ኢትዮጵያ የሴካፋን ውድድር ታስተናግዳለች

የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ሴካፋ) ቀጣይ የውድድር መርሐ ግብሮቹን ትናንት ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር እንድታስተናግድ መመረጧ ታውቋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር ላይ የሚከናወነው ከ17 ዓመት በታች የዞኑን ሻምፒዮና እንድታስተናግድ መመረጧን ሴካፋ በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም ሴካፋ የ2025 የውድድር መርሐ ግብሩን ይፋ አድርጓል:: በዚህ መሠረት የሴካፋ ሴቶች ሻምፒዮና በታንዛኒያ እንደሚካሄድ አሳውቋል:: አዘጋጇ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን በዚህ ውድድር እንደሚካፈሉ አረጋግጠዋል:: ከሰኔ 5-15/2017 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የውድድር ዳይሬክተር ዩሱፍ ሞሲ ውድድሩ በሚቀጥለው ወር ከቶታል ኢነርጂስ ካፍ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ (ዋፍኮን) በፊት እንዲካሄድ መወሰኑን ተናግረዋል።

“የእኛን ወኪሎቻችንን በመርዳት የዋፍኮን ታንዛኒያ የተሻለ ዝግጅት እና ሌሎች ቡድኖች ደግሞ በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር ለሚቀጥሉት የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ 2026 ማጣሪያ ይዘጋጃሉ” ሲሉ ሞሲ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል አስተናጋጇ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ተሳታፊ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያ እና ሌሎች ተጨማሪ ቡድኖች እንደሚያረጋግጡ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ በውድድሩ እንደማትሳተፍ ማረጋገጧን ዘግይተው የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድርም በታንዛኒያ እንደሚደረግ ሴካፋ አሳውቋል:: ውድድሩ ከነሐሴ 28 እስከ መስከረም 9 ቀን 2018 ዓ.ም በዳሬሰላም ይከናወናል::

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው ውድድር የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል:: የኢትዮጵያን የሴቶች ፕሪሚየርሊግ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ ማንሳት የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ዘንድሮም ኢትዮጵያን በመወከል በዞኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር የሚሳተፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ የአንድ ጨዋታ የደርሶ መልስ ፍልሚያ ብቻ እንደሚቀረው ይታወቃል። ሉሲዎቹ ከሁለት ወር በፊት ከዩጋንዳ ጋር ያደረጉትን የማጣሪያ ጨዋታ ካምፓላ ላይ የገጠማቸውን የ2ለ0 ሽንፈት በሜዳቸው ቀልብሰው በመለያ ምት በማሸነፍ ነበር ለመጨረሻው ማጣሪያ የደረሱት። በመጨረሻው ማጣሪያ የሚገጥሙትም ታንዛኒያን ይሆናል።

ይሁን እንጂ በቀጣይ ታንዛኒያ በምታዘጋጀው የዞኑ ሻምፒዮና አለመሳተፋቸው የስፖርት ቤተሰቡን እያነጋገረ ይገኛል። ሉሲዎቹ ምናልባትም በዞኑ ሻምፒዮና ቢሳተፉ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከታንዛኒያ ጋር ለሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ እንደ አቋም መለኪያና ዝግጅት ሊረዳቸው ይችል ነበር የሚሉ ሃሳቦች ከስፖርት ቤተሰቡ ተሰንዝረዋል።

ከዚያ ባሻገር ሴካፋ ይፋ ባደረገው መርሐ ግብር መሠረት የሴካፋ የክለቦች የሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ወድድር እና የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚጀምርበት ቀን በሦስት ብቻ መለያየቱ ጥያቄ ፈጥሯል።

ይህም በሉሲዎቹ ስብስብ ውስጥ በርካታ ተጫዋቾችን የያዘው የንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀምር ከአራት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በውድድሩ ሊገኝ አለመቻሉ ነው። ንግድ ባንክ የሴካፋን ዋንጫ ካሸነፈና እና ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር መግባት ከቻለም ለተጨማሪ አንድ ወርና ከዚያ በላይ ለሚፈጅ ጊዜ የሀገሩ ሊግ ከስምንት ጨዋታ ያላነሰ ያመልጠዋል። ይህ ሁሉ ተስተካካይ ጨዋታ መች ሊደረግ ነው የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ሉሲዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካለፉ እና ጥር ላይ አፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መልሶ ለአንድ ወር ይቋረጣል። ስለዚህ ንግድ ባንክ ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የሊጉን ትክክለኛ መርሐ ግብር ሳይሆን ተስተካካይ ጨዋታ ለማድረግ ብቻ ረጅም ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You