በአዲስ አበባ ከተማ በቃሊቲ ክፍለ ከተማ እየተገነበ የሚገኘው የቃሊቲ አደባባይ- ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት የሀገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ዋና መተላለፊያ መንገድ በመሆኑ ልዩ ቦታ የሚሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት ነው። በተለይም ከጂቡቲ ወደብ የሚገባውን እና በዚያ ወደብ የሚወጣውን የሚያሳልጥ ትልቁ የወጪ ገቢ ንግድ የልማት ኮሪደር ነው። ከፍተኛ የወጪ ገቢ ንግድ የሚተላለፍበት መንገድ በመሆኑ 24 ሰዓት የሚያገለግል የበርካታ ተሽከርካሪዎች መመላለሻ ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም ነበር የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት። ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ወቅት ግንባታውን በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የተበጀተለት ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ሲሲሲ የተሰኘ የቻይና የመንገድ ግንባታ ተቋራጭ እየገነበው ይገኛል። ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አልቻለም። በቀኝ መስመር ያለው የመንገዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ አስፋልት ለብሷል። ተሽከርካሪዎች ይህን አስፋልት የለበሰውን የመንገድ ክፍል አንዳንዶች ደግሞ አስፋልት ያልለበሰውንም የመንገድ ክፍል በመጠቀም ማሽከርከራቸውን ቀጥለዋል።
የመንገድ ግንባታው በመጓተቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ተገልጋዮች ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዳርጓቸዋል። በክረምቱ ወቅት በጭቃ፣ በበጋ ደግሞ በአቧራ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል።
መንገዱ ለግንባታ ተቆፋፍሮ ሳይሰራ በመቆየቱ ምክንያት ተሽከርካሪዎቻቸው ለብልሽት እንዲሁም ለጥገና ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን አሽከርካሪዎች ይናገራሉ። የሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለቤት እና አሽከርካሪ የሆኑት አቶ ቤዛሁን ታምራት ይሄንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ። ተሽከርካሪያቸው ላይ ተደጋጋሚ ጉዳቶች ስለሚደርሱ የመኪና ዕቃ ለመቀየር እንደሚገደዱ ይናገራሉ። በዚህም ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጋቸውን ነው የሚያነሱት።
የመንገድ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ቢደረግ ከአምስት ደቂቃ በላይ የማይፈጀውን መንገድ እስከ አንድ ሰዓት በመንዳት እንደሚገደዱ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ውድ ጊዜያቸውን በመንገድ ላይ ለማሳለፍ ተገድደዋል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለመንገድ ፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሀላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን እንደሚሉት የቃሊቲ- ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት፣ 50 ሜትር የጐን ስፋት ያለው ነው። መንገድ የግንባታ ስራውን የቻይናው ሲ.ሲ.ሲ.ሲ (ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ካምፓኒ) የተባለው የስራ ተቋራጭ እያከናወነው ሲሆን ሰፊ ስትራክቸር አለው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሶስት ማሳለጫ ድልድዮች ያሉት መሆኑን ያብራሩት አቶ ኢያሱ፤ የመጀመሪያው ማሳለጫ የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ ማሰልጠኛ አደባባይ ነው። ይህ የላይ ማሳለጫ ድልድይ 240 ሜትር ርዝመት ያለው ነው። ማሳለጫው ከሳሪስ አቦ የሚመጣውን ትራፊክ ተቀብሎ ወደ ቃሊቲ የሚያሻግር ሲሆን ከስር ያለው ነባሩ የቃሊቲ አደባባይ ደግሞ ወደ ሳሪስ አቦ እና ሀይሌ ጋርመንት አደባባይ የሚያሳልጥ ይሆናል።
ሁለተኛው ማሳለጫ ደግሞ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከደራርቱ ትምህርት ቤት ወደ አቃቂ ከተማ የሚወስድ መሆኑን ያብራራሉ።ይህም ድልድይ 90 ሜትር ርዝመት እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ሶስተኛው ማሳለጫ የአቃቂ ከተማ መዳረሻ አካባቢ ረጅም ርቀት ያለው በተለምዶ ጋሪ ድልድይ እየተባለ የሚጠራው ሲሆን 20 ሜትር ስፋትና 50 ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት 55 ነጥብ 6 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን በተባለለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ አንዱ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው ወሰን ማስከበር ችግር ነው፤ ከወሰን ማስከበሩ ጋር ተያይዞ አብዛኞቹ ችግሮች አሁን ተፈተዋል። አንዱ ችግር ግን ሳይፈታ በመዝለቁ መንገዱ ተጓትቷል። ይህም ከመንገዱ አጠቃላይ 11 ኪ.ሜ ርዝመት ውስጥ 10 ኪሎ ሜትር በሚሆነው የመንገድ ፕሮጀክቱ የግራ መስመር ላይ ከአቃቂ ከርሰ ምድር የሚመጣ ትልቅ የውሀ መስመር በጊዜ አለመነሳቱ የመንገድ ግንባታው እንዲጓተት ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ይጠቅሳሉ ።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ፤ ችግሩን ለመፍታት ከውሃና ፍሳሽ ጋር በተደረገው ውይይትና ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው አቅጣጫ እንዲሁም የሚመለከተው የፌዴራል መንግስት አካላትም ባደረጉት ድጋፍ የውሃ መስመሩን ቦታ ለመቀየር የተደረጉት ጥረቶች ጥሩ ውጤት አስገኝተዋል። ለውሃ መስመሩ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ከውጭ የማስገባት ስራዎች ተገባደዋል።
መስመሩን የማንሳት እና የመሸጋገር ስራዎች መጀመሩን የገለጹት አቶ ኢያሱ እስከ ክረምት ወራት መጠናቀቂያ ድረስ ውሃ መስመሩን ቦታ የመቀየር ተግባራት ይከናወናል ብለዋል። በክረምት ወራት የግንባታ ስራውን ማከናወን ስለማይቻል፤ በክረምት ወራት ቦታ የመቀየር ስራውን በማጠናቀቅ ክረምት እንደወጣ መንገዱን የማጠናቀቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወደ 240 ሜትር ርዝመት ያለው ቃሊቲ ማሰልጠኛ አካባቢ ያለው ድልድይ እንዲሁም በቀኝ መስመር ያለው የመንገዱ አስፋልት ሙሉ በሙሉ አስፋልት ያሉት አቶ ኢያሱ ተሽከርካሪዎች ይህንን የመንገድ ክፍል በመጠቀም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል። በቀጣይ ዓመት ቀሪውን የመንገድ ክፍል ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013