አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ከሚጠሩ የሀገራችን ከተሞች አንዷ ነች። በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የሪፎርም ከተሞች ቀዳሚ ስትሆን የተቆረቆረችው በ1917 ዓ.ም ነው። ከባህር ጠለል በላይ ከ1ሺህ 500 እስከ 2ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። የሙቀት መጠኗ ከ15 እስከ 25 ዲግሪ የሚደርስ ሲሆን፣ አማካይ የዝናብ መጠኗ ከ900 እስከ 1ሺ 300 ሚሊ ሜትር መሆኑን መረጃዎች ይጠቅሳሉ። የአፈር ዓይነቷ አሸዋማ እንደሆነም ይጠቁማሉ።
በምዕራብ፣ ሰሜን እና ደቡብ ዳርቻዎች ከፍተኛ ተዳፋታማነት ሲኖራት ይሄም በዕድገቷ ማነቆነት የተለየበት ሁኔታ መኖሩን ከከተማ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ይገልፃል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ምስራቅ ላይ ስትገኝ የቆዳ ስፋቷ 200 ኪሎ ሜትር ነው።
አዳማ የኢንዱስትሪና ንግድ ማዕከልነቷ ጎልቶ ይስተዋላል። ከተማዋ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ምዕራብ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ ደግሞ ከሌሎች ከተሞች ይልቅ በብዙ ነገሮች ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እንድትተሳሰር ዕድል ፈጥሮላታል። በዕድገት ፍጥነትና በኮንፈረንስ ቱሪዝም እየተቀራረበች መጥታለች። በትንሹ እንኳን ለረጅም ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የኖረው የ4G ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗ በማሳያነት ሊገለፅ ይችላል። የኦሮሚያ ክልል ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ልጅ ዓለም አየለ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ሚኒስቴር በቅርቡ አዳማን ጨምሮ ለስድስት የሀገሪቱ ከተሞች ያስተላለፈው የከተሞች ፖርታል ተጠቃሚ መሆኗንም ያነሳሉ። እንደ ዶክተር ልጅዓለም የከተሞች ፖርታል (በመረጃ የበለፀገ ቋቱ ) ከተሞችን በዓለም ለመወዳደር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። ይህም አዳማን ከሌሎች ከተሞች ጋር በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ዘመናዊ ከተማ ያደርጋታል። የከተማ ነዋሪዎች በቴክኖሎጂው ተጠቅመው የተሻሻለ ኑሮ መኖር እንዲችሉም ያስችላል። በተለይ የከተሞች የመንግስት አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ የተሳለጠና የፈጠነ እንዲሆን ያለው አበርክቶ የላቀ ነው። በጥቅሉ በአዳማ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል።
የአዳማ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ እንደሚናገሩት፤ ከተማዋ ከኢትዮጵያ ሜትሮ ፖሊታን ከተሞች አንዷና የከተሞች ዲጂታል ፖርታል ቴክኖሎጂም ተጠቃሚ እንደመሆኗ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ እንደ ጅማ፣ ሻሸመኔ፣ አሰላና ሌሎች ከተሞች አርአያ ለመሆን የምትችል ናት። በመሆኑም የቴክኖሎጂ ማዕከልና የዘመነች ከተማ የማድረጉ ሥራም ተጀምሯል። ቴክኖሎጂው በተለይ አሁን ላይ ቀደም ብለው ሲነሱ የነበሩ የነዋሪውን ችግሮች እየፈታ፣ ወቅታዊና የሕዝብ አመኔታን የሚያስገኝ አገልግሎትና መረጃን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። ከተማዋን የሚመጥናትና በ1996 ዓ.ም የተዘጋጀ መዋቅራዊ ፕላን አላት። ነዋሪውንና ገቢ ወጪውን በተገቢው መልኩ የሚያገለግል የከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ባለቤት ነች። በአጠቃላይ 14 የከተማና አራት ገጠር ቀበሌ አስተዳደሮች አሏት።
ተቀዳሚ ከንቲባው እንደሚሉት፤ ከተማዋ የከባድ ጭነት መኪኖች መመላለሻና የትራንስፖርት ማዕከል ነች። በየቀኑ አዳማ ካለው መናኸሪያ ወደ 12 ከተሞች የሚወጣ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል። በከተማዋ ውስጥ በትራንስፖርት አገልግሎት የተሰማሩ በርካታ ባጃጅ፣ ሚኒባስ ታክሲዎችና በፈረስ የሚጎተቱ ሁለት ሺህ ጋሪዎች ይገኛሉ። ከመሰረተ ልማት አኳያም ቀድማ የሄደች በመሆኗ በብዙ አትታማም። ከተማዋ በአራት አቅጣጫ ዋና ዋና መንገዶች ሲኖራት 19ነጥብ 29 ኪሎ ሜትር የጠጠር ፣ 47 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 93 ነጥብ 29 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ (የኮብልስቶን)፣ 281 ነጥብ 99 ኪሎ ሜትር የተደለደለ መንገድ ይገኛል። ከብሔራዊው የኃይል መረብ ጋር የተገናኘ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ታገኛለች። የተንቀሳቃሽና መደበኛ ስልክ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች፣ 3ሺህ 500 ሳጥን ያለው ቅርንጫፍ ፖስታ አገልግሎት በከተማዋ ይገኛሉ። የውሃ አቅርቦት የምታገኘው ከአዋሽ ወንዝ ሲሆን፣ በቧንቧና በ156 ቦኖ ውሀ መስጫዎች ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ዝግና ክፍት የጎርፍ ውሃ ማስወገጃ ቦዮችም ተዘርግተውላታል። ከ 11 ሺህ ከ138 በላይ የመንግሥትና የግል ቤቶች ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ ቤቶች የተገነቡት ከእንጨትና ጭቃ ቢሆንም ለግንባታ የሚያገለግሉ እንደ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ብሎኬት እና ቆርቆሮ ያሉት የኮንስትራክሽን ግብአቶች በከተማዋ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ።
በከተማዋ 370 ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ 6ሺህ 808 ጅምላ አከፋፋይና ችርቻሮ ንግዶች፣ ስምንት ነዳጅ ማደያዎች፣ አራት ሺህ 981 አገልግሎት እና 73 ጋራዦች መኖራቸውን ነግረውናል። አንድ የመንግስት ባንክ፣ አስራ ሶስት የግል ባንክና ሶስት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅሟ ጠንካራ ሲሆን፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ባለ የጋራ ተጠቃሚነት የተቃኘ ነው።
አዳማ ከተማ የሚያስፈልጋትን የሰው ጉልበት የምታገኘው ከኦሮሚያ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች ነው። ከአካባቢዋ፣ሌሎች ከተሞችና ክልሎች ጋር ብርቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላት። ከተማዋ ከጂቡቲ የፋብሪካ ምርቶችና ግብርና ግብአትን፤ የእህል ምርቶችን ደግሞ ከአድአና የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች፣ እንስሳትን ደግሞ ከአርሲ፣ ባሌና ቦረና ታስገባለች። ከከረዩና አፋር የተፈጥሮ ሀብት (የማገዶ እንጨትና ከሰል) የምታገኝ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
በጤና ተቋማት ደረጃ አንድ የመንግስትና ሶስት የግል ሆስፒታል፣ አንድ የመንግስት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና 85 የግል ክሊኒኮች ይገኛሉ። በተለይ በትምህርት ተቋማት ብዛት የበለፀገች ነች። በከተማዋ ሰባ አምስት መዋዕለ ሕጻናት፣ ዘጠኝ የመንግሥት፣ ሃምሳ አንድ የግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 25 የግልና 16 የመንግሥት መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ መሰናዶን ጨምሮ አስራ ሰባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም አንድ የቴክኒክና እና ሙያ ተቋም አላት። እንዲሁም አስር የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች እና አንድ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ይገኙባታል። የእርድ አገልግሎት የሚሰጥ ቄራ፣ አራት የህዝብ ቤተ መጽሐፍትና የህዝብ የመሰብሰብያ አዳራሽ ባለቤትም ነች። በሳምንት ሁለት ቀን የከተማዋ የገበያ ቀን ሲሆን የእንስሳት ገበያም በሳምንት አንድ ጊዜ ቀን እንዲሁም በሁለት አካባቢዎች ዝቅተኛ ገቢ ያለው የከተማዋ ነዋሪ የሚገለገልባቸው ጉሊቶች አሏት።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮከብ አክሊሉ እንደሚናገሩት ከተማዋ ለተለያዩ ስብሰባዎች ተመራጭ በመሆኗ በየዕለቱ ወደ ከተማዋ የሚገባውና የሚወጣው ህዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም። ለአብነት ማዘጋጃ ቤቱ ከ2000 እስከ 2004 ዓ.ም መዝናኛን ጨምሮ በአማካኝ ከታክስ፣ ከመሬት ሊዝ፣ግብርና፣ ምርት ማቀነባበሪያ ዋና ዋና ምንጮች 428 ሚሊዮን 527 ሺህ 581 ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ገቢ ወጪዋ ከዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያና ከመዝናኛ ማዕከልነቷ ጋር የተሰናሰለ (የተያያዘ) ነው። ከገቢ ውጪ፣ ከአጠቃላይ የነዋሪው እንቅስቃሴ፣ የንግድና የስብሰባ ማዕከልነቷ ጋር በተያያዘ በየዕለቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ ታመነጫለች። ከሚመነጨው ቆሻሻ 70 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ወደ ሀብትነት ሊቀየር የሚችል ነው። ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የመቀየሩ ሥራም መተግበር ከጀመረ ከራርሟል። ቆሻሻውን ወደ ሀብትነት በመቀየር ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ በወጉ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። በትንሹ በአራት ማህበራት ለተደራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በየአንዳንዱ ማህበር አሥር አሥር አባላት ሲኖሩ በድምሩ 40 አባላት ታቅፈዋል። እነዚህ አባላት ደግሞ በየፊናቸው ለተወሰነ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። እራሳቸውም ሥራ አጥ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር የተፈጠረው የሥራ ዕድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቤተሰብ የመሰረቱና ልጆች ያፈሩ ከመሆናቸው አንፃር የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠርና የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የአዲስ ራዕይ ደረቅ ቆሻሻ መልሶ ማልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አልማዝ አሊ ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ይናገራሉ። እንደነገሩን ማህበራቱ ቆሻሻውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ሀብትነት የመለወጥ ተግባር የሚያከናውኑት በዓመት አራት ጊዜ ነው። የመጀመሪያ ዓላማቸው ግን በከተማዋ ያለውን የሥራ አጥነት ቁጥር የሚቀንስ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደነበር ያስታውሳሉ። ሁለተኛውና ትልቁ ግን የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነትና ውበቷን መጠበቅ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በግላቸው ከሥራ አጥነት በመላቀቅ በሚያገኙት ገቢ እራሳቸውንና ሦስት ልጆቻቸውን በማስተዳደር ከተረጅነት ተላቅቀው ለከተማዋ ኢኮኖሚ ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል።
አዳማ አሁን ላይ አረንጓዴ መላበስና ለዓይንም ሳቢና ማራኪ መሆን እንድትችልም አድርገዋል። ‹‹የቆሻሻ መልሶ ማልማት ፋይዳ ይሄ ብቻ አይደለም›› የሚሉት ሥራ አስኪያጅዋ ወይዘሮ አልማዝ ዋና ዋና ጥቅሞቹ ቆሻሻውን ወደ ምርት መቀየር፣ ለከተማዋና ለአካባቢው አረንጓዴ ልማት ላይ መዋል በተለይም ምርቱን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነም ያመለክታሉ።
አቶ በድሉ ወንድሙ የግሪን ኢትዮጵያ ፅዳትና ውበት መልሶ ማልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ማህበራቱ የሚሰሩት ስራ ከተማዋን ከቴክኖሎጂ ባሻገር በጽዳትና ውበት የዘመነች ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። በዓመት አራቴ ከቆሻሻ ኮምፖስት(የተፈጥሮ ማዳበሪያ) በማምረት ለማዘጋጃ ቤቱ ያቀርባሉ። አሁን ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ጋር ባላቸው ውል እያመረቱት ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በከተማዋ ለሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች እየዋለ ይገኛል። ለመዝናናት ወደ ከተማዋ የመጣውም ነዋሪውም ጥሩ አየር እንዲተነፍስ አስችሏል። ለዓይንም በጣም ደስ የሚል እየሆነ ነው።
ሌላው የአዳማ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ባዩ እንደሰጡን አስተያየት ከተማዋ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መንገድ መካከል እንደ መገኘቷ ከአዲስ አበባ ለመውጣትም ሆነ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት አስቻይ መጓጓዣ ናት። ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ የሚሄደው ምድር ባቡርም አዳማን ያቋርጣል። እነዚህም ዕድገቷ ፈጣን እንዲሆን አግዟል። በቅርቡም እንደ ሀገር ለስድስት ከተሞች የተላለፈው የዲጅታል ፖርታል(የመረጃ ቋት)ተጠቃሚ ሆናለች። ይሄ በአጭሩ ማንኛውንም የመንግስት አገልግሎት ተደራሽ ያደርጋል። ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ያስችላል። መፍጠር የሚችል ማህበረሰብ በማፍራት አስተዋጽኦ ማበርከቱም አያጠያይቅም። እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲወርዱ ማህበረሰቡ አብሮ እኩል እንዲራመድ ያስችሉታል። እኛም ሁሉም ከተሞች ራሳቸውን ለማዘመን ይትጉ በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013