የልጅነት ዕድሜን ብዙ ያስቡበታል። እልፍ ያልሙበታል። ይህ ጊዜ ከደስታና ፈንጠዝያ ባለፈ ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ መልካምና በጎው የሚታቀድበት ነው።ብዙዎች ልጅነት የሁሉ ነገር መሰረት ስለመሆኑ ይስማሙበታል። የዚህ ወቅት አዕምሮ ሁሌም በሰላምና ደስታ የተሞላ ነው። ከተንኮልና ሸፍጥ ርቆ በብሩህነት የደመቀው የልጅነት ዕድሜ በማርና ወተት ተመስሎ ጣፋጭ እንደሆነ ይቋጫል።
የልጅነት ዓለም ሁሌም ከተንኮል የጸዳ የንጹህ ሀሳብ ውሎ ማደሪያ ነው። ይህ መልካም ህይወት መሽቶ በነጋ ቁጥር ጨልሞ አያውቅም። ደስታና ፍቅርን ሰናቂው ንጹህ ማንነት በአካል ዳብሮ፣ በአይምሮ ጎልብቶ አዋቂ እስከሚባል የተሰራበት ቀለም አይወይብም፣ የተቸረው ልምላሜ አይጠወልግም። ይህ አይነቱን ዕድል ያልተቸሩ አንዳንዶች ግን የልጅነት ዓለማቸውን፣ የህጻንነት ህልማቸውን በድንገት ይነጠቃሉ።
በርከት ብለው ከቆሙት ታዳጊዎች ገጽታ ግራ መጋባት ይነበባል። ከሚያለቅሱ ዓይኖች፣ ከተከፉ ፊቶች፣ ካቀረቀሩ አንገቶች በስተጀርባ በግልጽ የሚስተዋል ተስፋ ቢስነት ነግሷል። ሁሉም በድካምና ጉስቁልና ውስጥ ናቸው። ያለ ምግብና ውሃ የከረመው አንደበታቸው ብዙ ይመሰክራል። ያለጫማ የተጓዙበት እግር፣ በድካም እንደዛለ ነው። የአለባበሳቸውና የጸጉራቸው ሁኔታ ያሳለፉትን አስቸጋሪ እውነት ይጠቁማል።
ታዳጊዎቹ በእጅጉ ሆድ ብሷቸዋል። የትናንቱ በጎ ህልም ዛሬ ከእነሱ ጋር የለም። የልጅነት አይምሯቸው እስከዛሬ ያኖረው ደማቅ ተስፋ በድንገት መነጠቁን እያሰቡ ቀን ጨልሞባቸዋል ።
አዎ ! ማልደው ከቤት መውጣታቸውን የምታውቅ እናት መምጣታቸውን እየናፈቀች እንደምትጠብቃቸው ያውቃሉ። እነሱ ግን በር ለቆመችው እምዬ በሰዓቱ አልደረሱም። ባላሰቡት ወጥመድ ተጠልፈው እግሮቻቸው ከአፋር በርሀ ቆመዋል። አካላቸው፣ ከትውልድ ቀያቸው ርቋል። ታዳጊዎቹ ዕንባ በሞላው አንደበት የሆነውን እውነት ይናገራሉ።
የመቀሌዋ ታዳጊ እየሩሳሌም ሀይላይ ልጅነቷን አፈር ፈጭታ ውሀ ተራጭታ አሳልፋለች። ዛሬም ቢሆን ያለችበት ዕድሜ ካሳለፈችው ዓለም እምብዛም አልራቀም። ልጅነቷን በወጉ ኖራ ያልጨረሰችው እየሩስ ትናንት እንደማንኛውም ልጅ ታላቅ ህልም ነበራት። ተምራ ራሷን መለወጥና ቤተሰቦቿን መርዳት ምኞቷ ሆኖ ቆይቷል።
አንድ ቀን ግን ታዳጊዋ አብሯት የኖረውን ብሩህ ተስፋ በድንገት ተነጠቀች። እሷና እኩያ ባልንጀሮቿ ምህረት በሌላቸው ግፈኞች እጅ ወደቁ። እነ እየሩስን ያገኝዋቸው ጨካኞች ጊዜ አልሰጧቸውም። እያጣደፉ፣እያዋከቡ ከሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መኪና ላይ ጫኗቸው። ልጆቹ ወዴት እንደሚሄዱ አልገባቸውም። የያዟቸው ጨካኞችም ቢሆኑ ይህን ለማስረዳት ጊዜ የላቸውም። ጥቂት ቆይቶ ግን እነ እየሩስ ወደ ውጊያ ለመሄድ መታፈናቸውን አወቁ።
አፋኙ ግብረሀይል ህጻናቱን በእጁ እንዳስገባ አስቸኳይ የጦርነት ግዳጅ ሰጣቸው። በለበሱት ልብስ እንደወጡ የቀሩት ልጆች ለምን? የማለት መብት አልነበራቸውም። የተባሉትን ሊፈጽሙ ወደ ውጊያው አውድማ መግባት ግድ አላቸው። አንድ መሳሪያ ለቡድን አስይዞ ተዋጉ ያላቸው ሀይል አፋር ምድር ‹‹ፈንቲ ሩሲ›› ከተባለ ስፍራ እነሱን ከፊት አስቀደመ። ውጊያው ሲጀመር ከአጠገባቸው በርካቶች እንደቅጠል ረገፉ። ይህን ያዩት ተማሪዎች መግቢያ መውጫው ጠፋቸው።
አሁን ከባድ መሳሪያ፣ በላያቸው እያፏጨ ነው። ከሁሉም አቅጣጫ የሚዘንበው ጥይት አስደንጋጭ የሚባል ሆኗል። ያልበረታው የህጻናቱ ጉልበት በእጅጉ ተብረከረከ። ከእስኪርቢቶ በቀር መሳሪያን መያዝ የማያውቀው እጅ ወደላይ ተነስቶ ምርኮን ናፈቀ።
እየሩስና ጓደኞቿ ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን ለመስጠት ወሰኑ። አደረጉትም። ህይወታቸውን አትረፈው፣ በእነሱ የሆነውን ሲመሰክሩም ይህን የግፍ ድርጊት ዓለም እንዲያውቀው፣ ህዝብ እንዲያወግዘው በመማጸን ሆነ።
የትግራይ ምድር ያፈራችው ኢሳያስ ዓለም የልጅነት ህልሙ ሩቅና ብዙ ነበር። እሱም እንደሌሎች ተምሮ ራሱን መቀየር፣ ቤተሰቦቹን ማገዝ ተስፋው እንደሆነ ዘልቋል። በድንገት ይህን ህልሙን ያስቀየረው ግን አንድ ቀን ከክፉዎች የተሰበከው ክፉ ሀሳብ እንደሆነ ይናገራል።
ኢሳያስ ‹‹እናውቅላችኋለን›› የሚሉ የጁንታው ቡድኖች እሱንና መሰሎቹን በአጋዥነት መለመሏቸው። እነ ኢሳያስ ለዚህ ዓላማ ሲታጩ ‹‹ትግራይ ታሸንፋለች›› በሚል አጉል ስብከት ተታለው እንደሆነ ያስታውሳል። ወደ ውጊያው ሲዘልቁም እንደተነገራቸው ለወንድሞቻቸው አጋር ለመሆን ነበር።
ኢሳያስና አንድ ጓደኛው አንድን መሳሪያ ለሁለት ተረከቡ። እነሱን ጨምሮ ሌሎች እኩዮቻቸው የውጊያ ግዳጅ ተጥሎባቸዋል። በርካቶች አካላቸው ያልጠነከረና ለጦርነት ያልደረሱ ታዲጊዎች ናቸው።
ኢሳያስና ባልንጀራው አንዱን መሳሪያ ለሁለት ይዘው ውጊያው መሀል ገቡ። የከባድ መሳሪያ ድምጽ ፍጥረትን ማራድ ጀምሯል። ከዚህም ከዚያም የሚወነጨፈውን ጥይት እንደዋዛ ማለፍ አዳጋች ሆኗል። ልምድና ዕድሜ ያላገዛቸው ልጆች ጦርነቱን መቋቋም አልቻሉም።
አሁን በብዘዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከጎናቸው እየወደቁ ነው። የበርካቶች ሬሳ በየደቂቃው መከመር ጀምሯል። ኢሳያስ እንደተጨነቀ መሳሪያ የያዘ አጋሩን አስተዋለው። እሱም እንደሌሎቹ ህይወቱ አልፏል። በእጅጉ ደነገጠ። ግራ ገባው።
ኢሳያስ በደመነፍስ እየተመራ ከወደቀ ባልንጀራው መሳሪያውን ወሰደ። ወዲያውም እንደዓቅሙ ውጊያውን ለመሞከር ተፍጨረጨረ። እንዳሰበው አልሆነም። የልጅነት ጉልበቱ፣ ልምድ የለሽ ማንነቱ ለድል አላበቃውም። በውጊያው የነበሩ እሱና ጓደኞቹ በመከላከያ ሰራዊት እጅ ወደቁ።
ዛሬ የትናንቱ ተማሪ የጦር ምርኮኛ ሆኗል። አሁን ስለትምህርትና፣ ስለነገው በጎ ህይወት አያስብም። ከወላጆቹ ነጥቀው ከጦር ሜዳ ያዋሉትን ክፉዎችን ሲያስብ ከልብ ይከፋል። ለዚህ ዕጣ ባበቁት አመራር ተብዬዎችም ሌሎች ወጣቶች እንዳይታለሉ ይመክራል።
ምርኮኞቹ ህጻናት አብረዋቸው ከወጡት እኩዮቻቸው አብዛኞቹን አጥተዋል። እነሱ ዕድለኞች ቢሆኑም ዛሬም የት እንደደረሱ ስለማያውቁት ወላጆቻቸው ይጨነቃሉ። አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም የድሀ ልጆችን እያፈነ ለጦርነት መማገዱን ቀጥሏል። ይህን እውነትም ህጻናቱ በታላቅ የሀዘን ስሜት ይመሰክራሉ።
ከዛፍ ተሰቅሎ ህይወቱን ያተረፋው ሀይልሽ ተክሉም ይናገራል። ከመቀሌ በአፋኝ ቡድኑ ተጠልፎ ከጦር ሜዳ ሲውል ያለአንዳች የስልጠና ዝግጅት ነው። ሀይልሽ የተሰጠው ሀላፊነት ከኋላ ሆኖ ቁስለኞችን እንዲያገል ነበር። ይህን አስቸጋሪ ተልዕኮ ያለምንም መሳሪያ እንዲወጣ የተገደደው ታዳጊ ብዙዎች ከጎኑ ሲሞቱና ሲቆስሉ ተመልክቷል፣ በውጊያው እሱና ጓደኞቹ የፊተኞችን መከተል ግዴታቸው ነበር።
የውጊያው ሀይል ሲጨምርና መድረሻ ሲታጣ ግን ሀይልሽ ሀሳቡን ቀየረ። እየወደቀ እየተነሳ ከአንድ ዛፍ ተንጠላጠለ፣ ዛፉ ድንጋጤ ያራደውን ታዳጊ በቅጠሎቹ ሸፍኖ ለሰዓታት ደበቀው። ጊዜው ሲደርስ ትረፊ ያላት ነፍስ ከመከላከያ ሰራዊት እጅ ወደቀች።
ብሶተኛዋ ታዳጊ ሄለን ይህደጎም በአፋኙ የህወሓት ቡድን በአስገዳጅነት ከተጠለፉት አንዷ ናት። ሄለን ኑሮዋ መቀሌ ከተማ ነው። እሷና ባልንጀሮቿ በድንገት ተይዘው ወደ ጦርነት ሲገቡ ያለምንም ስልጠናና ያለአንዳች መሳሪያ ነበር። በንግግሯ ዕንባ የሚቀድማት ጉስቋላዋ ልጅ መሪ የጁንታው መሪዎች እሷና ጓዶኞቿን በግዳጅ ወደ ውጊያው እንደማገዷቸው ትናገራለች።
ውጊያው ተጀምሮ ተኩሱ ሲጧጧፍ እነሄለን ግራ ተጋቡ። ባለመሳሪያዎቹ የፊተኞቹን እያዩ እንዲተኩሱ ተነግሯቸዋል። ሌሎቹ እነሱን እያዩ ከኋላ መከተል ያዙ። ጦርነቱ ተፋፋመ። አካሄዳቸው አላዋጣም። ዞር ብለው አለቆቻቸውን ፈለጉ። ትተዋቸው ጠፍተዋል።
ሁሉም ለአካባቢው አዲስና እንግዳ ናቸው። ታዳጊዎቹ ከዕንባና ጭንቀት ጋር በጭቃ ተውጠው የሚሆነውን ጠበቁ። አጋጣሚው ቀናቸው። ዕድላቸው መልካም ሆነ። በመከላከያ እጅ ወደቁ። ዛሬ በህይወት ተርፈው ታሪካቸውን ለማውጋት፣ የግፈኞችን ድርጊት ለመመስከር ጊዜ አገኙ።
ዛሬም አሸባሪው ቡድን ህጻናትን ከእናቶች ጉያ መንጠቁን ቀጥሏል። አሁንም ህወሓት የራስ ወዳድነቱ ስሜት እንዳለ ነው። አገር ለማፍረስ ህዝብ ለመበትን የሰነቀው ክፋት የምስኪኑ ድሀ ልጅ በእሳት እስከመማገድ አድርሶታል። አሁን እናቶች ከጉያቸው የተነጠቁ ልጆቻቸውን እየናፈቁ ያነባሉ።
ይህ ግፍና በደል ጸሀይ የሞቀው፣ አገር ያወቀው እውነት ሆኗል። አሁንም ግን ዝምታ የሸበበው የዓለም ማህበረሰብ እንዳልሰማ ሆኖ ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለ ነው። ግፍ የተፈጸመባቸው፣ የልጅነት ዘመናቸውን የተነጠቁ እና የጦርነት ሀሩሩ ያገኛቸው የትግራይ ህጻናት ግን በራሳቸው ዋቢነት ሀቁን ይናገራሉ። ‹‹ዓለም ይወቀው፣ ህዝብ ይፍርደው›› ይላሉ።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013