የኮማንደሯ ወርቃማ ፍሬዎች

ዛሬ ላይ ቆመው ስላለፉት ትናንት ሲያወጉ ፊታቸው በደማቅ ፈገግታ ይበራል። ይህ ፈገግታ በዋዛ የመጣ፣በቀላል የተገኘ ጸዳል አይደለም። ለዚህ ድንቅ ስሜትም የእሳቸው ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በመልካም ርምጃዎች መሀል ከባድ ዋጋ ተከፍሎበታል። በፈታኝ መንገዶችም ጠንካራ ትግል አግኝቶታል። እነዚህ ክፍያዎች ትናንትን እያስታውሰ ‹‹ነበር›› ቢያስብላቸውም ያለፈው ማንነታቸው ህያው ምስክር ሆኖ በስኬት አራምዷቸዋል፡፡

ኮማንደር መስከረም ብሩ ለፖሊስነት ሙያ ሕይወታቸውን ሰጥተው ዓመታትን አገልግለዋል። ፖሊስ መሆን ለእሳቸው ልዩ መለያና ኩራታቸው ነው። በደማቸው የሰረጸው ይህ ክቡር ሙያ እንጀራ ከመሆን አልፎ የስኬታቸው መንገድ፣ የማንነታቸው መለያ መሆኑን በሙሉ ልብ ይናገራሉ፡፡

ከዛሬ 38 ዓመት በፊት የዛኔዋ አፍላ ወጣት መስከረም ብሩ በወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋም ብቁ ፖሊስ ሆነው ሲመረቁ እንደማንኛውም አቻ ባልንጀሮቻቸው ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት አደራ ተቀብለው ነበር፡፡

ወጣቷ ፖሊስ ግን ይህ ብቻ አልበቃቸውም። ከቆይታ በኋላ በጤና ረዳትነት መማር ፈለጉ። እንዳሰቡት ሆኖም ተሳካላቸው። መስከረም የመጀመሪያውን ሥራ በጀመሩበት የፖሊስ ሆስፒታል ሙያቸውን በብቃት መወጣት ያዙ። የቆዩባቸው ሶስት ዓመታት ግን አዕምሯቸውን በብዙ ዕቅዶች መሀል አመላለሱት፡፡

እሳቸው ባሉበት ሥራ ላይ ያለ ለውጥ ሲያገለግሉ መቆየትን አልፈለጉም። በእጃቸው ያለው ሰርተፊኬትም ለእሳቸው ፈጽሞ በቂ የሚባል አይደለም። እናም ከሚገኙበት ደረጃ ከፍ ብሎ የሚገኘውን የነርስነት ሙያ አጥብቀው ፈለጉት። ሥራውን በጀመሩ ጥቂት ጊዜያት ትዳር ይዘው ልጅ ወልደዋል። ወዲህ የቤተሰብና ልጅ የማሳደግ ጉዳይ፤ ወዲያ ደግሞ ሥራን በብቃት የመወጣት ሃላፊነት ይዟቸዋል፡፡

እንዲያም ሆኖ ያሰቡትን ከማድረግ የሚመልሳቸው እንደሌለ ከራሳቸው ጋር ሲመከሩ ይውላሉ። ይህ ምክራቸው በውስጣቸው ተቀብሮ እንዲቀር ደግሞ ለራሳቸው ፊት አይሰጡትም። እሳቸው ጠንክረው ከተማሩና በዓላማቸው ከጸኑ ያሠቡትን ዳር ለማድረስ እንዳማያቅታቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ አንድ ርምጃ ወደፊት መፍጠን አለባቸው፡፡

መስከረም ከዘወትር ሃሳባቸው አልተገቱም። ቀን እየሠሩ ማታ በነርሲንግ ሙያ መማር ጀመሩ። ሥራና ትምህርት ቢያደክማቸውም ፈጽሞ እጅ አልሰጡም። በልጅነት የመሠረቱት ትዳር በፍሬ ባርኳቸዋል። አንዱ ልጅ ከፍ ሲል ሌለው እየተወለደ የእናትነት ደርሻቸውን እያበዛው ነው። እሳቸው ግን ይህን ከፈተና አልጣፉትም። እየተማሩ፣ እየሠሩ፣ ልጅ እያሳደጉ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ያሰቡት ሁሉ ከመሆን አልቀረም። ቆይታቸውን አጠናቀው ነርስ ሆነው ተመረቁ፡፡

የመስከረም አዕምሮ አሁንም ‹‹እፎይ!›› ሲል አላረፈም። በነርስነቱ እየሠሩ ልባቸው አርቆ አሰበ። ከዚህ ቀድሞ ጤና ረዳት ሳሉ ከህሙማን የሚወሰደውን ናሙና በመቀበል ብቻ ዓመታትን ገፍተዋል። ይህ ቁጭትም ከነበሩበት አንቅቶ ወደ ነርስነት አራምዷቸዋል። ዛሬም ግን ይህ ብቻ የበቃቸው አይመስልም። ልማደኛው ልባቸው አሁንም አርቆ ማሰብ፣ ማለሙን ይዟል።

አስተማሪው ባለቤታቸው የዲግሪ ምሩቅ ናቸው። መስከረም ደግሞ ሰርተፊኬቱን አሳድገው ዲፕሎማቸውን ይዘዋል። እንዲህ መሆኑ ራሳቸውን ከሚዛን አስቀምጦ ልካቸውን አሳያቸው። አዎ! በእሳቸው ዕምነት አሁንም ብዙ ይቀራቸዋል። በባለቤታቸው ደግሞ በትምህርት መበለጥን አይሹም። እናም ርምጃቸውን ለማስተካከል ፍጥነታቸውን ጨመሩ። አሁንም ልጆች መውለድ፤ መማርና መሥራታቸውን ቀጥለዋል። ሁሉንም ያለአንዳች ስብራትና ጉድለት እያስኬዱት ነው፡፡

ቀን ከሥራ ውለው ማታ ከትምህርት ማምሸት ልማዳቸው ሆኗል። ምሽቱን ቤት ሲገቡ ልጆቻቸው በናፍቆት ይጠብቋቸዋል። ጊዜ ሰጥተው፣ ጣታቸውን ይዘው ፊደል ያስቆጥሯቸዋል። ጓዳቸው ሁሌም የእሳቸውን እጅ ይሻል። ‹‹ደከመኝ ፣ አመመኝ ›› ብለው እጅ አይሰጡም። የሴትነት ሙያቸውን ሳይሰስቱ በየቀኑ ለቤተሰቡ ያደርሳሉ።

አሁንም የሥራና የትምህርት ዘመን በእኩል መራመድ ይዘዋል። ዛሬም መስከረም መማርን አላቆሙም። ይሠራሉ፣ ይማራሉ፣ ልጆች እያሳደጉ ቤታቸውን ይመራሉ። መምህሩ ባለቤታቸው እንደሚስት ጊዜ እንዲሰጧቸው ይሻሉ። ዓላማቸውን ሲረዱ ግን በይሁንታ ፈቅደው ‹‹አለሁሽ›› ይሏቸዋል። ልጆቻቸው በጨቅላ አዕምሯቸው የእናታቸውን ዓላማ አላጡትም። ጠዋት ማታ በፈገግታ እየሸኙ በፍቅር መቀበልን ለምደዋል፡፡

መስከረምና ትምህርት ፈጽሞ አልተላቀቁም። አንድ ቀን መለስ ብለው ዲፕሎማቸውን አሰቡት። ነርስ ሆነው ቢሠሩም ይህ ብቻ ብቁ እንዳልሆነ ተሰማቸው። ልማደኛው የመስከረም ልብ አሁንም አርቆ ማሰብ ያዘ። እንደወትሮው መድረሻውን አልሳተም። በዲግሪ በላብራቶሪ ሙያ ቀጥለው በብርታት መማርን ጀመሩ። አሁን ልጆች እያደጉ ነው። እነሱም ከትምህርት ውለው ነገን ማለም ይዘዋል። ባለቤታቸው ከሥራ ውለው ይገባሉ፡ ፡እማወራዋ ከትምህርት ጋር ፍቅራቸው ቀጥሏል፡፡

መስከረም የዓመታት ልፋት ጥረታቸው ዛሬም እንዳለ ነው። ዛሬም በብቃት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ኢንጂነሪንግ ከተማረው የመጀመሪያ ልጃቸው ጋር በእኩል ተመርቀው ደማቁን ስኬት አጣጣሙ። አሁን ኮማንደር መስከረም የላብራቶሪ ቴክኒሻን ናቸው፡፡

በሆስፒታሉ በጤና ረዳትነት የጀመሩት ሙያ ከፍ አድርጎ ከሌላ ሙያ ላይ አውሏቸዋል። የዛኔ በአፍላነት ዕድሜ የቆዩበትን ከህሙማን ናሙና የመውሰድ ሥራ ዛሬም ድረስ አይረሱትም። ይህ አጋጣሚ ለአሁኑ ማንነታቸው መሠረት፣ ለዕድገታቸውም መነሻ ነው። ለምን እንዴት የሚለው ከራስ ጋር ክርክር ለበጎ ሆኖ ለውጣቸውን አፋጥኗል፡፡

ሥራና ትምህርት፣ ቤተሰብና ማህበራዊ ሕይወት የኮማንደሯ ዕለታዊ ግዴታዎች ሆነዋል። እነዚህ እውነታዎች ለእሳቸው አይቀሬ፣ ፈታኝና ጣፋጭ የኑሮ መገለጫዎች ናቸው። ከመሆን የማይቀሩ ፣ ከመኖር የማይዘለሉ መልከ ብዙ ሐቆች፡፡

እነሆ! ዓመታት እንደዋዛ እየነጎዱ ነው። ዕድሜ እየገፋ፣ ልጆች እያደጉ ቀጥለዋል። አሁን መስከረምና ልጆቻቸው በእኩል ተምረው ይገባሉ። በዚህ ቤተሰብና ጎጆ ውስጥ ይህ አይነቱ ሕይወት ደግሞ ብርቅ ሆኖ አያውቅም። መስከረም ከሰርተፊኬት ተነስተው ዲግሪ ያደርሱት ትምህርት በሙያቸው ተደግፎ ውጤታማ አድርጓቸዋል። ዛሬ እንደትናንቱ ስለ ትምህርት የበታችነት አይሰማቸውም። በሙያቸው ነርስና የላብራቶሪ ቴክኒሻን ሆነዋል፡፡

አሁንም ግን የኮማንደሯ ውስጠት አርፎ የተኛ አይመስልም። ዛሬም ልማደኛው ልባቸው ስለትምህርት እያሰበ ነው። እሳቸው በቀጣይ ዓመታት የግላቸውን ሥራ የመሥራት ህልምን ሰንቀዋል። ለዚህ ዓላማቸው የሚበጀውን የትምህርት ዝግጅት መያዙ ወሳኝ መሆኑን ካመኑበት ቆይተዋል። መስከረም ይህን እንዳሰቡ ፊታቸውን ዳግም ወደ ትምህርት መለሱ፡፡

ኮማንደሯ በሥራ ዓለም ዕድሜ ልክ እንደማይቆዩ ያውቃሉ። ነገ ሥራቸውን ቢለቁ በራሳቸው መተዳደሪያ ሊኖሩ የግድ ነው። ለዚህ ዕቅዳቸው ደግሞ የቢዝነስ አሠራርን ማወቅ አለባቸው። ይህ ድንገት ውል ባላቸው ጊዜ እንደሁሌው ከራሳቸው መከሩ። የምክራቸው ጫፍም በቢዝነስ አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ የማስትሬት ዲግሪያቸውን እንዲመዘገቡ አነሳሳቸው። ከማድረግ ወደኋላ አላሉም። በሙያው ለተጨማሪ ዓመታት ተምረው ማስትሬታቸውን ከሶስተኛ ልጃቸው ዲግሪ ጋር በእኩል ተቀበሉ፡፡

ኮማንደር መስከረም ያለአንዳች ማቋረጥ ለ13 ዓመታት የቆዩበት የትምህርት ጉዞ ከዓላማቸው አገናኝቶ ከግባቸው አድርሷቸዋል። እነዚህ ዓመታት በበርካታ ውጣወረዶች የተሞሉ ቢሆኑም ለእሳቸው ስኬትን ያስጨበጡ ወርቃማ ጊዜያቶች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

ኮማንደር መስከረም ትናንትናን መለስ ብለው ሲያወጉ ከቀናት በአንዱ ከአንድ ሰው የተበረከተላቸውን ድንቅ ስጦታ አይዘነጉትም። በወቅቱ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው የእኛ ይሉት ቤት አልነበራቸውም። እንደ ብዙዎች በኪራይ ቤት እየኖሩ ሕይወትን ይገፋሉ። አጋጣሚ ሆኖ ግን የቤቱ ባለቤት ለእነሱ መልካም የሚባሉ ሰው ነበሩ። እናም በተባረከች አንዲት ቀን ካሏቸው ከብቶች መሀል አንዲት የወተት ላምን መርጠው ለቤተሰቡ ‹‹እነሆ›› ሲሉ አበረከቱ፡፡

ይህ እውነት ለመስከከረምና ቤተሰቦቻቸው ጉራማይሌ ስሜትን ፈጠረ። በወቅቱ ከእሳቸው በቀር ላሚቱን በስጦታ ለመቀበል የፈቀደ አልነበረም ። ባለቤታቸውን ጨምሮ ልጆቹ ጠዋት ወጥተው ከመግባታቸው ጋር የእሷን ወደ እነሱ መምጣት ከስጋት ጋር ተቀበሉት። ኮማንደሯ ግን ቆፍጠን ብለው ለመላው ቤተሰብ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡

እሳቸው የስጦታ ላሟ ለቤተሰባቸው ታላቅ በረከት መሆኗ አልጠፋቸውም። ይህን እውነት ለሌሎች ለማጋባትም ሁሉንም ማሳመን እንዳለባቸው ወሰኑ። በወቅቱ እናት ሥራውን የጀመሩት ከልጆቻቸው ብርታት በመነሳት ሆነ። የእሳቸውን ወታደርነት፣ የአባታቸውን መምህርነት እየጠቀሱ የገቢያቸውን ማነስና የኑሮን መክበድ አስረዷቸው። የላሟ ከእነሱ መኖርም ጥቅሙ ለመላው ቤተሰብ መሆኑን ዘርዝረው የወደፊቱን በጎ ህልም ነገሯቸው። ልጆቹ የእናታቸውን ቃል ሰምተው በይሁንታ እጅ ሰጡ፡፡

የታቀደው ቀን ደረሰ። እናትና አባት ሥራ ከመሄዳቸው በፊት ወተት ማለብ፣ አዛባ መዛቅ ጀመሩ። በወቅቱ ተማሪዎች የነበሩት ልጆችም ጠዋት ትምህርት ቤት ሲሄዱ በየቦታው ወተት ማድረስን ለመዱ። ሲመለሱም የወተት ዕቃዎችን ማጠብ ግዴታቸው ሆነ። በቤተሰቡ ኑሮ የሥራ ባህል ተለመደ። ሁሉም ግዴታውን አውቆ በተግባሩ ላይ ተሰማራ፡፡

ይህ አጋጣሚ ለኮማንደሯና ቤተሰቦቻቸው የጥንካሬ መሠረትን ገነባ። በወላጆች ልፋትና ድካም ልጆች በተሻለ ትምህርት ቤት ተምረው ለመልካም ውጤት በቁ። ኮማንደሯ ለቤተሰቦቻቸው የከፈሉት ታላቅ ዋጋ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ከእሳቸው መማር ጎን በእኩል የተማሩት ልጆቻቸው ዛሬ ሁሉም ከቁምነገር ደርሰዋል። የመጀመሪያ ልጃቸውን በኢንጂነሪንግ አስመርቀዋል። ሁለተኛ ልጃቸው ዶክተር ነው።

ዛሬ እሳቸው ባገለገሉበት የፖሊስ ሆስፒታል ሀኪም ሆኖ እየሠራ ይገኛል። ሶስተኛዋ ልጃቸው ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የአካውንቲንግ ምሩቅ ናት። አራተኛውና የመጨረሻው ልጅ የአስር ዓመት ህጻን ሲሆን፤ በትምህርት ዓለም ይገኛል፡፡

የኮማንደሯ ቤተሰቦች እያንዳንዳቸው ዐሻራ ባኖሩባት የስጦታ ላም የድካም ልፋታቸውን ፍሬ አላጡም። ዛሬ ያቺ ላም ውላ አድራ በብዙ ተራብታለች። አንዷ 22 ደርሳም በረት ሙሉ በረከት ሆናለች።

ኮማንደር መስከረም ብሩ ለ38 ዓመታት ያገለገሉበትን የፌዴራል ፖሊስ በዘንድሮው የመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በክብር ለቀው ተሰናብተዋል። የፖሊስ ቤት ማለት ለእሳቸው የልጅነት ወዛቸው፣ የትምህርት ፍሬያቸው፣ የዕድሜያቸው ወግ ማዕረግ ነው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በተጓዙበት ተቋም ስኬታቸውን ጨብጠው የሕይወት ሽልማታቸውን በክብር ተቀብለውበታል፡፡

ኮማንደሯ ያለፉበት እያንዳንዱ ርምጃ በምክንያትና ሰበብ የሆነ ነበር። ዓመታትን በሥራና ትምህርት ገፍተው ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበሉት ሁለተኛ ዲግሪም የራሱ መነሻና መሠረት ነበረው። ከሥራ በኋላ ሊሠማሩበት ላሰቡት የቢዝነስ ዓለም ሃይልና ብርታት ሊሆን ክንዳቸውን አፈርጥሟል፡፡

ዛሬ ኮማንደር መስከረም ከክብር ጡረታ በኋላ በአዲስ የሥራ ሕይወት የራሳቸውን ቢዝነስ ጀምረዋል። ይህን ሲያደርጉ ለአንዲትም ቀን ያለሥራ ለመቀመጥ በመወሰን ነው። ዛሬ በከፈቱት ዘመናዊ ሱቅ ‹‹መስኪ›› የድፎ ዳቧቸው በብዛትና ጥራት እየተመረተ ለብዙኃን ይደርሳል። ጣፋጩ የኀዘንና ደስታ አገልግላቸውም በበርካቶች ዘንድ ተፈላጊና ተመራጭ ነው። ለቤተሰቦቸው የሥራ ባህልን በጠዋቱ ያስተማሩት ብርቱ ሴት ዛሬ ልጆቻቸው የታላላቅ ድርጅቶችና የሚያኮራ ዕውቀት ባለቤት አድርገዋቸዋል፡፡

ኮማንደር መስከረም ለዓመታት የሠሩበትን የፌዴራል ፖሊስ ተቋምና የሥራ ጓዶቻቸውን ውለታ ፈጽሞ መርሳት አይቻላቸውም። በተለይ ደግሞ እንደሳቸው በክብር የሚሰናበቱ አባላት የመጨረሻ መድረሻ ሁሌም ሲያሳስባቸው ቆይቷል። ይህን እሳቤያቸውን እውን ለማድረግ በእሳቸው መስራችነት የተቋቋመው የአንድነት ማህበር በመንግሥት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ አሁን ላይ የአባላቱ ቁጥር ከ470 በላይ ይቆጠራል። በእሳቸው የሚመራው ይህ ማህበር ማንም ሰው በጉብዝና ጊዜው አገልግሎ በጡረታ ዘመኑ ሊረሳና ሊተዉ አይገባውም የሚል መርህን ያራምዳል፡፡

ኮማንደሯ አሁንም ሞላ ደርበብ ያለው ሰውነታቸው በብርቱ የሕይወት ሩጫና ትግል መሃል ያለፈ አይመስልም። ዛሬም ቢሆን በርካታ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ በእጃቸው እንደሆነ በኩራት ይናገራሉ። ለልጅነት በባለቤታቸው የተለየ አክብሮት ያላቸው መስከረም በእሳቸው መልካምነት እዚህ መድረሳቸውን ባሰቡት ጊዜ ምስጋናቸው ከልብ ነው፡፡

ኮማንደር መስከረም ዛሬም ከጡረታቸው ማግስት ሕይወትንና የሥራ ባህልን እንደ አዲስ ለመዘወር መንፈሳቸው የነቃ ፣ሃሳባቸው የበቃ ነው። አሁንም በውስጣቸው የሰረጸው የመማር ፍላጎት ዘወትር ከዕውቀት መንደር አሳድሮ ይመልሳቸዋል። ብርቱዋን ኮማንደር መስከረም ብሩን።

በመልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You