ያልጸደቅንባቸው የኩነኔ አፋፎች

ገራችን ጦርነትን እንደባሕላዊ ውርስ እየተቀባበለች ዛሬ ላይ ደርሰናል:: ያለፍንባቸው የፖለቲካ ሰርጦች ጦርነት ጠማቂ በመሆን ያሻገሩን መስለው ሲጥሉን አይተናል:: አወዳደቃችንም ቢሆን ለማንም ያልበጀና የማይበጅ ነው:: ሀውልቶቻችን ላይ ከተጻፉ የጀግንነት መፈክሮች በላጩ ገሎ በመሞት የተሰጡን ስሞች ናቸው:: ከመጠሪያዎቻችን ጎን ያሉ የክብር ተቀጽላዎቻችን በወንድሜ ላይ በጨከንኩት ልክ ለሽ ጭካኔ የተቸሩኝ ናቸው:: እናስ በማንጸድቅበት የኩነኔ አፋፍ ላይ አይደለን?

በሀሳብ እና በብስለት መፎካከር አቅቶን በምንስላቸው ገዳይ ካራዎቻችን ፉክክር ጀምረናል:: የሀገር የሉአላዊነት ክብር በእርስበርስ የፉክክር ኢላማ ውስጥ ገብቶ ለማንም በማይበጅ የትርክት አረንቋ ስር ወድቀናል:: ፈትለን የሸመናቸው የጋራ ድሮቻችን ጋቢ መሆን ተስኗቸው በነጠላነት ሲረግፉ ተመልክተናል:: እናስ በማያጸድቅ የኩነኔ አፋፍ ላይ አልቆምንም?

ለየትኛውም ትውልድ ጦርነት ውርስ ሊሆን አይችልም:: ጦርነትን ውርሳቸው ያደረጉ ሀገራት ዛሬ ላይ ከመጠሪያ ስሞቻቸው መሀል ድህነት እና ኋላ ቀርነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ:: በዓለም ታሪክ ከታላላቅ በጎ ውርሶች መሀል አንዱ ሰላም እና ሰላም የሰፈነበት ሀገረ ግዛት ነው:: ውርሱን ጦርነት ያደረገ ትውልድ በመከራ ውስጥ ካልሆነ ሰላምን በንግግር መፍታት አይቻለውም:: ለሰላም ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርገን የመኖራችንም እውነታ ከዚህ የዘለለ ትርጉም አያገኝም::

ከኩነኔ ባለፈ ያልጸደቅንባቸው የጥላቻ ውርሶች ብዙ ናቸው:: በጥላቻ ተጠምቀው የተወለዱ ለራስም ሆነ ለሌላው የምርግ ያህል የከበዱ መከራዎች ጥቂቶች አይደሉም:: ሕይወት እየገበሩ በጀግንነት መጠራት፣ ሀገር እያፈረሱ በአንቱታ መጀገን ከከባድ የመከራ ምርጎቻችን መሀል ጥቂቶቹ ናቸው:: ጫንቃዎቻችን አልችል ያሏቸው፣ ትከሻዎቻችን አልበቃ ባሏቸው የግፍ ውርሶች ስር በሰው መሆን መጠራት ለኔ አሳፋሪ ነው::

በዘመናት ውስጥ በተፈጸሙ የእርስ በርስ ጦርነቶች ከትውልዱ ተርፈው ለትውልድ የተቀመጡ ብዙ ግፎች አሉ:: ሁሉን ትተን ለሁለት ዓመታት በቆየው የሰሜኑ ጦርነት የነበረውን ብናስታውስ የጦርነትን አስከፊነት ከመረዳት አልፈን ምን ሆነን ነው? እንድንል የምንገደድበት ነው:: ጦርነት እየሞቱ መግደል ብቻ እንዳይደለ በጦርነት ስም በተፈጸሙ ስርቆቶች፣ በተፈጸሙ የሀገር ክህደቶች፣ በተፈጸሙ ዘረፋዎች እና መሰል ድርጊቶች መረዳት ችለናል::

የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት ቃለመጠይቅ ከጦርነት ጀርባ ስለነበሩ በርካታ ገመናዎች መስማት ችለናል:: በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በሀገር እና ሕዝብ ላይ ስለተፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች እስከ ዓላማ የለሽ ውጊያ ድረስ የነበረውን አንስተዋል::

ወጣቶችን ለእገታ፣ ለወንጀል፣ ለጥላቻ፣ ለሕገወጥ ስደት፣ ለዝርፊያ እንዲሁም ለመሰል ሕገወጥ ድርጊቶች የሚጠቀሙ አመራሮች እንደነበሩ ተገልጸው የሀገር ሀብት የሆነን ባንክ በመዝረፍ ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው ከማዋል እስከማሸሽ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ፤ በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ አመራሮች በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት መዘረፋቸው ሳይበቃ የጥላቻ ትርክት በመፍጠር ተጠያቂነት እንዳይኖር እንደሚሠሩ ተነስቷል::

ዋጋ የከፈልንባቸው እነዛ የእርስ በርስ ጦርነቶች እንደተባለው ለነጻነት እና ለሰላም ሳይሆን ለጥቂቶች ዓላማ ማስፈጸሚያነት እንደሆነ በገሀድ ሰምተናል:: ለዓላማ የለሽ ጦርነት ያን ሁሉ ዋጋ መክፈላችን በእርግጥም የሚያስቆጭ ነገር ነው:: በሕዝብ ስም ግለሰቦች ነግደው ያተረፉበት ጦርነት እንደነበር ሰምተናል::

ማን ይናገረ የነበረ እንዲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በአይናቸው ያዩትን እና ከብዙዎቻችን የተሸሸገውን ከመጋረጃ ጀርባ ስለተደበቀው ሚስጢር ሲናገሩ አንድም ጦርነት አክሳሪ መሆኑን እየነገሩን ነው በሌላ መንገድ ደግሞ በሕዝብ ሽፋን ወንበዴ እና ዘራፊዎች በሀገር እና ሕዝብ ላይ ቁማር እየቆመሩ እንደሆነ እያጋለጡ ነው:: አብዛኞቹ በሕዝብ ስም የሚጀመሩ ጦርነቶች ዓላማቸው ሀገር እና ሕዝብ እንዳይደለ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም የሰሜኑ ጦርነት ግን በዚህ ልክ ለውንብድና የተመቸ እንደነበር የገመተ አልነበረም::

ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጥላቻ ትርክቶች ጦርነትን ማሸነፊያ መርሆች ይመስሉ በሁሉም አመራር ነን ተብዬዎች ዘንድ ሲተገበሩ ነበር:: በጦርነት ስም በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚደረጉ ክህደቶች ዋጋ በማስከፈል የሚደርስባቸው የሉም:: ሁሉም ጦርነት እዳ አለው:: ዛሬ ላይ የትላንት የጦርነት እዳዎቻችንን እየከፈልን ነው:: ከመንግሥት ካዝና የተዘረፉ ገንዘቦች በኑሮ ውድነቱ ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: የተፈናቀሉ እና የተደፈሩ ሴቶች ባልፈቀዱት ሕይወት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል:: እኚህን እና እኚህን መሳይ ነውረኛ ድርጊቶች ዳፋቸው በሀገር ላይ በመሆኑ የሚያስከፍሉት ዋጋ የበዛ ነው::

ከሰማነው እና እየሰማነው ካለው በመነሳት ጦርነት ለጥቂቶች ትርፍ ብዙዎች የሚከስሩበት እንደሆነ መረዳት እንችላለን:: በሀገራችን ያሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች በዚህ መሰሉ ድርጊት ውስጥ ለማለፋቸው የሰሜኑ ጦርነት ምስክር መሆን የሚችል ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ሕዝብ ነው:: የሚታወቀውም የሰላም ዜማን ሲያዜም ነው:: ነገር ግን በጥቂቶች ቂም ብዙሀኑ ቆስሏል:: በጥቂቶች ሴራ እልፎች ተንሸራተዋል:: እያየነው እንዳለው ጦርነት የውርደት፣ የጉድለት እና የክብረነክ ወጀብ ነው:: በወጀቡ ብዙ ነገራችን ተወስዷል:: እጆቻችን ከቃታ ተላቀው የሰላም ጡብ እንዲገነቡ ማስቻል ሰላማችንን ከምናስመልስበት መንገድ አንዱ ነው::

በእስካሁን ጉዟችን የሌሎችን ወስደናል የእኛም ተወስዶብናል:: ትርፋችንን ካየነው ግን ምንም ነው:: ምንም ትርፍ ለሌለው ነገር እንደመድከም የሰው ልጅ አለማወቅ አልተሰጠውም:: ብስለት የሚለው የልህቀት ስያሜ ‹ሰው ለሚጠቅመው ከሚጠቅመው ጋር በማበር› የሚገለጽ ነው:: የራስን ከማጣት ባለፈ ምንም ትርፍ ለሌለው ነገር የምናደርገው ትግል ባለማወቅ ካልሆነ በምንም አያስጠራንም:: ተከባብረን እና ተቻችለን ሳንነካ እና ሳናስነካ የምንኖርበት የአብሮነት ዘመን ለምን እንደራቀን ለሁልጊዜ እጠይቃለው::

አንድ ነገር እስካልገባን ድረስ ከመከራው ማምለጥ አንችልም:: እየጎዱን ያሉት ነገሮች ያልገቡን አሊያም ጠልቀን ያላወቅናቸው ናቸው:: ዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ስለጦርነት አስከፊነት እንዲጽፍ እና እንዲናገር እድል ቢሰጠው እንደእኛ ጥሩ የሚጽፍ እና እውነት የሚናገር አይኖርም:: ለዘመናት ኖረንባታል አሁንም እየኖርንበት ነው:: ግን አሁንም እየተገረፍን ነው:: አሁንም እንዳላዋቂ ከድጡ ወደማጡ እየገባን ነው::

ጦርነትን ብዙ ስም ብንሰጠው ልክ የምንሆነው በኪሳራው ብቻ ነው:: ትርጉሙ ኪሳራ እና ኪሳራ በሆነ ትንቅንቅ መሀል ውድ ነገራችንን አጥተናል:: በጦርነት የምትኮስስ ሀገር ካልሆነች የምትፈጠር ሀገር የለችም:: ጦርነትን አንድ መልካም ስም ብንሰጠው በሀገር ስም ለሉአላዊነት መሞት አሊያም በሉአላዊነት ስም ለሀገር መሞት ይገልጸዋል:: የእኛ ሀገር የጦርነት ትንቅንቅ ግን ከዚህ የተለየ ትርጉም ያለው ሆኖ የሚነሳ ነው::

ካለፈው የተቀበልነው ለመጪው ልንሰጠው ያዘጋጀንው ውርስ ምንድነው? ስፍራው በወርቅ እንዳጌጠ እንደከበረ ሉል እንቁዎቻችንን በፍቅር እና በአብሮነት ለብጠን የጋራ ሰርጥ ካላበጀን ውርሳችን ሞት ነው የሚሆነው:: ላልጸደቅንባቸው እና ለማንጸድቅባቸው የኩነኔ አፋፎች ሕይወት ማዋጣታችንን ትተን በይበቃል ካልታደስን ወርቆቻችን ትርጉም የለሽ ናቸው::

ማን ምን አይነት አዚም እንዳደረጉብን ሳናውቅ ትርፍ ለሌለው ርስት ሀገራችንን እንገብራለን፣ ዋይ ዋይ እንላለን:: ለማይበልጠው የሚበልጠውን እናጣለን:: ለማይጠቅመን የሚጠቅመንን እንገብራለን:: ሁሉ ነገር ቀርቶብን፣ ያወቅነው እና የገባን ተሽሮ ስለጦርነት ብቻ አንድ የጋራ እውነት ቢኖረን እላለው:: ዘመናችንን በእውነት የሚለውጠን ባገኝ እላለው::

ስለሆነው እና ስለሚሆነው ሳስብ ትርፍ የለሽ በሆነ የስቃይ ስፍራ ላይ በነፍሳችን የተወራረድን ይመስለኛል:: ዘሩን ጭንጫ ላይ ዘርቶ ሀገር ለማብቀል የምንሞክር እኮ ነን:: በበርሀ ላይ ተንጠባጥበን ሀገር እና ሕዝብ ለመሆን የምንጓጓ ነን:: እና አናሳዝንም?

በብዙሀን ስም በተጫረ እሳት ጥቂቶች እየሞቁ፣ ለግል ጥቅም በተዋጀ አዋጅ ወጣቱን ለሞት አሰልፎ የራስን ከርስ መሙላት እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ ከመንግሥት በተዘረፈ የሀገር ሀብት የራስን ስም መገንባት ያለፉና ያሉ የጦርነት መልኮቻችን ከሆኑ ሰነባብተዋል:: የምንዋጋው እና እየተዋጋን ያለነው ለእንዲህ አይነቱ ብዙዎች ለሌሉበት ለጥቂቶች ድግስ ነው::

በሰሜኑ ጦርነት በሕዝብ ስም ጥቂቶች እንደዘረፉ፣ እንደጠገቡ፣ እንደተደላደሉ ሰምተናል:: ከድሀ እናት ጉያ በተወሰደ የወጣት ደም ብዙዎች ያለቀሱበት የማይረባ ታሪክ ተፅፏል:: መነሻ እንጂ መድረሻ በሌላቸው የእልህ አጀቦች ምኩራቦቻችንን ደርምሰን ወጀብ አልፋ ሆነናል:: ያልተሸፈኑ ሽንቁር ገላዎች ለብርድና ሀሩር እንደሚጋለጡ ሁሉ በጦርነት የሳሱ ልቦቻችንም እንዲሁ ናቸው::

ጉድ እስኪወጣ ድረስ ድብቅ ነው:: የሞትንላቸው እና የተጎሳቆልንላቸው ታሪኮቻችን ከኋላ ብዙ ጉድ የደበቁ ሆነው እየተሰሙ ነው:: በምንም አይነት ጉዳይ ላይ ይነሳ ጦርነት ውብ መልክ የለውም:: በዚህ ዘመን ላይ በታላቅ ማንነት የሚጠሩ ካሉ ሰላማቸውን ያላስነኩ ግለሰቦች፣ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም ሀገርና ሕዝቦች ናቸው::

እየሰማናቸው ያሉ ጦርነት ወለድ ድራማዎች ኢላማቸው ሀገርና ሕዝብ ነው:: የሚዘረፈው ከሀገር ነው:: የሚሰረቀው ከሕዝብ ነው:: የምትደፈረዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት:: የሚሰደደው ወጣቱ ነው:: የሚሞተው እና እየሞተ ያለው ሕዝብ ነው:: የምትዋረደው ሀገር ናት:: ተስፋ የሚያጣው ትውልዱ ነው:: እንዴትም እንነሳ ማብቂያችን ሀገር ናት:: የሀገርን እዬዬ ያላስቀረ ትግል፣ የሕዝብን እንባ የማያብስ ጦርነት በኪሳራ ካልሆነ በምንም ቢገለጽ ትክክል የማይሆን ነው::

ጦርነት ላይ የፈሰሰው የወጣቱ ሀይል በሀገር ግንባታ ላይ ውሎ ቢሆን፣ ለጦርነት የፈሰሰው ገንዘብ ለኢንዱስትሪ ልማት ውሎ ቢሆን፣ የፈራረሱ የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች ተጠብቀው ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገሮች ቀላል መሆን ይችሉ ነበር:: በተወሳሰበች ሀገር ላይ የተወሳሰበ የፖለቲካ ርምጃ ጦርነትን ካልሆነ ሰላምን የመፍጠር አቅም አይኖረውም:: ሀገር ለመፍጠር ብሄርተኝነት ሳይሆን ብሄራዊነት ነው የሚያስፈልገን:: ድሎቻችንን ከጎጥ ጉያ አውጥተን ሀገራዊ እስካላደረግን ድረስ ብናረግዝ ጦርነትን ብንወልድ ዘረኝነትን ነው::

ጦርነት ሀገርን ለጠላት መስጠት ነው:: ግርግር ለዘራፊ ይመቻል እንዲሉ ስንጣላ፣ እርስ በርስ ስንበላላ ጨዋ መሳዮች ሕልውናችንን እንዲነኩ እድል እየሰጠን ነው:: ሀገር በደም አትጸናም:: ያለምንም ደም ሀገር የምትቀድምበት የእርስ በርስ የተግባቦት ጉባኤ አስፈላጊ ነው:: ለጥቂቶች ድል ብዙሀኑ የሚዋረድበትን የጦርነት ውርስ ትተን ስለብዙሀኑ ጥቂቶችን ማሳፈር አለብን::

ያልጸደቅንባቸው የኩነኔ አፋፎች በነውረኝነት ከማስጠራት ባለፈ ኋላ አቁመውናል:: የጸሀይ መውጫ ምስራቆቻችንን ከልለን በምዕራፍ አፋፍ ስር መቆም ለጨለማ ካልሆነ ለንጋት ተስፋ የለውም:: ተስፋዎቻችን በጦርነት ቀጭጨዋል:: ራዕዮቻችን በደም ፖለቲካ ቀንጭረዋል:: ድሎቻችን ከጦርነት ወለድ ወደ ሰላም ወለድ እስካልተሸጋገሩ ድረስ ከእልቂት ውርስ አንወጣም::

የሰላም ስፍራዋ ሀገር፣ ማህጸንተ ለምለም ምድር ስለሰው ልጅ ክብር እና ዋጋ ጥንተ ስሟ እንዲመለስ ስለጥላቻ መቧደናችን ይቁም:: ስሟ ኢትዮጵያ የሚባል ጥንተ ጠዋት ከሰው ቀድማ በጎህ የነቃች አድባር በወንድማማቾች ደም መጨቅየት የለባትም:: ሰማይን ያሰረ የሕብረቀለም አርማዋ አስታራቂ ሆኖ በልባችን እንዲሰመር ለዘወትር እጸልያለው::

በአትሮኖስ ወርቅ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You