የቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጨረሻው የውድድር ዕለት ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም፤ የዓለም ሕዝብ ዓይንና ጆሮውን በአንድ ጉዳይ ላይ ነበር አትኩሮቱን ያደረገው።አጓጊው የወንዶች ማራቶን ሰዓቱ ደርሶ ሲጀመርም 68 ተሣታፊ አትሌቶች በስታዲየሙ ተገኙ፡፡ አረንጓዴና ቀይ የመሮጫ ልብስ ያደረገው አበበ ቢቂላም እንዳለፈው ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሣይሆን፤ የመሮጫ ጫማውን በነጭ ካልሲ ተጫምቶ ዘግየት ብሎ አትሌቶቹን ተቀላቀለ፡፡
እንደ አመጣጡም ከሁሉም ኋላ ሆኖ ሩጫውን ጀመረ፤ በቶኪዮ ጎዳና ግራና ቀኝ የተገኙት ጃፓናዊያንም በታላቅ ሥሜት በጭብጨባ ለሯጮቹ ድጋፍ ይሰጡ ነበር፡፡ ኪሎ ሜትሮች እየተቆጠሩ ርቀቱም እየጨመረ ሲመጣም ጥቁሩ የማራቶን ጄነራል እንደለመደው ጎዳናውን ብቻውን ተቆጣጥሮ ታየ፡፡ ሌሎች አትሌቶች ኃይል ሰጪ ፈሣሾችን ሲጎነጩና ፍጥነታቸውን ቀንሰው እረፍት ሲያደርጉም፤ 17 ቁጥርን የለበሰው አትሌት ግን በውሃ አፉን ከማርጠብና ራሱ ላይ ከመጨመር ባለፈ ሩጫውን ሣይገታ ወደ ስታዲየሙ ገባ፡፡ በመጨረሻም ሩጫውን ቢያበቃም 42 ኪሎ ሜትሮች ያነሱት ይመስል ግን ሰውነቱን የሚያዝናና የአካል እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡
በስታዲየም የተገኙና ውድድሩን በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከቱ የስፖርቱ ቤተሠቦችም በነገሩ ተደነቁ፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የዕለቱ የወሬ ማሟሻ ሲያደርጉት፤ ጋዜጦችና መጽሄቶችም በፊት ገጻቸው ዜናውን ይዘው ወጡ፡፡
የካናዳው ጋዜጣ ካልጋሪ ሄራልድ ‹‹ፈጣኑ ማራቶን አበበ አልደከመም›› በሚል ርዕስ በሩጫው ወቅት የነበረውን ሁኔታ አትቷል፡፡ ጋዜጣው ‹‹አንዴም ወደኋላ አልተመለከተም፣ የሥሜት ለውጥም አልታየበትም፣ ፍጥነቱንም አልቀነሰም፤ አልፎ አልፎ ብቻ ላቡን ከፊቱ ላይ ይጠርግ ነበር፡፡ በዚሁ ሁኔታ በአካልና በቴሌቪዥን ሚሊዮኖች እያንዳንዱን እርምጃውን እየተመለከቱት ከስታዲየም ገባ፡፡ አንዴ ስታዲየሙን ከዞረ በኋላም የመጨረሻዋን መስመር ሲረግጥ እጁን አነሣ፤ ከዚያም ሣር ወደለበሰው ሜዳ አመራ፡፡ በወገቡ ተኝቶም እግሮቹን በአየር ላይ ብስክሌት እንደሚነዳ ሰው በማድረግ አካላዊ እንቅስቃሴ አደረገ፡፡ ሲጨርስም በታላቅ ድምጽ ድጋፋቸውን እየሰጡ ላሉት ደጋፊዎቹ እጁን አንስቶ ሦስቴ እጅ ነሣ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አንዴም በከባድ ሁኔታ እንኳን አልተነፈሰም ነበር›› ሲል አስነብቧል፡፡
አፍሪካዊ ጉዳዮችን የሚያስነብበው አፍሪካ መጽሄትም ‹‹ከእንግዲህ እርሱ የኢትዮጵያዊያን ጀግና ብቻም ሣይሆን የፓን አፍሪካም ጀግና ነው›› በሚል ነበር ድሉን የዘገበው፡፡ የደይሊ ሚረር ጋዜጣ ዘጋቢው ፒተር ዊልሰን ደግሞ የአበበ አሯሯጥ ቢያስደንቀው ‹‹በርግጥም ጥቂት እንኳን ሕመም በእግሩም ሆነ በሰውነቱ ላይ እንደሌለበት አሞራ ነው›› ሲል ነበር ያየውን ያሰፈረው፡፡
ዘ ዴዘርት ኒውስ የተባለው ጋዜጣ በበኩሉ አበበን የኦሊምፒኩ ልዩ ክስተትና ተወዳጅ እንደነበረ ሲገልጽ ‹‹በርግጠኝነት ሕዝቡ ለቶኪዮ ከንቲባነት ድምጽ ስጥ ቢባል አበበን ይመርጣል›› ሲል በወቅቱ ያተረፈውን ዝናና ውዴታ ጠቁሟል፡፡ የክቡር ዘበኛ አባል መሆኑ በኦሊምፒኩም ላይ የሚያሣየውን እንቅስቃሴ የተመጠነና ሥርዓት ያለው እንዲሁም ሥራው ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረጉ ደግሞ ሌላኛው ትኩረት ሣቢ ትዕይንት እንደነበረም በዘገባው ተካቷል፡፡
የጀግናው አትሌት የአሸናፊነት ብሥራት በኢትዮጵያ ሲሰማም የያኔው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን አሸናፊ ሆነ›› በሚል ርዕስ ነበር የዘገበው፡፡ አስከትሎም ‹‹ቅልጥሞቹ እንደ ብረት የሚጠነክሩት ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ፤ በቶኪዮ የማራቶን ውድድር ከሚደረግበት ሥፍራ አንስቶ እስከመጨረሻው ድረስ ይታይበት የነበረው ፈገግታ ፍጹም አልተለወጠም ነበር›› ሲል ሮይተርስ አስረድቷል፡፡ የአበበ አሸናፊነት በዓለም መዝገብ ውስጥ እስከ ዘለዓለም የሚኖር ቋሚ ትዝታ አትርፏል፡፡ አበበን በየመንገዱ ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ ሕዝብ በላይ ተሰልፎ የጋለ ሥሜቱን ይገልጽለት ነበር›› በማለትም አትቷል፡፡ ታዋቂው ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠም ዛሬም ድረስ የሚዜመውን ‹‹በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ፤ አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ›› ሲል የሕዝቡን ደስታ በድምጹ አስተጋብቷል፡፡
ወደ ሃገሩ ሲመለስም ሕዝቡ በአደባባይ ወጥቶ የጀግና አቀባበል አድርጎለታል፡፡ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ቡድኑን በቤተመንግሥታቸው ጋብዘው ለአበበ ቢቂላ የሙሉ መቶ አለቅነት ማዕረግ እንዲሁም የዳግማዊ ምኒሊክን የመኮንን ደረጃ ኒሻን እንደሸለሙትም በጋዜጣ ታትሟል፡፡
ርግጥ ነው፤ ጀግናው አትሌት በማራቶን ሁለቴ በተከታታይ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቁና ለራሱና ለሃገሩም ክብርን መደረቡ አስደናቂ ገድል ነው፡፡ በዚህም መላው ዓለም የሚስማማበት በመሆኑ እስካሁንም ድረስ ሥሙን ከጀግኖች የታሪክ መዝገብ እንዲሰፍር ሆኗል። ይሁን እንጂ ጃፓናዊያን አበበን የሚያውቁትና ሥሙ ሲጠራም የሚያሣድርባቸው ሥሜት እጅግ ጥልቅ ነው። ጀግናው አትሌት በሃገሩ ከሚሰጠው ክብርና ውዳሴ የሚስተካከል አድናቆት ከሩቅ ምሥራቃዊያኑ ዘንድ ይሰማል፡፡ ታዲያ አበበ እንዲሁም እርሱ የወከላት ኢትዮጵያ በጃፓናዊያን ዓይን እንደምን ሊገዝፉ ቻሉ?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ወደኋላ መለስ ብሎ ሩጫውን ማስታወስ ያሻል፡፡ አበበ ያሸነፈውን የወርቅ ሜዳሊያ ሊያጠልቅ ወደ መድረክ በወጣ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄራዊ መዝሙር ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡ ስለዚህም የኦሊምፒኩ አዘጋጅ ሃገር ጃፓን ‹‹ኪሚጋዮ›› የተሠኘውና ጥንታዊው ብሄራዊ መዝሙራቸው ተሠማ፡፡ በወቅቱም አበበ የታመመላትንና ከቀዶ ጥገናው ሣያገግም ሮጦ ድል ያደረገላትን ባንዲራ በክብር ወደላይ ስትወጣ በስስት ሲመለከት፤ ሦስተኛ የወጣው ጃፓናዊ አትሌትና በስታዲየሙ የታደሙ ዜጎቻቸው ደግሞ በሥሜት ይዘምሩ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ ሁነት በልዩ ሁኔታ ከጃፓናዊያን ልብ ታትሞ ሊቀር ችሏል፡፡ አንጋፋ ጃፓናዊያን አሁንም ድረስ በዓይነ ልቦናቸው አበበን ሲመለከቱ፤ የማያውቁት ወጣት ዜጎች ደግሞ በምኞት ያስቡታል፡፡
ጃፓናዊያን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም በተለይ ለአትሌቶች ያላቸውን ክብር ሣይገልጹ አይመለሱም። ለአብነት ያህል የቀድሞ የሃገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ይጠቀሣሉ፡፡ እአአ 2014 ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት፤ ደራርቱ ቱሉ፣ መሠረት ደፋር፣ ቲኪ ገላና እና ኢብራሂም ጄይላን የመሣሰሉ አትሌቶችን በአካል አግኝተዋል፡፡ አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀበት ውድድር ላይ ሣለ የተነሣውን ፎቶ ግራፍ በልጁ የትናየት አበበ ቢቂላ ተበርክቶላቸዋል፡፡ በወቅቱም አበበ በጃፓናዊያን ዘንድ ባሣደረው ተጽዕኖ መሠረት የእርሳቸው ሥም ‹‹አቤ›› አበበ ከሚለው የተወሰደ እንደሆነ የሚታሰብና በሥሙ የሚጠሯቸውም መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኦሊምፒኩ ሲካሄድ የ10 ዓመት ልጅ ቢሆኑም፣ በውድድሩ ወቅት በርካታ ጃፓናዊ አትሌቶች ራሣቸውን ሲስቱ አበበ ግን ሰውነቱን ሲያሳስብ መመልከታቸው አድናቆት ፈጥሮባቸው እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት (በኦሊምፒኩ መካሄድ ዋዜማ) ደግሞ ጃፓን ለኢትዮጵያ ግብዣ አድርጋ ነበር፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በሥፍራው ተገኝታ የጃፓን ኦሊምፒክ ሚኒስትር ከሆኑት ሃሺሞቶ ሲኮ ጋር ቆይታ አድርጋ ነበር፡፡ በወቅቱም ሚኒስትሯ ለኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ያላቸውን ክብር የገለጹ ሲሆን፤ በታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ የተሠየመ የግማሽ ማራቶን ውድድር እንደሚካሄድም ገልፀዋል፡፡
በዚያው ዓመት አንድ ጃፓናዊ የአበበን ቤተሠቦች አግኝተው ያስተላለፉት መልዕክትም አትሌቱን ምን ያህል ያከብሩት እንደነበር በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡ እኚህ የ74 ዓመት አዛውንት ከአበበ ልጅ የትናየት አበበ ቢቂላ ጋር በተገናኙበት ወቅትም እንዲህ አሉት ‹‹እአአ በ1964 እናቴ ክፍሉን በማጽዳት ላይ ሣለች ቀለበት አግኝታ ወደቤት አምጥታ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ያደረገችው ባለማወቅ ስለነበር፤ በሕይወት ለሌለችው እናቴና ቤተሠቤ ይቅርታ እንድታደርጉልን እንፈልጋለን››፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ እናት የስታዲየም መታጠቢያ ቤቶችን በማጽዳት ላይ ሣሉ ቀለበቱን አገኙ፤ ከሣምንታት በኋላም የመጥፋቱ ዜና በጋዜጦች ተነበበ። በወቅቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣም የቀለበቱን መጥፋት የዘገበ ሲሆን፤ ቀለበቱ አበበ በሮም ኦሊምፒክ ድል አድርጎ እንደተመለሰ የተበረከተለትና የንጉስ ኃይለሥላሴ ፊርማ እንዲሁም ‹‹ሮም 1960›› የሚል ጽሁፍ ያረፈበት እንደነበረም ጠቁሟል፡፡ ቤተሠቡ ይህንን እንደተረዳም በቀጥታ ዜናውን ወደተመለከቱበት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በማምራት ቀለበቱን መለሱ፤ ከወር በኋላም ለአበበ ሊላክ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ እኛ እናት ፀፀቱ ሣይለቃቸው አረፉ፡፡ የያኔው ወጣት ያሁኑ አዛውንት ልጃቸውም ከ55 ዓመት በኋላ የአበበን ቤተሠብ አግኝተው ይቅርታ መጠየቃቸውን የጃፓን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስመልክቷል፡፡
ካሣማ የተባለችው የጃፓናዊያን ከተማም በተመሣ ሣይ ኢትዮጵያዊውን አትሌት በቋሚነት የምትዘክር ሥፍራ ናት፡፡ በዚህ ሥፍራ በየዓመቱ ሥያሜውን በታላቁ አትሌት ያደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፤ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን የስፖርቱ ሰዎችም ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ ውድድሩን የሚያስጀምሩት ኢትዮጵያዊያን እንግዶችና ተጋባዥ የስፖርቱ ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ሃገሪቷን ለማስታወስም ባህላዊ የቡና ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡
አበበ በጃፓን አፈር ላይ ሮጦ የመጀመሪያውን ድል የተቀዳጀው የጃፓን ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አስቀድሞ በሮም ኦሊምፒክ ማግሥት (እአአ 1961) ነበር፡፡ ይኸውም እአአ ከ1946 ጀምሮ መካሄድ በጀመረው ጥንታዊውና በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የኦሣካ ማራቶን ነው፡፡ በወቅቱ ከሌላኛው አንጋፋ አትሌት ዋሚ ቢራቱ ጋር የተካፈለ ሲሆን፤ ከሙቀቱ የተነሣ በእግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን የቡድን አጋሩን አስከትሎም ነበር ውድድሩን የፈፀመው፡፡
ታዲያ ጃፓናዊያን በአፍሪካዊያኑ አትሌቶች እጅግ በመደነቃቸው የተለየ አክብሮትና እንክብካቤ እንደተደረገላቸው ሕያው ምሥክር የሆኑት የ105 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ይገልጻሉ። ይህም ከንጉሣዊያኑ ቤተሠቦች ሣይቀር ማበረታቻ የተሰጣቸውና ሃገሪቷንም መጎብኘታቸውም ኢትዮጵያ በጃፓናዊያን ልብ ምን ያህል ቦታ እንዳላት ማሣያ ይሆናል፡፡
በወቅቱ መቀመጫውን በዚያው በኦሣካ ያደረገና ‹‹ኦኒትሱካ ታይገር›› የተባለ የጃፓን የስፖርት ጫማዎች አምራች ለአበበ የ‹‹ስፖንሰር እናድርግህ?›› ጥያቄ አቀርቦለት እንደነበረም የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ። ይሁንና አበበ በወቅቱ በፑማ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ስፖንሰር ይደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጀግና የሆነው ሻለቃ አበበ ቢቂላ በሃገሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ስታዲየሞች፣…ሌሎችም ተቋማት ለማስታወሻነት በሥሙ ተሠይመዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ውድድሮች፣ የስፖርት ትጥቆች፣ ሽልማቶችን ጨምሮ በርካታ መታሠቢያዎች ተሠርተውለታል፡፡ ነገር ግን ስለ አበበ ዘጋቢ ፊልም በመሥራት ጃፓኖችን የቀደመ የለም፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ማግሥት እአአ 1965 ጃፓናዊው የፊልም ዳይሬክተር ኮን ሊችካዋ ‹‹ቶኪዮ ኦሊምፒያድ›› የሚል ርዕስ ያለው ፊልም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞች በእንግሊዝኛና አማርኛ ፊልሞች ተሠርተዋል፡፡
እአአ 1992 ደግሞ ሌላኛው ጃፓናዊ ጸሐፊ ያማዳ ካዡሮ ስለ አበበ ቢቂላ ሙሉ የሕይወት ታሪክ የሚያወሣ የመጀመሪያውን መጽሃፍ በማሣተምም፤ ጃፓን ለአትሌቱ ያላቸውን ልባዊ ፍቅርና አክብሮት አሣይቷል፡፡ ይህ መጽሃፍ ‹‹አበበን ታስታውሱታላችሁ?›› የሚል ርዕስ ያለውም ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር 90 ዓመታትን የዘለቀ ወዳጅነት ያላት ሃገረ ጃፓን በበርካታ ጉዳዮች መልካም አጋርነቷን በተግባር የምትገልጽ ሃገር ናት፡፡ አበበና አትሌቲክስ ሲነሱ ግን ልባቸው በበዛ ፍላጎትና ከልብ በመነጨ አክብሮት ይሞላል፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ምሥራቅ አፍሪካዊቷን የሯጮች ምድር እግራቸው ከረገጠም፤ አበበንና ቤተሠቦቹን የማየት ጉጉት ያድርባቸዋል፤ ለምንጊዜም ጀግናቸው አድናቆታቸውን ከመግለጽም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013