በኦሊምፒክ መድረክ በየትኛውም ውድድር የሚመዘገብ ውጤት እኩል ነው። በተመሳሳይ በየትኛውም ውድድር የሚጠፋ ውጤት እኩል የሚያስቆጭ ነው። በኦሊምፒክ መድረክ በአስር ሺ ሜትር የሚመዘገብ ድልና የሚጠፋ ውጤት ግን ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ከሌሎች ውድድሮች የተለየ ነው። አስር ሺ ሜትር ከኢትዮጵያውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ትልቅ የታሪክ ትስስር ያለው ውድድር ነው። ኢትዮጵያውያን ይህ ርቀት ባህላቸውና የድል ተምሳሌታቸው ነው። ለዚህም ነው እንቁዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራት ቃለ መጠይቅ ‹‹በአስር ሺ ሜትር ስንሸነፍ በጣም ያናድደኛል›› ያለችው። እውነት ነው ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች በርቀቱ ኢትዮጵያውያን ከድል በመራቃቸው ብዙዎቹ የተቆጡ በዚሁ ምክኒያት ነው።
ከጀግናው አትሌት ማሞ ወልዴ ጀምሮ አስር ሺ ሜትር በኦሊምፒክ መድረክ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው። በማሞ የነሐስ ሜዳሊያ የተጀመረው የርቀቱና የኢትዮጵያ ትስስር በማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር ወርቅ ደምቆ በጀግኖቹ አትሌቶች በሀይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ አራት ወርቆች የኢትዮጵያውያን የድል መገለጫ ሆኗል። ከቀነኒሳ በኋላ በዚህ ርቀት ኢትዮጵያውያን ከድል ርቀው በቆዩባቸው አመታት ትልቅ ቁጭት አድሮባቸው ታሪኩን የሚያስቀጥል ጀግናም አጥተው ቆይተዋል። የትናንቱ ቀን ግን አዲስ ታሪክ ዳግም የተፃፈበት በርቀቱም አዲስ ኢትዮጵያዊ ጀግና የተፈጠረበት ሆኖ ታሪክ ራሱን ደግሟል። ኢትዮጵያም ለጊዜው ነው እንጂ የአስር ሺ ሜትር ጀግና እንደማይነጥፍባት በአዲሱ የድል አልጋወራሽ አስመስክራለች።
አዲሱ ጀግና ወጣቱ ሰለሞን ባረጋ የኢትዮጵያና የአፍሪካ የኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ፈር ቀዳጁ አትሌት አበበ ቢቂላ በደመቀባት ቶኪዮ ከተማ ከሃምሳ ሰባት አመታት በኋላ በሩቅ ምስራቋ አገር በወርቅ ደምቋል። ገና ከአትሌቲክስ ህይወቱ ጅማሬ አንስቶ የቀነኒሳ ተተኪ እንደሚሆን በርካቶች ተስፋ የጣሉበት ሰለሞን በእርግጥም ትክክለኛው ተተኪ መሆኑን ትናንት በፈፀመው ጀግንነት አስመስክሯል። ከቀነኒሳ በኋላም የአስር ሺ ሜትርን ድል በታላቅ ተጋድሎ ወደ ቤቱ መመለስ ችሏል።
በውድድሩ ሰለሞን ገና ከጅምሩ አፈትልኮ የወጣውን ዩጋንዳዊ አትሌት አምስተኛው ዙር ላይ ደርሶበት ፉክክሩን በማርገብ አስር ያህል ዙሮች የታገለበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ከአስራ አምስተኛው ዙር በኋላም ሰለሞን ወደ ኋላ ተመልሶ የቡድን አጋሮቹን ዮሚፍ ቀጄልቻንና በሪሁ አረጋዊን ወደ ፊት ለመሳብ ጥረት አድርጓል። ሰለሞን በዚህ አጋጣሚ ወደ ኋላ መቅረቱ በርካቶች ውድድሩ እንደከበደው ቢያስቡም መሃል ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ግምት የተሰጠውን ዩጋንዳዊውን የርቀቱ ባለ ክብረወሰን እግር በእግር እየተከተለ አላፈናፍን ያለው ዮሚፍ ቀጄልቻ ላይ ተስፋ እንዲጣል አድርጓል። የሃያ አንድ አመቱ ሰለሞን ግን ውድድሩ ከብዶት ሳይሆን ውድድሩን በራሱ መንገድ ከኋላ ሆኖ እየተቆጣጠረ ነበር። ውድድሩ ጥቂት ዙሮች ሲቀሩትም የቡድን አጋሮቹን ወደ ፊት ለመሳብ ጥረት አድርጎ ምላሽ ባለማግኘቱ የራሱን ርምጃ ለመውሰድ ተገዷል። ልብ አንጠልጣይና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ቁጭ ብድግ ባደረገው ፍልሚያ ሰለሞን በስተመጨረሻ ከርቀቱ ባለክብረወሰንና ሌላኛው አስደናቂ ብቃት ላይ ካለው ዩጋንዳዊ ጃኮብ ኪፕሊሞ ጋር ተናንቆ ብቻውን ከሁለቱ ዩጋንዳውያን እጅ የወርቅ ሜዳሊያውን ፈልቅቆ ማውጣት ችሏል። 27:43:22 በሆነ ሰአትም በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት አዲሱ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን በመሆን የወርቅ ዘውዱን ደፍቷል። ባለክብረወሰኑ ዩጋንዳዊው ቺኘቴጌ የቋመጠለትና በፍፁም የራስ መተማመን ለአገሩ የመጀመሪያ የርቀቱን ድል ለማስመዝገብ በእጁ የነበረው እድል ባይበገሬው ኢትዮጵያዊ ህልም ሆኖ ቀርቷል። ያምሆኖ ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ጋር ተናንቆና ሌላኛውን የአገሩን ልጅ አስከትሎ በመግባት በ27:43:63 የብር ሜዳሊያ ወስዷል። የነሐስ ሜዳሊያውም በ27:43:88 ወደ ጃኮብ ኪፕሊሞ አምርቷል።
በውድድሩ ዩጋንዳውያን የኢትዮጵያውያንን አትሌቶች የሚጠበቅና የተለመደ የውድድር ታክቲክ በቡድን ስራ ገና ከመጀመሪያው ማክሸፍ ችለዋል። ለሁለቱ አትሌቶች የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ስኬትም ሌላኛው ዩጋንዳዊ ራሱን ሲሰዋ ታይቷል። ያም ሆኖ ያከሸፉት የኢትዮጵያውያን ታክቲክና የሰሩት የቡድን ስራ ከሰለሞን የግል ብቃት ልቆ ለወርቅ አላበቃቸውም። ሰለሞን የቡድን ስራ ለመስራት ያደረገው ጥረት በሌሎቹ የቡድን አጋሮቹ ቢታገዝ ምናልባትም ኢትዮጵያ ከወርቁ በተጨማሪ ሜዳሊያዎች የማግኘት እድል ይኖራት ነበር። ዮሚፍና በሪሁ ከዩጋንዳውያኑ አትሌቶች አንፃር የተሻለ እንጂ ያነሰ አቅም የሌላቸው አትሌቶች እንደመሆናቸው መጨረሻ ላይ ያደረጉት ተጋድሎ ከመጀመሪያ አንስቶ በቡድን ስራ ቢታገዝ ተፎካካሪዎቻቸውን ከውድድር ውጪ በማድረግ ሜዳሊያ ውስጥ የሚገቡበት እድል ዜሮ አለመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ከድሉ ፌሽታ በተቃራኒ የሚያስቆጭ ነው።
ከቁጭቱና ከድሉ ጎን ለጎን ሰለሞን የዓለም መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል፡፡ በርካቶችም ሰለሞን ማነው እያሉ መነጋገሪያ ርዕስ አድርገውታል፡፡ አዲሱ የድል አልጋ ወራሽ ከወጣባት ትንሽ የጉራጌ የገጠር መንደር ተነስቶ ዛሬ ላይ በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ገና በሃያ አንድ ዓመቱ ነግሷል፡፡ ሰለሞን የበቀለበት የጉራጌ ማህበረሰብ በንግድና በጠንካራ የስራ ባህሉ ነው የሚታወቀው፣ የጉራጌ ማህበረሰብ በስፋት ትኩረቱ በንግድ ስራ ላይ በመሆኑ ስፖርት ላይ ያለው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ ይሁን እንጂ ማንም ሰው በፈለገው መስክ ታታሪነትን ባህሉ አድርጎ ከተነሳ ለስኬት ይበቃል›› የሚል እምነት ሰንቆ ወደ አትሌቲክሱ ብቅ ያለው ወጣት ዛሬ ላይ አገሩን በዓለም አደባባይ አስጠርቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለቶኪዮው የአትሌት ሰለሞን ባረጋ የወርቅ ድል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ሩጫ በሰለሞን ባረጋ አማካኝነት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘቷ እንኳን ደስ አለን ማለት እወዳለሁ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ለቀሩት ተወዳዳሪዎቻችንም መልካም ዕድል እመኛለሁ። ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በማለፍ ድል ማስመዝገቧን ትቀጥላለች” ብለዋል።
በተመሳሳይ በጃፓን ቶኪዮ የምትገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች።
በተመሳሳይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ “የወርቅ ድል፤ የኢትዮጵያ ድል፤ በአትሌቶቻችን” በሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያውነት መንፈስ እንዲጎላ እና ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በግልም በጋራም በመንቀሳቀስ ዛሬም ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ አደባባይ አይበገሬ ልጆች እንዳላት ለዓለም እያረጋገጡ ነው ሲሉ አስታውቀዋል። “በ10ሺህ ሜትር በአገኘነው ድል እንኳን ደስ አለን፣ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በቶኪዮ ኦሊምፒክ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኝቷል፡፡ ለተገኘው ድል እንኳን ደስ አለን” ብለዋል። የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013