አብዛኛዎቻችን ሞልቃቃ የሚባለውን ቃል ከልጅነት ጊዜ አስተዳደግ ጋር አያይዘን እናየዋለን።ልጆች በወላጆች ወይም በአሳዳጊዎች አስተዳደግ ሁኔታ የተነሳ ተሞላቀው ያድጋሉ። በልማድ እንደሚታወቅ አያት ያሳደገው ልጅ ሞልቃቃ ነው ይባላል።እንግዲህ ሞልቃቃነት የሚመነጨው በልጅነት የምንፈልገው፤ ያማረንን ወይም የምንሻውን ነገር ሁሉ፤ በፈለግንበት ጊዜና ሰዓት የሚቀርብበት ሁኔታ ሲመቻችልን ነው።በተመሳሳይ ደግሞ የማንፈልገውን ወይም የማይመቸንን ነገር ለራሳችን በሚመቸን መልኩ መፈጸም ስንችል ነው።
ሞልቃቃ ልጅ ሞልቃቃነቱ የሚታወቀው ከሌሎች ልጆች በተለየ መልኩ ይህንን እፈልጋለሁ፤ ይህንን አልፈልግም ብሎ በራሱ ስሜት በመምራት ነገሮች ማስፈጸምና መፈጸም ሲችል ነው። አብዛኛው ጊዜ በአዲስ አበባ ሞልቃቃነት ምሳሌ ሆኖ የሚነገረውን የፈረንሳይዋ ሞልቃቃ ጉዳይ ትዝ አለኝ።አንዲት የፈረንሳይ ሞልቃቃ ናት አሉ።ሰዎች ሰልፍ ወጥተው ሲጮሁ አይታ።‹‹ምን ሆነው ነው?›› ብላ ትጠይቃለች።‹‹የሚበሉት አጥተው ተርበው ነው ›› ይላታል፤ ህዝቡ በእርሷ አባት ላይ አምፆ መሆኑን አልተረዳችም።ልጅት ታዲያ! ምንብትል ጥሩ ነው መሰላችሁ? ለምን ኬክ አይበሉም ብላ እርፍ አለች ይባላል።
የፈረንሳይዋ ሞልቃቃ ይህንን አለች ብለን ተገርመን ይሆናል።ሆኖም ግን የባሰው መጥቷል። አሁን ላይ ብቅ ያለው ሞልቃቃ ደግሞ በባህሪው ለየት ያለ ነው።ከፈረንሳይዋ ሞልቃቃ ንግግር ጎልቶ የሚታየው ልጅነቷና አለማወቋ ነው ልንል እንችላለን።የሰሞኑ ሞልቃቃ ግን የሚያስደንቅ ነው። ‹‹ጉድ መጣ !ጉድ መጣ ! ገንፎ ዛፍ ላይ ወጣ ›› አይነት የሆነብን የጃጁ ሞልቃቃዎች ጉዳይ ነው። ለካስ! የሞልቃቃም ብዙ አይነት አለ ።እነዚህ ሞልቃቆች ለይቶላቸው በአደባባይ ሲሞላቀቁ ጆሮ አይሰማው የለ ሰማን።ታዲያ እየፈጩ ጥሬ ማለት ይሄኔ አይደል።
ሞልቃቃው አሸባሪ ህወሐት በሥልጣን ዘመኑ ሲሞላቀቅበት ከነበረው መንበር ከወረደ በኋላ ምቾት የህልም እንጀራ ሆኖበት ቆይቷል። መንግሥት የህግ ማስከብር ዘመቻን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንኳን ሊሞላቀቅ በመኖር እና በሞት መሃል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከሞት አፋፍ የተረፉት ጥቂት የሞልቃቃው አሸባሪ ቡድኖች በቀበሮ ጉድጓድ ሆነው ከሞት አፋፍ አድኑን ጩኸት ለደጋፊዎቻቸው ዓለም አቀፉ ሚዲያዎችና ምዕራባዊያን አስተጋብተዋል ።
መንግሥትም የጥሞና ጊዜን ለመስጠት ሲል የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረጉ ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ወጣ።የአሸባሪው ቡድን አባላት ከተደበቁበት ወጥተው ‹‹አለን ከሞት አፋፍ ደርሰን ተመልሰናል›› ሲሉ ተደምጠዋል።ሆኖም ግን ከሞትም አፋፍ ቢተርፉ አብሯቸው ያልተቀረበው መጥፎና መሰሪ ባህሪ በጥሞና እንዲቆዩ አላስቻላቸው።በአማራ እና በአፋር ክልል ተኩስ በመክፈት የተለመደ የትንኮሳ ባህሪያቸውን ቀጠሉ።
በማንአለብኝነቱ የሚታወቀው አሸባሪ ቡድን ጦርነት የባህርይ መገለጫው ነውና ወጣቶች፣ ለእድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናት በአደንዛዥ እጽ አስክሮ ወደ ጦርነት እያማገዳቸው ይገኛል።የትግራይ እናቶች ለስምንት ወራት ያሳለፉት ስቃይና ሰቆቃ አይበቃችሁም ብሎ ህጻናት ልጆቻቸውን ከጉያቸው እየነጠቀ ወደ እሳት እየማገደ መራራ እንባን እያስነባቸው ይገኛል።
የትግራይ ህዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው እግዚኦ ደረሱልን እያለ ሲማጸን የቆየው አሸባሪ ቡድን ሰብዓዊ እርዳታ ህዝቡ እንዳይደርስ መንገድ ሲዘጋ ቆየ።ገና ከጅምሩ የተከዜ ግድብን በማፍረስ፤ እርዳታው አማራጭ በሆነው የአፋር ክልል በኩል እንዳይጓጓዙ ሲያስተጓጉል ነበር።በመሆኑም በአፋር ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የጫኑ 170 ተሽከርካሪዎች እንዳይጓዙ ማገዱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዲቪድ ቢዝሊይ በትዊተር ገጻቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው።የትግራይ ህዝብ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሰው በማድረግ በገዛ ወገኖቹ ላይ ጭካኔ የተሞላው የግፍ ግፍ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።
የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ ማለት አሁን ነው። ሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በጌታቸው ረዳ ይፋዊ የትዊተር ገጹ በኩል ሰሚውን ግራ ያጋባ የአሸባሪው የአቋም መግለጫ ወጥቷል።ጌታቸውን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱን መምራት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም።ካለ በኋላ በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ችግሮችን ለመፍታት ዋና የፖለቲካ ተዋናዮችን ያቀፈ አካታች ፖለቲካዊ ሂደት እና የሽግግር ሥርዓት እንዲካሄድ ጥሪ እናቀርባለን ሲል አስቀምጧል።እውን እነ ጌታቸው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን አልሰማንም ለማለት ነው፤ ሌባ እናት ልጆቿን አታምንም ማለት ይሄም አይደል።
ምን ይሄ ብቻ! በሚገርም ሁኔታ ተሞላቅቀውብናል። በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መጀመር አለባቸው ብሏል።ወደው አይስቁ አሉ ! እንዲያው እኮ የትሄጄ ልፈንዳ ያለችው ማነች? ከህግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ መንግሥት የወደሙትን ወደነበሩበት ሲመልሱ አልነበር እንዴ! ታዲያ ማን ነው የነበረውን በድጋሚ እንዳልነበር እንዲሆኑ ያደረጋቸው? ጥፋትና ጥፋት አላማው የሆነው አሸባሪ ለዚህ መቼ ያንቀላፋና ነው።
መንግሥት መሠረተ ልማቶች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ያወጣውን ወጪ ከመጥኤፍ ሳይቆጥሩ ማፈራረሳቸው ተረሳ እንዴ? ልክ እንደነሱ ከውጭ አካላት የተገኘ ድጋፍ አለመሆኑን ዘነጉት እንዴ? ኧረ በፍጹም! ይህ መች ጠፍቷቸው እነርሱ እያጠፉ ሌላው እያለማ ልኑር አይነት ሞልቃቃነት ነው እንጂ።
ከቀደሙቱ ይባስ ብሎ የሚገርመው እና የሚያስደንቀው ደግሞ የ2013 ዓ.ም. እና የ2014 ዓ.ም. በጀት በፍጥነት መለቀቅ አለበት ማለታቸው ነው። ይቺ አሁን ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ማምለጫ ዙሪያ ገባ መቃኘቱ የግድ ሲሆንበት እና ግራ ሲገባው የሚጠቀማት ዘዴ ናት። ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ተቆጣጥሬዋለሁ በሚለው የትግራይ ክልል ውስጥ አሉ ያላቸው የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች ይውጡልኝ ማለቱ ሞልቃቃው አሸባሪ አድርጎታል።
አስገራሚ ሞልቃቃ አሸባሪ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ለሁሉም አይነት የትራንስፖርት አማራጮች በርካታ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት መደረግ አለባቸው የሚል ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል።‹‹አልሰሜን ግባ በለው ›› ማለት ይሄኔ ነው። እንግዲህ ሞልቃቃ አሸባሪ በምን መግለጽ ይቻል ይሆን! እንዳይገባ ሲከለከል የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ ዳግም መሻቱ እሱ በሚፈልገው መልኩ ካልሆነ የትግራይ ህዝብ ተራበ አልተራበ ደንታው እንዳልሆነ ማሳያው ነው ።
ቀደም ሲል መንግሥት በትግራይ ክልል በሚገኙ መጋዘኖች ውስጥ ከ400 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ስንዴ እና ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የሚበልጥ የምግብ ዘይት ማስቀመጡን ተናግሯል። ሞልቃቃው አሻባሪ ይህንን ለራሱ መንደላቀቂያ በማድረግ ህዝቡ ልጆቹን ወደ ጦርነት ካልላከ እርዳታ አልሰጥም እያለ ያስፈራራል። ህዝቡን በረሃብ ሰቆቃ ውስጥ ከትቶ የተሞላቀቀ ኑሮ ይጎመጃል።
ፋታ ሲያገኝ ከህዝቡ እየነጠቀ ይሞላቀቃል። ህጻናቱን ወደ ጦርነት እየማገደ ህዝቡ እንዲራብ ከመፍረዱ ባሻገር ወደቀደመ ህይወቱ ለመመለስ ይቃጣዋል ።ታዲያ ከዚህ በላይ ሞልቃቃ አሸባሪ ታይቶ ተሰምቶ ይታወቃል እንዴ ? አሁን ጊዜው እያለቀ መደመደሚያ እየደረሰ ያለው ሞልቃቃው አሸባሪ፤ ይህንን ማለቂያ የለሽ ዲስኩር እየደሰኮረ ጆሯችንን ከሚያደማው ለሰከንድ ጆሮውን ዘንበል አድርጎ ቢያዳምጥ ይሻላል ባይ ነኝ። ኢትዮጵያ በቀላሉ ማፈራረስ እንደማይቻል ከዳር እስከ ዳር በነቂስ ነቅሎ የወጣው ህዝብ የፈጠረውን ማዕበል አይቶታል። ሞልቃቃዬ የእስካሁኑ ይበቃልና ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ወረድ! መልዕክቴ ነው።
እየሩስ አበራ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013