ከተጀመረ አንድ ሳምንት ባስቆጠረው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ የአትሌቲክስ ውድድሮች ትናንት ሌሊት ተጀምረዋል። ኢትዮጵያውያን በጉጉት የሚጠብቁት የወንዶች 10ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድርም ዛሬ ከሰዓት 8:30 ላይ ይካሄዳል። በርቀቱ ገናና ስም ያተረፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች ከድል ቢርቁም ቶኪዮ ላይ በአዳዲስ ወጣት አትሌቶች ወደ ተለመደው ድል ለመመለስ ትልቅ ተስፋ ሰንቀዋል።
በርቀቱ ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች የነገሰው እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ዘንድሮ ወደ ቶኪዮ ለማቅናት አስፈላጊውን ሰዓት ማሟላት አለመቻሉን ተከትሎ በ10ሺ ሜትር አዲስ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን ዛሬ መፈጠሩ የግድ ሆኗል። ለቻምፒዮንነት ከታጩ አዳዲስ አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያውያኑ ወጣት አትሌቶች ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ከታሪካዊው ማርሽ ቀያሪ አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ጀምሮ በኃይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ ተደጋጋሚ ድሎች በኦሊምፒክ መድረክ በ10 ሺ ሜትር ገናና ስም ያተረፈችው ኢትዮጵያ የርቀቱን የድል ታሪክ ለመመለስ ወጣትና ባለተሰጥኦ የሆኑትን አትሌቶች ዮሚፍ ቀጄልቻ ፣ ሰለሞን ባረጋና በሪሁ ዓረጋዊን አሰልፋለች።
ወጣት ቢሆንም በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ከዕድሜው የበለጠ የአትሌቲክስ ስኬትን የተጎናፀፈው ሰለሞን ባረጋ በርቀቱ ወደ ኦሊምፒክ ለማቅናት ሄንግሎ የተካሄደውን የማጣሪያ ውድድር በድንቅ ብቃት 26:49.51 በሆነ ሰዓት በማሸነፍ በኦሊምፒክ መድረክ የቀነኒሳ በቀለ ሁነኛ ተተኪ እንደሚሆን ፍንጭ አሳይቷል። የዓለም ቻምፒዮና የ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ሰለሞን አስደናቂ የሩጫ ተሰጥኦና ታታሪነትን አክሎ በዛሬው ፍልሚያ ምን ዓይነት ታሪክ እንደሚሠራ በርካቶች ጓጉተዋል። የዓለም መገናኛ ብዙሃንም በዛሬው ውድድር ዓይናቸውን በሰለሞን ላይ ጥለዋል።
ሌላኛው ባለተሰጥኦ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ 26:49.71 ሰዓት የሄንግሎውን ማጣሪያ ሁለተኛ ሆኖ በመፈፀም ለዛሬው ወሳኝ ፍልሚያ ሲዘጋጅ ቆይቷል። የርቀቱ የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ዮሚፍ ልክ እንደ ሰለሞን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከዕድሜው የበለጠ ስኬቶችን በመጎናፀፍ በረጅም ርቀት ኢትዮጵያ አዲስና ጠንካራ ትውልድ በቅርቡ እንደሚኖራት ማረጋገጥ የቻለው ቀድሞ ነው፡፡ ዮሚፍና ሰለሞን በኦሊምፒክ ለመድመቅ ትክክለኛ ዕድሜ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ፉክክር በሁለቱ ወጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል እንደሚሆን ብዙዎች ይጠብቃሉ፡፡
ሁለቱን አትሌቶች ባለፈው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ቀድሞ በመግባት የርቀቱ አዲስ ክስተት የሆነው ወጣት አትሌት በሪሁ አረጋዊ በሄንግሎው ማጣሪያ 26:50.37 ሰዓት ሦስተኛ በመሆን የኦሊምፒክ ትኬቱን ቆርጦ ዛሬ ይሰለፋል፡፡ የሦስቱ ወጣትና ጠንካራ አትሌቶች ብቃትም የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ አዲስ ትውልድ አስፈሪ ስብስብ ያደረገ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሦስት ወጣት አትሌቶች ከኮቪድ- 19 ስጋት ጋር በተያያዘ በዘንድሮው ዓመት በርቀቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማድረግ ባይችሉም ከስምንት ወራት በላይ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዛሬ አዲስ ነገር ካልተፈጠረም በሙሉ ጤንነትና ጥሩ አቋም ላይ መገኘታቸው ምናልባትም ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ ከምታሳካቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል በእነዚህ አትሌቶች የሚመዘገብ እንደሚሆን ተስፋ ተደርጓል። በርቀቱ ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በበለጠ የታሪክም ሆነ የብቃት ትልቅ ልዩነት የሚፈጥር አትሌት አለመኖሩም አዲስ ቻምፒዮን ለመሆን የአትሌቶቹ ጉጉት ትልቅ ሆኗል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይህን ድል ወደ ቤቱ ለመመለስ ከተፎካካሪዎቻቸው አንፃር በወረቀት ላይ የተሻለ የአሸናፊነት ግምት ቢያገኙም ከዩጋንዳና ኬንያ አትሌቶች ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃቸው ግልጽ ነው። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርቀቱ ከጠንካራ ተፎካካሪነት አልፈው ወደ ድል የተሸጋገሩ ሁለቱ ዩጋንዳውያን አትሌቶች ጆሽዋ ቺፕቴጊና ጃኮብ ኪፕሊሞ የኢትዮጵያውያኑ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዘው የቆዩትን የ5ና10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኖች በዘንድሮው ዓመት በእጁ ያስገባው ቺፕቴጌ ከዚህ ስኬቱ ጋር ተያይዞ በዛሬው ውድድር አዲስ ነገር መፍጠር የሚችል አቅም የለውም ማለት አይቻልም። ያምሆኖ ክብረወሰን ማሻሻል ብቻውን ለኦሊምፒክ ቻምፒዮንነት ያበቃል ማለት እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ። ይህ ዩጋንዳዊ አትሌት ባለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ በዚሁ ርቀት ተሳትፎ ስድስተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም በዶሃ የዓለም ቻምፒዮና ሳይጠበቅ ማሸነፍ ችሏል። በዚያ ቻምፒዮና ዮሚፍ ቀጄልቻ በአጨራረስና በጥቃቅን የታክቲክ ስህተቶች ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። ዛሬ ግን ዮሚፍ ከሰለሞንና በሪሁ ጋር የሚፈጠረው ጥምረት ከአትሌቶቹ ጥንካሬ አንፃር አስፈሪውን ተቀናቃኝ ለመቁረጥና ከጨዋታ ውጪ የማድረግ አቅሙ እንዳለው ማስቀመጥ ይቻላል። ቺፕቴጌ እንደ ኢትዮጵያኑ አትሌቶች ሁሉ ካለፈው ጥር ወዲህ ውድድሮችን አለማድረጉ ወቅታዊ አቋሙ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገመት አይቻልም።
ሌላኛው ዩጋንዳዊ ኪፕሊሞ በአንፃሩ ባለፈው ግንቦት ኦስትራቫ ላይ በርቀቱ 26:33:93 የሆነ ፈጣን ሰዓት መሮጡ ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያደርጋል። ይህም ሰዓት እኤአ ከ2008 ወዲህ በርቀቱ የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት መሆኑ የዩጋንዳውያን ስብስብ ሁለት ቢሆኑም አስፈሪ ያደርገዋል።
የ10ሺ ሜትር ውድድር ሲነሳ ኬንያውያንን መዘንጋት አይቻልም። በእርግጥ ኬንያውያን በዚህ ርቀት እኤአ ከ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ናፍታሊ ቴሙ ድል በኋላ በርቀቱ አሸንፈው አያውቁም። ያምሆኖ ከጠንካራ ተፎካካሪነት ርቀው አያውቁም። ሞ ፋራህ በርቀቱ በነገሠበት ወቅትና ኢትዮጵያውያን በተዳከሙበት ጊዜ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ያለው የ2015 የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ጂኦፍሪ ኮምዎረር በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ፉክክር ውጪ መሆኑ የኬንያውያንን ስብስብ አሳስቶታል። ያም ሆኖ የዓለም ቻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊው ሮኔክስ ኪፕሩቶ፣ ሮጀርስ ኪሞይና ዊልደን ኪፕኪሩይ ኬንያን ወክለው በዛሬው ውድድር ይፋለማሉ።
በኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ታሪክ እኤአ በ1980 ሞስኮ ኦሊምፒክ ምሩፅ ይፍጠር ለኢትዮጵያ ወርቅ ካስመዘገበ ወዲህ በአትላንታና ሲድኒ ኦሊምፒኮች ኃይሌ ገብረስላሴ ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገቡ ይታወቃል። ኃይሌን ተከትሎም ቀነኒሳ በቀለ በአቴንስና ቤጂንግ ኦሊምፒኮች የርቀቱ ድል የኢትዮጵያውያን ባህል እንዲሆን ታሪክ ሠርቷል። ከቤጂንግ በኋላ ግን በለንደንና በሪዮ ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያውያን ከድል ርቀዋል። ዛሬ ግን አዲሱ ትውልድ የርቀቱን የድል ባህል ወደ አገሩ ለመመለስ ከምን ጊዜውም በበለጠ ትልቅ ዕድል ያለው ይመስላል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013