ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኝት ከቅርብ ጊዘያት ወዲህ እየተለመደ የመጣ ተግባር ነው። ነገር ግን የታሰበውን ያህል ወጣቶች ተሳትፎ እያደረጉበት አለመሆኑ ይነገራል፡፡በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽን ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ ወጣቶች በአካባቢያቸው ተደራጅተው አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል። ተወሰኑት ደግሞ በማህበር በመደራጀት እውቅና አግኝተው ዘላቂ የሆኑ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን ማንሳትና አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች መርዳት በበጎ ፈቃኞች እየተሰራ ይገኛል፡፡ይህንን ስራ ማዕከል ከፍተው ድጋፍ የሚያደርጉም እየተበራከቱ ነው፡፡ለዛሬ መነሻውን ሆሳዕና ከተማ አድርጎ በተወሰኑ ከተሞች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን ብርቱ ተስፋ የህፃናት ማዕከልን እንቃኛለን፡፡ከማዕከሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መድህን ስዩም ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡መልካም ንባብ፡፡
የማዕከሉ ራዕይ ህልሙ ቅዠት፣ ተስፋው መና የሆነበትን ትውልድ፤ ከጎዳና ማንሳትና ተስፋን በመዝራት ህልምን ማልማት ላይ ያተኮረ ነው፡፡እንደ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ደግሞ ወላጅ እና አቅም በማጣት ምክንያት የተጎዱ ህጻናትን በመደገፍ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይጎሉ ማድረግ፣ ህጻናት ከጎዳና በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀል እንዲሁም ቤተሰብ ለሌላቸው ማቆያ ማዘጋጀት፣ አቅመ ደካማ ቤተሰቦችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም በአገሪቱ የመረዳዳት ባህል በትብብርና በአንድነት ማሳደግን ነው።
አመሰራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
ማዕከሉ 2005 ዓ.ም ላይ ሁለት ህፃናትን በመያዝ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ሆሳዕና ከተማ ተመሰረተ፡፡ስራው ሲጀመር የማህበሩ አባላት ገና ተማሪዎች ነበሩ፡፡አጠቃላይ ስራው በአስራ ሰባት አባላት የተጀመረ ሲሆን በወቅቱ አባቱ በሞት የተለየው አንድ ህፃን እና ከጎዳና ላይ የተገኘ ህፃንን በመያዝ ስራዎች ተጀመሩ፡፡በአሁን ወቅት ህፃናቱ የሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነዋል፡፡ልጆቹ በተደረገላቸው ድጋፍ ትምህርታቸውም ላይ ጎበዝ ሆነው የሚማሩ ናቸው፡፡የማዕከሉ እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እያደገ 2010 ዓ.ም ላይ ከትምህርት ቤት ክበባት ወደ ህጋዊ ማዕከልነት እንዲያድግ ተደረገ፡፡
2010 ዓ.ም ላይ አጠቃላይ ወጪያቸውን በመቻል 35 ህፃናትን መደገፍ ተጀመረ፡፡ልጆቹን በግልና በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ እንዲማሩ ስራዎች ተሰርተዋል።በቋሚነት ከሚረዱ ህፃናት ውጪ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የሚደረግላቸው ነበሩ፡፡እነዚህ ህፃናት በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡በማንኛውም ምክንያት ህፃናት ከትምህርት ውጪ ጎዳና ላይ እንዳይውሉ ማዕከሉ አላማ አድርጎ እየሰራ ነው፡፡
በጎዳና ላይ ህፃናት ኑሯቸውን እንዳያደርጉ ማዕከሉ ጠንክሮ የሰራ ሲሆን ህፃናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ በመከላከልና ጎዳና ላይ የወጡትን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ስራዎች ተሰርተዋል። ማዕከሉ አገር በቀል እንደመሆኑ ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በትብብር ይሰራል፡፡በአሁን ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ማስተባበሪያ ቢሮ ተከፍቶ በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕና፣ በሀመር፣ በድሬዳዋ፣ በመተሃራና በቱሉ ቦሎ አካባቢ ተመሳሳይ የበጎነት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ቀድሞ የተጀመረባቸው አካባቢዎች ማዕከል ተከፍቷል፡፡በማዕከሉ ውስጥ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን በማንሳት ቤተሰቦቻቸው እስኪገኙ ድረስ ይቆያሉ፡፡ቤተሰባቸው ያልተገኘ ህፃናት ማዕከሉ ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡
እስካሁን በማዕከሉ ወደ ሁለት ሺህ 200 ህፃናት እየተደገፉ ይገኛሉ፡፡በቀጣይ ይህን ቁጥር ወደ አስር ሺህ ለማሳደግ በሁሉም ቦታዎች ላይ ይሰራል፡፡በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የመደገፍና የመጎብኘት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ማዕከል በሚገኝባቸው አካባቢዎች ከዞን አስተዳደሮች ጋር በመተባበር ሙሉ ህፃናትን ከጎዳና ላይ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ለአራት ወራት አካባቢ ስራው ተሰርቷል፡፡እንቅስቃሴው ውጤት የታየበት ቢሆንም ክፍተቶች ነበሩበት፡፡በየአካባቢዎቹ የሚታዩትን ችግሮች በተቻለ አቅም ለመቀነስ እንጂ ለማጥፋት ሙሉ አቅም የለም፡፡ነገር ግን ትንሽ ጊዜም ቢሆን የህጻናቱን ህይወት መታደግ ተችሏል፡፡
በአሁን ወቅት ወረርሽኙ ተስፋፍቶ በሚገኝበት ወቅት ቢሆንም ቀደም ብሎ ከአመለካከትም አንፃር ከባድ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡በወቅቱ ሁሉንም ህፃናት በማእከል ውስጥ በማቆየት ጤናቸው እንዲጠበቅና ከማንም ሰው ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል። ይህ እንቅስቃሴ ሁለት ጥቅሞች ነበሩት፡፡በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናት በወረርሽኙ የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። ወደ ሌላም ሰው የማስተላለፋቸው እድልም በተመሳሳይ ሰፊ ነው፡፡በሁለቱም አቅጣጫ ያለውን ሁኔታ ለመቀነስ ጥረት ተደርጓል፡፡
የማዕከሉ የገቢ ምንጭ መጀመሪያ አካባቢ ጫማ በማፅዳት ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ይሰራ ነበር፡፡የማዕከሉ መስራች አባላት ቤተሰቦቻቸው ከሚሰጧቸው በማጠራቀም ያዋጡም ነበር፡፡በተጨማሪም አባላቱ ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ለትራንስፖርት የሚሰጣቸውን ለእርዳታ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ከጊዜ ሂደት በኋላ ወጪዎች እያደጉ ሲመጡ አገር ውስጥ ስፖንሰሮች መጠየቅና ድጋፍ ማድረግ ተጀመረ፡፡በሌላ በኩልም የአባላቱ ቤተሰቡ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች እየደገፉና ሌሎችንም ሰዎች እንዲደግፉ ያደርጉ ነበር፡፡
ማዕከሉ የትኩረት አቅጣጫው ላለመልቀቅ ህፃናት ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው፡፡‹‹የአገርን ሰው በአገር ልጅ መርዳት›› እንደ መሪ ሀሳብ ተይዞ እየተሰራበት ነው።ማህበሩ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን የማያስተናግድ ሲሆን ሁሉንም ስራዎች ያከናወነው በህብረተሰቡ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡የመርዳት ባህል ባለማደጉ እንጂ በሁሉም ሰው ውስጥ የመርዳት ፍላጎት አለ፡፡በጎ ማድረግ ሰፊ ነገር በመሆኑ ለምሳሌ የአረጋውያንን ቤት መጠገን፣ ከአረጋውያን ጋር በዓላትን አብሮ ማክበር፣ በከተሞች ላይ የፅዳት ስራ ማከናወን እንዲሁም በሌሎች ስራዎች ላይ ማዕከሉ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከኬጂ-1 እስከ 1ኛ ክፍል ድረስ በማዕከሉ ስር የትምህርት ቤት አገልግሎት እና በሆሳዕና ከተማ ከትምህርት ገበታ በመጉድል የሚመጣውን ጎዳናዊነትን ከመከላከል በተጨማሪ የጎዳና ህጻናትን ከጎዳና በማንሳት የአእምሮው ለውጥ ትምህርት በመስጠት የማቀላቀል እና የማቆየት ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡ይህም እንቅስቃሴ ጅምሩ ጥሩ በሚባል መልኩ ከሆሳዕና በስቲያ በአርባምንጭ እንዲሁም በድሬዳዋ እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ማስተባበሪያ ቢሮውን አዲስ አበባ በማድረግ ከሆሳዕና ከተማ አርባ ምንጭና ድሬዳዋ ተጨማሪ ቱሉቦሎ፣ ቻግኔ፣ ሐመር እና ደሴ እንቅስቃሴ ለማድረግ በዝግጅት ላይም እንገኛለን፡፡
የማዕከሉ ህጋዊ ሰውነት ጉዞ ሲታይ ደግሞ ከ2005 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም በትምህርት ቤት ክበብነት፤ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2009 ዓ.ም በቀበሌ ፈቃድ፤ ከ2010 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በዞን ፈቃድ፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል ፈቃድ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ይህም ማለት የገንዘብ እንቅስቃሴ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በወጪ ኦዲተር እንዲሁም የመንግስት እና በበጎ ፈቃደኛ ተጠሪዎች ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት ማዕከል ነው ማለት ነው፡፡
የህብረተሰቡ አቀባበል
የድጋፍ ስራዎች ከተጀመሩ በኋላ የህብረተሰቡ አቀባበል ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል። ጥሩ እንቅስቃሴ ያለው በአዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ከአዲስ አበባ ውጪ የግንዛቤ ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡በአንዳ ንድ ቦታዎች ላይ ድጋፍ ለማሰባሰብና ሰውን ለመርዳት ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ሲታይ በሁሉም ቦታዎች እንደ ግለሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች በብዛት አሉ፡፡ በተጨማሪም ከደመወዛቸው ጭምር በየወሩ የሚያዋጡ ሰዎች አሉ፡፡በመንግስት ደረጃ በተመሳሳይ ድጋፎችን የሚደረጉ ሲሆን በተለይ አመራሮች ባላቸው አቅም ሁሉ ከማዕከሉ ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡በሁሉም ደረጃ ስለ ድጋፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡
ማዕከሉን ያጋጠሙ ችግሮች
የበጎ አድራጎት ስራ ሲጀመር እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች አሉ፡፡የገንዘብ እጥረት፣ ማህበረሰቡ በራሱ ለምን እንደዚህ አይነት ነገር ስራ ፈታችሁ ትሰራላችሁ በማለት አባላቱን መውቀስ እንዲሁም በኮሮና ወረርሽን ወቅት የራስን ጤንነት አጋልጦ ለሌላው መስራት አስቸጋሪ ነበር፡፡ምንም አይነት ጥቅም በማይገኝበት ለምን እራስን አደጋ ላይ ተጥሎ የሚሰራው የሚሉ አስተያየቶች ነበሩ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመንግስት አካላት ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነቶች አለመኖር ተጠቃሸ ነው፡፡በአዲስ አበባ አካባቢ ድጋፍ ማድረግ የሚበረታታ ስራ ሲሆን በሌሎች ከተሞች ላይ ግን የሚፈለገውን ያክል አይደለም፡፡ከሁሉም አስቸጋሪ የነበረው በህፃናት ህይወት ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሰዎች ፍላጎት አለማሳየታቸው ነው፡፡አቅምና እድል ያላቸው ሰዎች በተቸገሩ ሰዎች ህይወት ውስጥ እጃቸውን ቢያስገቡ ነገሮችን መቀየር ይችላሉ፡፡
የማዕከሉ ቀጣይ እቅድ
ማዕከሉ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ይዞ እየሰራ የሚገኝ ነው፡፡የአጭር ጊዜ እቅዱ ለአስር ሺህ ህፃናት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ማዕከሉ እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች ሁሉም ቦታ ጥናት ተካሂዷል፡፡አሁን ግብዓት የማሰባሰብ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ይህን ስራ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሚከናወን ይሆናል፡፡ማንኛውም ተማሪ የመማሪያ ቁሳቁስ አጥቶ ትምህርት እንዳያቋርጥ ነው ስራው የተጀመረው፡፡
የማዕከሉ የመካከለኛ ጊዜ እቅዱ ሁለት ሺህ 600 ህፃናትን ጠቅልሎ የሚይዝ የማዕከል ግንባታ ማከናወን ነው፡፡ግንባታውን ለማከናወን የቦታ መረጣ ተጠናቆ ወደ ግንባታ ሂደት እየተገባ ይገኛል፡፡የማዕከል ግንባታውን ሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያደርግለት ቃል የተገባ ሲሆን ይህን ስራ ወደ ተግባር በመለወጥና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ የሚገኙ በጎዳና የሚኖሩ ህፃናትን ለመሰብሰብ እቅድ አለ፡፡ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶችን የመቀነስ ሁኔታም ይፈጥራል፡፡የማዕከሉ የረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን ማንሳት እና ጎዳና የመንቀሳቀሻ ስፍራ እንጂ መኖሪያ አለመሆኑን በተግባር ለማሳየት የተያዘ ሀሳብ አለ፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013