ደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉት ስውሩ ጦርነት

ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያን የሚለየው አጥር የኤሌክትሪክ ገመድ አለው። ይህን አጥር የሚጠብቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችም ተደርድረዋል። በየመሐሉ ቅጠልማ የወታደር ልብስ ቀለም የተቀቡ ግዙፍ የድምፅ ማጉያዎች ተሰቅለዋል። የቢቢሲዋ ጃን ማኬንዚ ባለፈው ወር ወደስፍራው አቅንታ በነበረበት ወቅት አንደኛው ድምፅ ማጉያ የደቡብ ኮሪያ ሙዚቃ ሲለቅ ሰምታለች። ሙዚቃው ቅኔ አዘል ነው። “ወደ ውጭ ስንጓዝ ጉልበት እናገኛለን” ይላል። ሰሜን ኮሪያውያን ከሀገራቸው መውጣት አለመቻላቸውን በሾርኔ ለመንካት የተከፈተ ሙዚቃ ነው።

ከሰሜን ኮሪያ ድምፅ ማጉያም ወታደራዊ ፕሮፖጋንዳ የሚነዛ ሙዚቃ ይሰማል። ምንም እንኳ ደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ ጥይት ባይተኳኮሱም አሁንም ጦርነት ላይ ናቸው። ይህ ጦርነት የመረጃ ጦርነት ነው። ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን መረጃ ታሾልካለች። የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደግሞ ይህ የመረጃ ፍሰት ለመግታት ተግተው ይሠራሉ። ሕዝባቸው ከውጭ የሚመጣ መረጃ እንዲሰማ አይሹም። ሰሜን ኮሪያ ኢንተርኔት ዘልቆ ያልገባባት የዓለማችን ብቸኛዋ ሀገር ናት ማለት ማካበድ አይደለም። ሁሉም የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጣዎች የመንግሥት ናቸው።

“ይህ የሆነበት ምክንያት የኪም ቤተሰብ ታሪክ አፈ-ታሪክ መሆኑ ነው። ለሕዝባቸው የሚናገሩት አብዛኛው ነገር ሐሰት ነው” ይላሉ ማርቲን ዊሊያምስ። ማርቲን መቀመጫውን ዋሺንግተን ያደረገው ስቲምሰን ማዕከል ነባር አባል ናቸው። በሰሜን ኮሪያ ቴክኖሎጂ እና መረጃ ፍሰት ጥናት ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው። ደቡብ ኮሪያ እንዲህ ነው የምታስበው – መንግሥት የሚነዛውን ሐሰት ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ከተቻለ የሰሜን ኮሪያው አገዛዝ ይፈራርሳል።

የድምፅ ማጉያዎቹ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ከሚጠቅምባቸው መሣሪያዎቹ መካከል ናቸው። ጥቂት የሚባሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች በድቅድቅ ጨለማ ወደ ሰሜን ኮሪያ መረጃ ያስተላልፋሉ። ሰሜን ኮሪያውያን ይህን መረጃ መስማት የሚችሉት ከብርሃን እና ከመንግሥት ጆሮ ተደብቀው ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ዩአስቢ እና ማይክሮ ኤስዲ የተባሉ የመረጃ ቋቶች (ፍላሽ ዲስኮች) በድብቅ ወደ ደቡብ ኮሪያ ይገባሉ።

የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ድራማዎች እና የፖፕ ሙዚቃዎች እንዲሁም ዜናዎችን ይዘዋል። ዓላማቸው የሰሜን ኮሪያን ፕሮፖጋንዳ መገዳደር ነው። ነገር ግን በአካባቢው የሚሠሩ ሰዎች ሰሜን ኮሪያ ይህን የመረጃ ጦርነት እያሸነፈች ነው ይላሉ። ኪም የውጭ ሀገር ይዘት ያለባቸው ቋቶችን ይዘው የሚገኙ ዜጎች ላይ ከባድ እርምጃ እየወሰዱ ነው። ሌላኛው ስጋት ለዚህ ጦርነት የሚውል በጀት ጉዳይ ነው። የዚህ ሥራ አብዛኛው ገንዘብ የሚገኘው ከአሜሪካ መንግሥት ነበር። ነገር ግን አሁን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የምትሰጠውን ርዳታ መግታታቸው ሌላ ስጋት ፈጥሯል።

ዩኒፊኬሽን ሚድያ ግሩፕ (ዩኤምጂ) የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ የደቡብ ኮሪያ ተቋም ነው ዜና እና አዝናኝ ፕሮግራሞችን እየጫነ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚልከው። ድርጅቱ ዜናዎች እና የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በጎራ በጎራ ያስቀምጣል። አስጊ የማይባሉ ዩኤስቢዎች ውስጥ የኮሪያ ድራማዎች፣ የፖፕ ሙዚቃዎች እና የኔትፍሊክስ ተከታታይ ድራማ ይጫናል።

በጣም አስጊ በሚባሉ ቋቶች ውስጥ ደግሞ “ትምህርታዊ ፕሮግራሞች” ማለትም ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት የሚሰብኩ ይዘቶች ይካተታሉ። እነዚህ ዩኤስቢዎች በአሽከርካሪዎች ወደ ቻይና ድንበር ይላካሉ። የድርጅቱ ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ዩኤስቢዎቹን ወንዝ ያሻግራሉ።

የኮሪያ ድራማ ጉዳት ያለው ባይመስልም የደቡብ ሰው እንዴት በነፃነት እንደሚኖር ያሳያሉ። ግዙፍ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፈጣን መኪና ሲያሽከርክሩ እና ከትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምግብ ሲሸምቱ ይታያሉ። ይህ በሰሜን ኮሪያ የሚታሰብ አይደለም። ኪም የደቡቡ ሰው እጅግ ደሃ እና በጭቆና የሚኖር ነው ብለው ለሕዝባቸው ለሚነዙት ፕሮፖጋንዳ ይህ ትልቅ አደጋ ነው።

“አንዳንድ ሰዎች ድራማዎቹን ሲያዩ እንዳለቀሱ ይነግሩናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሕልም እንዳላቸው እንዳወቁም ያስረዱናል” ይላሉ የዩኤምጂ ዳይሬክተር ሊ ክዋንግ-ባክ። ምን ያክል ሰዎች የኮሪያ ድራማ እና ዜና እየኮመኮሙ እንደሆነ መረጃው ባይኖርም በቅርቡ የተሰሙ ምስክርነቶች መረጃዎቹ በሰፊው እየተሠራጩ እንደሆነ ያሳያሉ።

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም። አገዛዙን በግልፅ የሚቃወም ሰውም የለም። ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት የሚታሰብ አይደለም። ዳይሬክተሩ በመረጃዎቹ መሠራጨት ምክንያት ሰሜን ኮሪያውያን ትግል ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አላቸው ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You