ዛሬ የደርግ ዘመንን አሠራር በትምህርቱ፣ በጤናውና በፖለቲካው መስክ ምን እንደሚመስል ወደ ኋላ ዞር ብለን እንድንቃኘው የሚያደርጉን እንግዳ ጋብዘናል፡፡ እንግዳችን ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው ይባላሉ፡፡ የ1960ዎቹ ተማሪና ሠራተኛ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የብሔረሰቦች ጥናት ኢኒስቲትዩት ኃላፊና በዚሁ ዘመን የትምህር ሚኒስቴር ሚኒስትርም ነበሩ፡፡ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻውንም በሚገባ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የለፉና ውጤታማ የሆኑ ሰው ናቸው፡፡
በጤናው መስክም እንዲሁ ከኃላፊነት እስከ መምህርነትና ተመራማሪነት የሠሩ ሲሆኑ፤ በዘመኑ ለአገር ብዙ ካበረከቱ መካከል ናቸው፡፡ እናም በዚህ ጉዟቸው የቀሰሙትን ልምድና የህይወት ተሞክሮ እንዲያካፍሉን በዛሬው «የህይወት ገጽታ» ዓምዳችን እንግዳ አደረግናቸው ፡፡
ሞቷል የተባለው ልጅ
ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ናቸው። እናት በተደጋጋሚ ሲወልዱ ወንድ ከሆነ ይሞትባቸዋል። እናም ወንድ ልጅ አይወጣለትም ይባሉ ነበር። እርሳቸውም ሲወለዱ የተለመደ ነገር ስለነበር ሳያለቅሱ ስለቀሩ ሞቷል ተብለው ወደጎን ተተዉ፡፡ ሆኖም እህታቸው ተጠግታ ስታያቸው ትንፋሽ እንዳላቸው ስትረዳ ወዲያው ክርታሱን አነሳችላቸው፡፡ እርሳቸውም አለቀሱ፡፡ የዚህን ጊዜ እልልታው ቀለጠ፤ ቤተሰቡ በሁለት ደስታ ውስጥ ሆነ፡፡ የመጀመሪያው ልጁ በህይወት መኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው የመጀመሪያ ወንድ ልጅ መገኘቱ ነው። እናም ብርቅዬና የስለት ልጅ መስለው ነበር የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት፡፡
በ1932 ዓ.ም የተወለዱት ባለታሪካችን፤ የራስ ደስታ ሰፈር ልጅ ናቸው፡፡ ማሚቱ ተብለውም ጥሩ ቀሚስ እየተገዛላቸው እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ አድገዋል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም የሰው ዓይን ውስጥ እንዳይገቡባቸውና ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ እንደሆነ ያስታውሳሉ። እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ከቤት ራቅ ብለው እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም፡፡ ሥራም ቢሆን እንዲሰሩ እንዲሁ እድሉ አይሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ በቅርብ ርቀት እየተከታተሏቸው የፈለጉትን እያደረጉና እየሆነላቸው እንዲጫወቱ ነው የሚደረጉት። ከጨዋታ ሁሉ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ኳስ መጫወትን አብዝተው የሚወዱ ሲሆኑ፤ ጥሩ ሰርግ አድማቂም ነበሩ፡፡ ድምጻቸው በጣም ያማረ በመሆኑ አንድም ሰርግ ላይ አይቀሩም። ይህ ድምጻዊነታቸው ደግሞ አውሮፓ ድረስ ዘልቆ የአውሮፓ ጥላሁን ገሰሰዎች ይባሉ እንደነበርም አይረሱትም፡፡ በልጅነታቸው ማንበብ ከሚወዱትም መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ማንኛውንም መጽሐፍ ማንበብ ለእርሳቸው ልዩ ትርጉም አለው። ከሚነበብ ነገር ሁሉ ቁምነገር አለ ብለው ያምናሉ፡፡
ያየህይራድ የተባሉት ከሰባት ዓመታቸው በኋላ ሲሆን፤ ይህን ስምም ያወጡላቸው እናታቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ለምን እንዳሏቸው ግን አያውቁም፡፡ እንደውም አባታቸው ዳኛ በመሆናቸው ‹‹ይህ ስም ለኔ ነው ላንተ›› ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ስሙን ግን በጣም ይወዱት እንደነበር ይናገራሉ። እንግዳችን በልጅነታቸው መሆን የሚፈልጉት እንደአባታቸው ዳኛ አልነበረም፡፡ በእርግጥ ቤተሰቡ በሙሉ ዳኛ ትሆናለህ የሚል እምነት ያሳድሩባቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን እናታቸው በየጊዜው ይታመሙ ስለነበር ሀኪም መሆኑ የበለጠ እንደሚያጓጓቸው፤ ለዚያም ተግተው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ስለሆኑትም እጅግ ደስተኛ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎችን ማገዝ ችዬበታለሁ ብለው ያስባሉ፡፡
ከሲዊዲሽ ሚሽን እስከ ቦርዱ በትምህርት
ትምህርት የጀመሩት በሲዊዲሽ ሚሽን ትምህርት ቤት ነው፡፡ እስከ ሦስተኛ ክፍል በዚህ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ መምህራኑ በጣም ጎበዞች ቢሆኑም የሚደባደብ መምህር ያለበት ስለነበር ተማሪዎች በስቃይ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ስለዚህም የእርሳቸው እናት ይህንን ሰምተው ኖሮ ከዚያ ትምህርት ቤት መውጣት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ ወደ አርበኞች ትምህርት ቤትም እንዲዛወሩ ሆኑ፡፡ አርበኞች ትምህርትቤት ሲገባ በቀጥታ ማንም አይቀበልም፡፡ በፈተና ማለፍ ግድ ነው፡፡ እናም እንግዳችንም ፈተና ወሰዱ፡፡ ይህንን ጊዜ ያመጡት ውጤት አራተኛ ሳይሆን አንደኛ ክፍል የሚያስገባቸው በመሆኑ አንደኛ ክፍል እንዲገቡ ተነገራቸው፡፡ በዚህም የሲውዲሹ ትምህርት በዜሮ ተባዝቶ በአርበኞች ትምህርትቤት ከአንድ ጀምረው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሩ፡፡
ወደ አንደኛ ክፍል መውረዳቸው እንዳልጎዳቸው ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ የስምንት ዓመቱን ትምህርት በስድስት ዓመት ውስጥ እንዳጠናቀቁና በደብል በተሻለ አቅም እያለፉ እንደሄዱበት ይናገራሉ፡፡ ከስምንት በኋላ ደግሞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገባ የሚመረጡ የትምህርት መስኮች ስላሉ እርሳቸው ምንም እንኳን በትምህርትቤቱ ከፍተኛ ውጤት ቢያመጡም አካዳሚኩ የተሻለ እንደሆነ በማመናቸው በዚህ ዘርፍ ለመማር ወሰኑ፡፡ ኮሜርስ፣ መምህራን ማሰልጠኛ፣ ግብርና፣ ተግባረዕድ ወዘተ የሚባሉ ምርጫዎች ቢኖሯቸውም ይህንን አልፈለጉትም ነበር፡፡
የሚኒስትሪ ፈተና የወሰዱት 18 ተማሪዎች ብቻ እንደነበሩ የሚያስታውሱት እንግዳችን፤ ሲመድቧቸው በፈለጉት መስክ እንደነበር ያስታውሳሉ። የሚማሩበት ትምህርትቤት ግን ለእነርሱ ምቹ እንዳልነበርና በጊዜው በዚህ አንማርም ብለው እንዳመጹ ያነሳሉ። ትምህርትቤቱ ቅድስት ሥላሴ ሲሆን፤ መግባት የፈለጉት ዊንጌት ነው፡፡ እናም ትምህርትቤቱ ከመረጣችሁ ትገባላችሁ ካልመረጣችሁ ግን የአንድ ዓመት ስልጠና ወስዳችሁ መምህር ትሆናላችሁ ተባሉ፡፡ በሀሳቡም ተስማምተው ሄዱ፡፡ በወቅቱ ደግሞ እንግዳችን ካልተመረጡት መካከል እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
በዳይሬክተሩ ካልተመረጡት መካከል የሆኑበት ምክንያት የእርሳቸው ካርድ በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴርን የሚቆጣጠሩት ኃይለሥላሴ በመሆናቸው ተማሪዎችን በውጤት ነው የምንመድበው ብለው ስለነበር ካርዳቸው ተሰብስቦ ስለተሰጠ ወደ ዊንጌት ባለመላኩ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ያየህይራድ፤ እርሳቸው ግን ስም ዝርዝራቸው ባይኖርም በራሳቸው ፈቃድ ገብተው መማር ጀምረዋል። ስማቸውን ተጠይቀው ዳግም ቢታይም ዝርዝሩ ውስጥ የሉም፡፡ ሆኖም ውጣ ግን አልተባሉም። ስማቸው ያልተለመደና የመማር ፍቅራቸው ታይቶ ተተዉ። ቆየት ብሎ ካርዳቸው ሲመጣም ውጤታቸው የሚያስቀጥላቸው መሆኑ ተረጋገጠላቸውና እስከ 12ኛ ክፍል በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተል ቻሉ፡፡
12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁም በከፍተኛ ውጤት ነበር። ይሁን እንጂ ቀጥታ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ አልሆነም። ምክንያቱም በወቅቱ ወታደር ሆኖ አገርን ማገልገል እንደግዴታ የሚወሰድበት ጊዜ ነበር፡፡ እርሳቸውም መከላከያን መቀላቀል ግድ ሆነባቸው። ነገር ግን ሲታዩ ወታደር ለመሆን የሚያስችላቸው አይነት አልነበረምና የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዳይሬክተር ደብዳቤ ጽፈው ለመከላከያ አስረከቡ፡ አትሄድም ተባሉም፡፡ በዚህ ጊዜ ለእረፍት ወደ ድሬዳዋ አቀኑ። ከዚያ ሲመለሱ ግን ባህር ኃይል እንደወሰዳቸው ሰሙ፡፡ ነገር ግን ጅማ እህታቸው ጋር ጠፍተው ከወር በላይ ቆዩ፡፡
አባታቸው ታዋቂና ከአዛዦቹ ጋር በቅርብ አብረው የሚሰሩ በመሆናቸው ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ባህር ኃይል እንደሄዱ የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ የባህር ኃይል አዛዥ ልጁን የፈለግነው ለዘመቻ አይደለም። በባህር ኃይል ስር ሆኖ ሳይንቲስት እንዲሆን ነው። ተቋሙ በትምህርት ብዙ ሳይንቲስቶችን ለማውጣት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም እንደእርሱ ያለውን በዚህ ላይ ብናሳትፈው የተሻለ ነገር ለአገር ማምጣት ይችላል ብለን ስላመን ነውና ምንም አያስቡ ሲል አረጋገጠላቸው። በዚህም በባህር ኃይል ስር ሆነው በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሳይንስ ትምህርቱን ለሁለት ዓመት ተከታተሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው መቀጠል አልቻሉም ነበር፡፡ ባህር ኃይል የውጪ የትምህርት እድል አግኝተንልሀል ሲላቸው ምንም ሳያንገራግሩ ወደ ፈረንሳይ አቀኑ፡፡
በፈረንሳይ ቦርዱ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው በውድድር የሚገባባቸው ብዙ ትምህርትቤቶች በስሩ ስለያዘ እርሳቸው የባህር ኃይል የጤና ትምህርትቤት በሚባለው ውስጥ ተካተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህክምናው መስክ በስድስት ዓመት ቆይታ ሊያጠናቅቁ ችለዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ሲሆንም እጅግ በጣም ፈታኝ ነገር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን በዊንጌት ፈረንሳይኛ ቢማሩም በሁለት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ግን ጠፍቶ ነበር፡፡ ስለዚህም በፈረንሳይኛ ህክምና መማር ገና ፊደል እንደመቁጠር ነው፡፡ በዚያ ላይ የፖሊሲ ለውጥ ስለነበር ሰባት ዓመት የነበረው የትምህርት ጊዜ ወደ ስድስት ዓመት በመውረዱ ከፍተኛ ጫና ተማሪው ላይ አርፏል። ስለዚህም ሁለቱንም በበቂ ብቃት ለመወጣት ፈረንሳይኛ መማር ግድ እንደሚሆንባቸው አመኑ፡፡ ቋንቋውን ተምረውም ያሰቡትን አሳክተዋል፡፡
ትምህርት የሥራቸው ለውጥ መሠረታዊ ነገር እንደሆነ የሚያምኑት ዶክተር ያየህይራድ፤ በጤናው መስክ ማለትም በጤና አጠባበቅ ትምህርት ሬን በሚባል ከተማ ውስጥ ሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ ስፔሻላይዝድ አድርገዋልም፡፡ በቦርዱ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ጎን ለጎን የስፖርት ህክምና ፣ በሞቃታማ አገሮች ህክምና/ ትሮፒካል ሜዲስን/ እና የስርዓተ ምግብ ትምህርት ሰልጥነው ዲፕሎማ አግኝተዋል። ከዚያ በኋላ ግን በትምህርት ደረጃ አልቀጠሉም። ምክንያቱም የሥራ ሁኔታቸው የመማር እድሉን አልሰጣቸውም። ሆኖም በሥራቸው ሁልጊዜ ትምህርት ላይ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ከተማሪዎች፣ ከማስተማርና ከልምድ ሁልጊዜ ትምህርት ይገኛል፡፡ እኔም በዚህ ዙሪያ ስላለሁ ከትምህርት ርቄያለሁ ለማለት እቸገራለሁም ብለውናል፡፡
ሥራ
የሥራ ጅማሯቸው ምንም እንኳን ባሰለጠናቸው ባህር ኃይል አማካኝነት የሚወሰን ቢሆንም በወቅቱ ግን ለአገር የሚያስፈልገው መምህር እንደሆነ ይታመናል። ስለዚህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እንዲሰሩ ተፈቀደላቸው፡፡ ነገር ግን ባህር ኃይል ክሊኒክም ቢሆን መስራት ግዴታቸው ነበር፡፡ ስለሆነም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ክፍል መምህር ሆነው እንዲሰሩ የባህር ኃይል ሀኪም በመሆንም አገልግለዋል፡፡ መጀመሪያ በዩኒቨርሲቲው እንደገቡም በመምህርነት ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል መስራት ችለዋል፡፡
አብዮቱ ሲፈነዳ ደግሞ የእድገት በህብረት ዘመቻ ስለነበር እዚያ ላይ የጤና ክፍል ኃላፊ ሆነው ተሹመው መስራት ጀመሩ፡፡ በጤና በኩል ዘመቻው የተሳካ እንዲሆንም አደረጉ፡፡ ዘመቻውም በአገሪቱ በነፍስ ወከፍ ከሚመደበው በጀት በብዙ እጥፍ ተጨምሮ ተመድቦላቸው ማለትም በወቅቱ በአንድ ሰው የነፍስ ወከፍ ጤና ወጪ የሚመደበው 30 ወይም አርባ ሳንቲም ነው፡፡ ነገር ግን ለዘመቻ ሲሆን የአንድ ሰው የነፍስ ወከፍ ወጪ አራት ብር ተደረገ፡፡ ብዙ አደጋ በሚበዛበት ሁኔታም መቶ ቦታዎችን በመያዝ እየተዘዋወሩ ይህንን በጀት ለማጣጣም ሞከሩ፡፡ ይሁን እንጂ እጅግ ከብዷቸው እንደነበረና በመመካከር እንደፈቱት መቼም አይረሱትም። ዘመቻው ሲያልቅ ወደ መምህርነታቸው የተመለሱ ሲሆን፤ ምክንያቱ ሁለት ነበር፡፡ የመጀመሪያው ማስተማር ከምንም በላይ መውደዳቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በጊዜው ህክምናው ላይ በተለይም በጤና አጠባበቁ ላይ የሚሰሩ ሦስት መምህራን ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህም እዚያው ተመልሰው መስራቱ ለእርሳቸውም ሆነ ለአገር እንደሚበጅ ስለተረዱ ለተወሰነ ዓመት በማስተማሩ ዘርፍ ለመቆየት ወሰኑ፡፡ የትምህርት ክፍሉም ኃላፊ እስከመሆን ድረስ ደርሰው አገለገሉ፡፡
እንግዳችን ተማሪ ሆነው ሳሉ ጀምሮ ለውጥ ለማምጣት ከሚታገሉ ወጣቶች መካከል አንዱ ናቸው። እንደውም በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱትና ተዋቂ ከሆኑት መካከል አንዱ በሆነው መኢሶን ውስጥ ገብተው ይሰሩ ነበር፡፡ መምህር ሆነውም ይህንን ሥራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አብዮት ውስጥም ተራማጅ ከሚባሉት ተርታ ነበሩ። ሥራቸውና ተልዕኳቸው ግልጽ የወጣ ስላልሆነ ግን ማንም እዚህ አትገባም ብሏቸው አያውቅም፡፡ በዚህም ቀጣዩ የስራ ቦታቸው የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ሆነ፡፡ በዚያ በኮሚሽነርነት አገለገሉ። ኮሚሽኑን ከማቋቋሙ ጀምሮ እስከ መምራት ብዙ የለፉም ናቸው፡፡ በእርግጥ መጀመሪያ ሲገቡ በእርሳቸው ምርጫ አልነበረም፡፡ በችሎታቸው የሚያውቋቸው ሰዎች ለንጉሡ ነግረው ራሳቸው መርጠው ነው ያስቀመጧቸው። በዚህም የመረጧቸውን ሳያሳፍሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው መልኩ እየተወጡ ሁለት ዓመት ተኩል አገለገሉ፡፡ ወቅቱ ብዙ የተማረ ኃይል የሚፈለግበት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ደግሞ አስተምሮ ፍላጎትን መሙላት ይከብዳል፡፡ ስለዚህም በተለይ ሶሻሊስት አገር እየተላከ እንዲማሩ እድል ይሰጥ ነበር፡፡
በአገር ውስጥም ቢሆን ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሶስት ከፍ እንዲል መስራትና ማሰራት የእርሳቸው ኃላፊነት ነበር፡፡ እናም ይህንን በአግባቡ ተወጥተዋል። ሆኖም ለትምህርት ወደ ውጪ የተላኩት ተማሪዎች ደርግ ላይ አመጹ፡፡ ይህንን ለማስረዳትና ለማሳመንም የተለያየ ስራ መስራት ጀመሩ፡፡ ተማሪዎቹ ከሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ጥናት አደረጉም፡፡ ይሁንና አንድ የደርግ አባል የእኛን ፕሮግራም ይዞ በመሄድ ሞስኮ ላይ አቀረበው። ስለዚህም ተማሪውም ሆነ መንግሥት የተለየ ምልከታ በእርሳቸው ላይ እንዲያመጡ አደረጋቸው፡፡ ይህ ደግሞ እርሳቸውን ተማሪ ስታደራጅ ነበር አስባላቸው።በስራ ጉዳይ ውጪ በሄዱበት ጊዜ ምንም ሳይነገራቸው ኮሚሽነር እንደተሾመ በሬዲዮ ሰሙ፡፡ ግን ምንም አልገረማቸውም፡፡ በጊዜው አባረውኛል ብለው አስበውም ነበር፡፡ ሆኖም ምንም ሳያደርጓቸው ዳግም ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው መስራት እንደሚችሉ ተነገራቸው፡፡ እርሳቸውም ወደሚወዱት የማስተማር ሙያ ገቡ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለአራት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ደግሞ ለዳግም ሹመት ተጠሩ፡፡ በኢሰፓአኮ ስር በሚገኘው የብሔረሰቦች ጉዳይ ኮሚሽን ምክትል ኃላፊም ሆነው መስራት ጀመሩ፡፡
በወቅቱ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ተሳስተን ነበር እንዳሏቸው ያስታውሳሉ፡፡ ምክንያቱም ሊገደሉ ታጭተው ነበርና ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ምክንያት እድል እንዲሰጣቸው ተደረጉና ዳግም ለሌላ ስራ ታጩ። በቦታው ከስድስት ወር በላይ ሳይሰሩም የብሔረሰቦች ጥናት ኢኒስቲትዩት በመቋቋሙ በጥልቅ የሚያውቁትም ከመስራቾቹም አንዱ በመሆናቸው በኃላፊነት መርጠዋቸው እንዲያስተዳድሩት ሆኑ፡፡
ኢኒስቲትዩቱ አምስት ዋና ዋና ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፤ ጉምቱ ጉምቱ ሰዎች የሚመሩትም ነው። አብዛኛውም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው። ለአብነት እነ ዶክተር ፋሲል ናሆም አይነት ሰዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ዘርፎቹ የአስተዳደር ጉዳዮች ፣ የህገመንግሥት ጉዳዮች ፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የማህበራዊ ጉዳዮችና የታሪክ ጉዳይ ይባሉ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉም መስኮች በጥምረት ሆነው ብሔረሰቡን ማዕከል አድርገው ህገመንግስቱን ማርቀቅ ዋነኛ አላማው አድርጎ የሚሰራባቸው ናቸው። ስለዚህም ይህንን በመምራት ሥራ ውስጥ ብዙ ልምድ የቀሰሙና ብዙ ሥራ የሰሩ እንደሆኑ በጭውውታችን መካከል አንስተውልናል፡፡
ይህንን ሥራ ሲሰሩ ስለ ብሔረሰቦች ብዙ ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ያጫወቱን ዶክተር ያየህይራድ፤ የኢትዮጵያን በጥልቅ የብሔረሰብ ውቅር የተሰራች፣ ያልተጠኑና ያልታወቁ የብሔረሰቦች ጥርቅም ያለባት አገር ነች፡፡ ጥቂቶቹን ለያውም በብሔር ነጥለን ብቻ እያነሳን የምንጠቋቆምባትም አገር ነች። ግን ይህ አባይን በጭልፋ የሆነው ብሔረሰቧ ብዙ ታሪክ ፣ ማንነት እንዳለው ተረድተነው ብንተባበርበት ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ የምናገኝበት ወርቅ ነበር፡፡ ሆኖም ከማየት ይልቅ ማጥላላት ልምዳችን ስላደረግነው አልተጠቀምንበትም ይላሉ፡፡
ዶክተር ያየህይራድ ‹‹የህዝብ አንድነት የሚፈጠረው በታሪክ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከ3ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለን ነንና በብሔረሰብ ጥንቅራችን ማንም የማይደርስብን ነን፡፡ ይህ ደግሞ ምንም የእኔነት ችግር ቢመጣብን እንኳን መፍትሄ እንድናገኝ አድርጎናል። አንድነታችን ዛሬ ጭምር ያልጠፋብንም ይህ ሁሉ ነገራችን በውስጣችን ስላለ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በፈተና ውስጥ ብንሆንም ጥቃቅን ነገሮች ሊወጡ ይችላሉ እንጂ አብሮ መኖራችንን ማንም አይገታውም። ዘላለማዊ ነው።›› ይላሉ ከሰሩበት መስሪያቤት የተማሩትን ሲያነሱ። ሌላው ዶክተር ያየህይራድ የሰሩበት ቦታ በደርግ ዘመን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩበት ነው። በወቅቱ ትምህርትን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ብዙ እቅዶች አቅደው በብዛት የፈጸሙ ናቸው። ይሁን እንጂ ያቀዱትን ያህል ሰርቻለሁ አይሉም፡፡ ምክንያቱም ጊዜው አገሪቱ በጦርነት ውስጥ የነበረችበት ነበርና አብዛኛው በጀት ለዚሁ ለጦርነት ውሏል፡፡ በዚህም እቅዳቸው ሙሉ እንዳልሆነላቸው አጫውተውናል፡፡ በተለይም በወቅቱ የነበሩ ቴክኖሎጂዎችን በትምህርት ስርዓቱ ጋር ለማላመድና ለማስተዋወቅ እንዲሁም ትምህርቱን ለማዘመን ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ከሰሩት ሥራ እረክቼበታለሁ የሚሉት የመሰረተ ትምህርት ዘመቻው ነው፡፡ በወቅቱ ማንበብና መጻፍ የሚችለው ህዝብ 10 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ እርሳቸውና አጋሮቻቸው በሰሩት ስራ ግን 75 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ማንበብና መፃፍ እንዲችል አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ስኬትም ከዩኔስኮ እውቅና እስከመሰጠት ያደረሰው እንደነበርም አይረሱትም፡፡ በተመሳሳይ የንባብ ጉዳይ ስፋት ያለው ህዝብን እንዲይዝም በየአካባቢዎቹ የንባብ ቤቶችን ማቋቋም አስችለዋልም፡፡ ከዚህ ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ተቋማትም እንዲሰፉ ብዙ ከለፉት መካከል ናቸው፡፡ ይህ የሆነውም በአራት ዓመት ቆይታ ነው፡፡ ማለትም ከ5/13/1979ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም ድረስ በሚኒስትርነት በአገለገሉበት ጊዜ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ሲገቡ ደርግ ሊወድቅ መጨረሻዎቹ አካባቢ ነበርና ደርግ ወድቆ ቦታውን ኢህአዴግ ሲረከብ ለእስር ተዳረጉ፡፡ ምክንያቱም የደርግ አመራር ነዎት ተብለዋል፡፡ ስለዚህም አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ያህል በብዙ ስቃይ ውስጥ እንዲያልፉ ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ከሌሎቹ አንጻር ሲታይ የእኔ ተመስገን ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ተገለዋል፡፡ የእስር ጊዜያቸው ሲጠናቀቅም በቀጥታ ወደተለመደው ስራ መግባት አልቻሉም፡፡ ፖለቲካው የትም እንዳይቀጠሩ አድርጓቸው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት እንቀጥርሀለን ብለው ከጠሯቸው በኋላ አይሆንም ይሏቸዋል፡፡ እናም በግላቸው መስራት ግድ እንደሆነባቸው አመኑ። በጤና እድገት ዙሪያ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ ድረስ በማማከር ይሰሩ ጀመር፡፡ ምርምርም እንዲሁ ዋና ስራቸው ሆነ፡፡
መልዕክት
መጥፎ አጋጣሚዎች ሁሌም መጥፎ ናቸው ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ያለምክንያት አልሆኑም። እናም ከመጥፎነታቸው በስተጀርባ ያለውን መልካም ነገር ፈልጎ አግኝቶ መጠቀም ስኬታማ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ማሳያው በመንግሥት አለመቀጠሬ በግሌ ተፍጨርጭሬ የራሴን ቤት እንድሰራ ሆኛለሁ። ስለዚህም ሰዎች በማንኛውም አጋጣሚ ክልከላ ሲደርስባቸው በበጎ ጎኑ ማየት የዘወትር ልምዳቸው ቢያደርጉት እላለሁ። ከመጥፎ ነገር መልካም እንደሚወጣም ማመን ይገባቸዋል፡፡
ማንኛውም መንግሥት የሚመሰርት አካል ሁለት ነገሮችን ለህዝብ ክፍት ማድረግ አለበት። የመጀመሪያው አዲስ ነገሮች መግቢያ እንዲያገኙ መፍቀድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለጎበዙ፣ ለሚሰራውና ለሚቃረነው መተንፈሻ አካባቢ መፍጠር ነው። ለዚህ በአብነት የሚነሳው የዘንድሮው ምርጫ ሲሆን፤ ብዙዎች መተንፈሻ መድረክ አግኝተዋል ብዬ አስባለሁ። በዚህም ጤናማ የሆነና አገርን ያስቀደመ ምርጫ እንዲከናወን እድል ሰጥቷል። ህዝቡ የራሱን ውሳኔ እንዲያስቀምጥም ረድቷል፡፡ እናም ስልጡንነታችንን በእነዚህ ሁለት ነገሮች ማሳየት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንትም ከትናንት ወዲያም ከባድና መወጣት አትችላቸውም የሚባሉ ችግሮች ገጥመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በህዝቦች አንድነትና ትብብር ሁሉም ድል ሆኗል፤ ታልፏልም። ኢትዮጵያን የሚያቆማት አንድና አንድ ነው፤ በህብረትና በመተሳሰብ መስራት፡፡ ጨለማው ጥቅጥቅ የሚለው ከመንጋቱ በፊት ነውና አሁን ባለንበት ሁኔታ መንጋቶች አሉ። ችግሮቻችን ጨለማ ቢመስሉንም ለመንጋት ጊዜ አይወስዱም፡፡ ስለዚህም ለመንጋቱ ተስፋ የሚሆነውን አንድነት ስንቃችን አድርገን ዘላለማዊት የሆነችውን ኢትዮጵያን እናምጣት። አገራችን የማናውቀው ከፍተኛ ኃይል ያለባት አገር ነች፡፡ ድቅድቅ ጭለማ ውስጥ ብትገባም ሁሉንም ታልፈዋለችና አንስጋ የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013