ሙሉጌታ አጥናፍ የተወለደው በአማራ ክልል ሀዊ ዞን ቲሊሊ ወረዳ አደጋጓሽታ ቀበሌ ነው። ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን በልጅነት እድሜው በጣም ፈጣን መሆኑን ቤተሰቦቹ ይነግሩት እንደነበር ይገልጻል። እርሱም እንደሚስታውሰው በልጅነቱ ክብት በመጠበቅ የዳጉሳ ገለባ ለከብቶች በመስጠት፣ ጥጆችና በጎችን በማሰር፣ መንከባከብና በመላላክ ቤተሰቦቹን ያግዝ ነበር። እስከ ስምንት ዓመቱ ድረስ ጤናማ ሆኖ ከመንደሩ ልጆች ጋር እየተጫወተ ማደጉን የሚናገረው ሙሉጌታ ልክ ፊደል መቁጠር እንደጀመረ በደረሰበት የጤና እክል ምክንያት ለአካል ጉዳተኛነት መዳረጉን ይናገራል። ሙሉጌታ እንደቀልድ አካል ጉዳተኛ የሆነባትን ቀንና አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሳታል።
‹‹ወሩ ጥቅምት ይመስለኛል። ቤተሰቦቼ ሰዎችን ደቦ ጠርተው ጤፍ ያሳጭዳሉ። እኔም ልጅ ስለነበርኩ አንዳንድ ቀላል ስራዎችን እሰራለሁ፣ እየተላላኩ፤ አንዳንዴም እየተጫወትኩ ከወዲህ ወዲያ እል ነበር። ልክ ስራው ሲያልቅ አጫጆቹ ወደ ሰፈር ይመጡና የሚበሉት ምግብና የሚጠጡት ጠላና አረቄም ይቀርብላቸዋል። እልፍ ብሎም በቆሎ እየተጠበሰላቸው ነበር። ምግቡ ተበልቶ እንዳበቃ በአቅራቢው ካለ አንድ ቀፎ ውስጥ ንቦች ይወጡና አካባቢውን ይወሩታል። ሰዎችንም ይረብሻሉ። ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች በልተው እንዳበቁ የተዘጋጀውን መጠጥ ሳይጠጡ ወደ ቀፎው በመሄድ ውሃ እየረጩ ንቡን ወደ ቀፎው ያስገቡታል። ሰዎቹ የስራ ውሏቸውን ጨርሰው ወደ ቤታቸው እንደሄዱ አመሻሽ ላይ እኔ በጣም እጮህና ተዝለፍልፌ እወድቃለሁ።
ድንገት ታምሜ የወደቅሁበትን ሁኔታ ቤተሰቦቼና የአካባቢው ሰው የተለያየ ትርጉም ይሰጡት ጀመር። አንዳንዶች መጠጡ በሰዓቱ አለመጠጣትን ተከትሎ የተከሰተ የእርኩስ መንፈስ ትንኮሳ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ስንቀዥቀዥ እንደተለከፍኩ ያወሩ ጀመር። አንዳንዶችም ድንገተኛ በሽታ እንደሆነና በመበጣት ሊድን እንደሚችል ሀሳብ ይሰጡ ነበር አሉ። በዚህ የተነሳ ይመስለኛል አባቴ በምላጭ እራሴ ላይ እና ክንዴ ላይ ይበጣኝና ደም እንዲፈሰኝ ያደርጋል። ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ህክምናዎች ብጠቀምም ለውጥ ሳላይ ቀረሁ። ትምህርቴም ተቋረጠ። በመጨረሻ ግን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እንደመሆናችን ቤተሰቦቼ ከሁለት ዓመት በላይ የተለያዩ ጸበል ቦታዎች እየወሰዱኝ ያስጠምቁኝ ጀመር። ጸበል ከመከታተሌ በፊት በመቀመጫዬ እየተንፏቀቅሁ ነበር የምሄደው፤ ኋላ ግን ወገቤ መሻሻል ሲታይበት በጉልበቴ ተንበርክኬ መሄድ ጀመርኩኝ›› ይላል ሙሉጌታ።
ሙሉጌታ የሚኖርበት አካባቢ ገጠር በመሆኑ እርሱ ተንበርክኮ ሲሄድ የሚያዩት መንገደኞች ቆመው እንደ ተዓምር ሲመለከቱት ከአካላዊ ጉዳቱ በላይ የስነ ልቦና ጫና እየተፈጠረበት እንደመጣ ይናገራል። ያንን በመጥላትም አብዛኛውን ጊዜ ከቤቱ ሳይወጣ ማሳለፍን ይመርጥ ነበር። ሙሉጌታ ታላቅ ወንድሙ ለትምህርት ከአካባቢው ርቆ ከሄደ በኋላ በጉልበቱ እየሄደ የእርሱን ስራ ለመስራት ይጥር ጀመር። ከብት መጠበቅ፣ ምንጣሮ መመንጠር አረም ማረም በአጠቃላይ ከእርሻ በስተቀር ያሉ ስራዎችን እየሰራ ቤተሰቡን ማገዝ ይጀምራል።
የሙሉጌታ ቤተሰቦች በልጃቸው ድንገተኛ ጉዳት ልባቸው ቢሰበርም ወደ ነበረበት ጤንነቱ እንዲመለስ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገውለታል። ኋላ ግን ተስፋ በመቁረጣቸው የተነሳ ልጃቸው ዳግም ትምህርት ቤት መሄድ እንደሌለበትና ይልቁንም እዚያው በሚኖርበት የገጠር ቀበሌ ከመኖሪያ ቤታቸው አጠገብ አነስተኛ ሱቅ ከፍተውለት እንዲኖር ይመክሩት ነበር።
እርሱ ግን ልቡ እየነገዱ ከመኖር ይልቅ ተምሮ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ ይፈልግ ስለነበር የቤተሰቦቹን ሃሳብ ሳይቀበል ይቀራል። ከዚያም በአቅራቢያው ወዳለችው ቲሊሊ ከተማ እንዲወስዱትና እዚያው ቁጭ ብሎ መማር እንደሚፈልግ ይገልጽላቸዋል። ሙሉጌታ ከመታመሙ በፊት ትምህርት እንደጀመረ ከአደጋጓሽታ ቲሊሊ የሶስት ሰዓት የእግር ጉዞ እያደረገ ለመማር ሞክሯል። አሁን ግን መመላለስ የማይታሰብ በመሆኑ እዚያው ተቀምጦ ለመማር ወስኗል።
ሙሉጌታ ቲሊሊ አጉታ ትምህርት ቤት ሶስተኛ ክፍል ገብቶ መማር ይጀምራል። ከደረሰበት የአካል ጉዳት በተጨማሪ የማህበረሰቡን ትኩረት መሳቡና የዓይን ማረፊያ መሆኑ ያሳቅቀው እንደነበር ይገልጻል። ትናንት ቆሞ የሚሄድ ልጅ በድንገተኛ አጋጣሚ በእንብርክኩ መሄዱን ሲያስብ በጣም ይገርመዋል። በሙሉ ጤንነት ላይ እያለ ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር እየተሯሯጠ የሚጫወተው ትውስ ባለው ቁጥር እድሉን እንደሚያማርርና አንዳንዴም እንደሚበሳጭ ይናገራል። ግን ደግሞ የተሰጠውን አምኖ በመቀበል እየኖረ ነው። ሙሉጌታ የውስጡን በውስጡ አድርጎ ነገውን የተሻለ ለማድረግ ወጥኖ አዲስ የህይወት መንገድን መከተል ጀምሯል። ኑሮውን ቲሊሊ ከተማ አድርጎ መማር ሲጀምር የትምህርት ፍላጎቱን ያየ አንድ ሰው የማረፊያ ክፍል ይሰጠዋል። አንዳንዴም የበሰለ ምግብ ያስልክለታል። እናቱም በሳምንት አንድ ቀን ብቅ እያሉ ስንቅ ያቀብሉታል።
ለመማር ጥረት በሚያደርግበት በዚያ ሰዓት ፈተና የሆነበት ትልቁ ጉዳይ ቤተሰቦቹ የሰዎችን አስተያየት እየተቀበሉ ትምህርቱን ትቶ በልመና ስራ ላይ ቢሰማራ እንደሚሻለው የሚያሳድሩበት ጫና ነበር። ሙሉጌታ ጫናው ሲበረታበት የጀመረውን የሶስተኛ ክፍል ትምህርት ጨርሶ የሰዎችን አስተያየት በመስማት በልመና ህይወቱን ሊገፋ አስቦ ነበር። ነገር ግን የሶስተኛ ክፍል ውጤቱ አመርቂ ስለነበር ትምህርቱን አጠንክሮ ቢይዝ አንድ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ፍንጭ በማየቱ የሀሳባቸው ተገዢ ሳይሆን ይቀራል።
የገጠር ሰው አካል ጉዳተኛ ለምኖ ከመኖር ውጭ አማራጭ እንደሌለው አድርጎ የሚያስበው በትምህርት ጥሩ ደረጀ ላይ የደረሱ አካል ጉዳተኞችን ስላላዩ እንደሆነ በማሰብ አልተቀየማቸውም። እርሱ ግን ጠንክሮ በመማር አካል ጉዳተኛ ተምሮ እራሱን ማውጣት የሚችል መሆኑን ለማሳየት ወስኗል።
ሙሉጌታ ከሶስተኛ ክፍል 3ኛ ደረጃ ይዞ ወደ አራተኛ ክፍል ካለፈ በኋላ ሞራል ያገኛል። የዓመቱን ትምህርት አጠናቆ ክረምት ወደ ቤተሰቦቹ መግባት ሲገባው እዚያው ከተማ ተቀምጦ የቄስ ትምህርት መማር ይጀምራል። በዚህን ጊዜ ታዲያ ቤተሰቦቹ ቃላቸውን ስላላከበረ ሊያግዙት አልፈለጉም። ክረምቱን ከቄስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ኮቾሮ እየተመገበ ካሳለፈ በኋላ መስከረም ትምህርት ሲከፈት የአራተኛ ክፍል ትምህርቱን መማር ይቀጥላል።
ሙሉጌታ በመጀመሪያው መንፈቅ ከጠቅላላው የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች አንደኛ ይወጣና ደብል እንዲልፍ ተደርጎ አምስተኛ ክፍል ይገባል። በጉልበቱ እየዳኸ የሚማረው አካል ጉዳተኛ በሚያስመዘግበው ውጤት በመምህራንና በተማሪው ዘንድ ትኩረት የሚስብ ተማሪ ሆነ። የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በእንብርክኩ እየተመላለሰ ለሚማረው ብላቴና ተማሪ ዊልቸር ለመግዛት ገንዘብ ማዋጣት ይጀምራል። በዚህም አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር አካባቢ ይሰበሰባል። በተለይም የክፍል መምህሮቹ እርሱን የመርዳት ጉጉትና ፍላጎታቸው ከፍተኛ እንደነበር የሚያስታውሰው ሙሉጌታ ይህ አሳቢነታቸው በትምህርቱ የበለጠ እንዲበረታ ትልቅ መነቃቃትን እንደፈጠረለት ይገልጻል። በተለይም ተማሪዎች እርጥብ ሳር /ቀጤማ/ እየሸጡ ጭምር ዊልቸር ሊገዙለት ያደረጉት ጥረት መቼም የማይረሳው ውለታ ነው።
ሙሉጌታ ከአጠቃላይ የክፍሉ ተማሪዎች አንደኛ የመውጣት ዝናው በከተማው ማህበረሰብ ዘንድ ሳይቀር ይናኝ ጀመር። በዚህ የተነሳም አንዳንድ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ያደርጉለት ጀመር። እንደውም አንድ በአካል የማያውቀው የቅርብ ዘመዱ ታሪኩን ከሰዎች እንደሰማ በግሉ ዊልቸር ገዝቶ ይሰጠዋል። ከትምህርት ቤቱ ተሰብስቦ የተሰጠውን ብርም ለሚፈልገው ሌላ ዓላማ ማዋል ያስችለዋል።
ሙሉጌታ ትምህርት ቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ ቁምጣ ሱሪ እንጂ ሙሉ ሱሪ አለመልበሱ አብረውት ከሚማሩ ተማሪዎች የሚለየው አንዱ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራል። በተለይም የእግሮቹ መሰለል ቁምጣ ሱሪ ለመታጠቅ ምቹ አለመሆኑና ሱሪ እንዲለብስ ገፋፍቶታል። ነገር ግን ሱሪ የሚገዛበት አቅም አልነበረውም። ለዚህም ነው ከትምህርት ቤት ከተሰበሰበለት ገንዘብ ላይ ቆንጥሮ መጀመሪያ ሱሪ የገዛው።
ሱሪ የመልበስ ህልሙን እውን ካደረገ በኋላ በቀሪው ብር ቤተሰቦቹ በሚኖሩበት አካባቢ ግማሽ ሄክታር መሬት ተከራይቶ እያሳረሰ ጎን ለጎን ትምህርቱን መማር ይጀምራል። እጁ ላይ የተረፈችውን ጥቂት ገንዘብ አሟጦ የልብስ መተኮሻ ካውያ በመግዛት ከሚኖርበት ቤት በር ላይ ልብስ እየተኮሰ መማር ይጀምራል። በተጨማሪም የሌስትሮ እቃ አሟልቶ ሁለቱንም ስራዎች አንድ ላይ እያስኬደ ህይወቱን ይመራል። ሙሉጌታ ይህን ያደረገው ሁልጊዜ የሰው እጅ እያዩ መኖር ከሚያሳድርበት ተጽእኖ ለመላቀቅ በማሰብ መሆኑን ይናገራል።
በኢኮኖሚ እራሱን እየደጎመ በትምህርቱም እየጎበዘ መሄድ ጀመረ። የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱንም ከአጠቃላይ ተማሪዎች 1ኛ ደረጃ መውጣት ቻለ። ከክልልና ከወረዳው ሽልማቶች ይበረከቱለት ጀመር። በአጎታ የመጀመሪያና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ከ9ኛ እስከ 12ኛ አጎታ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት መማሩን ይናገራል። በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታውም ከሌሎች ጎበዝ ተማሪዎች ጋር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ እየተቋደሰ እንዳሳለፈ ይገልጻል።
ሙሉጌታ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስዶ ጥሩ ውጤት በማምጣት ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ለመሆን በቅቷል። አሁንም ተግቶ እየተማረ ነው። የሰዎችን አስተያየትና የቤተሰቦቹን ጫና ተቋቁሞ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደ ትልቅ ድል ይቆጥረዋል። ከትንሿ የገጠር መንደር አደጋጓሽታ ተነስቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባበትን አስቸጋሪ የህይወት ጉዞ ሲያስብ ይገርመዋል። ለምኖ እንዲበላ የተፈረደበት አካል ጉዳተኛ ተምሮ እራስን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳየቱ አሸናፊ አድርጎታል።
ሙሉጌታ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ዓመት ቆይታው በተለያዩ መድረኮች ላይ ከታላላቅ ሰዎች ጋር መገናኘቱ ትንግርት ሆኖበታል። ገና ዩኒቨርሲቲውን እንደተቀላቀለ የመደመር መጽሐፍ ምረቃን አስመልክቶ ሁለት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በመግቢያ ውጤታቸው ተመርጠው በሚሊኒየም አዳራሽ በሚዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ የክብር እንግዳ እንዲሆኑ ሲደረጉ ሙሉጌታ አንዱ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ሙሉጌታ የመደመር መጽሐፍን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እጅ ይቀበላል። ያም ብቻ ሳይሆን ባለሞተር ዊልቸር እንደሚገዙለት ቃል ይገቡለታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ካለባቸው የስራ ብዛት አንጻር የእርሱን ጉዳይ አስታውሰው ባለመፈጸማቸው አይፈርድባቸውም። ክብር ሰጥተው ስላናገሩት ብቻ ያመሰግናቸዋል። ጊዜ ሲያገኙ አስታውሰው እንደሚያደርጉለትም ተስፋ ያደርጋል።
አሁን የሚጠቀምበት ዊልቸር አንድ ቀን ቆሞ እንቅስቃሴው እንዳይገታ ሰግቷል። ከሰሞኑ እዚያው ግቢው ውስጥ እየሄደበት ሳለ ጎማውን የተሸከመው ብረት ተሰብሮ መውደቁን ይናገራል። በጓደኞቹ ብርታት የተሰበረውን ብረት አስበይዶ መልሶ ቢጠቀምበትም ዊልቸሩ አሁንም አስተማማኝ ደህንነት የለውም። በጎ አድራጎት ድርጅቶችና አቅሙ ያላቸው ሰዎች የዊልቸር ጥያቄውን እንዲመልሱለት ይማጸናል።
ሙሉጌታ ራዕዩን እውን ለማድረግ እየተጋ መሆኑን ይናገራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ18 እስከ 20 በመቶ አካል ጉዳተኞች አሉ የሚለው ሙሉጌታ የችግሩን ስፋት ያህል ጉዳዩ ትኩረት አላገኘም ይላል። የማኔጅመንት ተማሪ ሆኖ ተቋማትን የመምራት ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው ሙሉጌታ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን አናሳ ትኩረት እየተገነዘበ ከመጣ ወዲህ ግን የህግ ተማሪ ሆኖ ስለ አካል ጉዳተኞች በመሟገት ዓለም አቀፍ መብቶችን ማስከበር የሚችልበትን መልካም እድል ማምከኑ እንደሚያስቆጨው ይናገራል። ያም ሆኖ አካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማህበረሰቡን ማንቃት እንደሚፈልግ ሌላው ምኞቱ ነው። እኛም ይሳካልህ ስንል ተሰነባበትን። በሚቀጥለው ሌላ ባለታሪክ ይዘን እንቀርባለን። መልካም ሳምንት!
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013