የስርቆት አመል (ህመም) መሆኑን ያውቃሉ። ይህ አመል ክለፕቶሜኒያ በተለምዶ ከምናውቀው የስርቆት ዓይነት ይለያል። ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚሰርቁት ውስጣዊ ደስታ ወይም እርካታን ለማግኘት እንጂ የዕቃውን ጠቀሜታ አስበው አይደለም። ማለትም ዕቃውን ሸጦ ትርፍ የማገኘት በሰረቁት ነገር የመጠቀም ሃሳብ ሳይሆን መስረቅ በራሱ በውስጣቸው ደስታ ስለሚፈጥርባቸው ነው።
ይህ ህመም ያለባቸው ሰዎች በመስረቅ ከሚያገኙ ደስታ የተነሳ ፈፅሞ ሊጠቀሙበት የማይችሉና ተራ ነገሮችን፤ በጣም የማይረቡ ነገሮችን ሊሰርቁ ይችላሉ።
ክለፕቶሜኒያ ለአመል ወይም ውስጣዊ እርካታን ለማግኘት የሚደረግ ስርቆት ስለሆነ ድርጊቱን በድግግሞሽ ያደርጉታል። ከዚህም የተነሳ ስርቆት ሱስ ሊሆንባቸው ይችላል። በሀገራችን እንዲያውም ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል የሚባል አበባል አለ፤ ይህ ለዚህ ሱስ ለላቸው ሰዎች የተባለ ይመሰለኛል።
ስርቆቱን በማድረግ ከሚያገኙት ደስታ ቀጥሎ ተገቢ ያልሆነ ነገር ማድረጋቸውን ሲያስቡ ከፍተኛ የሆነ ፀፀት፣ ጭንቀትና ሀፍረት ውስጥ ይገባሉ። ይህ ዓይነት ደግሞ ተደጋግሞ ወደ አዕምሯቸው እየመጣ ያቆስላቸዋል።
ምንም እንኳን ፀፀት እየተመላለሰ ቢጎዳቸውም በስርቆት የሚያገኙት ደስታ ወደ ከፋ ሱስ ስለሚቀየር ሁሌም ደስታን ለማግኘት ስርቆትን በተደጋጋሚ ይፈፅማሉ። በዚህ ችግርም ታዋቂ የሆኑ የሆሊውድ ተዋናዮች ሳይቀር ተጠቅተው ነበር። (ሚጋን ፎክስ፤ ብረቲኒ ስፒርስ፤ እና የመሳሰሉት…………..) በስርቆት ተይዘው በተለያዩ የገበያ ማዕከሎች በህይወት ዘመናቸው ድጋሚ እንዳይገቡ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ይህ ህመም ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ጎልቶ ይታያል። መንስኤው እንደ ማንኛውም የአዕምሮ ህመም በዘር የመጣ፣ በአዕምሮ ውስጥ የሚገኙ ስሜትን ለመቆጣጠር የሚረዱ ኬሚካሎች አለመመጣጠን እና በድግግሞሽ ከማድረግ ሱስ ውስጥ መግባት የመሳሰሉት ናቸው።
በሽታው ህክምና ያለው ሲሆን፤ በመድሀኒቶች እና በኮግኔቲቪ ብሄቪዬር ቴራፒ (Cognitive Behavior Therapy) ይታከማል።
ይሄንን ለወላጆች ይሁንልኝ ያልኩት ልጆቻችሁ በአጋጣሚ የስርቆት አመል ቢገጥማቸው ከዚህ ችግር የሚወጡበትን መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ወደ ከፋ ቅጣት እየሄድን ችግሩን እንዳናስፋፋው ለመምከር ነው ይላሉ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013