
አዲስ አበባ፡- ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጎሳ ፖለቲካ ሃሳብ እንደ ማንኛውም ፍልስፍናና ሃሳብ ተወልዶ አድጎ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን መሞቱን የክብር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አስታወቀ።
አርቲስት ቴዎድሮስ ትናንት የክብር ዶክትሬቱን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተቀበለበት ወቅት ባስተላለፈው መልዕክት፣ ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጎሳ ፖለቲካ ሃሳብ እንደ ማንኛውም ፍልስፍናና ሃሳብ ተወልዶ አድጎ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን መሞቱን አስታውቋል፡፡
ከዚህ በኋላ መላው የሃገራችን ሕዝብ በተለይም ወጣቶች በጎሳና በዘር እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሳትናወጡ ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነትና በፍጹም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ስሜት በተጠንቀቅ ጸንታችሁ መቆም ያለባችሁ፤ ወይንም ያለብን መሆኑን በአፅንኦት ለማሳሰብ እወዳለሁ ብሏል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ የገባችበት ከባድ አጣብቂኝ እና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ቢሆንም እንኳን ሀገር እናት ከመጨረሻው አስጨናቂ ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰተው ሁሉ አገራችንም ከገጠማትና ሊገጥማት ከሚችለው ማንኛውም ከባድ አደጋ በድል ወጥታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር እንደሌለው አመልክቷል፡፡
እኛ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የትንሳኤ ልጆች ኃይላችን፣ ጉልበታችንና መመኪያችን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ራዕያችንም ፍቅር፣ ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ታላቅና ገናና አንዲት ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ለተሰማራሁበት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ይህ የክብር ሽልማት ይገባሃል ብሎ ያከበረኝን አንጋፋውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲም አመሰግናለሁ ብሏል፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም