አለማችን በረቀቀ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እየታገዘች ሰው ሰራሽ ልህቀት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመረች ሰነባብታለች። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጆች ወይም እንስሳት ሊከውኗቸው የሚችሏቸውን ተግባራት በተቀላጠፈና በተሻለ የጥራት ደረጃ መፈጸም የሚያስችል ውጤታማ የሳይንስ እምርታ እንደሆነ በተግባር በአለማችን ላይ እየታየ ነው። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ማስመዝገብ የቻሉ የዓለማችን ሀገራት እየተበራከቱ በመምጣታቸው ቴክኖሎጂው በብዙ ሀገራት እየተስፋፋ ይገኛል። ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን በምን መልኩ በማሳደግ ለእድገቷ ልትጠቀመው እንደምትችል እና ቴክኖሎጂው ለሀገር እድገት ያለው አስተዋጽኦ ምን እንደሚመስል በሀገራችን ብቸኛ ከሆነው አይኮግላብ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ምንነት ኢንተለጀንስ ማለት ሰዎች፣ እንስሳት፣ እጽዋትና መሰል ከሚሊዮን በላይ ህይወት ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳትን ጨምሮ ባህሪያቸውን የሚያስረዳና የሚያስተምር ሳይንስ ሲሆን፤እነዚህ ህይወት ያላቸው ፍጡራን ለመራባት፣ ከአካባቢያቸው ጋር ተላምደው ለመኖር፣ ምግባቸውን ለማዘጋጀት፣ እራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል የተለያዩ ዘዴዎችና ባህሪያቶች አሏቸው። እንዲሁም ስራዎችን ለማከናወን የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይጠቀማሉ። ነገርግን ህይወት ካላቸው ፍጡራን ውስጥ የሰውልጅ አዕምሮ ከማንኛውም ፍጡር በጣም የላቀ በመሆኑ አርቆ ማሰብና ስለነገ መተንበይ፣ ማቀድ፣ መረዳት፣ መግባባት፣ አንድን ነገር ወደተሻለ ነገር የመቀየር የመሳሰሉ ችሎታዎች አሉት።በመሆኑም፤ ስራዎቹን ለማቃለል የሚያግዙትን መሳሪያዎችን ከማንኛውም ፍጡር በተሻለ መፍጠርና መጠቀም ይችላል። ይህን የተፈጥሮ ችሎታውን በመጠቀምም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ማበልጸግ ችሏል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተለያዩ እውቀት ተኮር ስርዓቶችን፣ ሮቦቶችን፣ ሀርድ ዌሮችንና የኮምፒዊተር ፕሮግራሞችን በማበልፀግና በመጫን በሰው ልጅ ጉልበት ሊሠሩ የማይችሉ አድካሚና ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልጉ ውስብስብ ሥራዎችን ማከናወን እንዲሁም ሰዎች ወይም እንስሳት ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸውን ተግባራት ተክተው ከስህተት በጸዳ መልኩ በተሻለ ፍጥነት ጊዜን፣ ወጭንና ጉልበትን ቆጥቦ ተግባሩን የሚወጣ የሳይንስና የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ነው። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሀገራዊ ፋይዳ በአሁኑ ጊዜ ያደጉ ሀገራት ቴክኖሎጂውን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመጠቀም ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ችለዋል። ሀገራቱ ትላልቅ ፋብሪካዎቻቸውን፣ ባንኮቻቸውን፣ ኢንሹራንሶቻቸውን የመሳሰሉ ተቋማቶቻቸውን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ እንዲታገዙ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ቴክኖሎጂው ስማርት ፎን ወይንም ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ለማደግ ከፈጀበት 10 አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የዓለምን ኢኮኖሚ እየተቆጣጠረ ይገኛል። እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮችም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከባህላዊ የአሰራር ዘዴዎች መላቀቅ ይችላሉ። በተለይም በሀገሪቷ የሚስተዋሉትን አንዳንድ የተንዛዙ አሰራሮችንና ከፍተኛ የሀብት ብክነት በማስቀረት በአጭር ጊዜ ወደ እድገት ጎዳና ለመድረስ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ቴክኖሎጂው የማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣መሰረተ ልማቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሟላት እጅግ ይጠቅማል። በኢትዮጵያም የቴክኖሎጂው ጥቅም እየታወቀ በመምጣቱ አገልግሎት ላይ መዋል ጀምሯል። ለአብነትም በማህበራዊ ድረገጽ አማካኝነት አሰሪና ሰራተኛን ማገናኘት ተችሏል።
በዚህም የስራ ፈላጊዎችን ጊዜና ጉልበት መቀነስ ተችሏል። ማህበረሰቡ መረጃን በቀላሉ የሚያገኝበት ዘዴ ተፈጥሯል። ድሮን የተባለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንዲሁ መሰረተ ልማቶች ባልተሟላባቸው አካባቢዎች በማድረስ እናቶች በወሊድ ወቅት ደም አጥሯቸው እንዳይሞቱና ለህፃናት ክትባቶችን ለማድረስ ተችሏል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ነዳጅ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሶማሌ ክልል ወደ ጅቡቲ የምትዘረጋውን ከ700 ኪሎ ሜትር እርዝመት በላይ የሚሸፍነውን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በሰው ኃይል ለማስጠበቅ የማይቻል በመሆኑ በድሮን ቴክኖሎጂ ለመጠበቅ ስራ ተጀምሯል። በአጠቃላይ ቴክኖሎጂው ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ፣ ያለውን እምቅ እውቀትና የሰው ሀይል በአግባቡ ለመጠቀም ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዛቸው ህንድ ህዝቧን መምራትና ማስተዳደር የሚያስችል ኢኮኖሚ የገነባቸው ከእነ ቦይንግ፣ ማይክሮሶፍት፣ አይቢኤም፣ ቦራክል ከመሳሰሉ ትልልቅ የአለማችን ኩባንያዎች ሥራ ተቀብላ በመስራትና ከስራው ባገኘችው የቴክኖሎጂ ሽግግር የተሻለ ነገር በመፍጠር ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች። ኢትዮጵያም እንደ ህንድ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ የወጣቱን አዕምሮ በትምህርት በማነጽ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ትችላለች። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ያላደገበት ምክንያት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ለቴክኖሎጂው ሥራ የሚያግዝ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ቴክኖሎጂውን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆኑ፣የተቀላጠፈ አሰራር አለመዘርጋቱ፣ለቴክኖሎጂ ስራ የሚውል በጀት አለመመደብ፣ለቴክኖሎጂው የሚደረገው ድጋፍና ትኩረት አነስተኛ መሆንና የመሳሰሉት ችግሮች ቴክኖሎጂው በሀገራችን ማበርከት ያለበትን አስተዋጾ እንዳያበረክትና መድረስ ያለበት የእድገት ደረጃ እንዳይደርስ እንቅፋት ከሆኑ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል።
የተጠቀሱት ችግሮች በጥናት ተለይተው መፍትሄ ቢሰጣቸው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተክኖሎጂዎች ሊስፋፉ ይችላሉ። ለውጥ በማምጣት ሀገሪቱን በፍጥነት መቀየር የሚችሉ ወጣቶችንም መፍጠር ይቻላል። በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥተው በመጠቀም ላይ ካሉት ሀገራት ሳውዲ አረቢያን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።በሚኒስቴር ደረጃ እንዲመራ በማድረግ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያም ከዚህ ልምድ በመውሰድ ቴክኖሎጂው ከሌሎች ዘርፎች ተለይቶ እራሱን ችሎ ቢደራጅ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፉ የተማረ ኃይል ማፍራት ከተቻለና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ተቀምሮ በስራ ላይ ከዋለ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል። በቴከኖሎጂ ታግዘው በኢኮሚ ካደጉ ሀገራት ጋር እኩል በመራመድ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የፋይናንስ ተቋማት እንዲያግዙ ስለቴክኖ ሎጂው ጥቅም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡ የፖሊሲና ስትራቴጂ ክለሳ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
የትምህርት ፖሊሲውም ሊቃኝ ይገባል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአመቱ በመቶ ሺዎች የሚመረቁ ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ እንጂ ሥራ ፈላጊ መሆን የለባቸውም። አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት የሌሎቹን ቀልብ መሳብ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያ በተጨባጭ የሰራው ሥራ ኩባንያው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት፣ሶልቭ ኢት (Solve it) በተ ባለ ፕሮግራም ችግር ፈች የፈጠራ ስራ ውድ ድሮችን በማዘጋጀት የፈጠራ ባለሙያዎች በማበረታት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። በዚሁ መሰረትም ከአሜሪካንና ከጃፓን ኢምባሲዎች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳ ደሮች በሁለት ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል። በዚህም ወጣቶች የፈጠራ ስራ ዝንባሌ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል። የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች በገንዘብና በተለያየ ድጋፍ በማገዝም የፈጠራ ሀሳባቸው እውን እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። በስልጠናው እውቀት ያገኙ አንዳንድ ወጣቶች የተለያዩ ስራዎችን ሰርተው ገበያ ላይ በማዋል ገቢ ማግኘት ችለዋል። ኩባንያው ክት ትልና ድጋፍን በማጠናከር ለተሻለ ውጤት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። አእምሮአቸውን ተጠቅመው ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ከቻ ሉት ሀገራት ጋር ለመወዳደር ብዙ መስራት ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ሶሎሞን በየነ
Your blog has helped me through some tough times and I am so grateful for your wise words and positive outlook