እንደ አሸባሪው ህወሓት በሕዝብ እና በሀገር ላይ አይን ያወጣ ክህደት የፈፀመ ዋሾና መልቲ ስብስብ በዲያጎን ፋኖስ እግር እስኪቀጥን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ቢፈለግ አይገኝም፡፡ በውሸት እንደሱ ጥርሱን ነቅሎ የጎለመሰ ድርጅት የለም። ውሸት ሴራ ክህደት ሌብነት ጭካኔና ተንኮል ለህልውናው እንደ ደም ስርና ልብ ናቸው። ያለውሸትና ግጭት ውሎ ማደር አይችልም። ሕዝብን ሀገርን ብቻ አይደለም ራሱን ሳይቀር የሚዋሽ መርህ የሚባል ነገር ያልፈጠረበት መርገም ነው። ገና በ1967 ዓ.ም ትግል ሜዳ የወረደው በሀሰተኛና የተሳሳተ ትርክት ድቡሽት ላይ በተቀለሰ ሰቀላ ስር ዶልቶ ነው። የ47 ዓመታት ባተሌና አጥፍቶ ጠፊ ታሪኩ በውሸት ብዕር የተከተበ ነው። የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከአሸባሪው የትህነግ ጁንታ ጋር ተገደን የገባንበት ትንቅንቅ በአውደ ግንባር ብቻ የተወሰነ አይደለም የሚባለው ከዚህ ታሪካዊ ዳራና ተፈጥሯዊ ባህሪ በመነሳት ነው።
አዎ ጦርነቱና ዘመቻው በእፉኝቱ ትህነግ ስፖንሰር ከሚደረገው ተልዕኮና ስምሪት ከሚሰጠው ዲጂታል ወያኔ ህልቁ መሳፍርት ከሌለው የሀሰት መረጃና ሆን ተብሎ ከተዛባ መረጃ እና የሴራ ኀልዮት ጋር ነው። ይህ የከሃዲና የሌባ ስብስብ ከ27 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ በህዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ ከመንበሩ ከተፈነገለ በኋላ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ 24 ሰዓት የውሸት፣ ሆን ተብሎ የተዛባና የሴራ ኀልዮትን ፍላጻ እያንበለበለ ይገኛል። ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ኦፊሴላዊ ሀሰተኛ መግለጫዎችን አውጥቷል። በዚህም በሀገሪቱ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። ንጹሐን ተገድለዋል። ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍ በስግብግቡ የትህነግ ከሀዲ ቡድን መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀስ እና ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባ የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ወናፍ በተናበበና በተቀናጀ አግባብ በማህበራዊና መደበኛ ሚዲያ የሀሰትና የተዛባ መረጃውን እያራገበ ይገኛል። ጦርነቱን እራሱ ለኩሶ እያለ የተወረርሁ ድቤውን ይደልቃል። ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ለዛውም በውድቅት ሌሊት ሰራዊቱ ላይ ክህደት ፈጽሞ አጥቅቶና የሀገሪቱን 80 በመቶ ከባድ መሳሪያ ዘርፎ ድባቅ ተመቶ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መሪዎቹን አጥቶ ምላሱ ግን የሌለ ግዳይ ከመጣል አትቦዝንም ። ያልታጠቀውን መሳሪያ ታጥቄያለሁ፤ በሰማዩ እንዳሻው ፈንጭቶ ወታደራዊ ኢላማውን መትቶ የተመለሰን ተዋጊ ጀት መትቼ ጣልሁ፤ ሰሞኑን ደግሞ አዲስ አበባ ገባሁ ለማለት እየቃጣው ነው ።
ሌ/ጄ ባጫን ባለከዘራውን ኮሎኔል ሻምበልንና ሌሎችን ማረኩህ ያለ አይነ ደረቅና ቀጣፊ ነው። ከወር ወዲህ ደግሞ መንግስት በሰብዓዊ ምክንያት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ በትግራይ አውራ ጎዳናዎች በሺዎች በሚቆጠሩ ኮንቦዮች ታንኩን ከባድ መሳሪያውን ትጥቁን ስንቁንና ሰራዊቱን ይዞ ከወጣ በኋላ ከየተደበቀበት ጎሬ ተጠራርቶ የሌለ ድል የሚያከብር፤ ወልድያን ደባርቅን ተቆጣጥሪያለሁ፣ ወልቃይት ጠገዴን ሁመራን ልይዝ ነው ፤ የጅቡቲን መንገድ ቆርጬ የሀገሪቱን ጉሮሮ አንቃለሁ ፤ የዐብይን ሰራዊት ከጥቅም ውጭ አድርጌዋለሁ፤ ወዘተረፈ አይነት ነጭ ውሸቶችን በፎቶ ሾፕና በቪዲዮ እያቀናበረ በመላው ዓለም በተበተኑ ጭፍራዎቹ አማካኝነት እየነዛና እያራገበ ይገኛል ።
ከተለያዩ ጦር ግንባሮች የሚሰማው ተጨባጭ መረጃ ግን ህወሓት ክፉኛ እየተወቃ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። አሜሪካ የአውሮፓ ህብረትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ህወሓት በለስ የቀናው ሲመስላቸው ዝምታን፤ በጀግናው መከላከያ ሰራዊት በልዩ ኃይሎች ከባድ ምት ሲያርፍበት ያለቅድመ ሁኔታ ተኩስ ይቁምና ድርድር ይደረግ እያሉ ማላዘን ይጀምራሉ። እነ ጋርዲያን ኒውዮርክ ታይምስ፤ ፋይናንሽያል ታይምስ፤ ዘ ኢኮኖሚስት፤ ሮይተርስ፤ ቢቢሲና አልጀዚራ በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ ከስር ከስር እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋቡታል ።
በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያው ሀሰተኛው፣ የተዛባው ሆነ አሳሳቹ መረጃ የትየለሌ በመሆኑ ሕዝብ በአሰስ ገሰስ የመረጃ አረንቋ መዋጡን ለማረጋገጥ የትህነግ ምንደኛ የፕሮፓጋንዳ ጭፍራ ማህበራዊ ሚዲያውንና ዘርፎ ያቋቋመቸውን መደበኛ ሚዲያውን እንዴት በውሸት እንዳጥለቀለቀው መመልከትና መረዳት ይችላል። ከጦርነቱ ይልቅ የመረጃ አውደ ውጊያው አየሩን፣ ምድሩንና መልካው ብቻ ሳይሆን ቨርቹዋል የሆነውን ዲጂታል አለምንም አዳርሶታል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሴረኛውን የትህነግ ወታደራዊ ቡደን ውሸትና ቅጥፈት ጠንቅቆ የሚያውቀው ቢሆንም ጥቂት የዋሆችን ማቄሉና ማሞኘቱ አልቀረም። ለዚህ ነው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ጭፍራዎቹ በድል ዜናው ሰክረው ተጎምጸጽ ሲሉ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀን ድርጅት በመደገፍ ተጠርጥረው የተያዙት።
አሸባሪው ህወሓት በሒትለሩ ጆሴፍ ጎብልስ “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል፤” በሚል ቀመር ለሚነዛው ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የሴራ ኀልዮትን፣ ሚስ ኢንፎርሜሽን እና ዲስኢንፎርሜሽን አንሰላስሎ እየተጠቀመ ይገኛል። ሚስ ና ዲስ ኢንፎርሜሽን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስለሚመስል እየተተካኩ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ብያኔአቸው ግን ለየቅል ነው። ሚስ ኢንፎርሜሽን የተሳሳተ ወይም አሳሳች መረጃ ሲሆን ዲስ ኢንፎርሜሽን ደግሞ እውነትን ለመሸፋፈን ወይም የሕዝብ አስተያየት ላይ ተዕጽኖ ለማሳደር ሆን ተብሎ የሚነዛ የሀሰት መረጃ ነው። እፉኝቱ ትህነግ በፕሮፓጋንዳ ጭፍራው አማካኝነት ስልጣን ላይ እያለም ሆነ ከተፈነገለ በኋላ አሳሳች፣ እውነት የሚያጠየም እና የሴራ ኀልዮትን እያዛነቀ ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል። በተለይ በሰሜን ዕዝን አረመኔያዊ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከወሰነበት ደቂቃ አንስቶ እስከዚች ደቂቃ ድረስ ምን አልባት በየዕለቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ፣ እውነትን የሚበርዙና የደባ መረጃዎችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያ እያንበለበለ ይገኛል። በጀግናው የመከላከያና የሚሊሻ ኃይሎች በቀናት አውደ ውጊያ ድባቅ ሲመታ ያለ የሌለ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና የዘረፈውን ሀብት ለፕሮፓጋንዳ ማሽነሪው እያዋለው ይገኛል ።
የሚያሳዝነው አሸባሪው ህወሓት የፖለቲካ ትርፍና ጥቅም እስካገኘበት ድረስ ምንም አይነት ዋጋና መስዋዕትነት ይከፈልለት ስህተቱን ከማመን ይልቅ አይኑን በጥሬ ጨው ታጥቦ መዋሸትን የሚመርጥ ከሀዲ ነው ። ለ17 ዓመቱ ትጥቅ ትግል ከ60 ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶች ሞተዋል። ቁጥራቸው ከዚህ የማያንስ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከ70ሺህ በላይ ዜጎች ተሰውተውና ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ለአካል ጉዳት ተዳርገው ህወሓት ግን ህይወትና አካል ለገበሩለት ትግራዋይና ሌሎች ዜጎች በትንሹ ሊታመንላቸው አልቻለም። አሁንም ለዕብሪቱና ለዘረኝነቱ ልጆቻቸውን ከጉያቸው እየነጠቀ እየማገደ እውነትን ለመናገር አይናቸውን ለማየት ድፍረት የለውም። መልቲውና ጉረኛው ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን ጥቁር መነጸሩን ደንቅሮ ትግራይ ቴሌቪዥን የተገኘው አይኗ በእንባ ተሞልቶ፤”ልጄስ? የት ማገዳችሁት? የት የአውሬ የአሞራ ሲሳይ አደረጋችሁት!? ባይሆን አስከሬኑ ስጡኝ!?”ብላ የምታለቅሰውን እናት ላለመያት ነው የተባለው። የትግራዋይ ወላጆችን አይኖች በጥቁር መነጸር ቢሸሻቸውም ከገዛ ህሊናዋና ከሀቁ ግን ሊሸሽ አይችልም። እልፍ አእላፍ የሞቱለት የቆሰሉለትና በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር ሀብት የፈሰሰበትን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በግዕብታዊነትና በጥድፊያ አልጀርስ ከተስማማ በኋላ፤ የሄጉ የድንበር ኮሚሽን ኢትዮጵያንና ኤርትራን ካከራከረ በኋላ ሚያዚያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም ብይኑን ሲሰጥ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ከ70 ኪሎ ሜትር ካሬ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ግዛት ለኤርትራ ለመስጠት ወሰነ፡፡ ለኤርትራ በተሰጠው መሬት ውስጥ ለጦርነቱ ኃጢያት ተሸካሚ (ስኬፕጎት ) የሆነችው ባድመ ስትካተት፤ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በታሪክ ምንም የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቶበት የማያውቀውን የኢሮብ መሬት በከፊል … እነ ዓይጋን፣ ወርዓትለን፣ ዘገልባን፣ ለኤርትራ ተወሰነ፡፡ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ግን ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነ በጦርነት ካገኘነው በላይ በፍትሕ አደባባይ ያገኘነው በልጧል ሲል ቁና ቁና እየተነፈሰ በነጭ ላብ ተጠምቆ የኢትዮጵያን ሕዝብ መዋሸቱን ሁላችንም የምናስታውሰው ሲሆን አቶ ገብሩ አስራትም “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ”በተሰኘ ማለፊያ መጻፋቸው አስነብበውናል። በነገራችን ላይ በዘሔጉ ውሳኔ መሠረት ሰሞኑን ባድሜን ጨምሮ የተወሰኑለትን አካባቢዎች የኤርትራ መንግስት እየተቆጣጠረ ነው።
እንደ መቋጫ
እውነተኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የተጋነኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ሽብር የሚለቁ መረጃዎችን መከላከል ይቻላል፡፡ መንግስትም ሆና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን ከስር ከስር የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እግረ መንገድ ሕዝብን ካልተገባ ፍርሀትና ውዥንብር መከላከል ይቻላል። ዳሩ ግን ትክክለኛ መረጃን የማድረስ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ አንድ መረጃ ከማጋራት ወይም ከመለጠፍ በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይሁን ለሌላ ተግባር በምንጭነት ከመጠቀም በፊት ከሌሎች ምንጮች ጋር ማመሳከር የተቀናጀ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ በሀሰተኛ መረጃ መወናበድና መሸበር የለበትም። ይህ እንዳይሆን ግን መንግስት ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ሰዎች ስለምናጋራው ጹሑፍ፣ ምስልና ድምፅ ቆም ብለን ማሰብ፣ ለዋቢነት፣ ለአጋዥነት ስለምንከፍተው ድህረ ገፅ፣ ጦማር ታማኝ ምንጭ መሆን አለመሆን ማጣራት በማስከተል አስተያየት (ኮሜንት) ከመስጠታችን በፊት ማውጣት፣ ማውረድና ማመዛዘን ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀሰተኛ፣ የተዛባና የጥላቻ መረጃ ዘርጋፊዎችን፣ ነዥዎችንና ለፋፊዎችን በሒደት ማስቆም እንችላለን፡፡
መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከወሰነ በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ከጎኑ ከመቆሞ ባሻገር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና ግምቱ ቀላል ያልሆነ የአይነት ድጋፍ በማድረግ ደጀንነቱን እንዳረጋገጠው ሁሉ በውጭም በአገር ቤት ያሉ ዜጎች በተወሰነ ደረጃ የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ እየመከቱ ቢሆንም፤ እውነትን ይዞና ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ ሀገርና ሕዝብ ለዛውም ከትህነግ ጋር ለሚደረግ የጸረ ፕሮፓጋንዳ ትግል ሁሉም ዜጋ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ሊንቀሳቀስና ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ሚሊሻ በጦር ግንባር ያስመዘገበውን አንጸባራቂ ድል እኛ በእሱ መስዋዕትነት በሰላም እየኖርን በእጅ ስልካችንና በኮምፒዩተር ቁልፎች የምንደኛውንና የቅጥረኛውን የዲጂታል ወያኔ ጭፍራ ፕሮፓጋንዳ መክተን የፕሮፓጋንዳ አውደ ውጊያውን ማሸነፍና የጀግናው ሰራዊታችንን አኩሪ ድል መደገምና ማህበራዊም ሆነ መደበኛ ሚዲያውን በሀገር ፍቅር ሱናሚና በአርበኝነት ማጥለቅለቅ ይጠበቅብናል። ለሀገራችን ሁላችንም አምባሳደር፣ ጋዜጠኛና ሕዝብ ግንኙነት ነንና። ይህ ዘርፈ ብዙ ጦርነት በድል እስኪደመደም ሁላችንም የእውነት፣ የፍትህና የሉዓላዊነት ሰራዊት መሆን አለብን። ለዚህ ክቡር አላማ የህይወት መስዋዕትነት ብንጠየቅ እንኳ ወደ ኋላ የማንል ጊዜያችንን፣ እውቀታችንንና ገንዘባችን ሰውተን የድሉ ተቋዳሽ መሆን ይጠበቅብናል ።
እዚህ ላይ ሳላነሳ የማላልፈው መንግስት ጊዜ ሳያጠፋ የተጣራ መረጃ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሚዲያዎች የሚያደርስ፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ፤” ማቋቋሙና ሰው መመደቡ የዲጂታል ወያኔን ፕሮፓጋንዳ በተወሰነ ደረጃ መመከትና በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡና በምዕራባውያን ዘንድ የነበረውን ብዥታ ለማጥራት መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ መረጃ የማጣራቱ ተግባራ ለዚህ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉም የመንግስት ሚዲያ መረጃ የማረጋገጫ /ፋክት ቼክ / ክፍል ሊያደራጅ ይገባል። በዘመነ ማህበራዊ ሚዲያ ሚሰና ዲስ ኢንፎርሜሽንና እና የሀሰት ዘገባን ተከታትሎ ማምከን የሚቻለው እውነትን የማጣሪያና የማረጋገጫ ራሱን የቻለ ክፍል ሲኖር ነውና። ዜጋውም የዚህ አካል ሊሆን ይገባል። ከዚህ ጎን የሕዝቡን የሚዲያ ግንዛቤ media literacy ለማሳደግ የሚያግዙ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል። በመንግስት ሚዲያዎች ላይ አጥቶት የነበረውን አመኔታ ለመመለስ ብዙ ስራ ይፈልጋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና እውነተኛ ዜጎች ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013