥባት እንደሚኖርባቸው ይመክራል።በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ 58 ከመቶ ያህሉ ህፃናት እስከ ስደስት ወር ድረስ ጡት እንደጠቡና 72 ከመቶ ያህሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት የጠቡ መሆናቸው እ.ኤ.አ በ2019 በተሰራ የስነ- ህዝብ ዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል።
ይህም 42 ከመቶ ያህሉ አስከ ስደስት ወር ድረስ ጡት እንደማይጠቡ መረጃው የሚያሳይ በመሆኑ እነዚህ ህፃናት ጡት እንዲጠቡ ተደራሽ መሆን ያስፈልጋል።በተመሳሳይ 28 ከመቶ ያህሉ ደግሞ እንደተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት እንደማይጠቡ መረጃው የሚጠቁም በመሆኑ እነዚህ ህፃናት በእንድ ሰዓት ውስጥ ጡት እንዲያገኙ አዋላጁ ወይም የጤና ባለሞያው ብሎም የልምድ አዋላጁ ማስተዋወቅና ማስተማር ይጠበቅበታል።
እነዚህ ቁጥሮች አሁንም እስከ ስደስት ወር ድረስ ምንም እይነት ምግብ ሳይወስዱ ጡትን ብቻ የማይጠቡ ህፃናት ያሉ በመሆናቸውና እንደተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ እንገር የእናት ጡት የማይጠቡ ስላሉ ሁሉም እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ይፈለጋል።ይህም በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችንም ይመለከታል።አንድ ህፃን እንደተወለደም ወዲያው ጡት ላይ መቀመጥ ይኖርበታል።የእንግዴ ልጅ ከመቆረጡ በፊት ራሱ ህፃኑ ጡት ላይ መቀመጥ አለበት።ከጤና ተቋማት ውጪ የተወለዱትን ልጆች በሚመለከትም ለእናቶቻቸው ይህንኑ የጡት ማጥባት ጠቀሜታና በተለይ ህፃናቱ በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት እንዲያገኙ ማስተዋወቅና ማስተማር ይገባል፡፡
እንደ ባለሙያዋ ገለፃ ህፃናት ለስድስት ወር ያህል ምንም ነገር ሳይቀላቅሉ ጡትን ብቻ ካልጠቡ የሚከተሉ የጤና ችግሮች አሉ፤ ለህመምም ሊጋለጡ ይችላሉ።ትክክለኛ ያልሆነ አካላዊ አድገት አለመኖር፣ በሽታን የመከላከል አቅም ማነስና መሰል ችግሮች በሚከሰቱበት ግዜም አስከ ህየወተ ህልፈት ሊያደርስ ስለሚችል ይህን ጡትን ብቻ ለስድስት ወር በማጥባት መከላከል ይቻላል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ 98 ከመቶ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ያጠባሉ።ይሁንና ጡት በሚያጠቡበት ወቅት ትክክለኛውን መንገድ ተከትለው አይደለም።ልጆቻቸው ስድስት ወር ሳይሞላቸው ሌላ ነገር የሚሰጡም አሉ።በባህላዊ መንገድ ፈሳሾችን የሚሰጡም ይኖራሉ።ከዚህ አኳያ እነዚህ ነገሮች ቀርተው ትክክለኛ የጡት አጠባብ ስርዓቶችን መከተል ይኖርባቸዋል።
ለጡት ማጥባት በእናቶች፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰቡና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ትኩረት ጥሩ ቢሆንም ጡትን በትክክል ማጥባት ላይ ሰፊ ክፍተቶች በመኖራቸው በቀጣይ በዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል።ይህንን ክፍተት ከመሙላትና ጡትን በአግባቡና በትክክል ህፃናት እንዲጠቡ በማድረጉ ሂደት ከእናቶች፣ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብ ብሎም በጤናው ዘርፍ ካሉ ባለሙያዎች ብዙ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013