የምርት ውድድርና የግብዓት ልዩነትን በአሸናፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ግብግብ የሚስተዋልበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ዓይነቱን የፉክክር ዕርምጃ በማፋጠን ከፍተኛውን ድርሻ ለመወጣት ደግሞ የማስታወቂያዎች ጉልበት ኃያል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
አሁን በቆምንበት ዘመን የማስታወቂያዎች ኃይልና ጥበብ የገበያውን ዓለም እየተቆጣጠሩት ይገኛል፡፡ ምርቶችን ከሌሎች ተመሳሳይ ግብዓቶች ጋር በልዩነት ለማሳየት ማስታወቂያዎች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በተለያዩ ጊዜያት የሚታዩና የሚነበቡ ማስታወቂያዎች የንግድ ፉክክሩን በማፋጠን ፣ምርቶች እንዲሸጡ፣ እንዲተዋወቁና ልዩነትን እንዲፈጥሩ ያደርጋሉ።
አንዳንዴ ስምና የማስታወቂያው ይዘት በእኩል የማይራመዱበት፣ አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ በማስታወቂያ ጥበብ ተማርከው ምርቱን የተጠቀሙ ብዙዎችም በእንዲህ ዓይነቱ ሂደት ቅሬታቸውን ሲያሰሙም ይደመጣል፡፡
በርካቶች እንደሚሉት ‹‹ለጥሩ ዕቃ ማስታወቂያ አያስፈልገውም›› ይህ ተደጋጋሚ አባባል የተለመደ ይሁን እንጂ በማስታወቂያ ጥበብና አቀራረብ የሚማረኩ ብዙሃን በሚያዩትና በሚሰሙት እውነት መማረካቸውን መደበቅ አይቻላቸውም፡፡ ይህም አይቀሬ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡
በማስታወቂያ ታጅቦ ለተጠቃሚዎች የሚተዋወቅ የምርት ዓይነት ገበያውን ለመቆጣጠር የሚኖረው ጉልበት ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም የአቀራረብ ስልቱ ለየት ያለና ከህሊና የማይጠፋ ከሆነ የበርካቶችን ልብ ለመግዛት የሚቻለው በከፍተኛ ፍጥነት ይሆናል፡፡
ማስታወቂያ ጽዕኖ ፈጣሪ፣ ማራኪና አይረሴ ከሆነ ብዘዎች ያተኩሩበታል፡፡ የሚተዋወቀው የምርት ዓይነት በተባለለት ልክ ከሆነ ደግሞ ገበያውን ለመቆጣጠር፣ ገበያተኞችን ለማብዛት የሚኖረውን ድርሻ ያልቀዋል። አንዳንዴ የማስታወቂያው ግነትና የምርቱ ዓይነት የማይመጣጠንበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ብዘዎች ለማስታወቂያው ንግርት የሚኖራቸው አመኔታ ከጥርጣሬ ይገባል፡፡
የሚቀርቡት ይዘቶች በተለይም ሜካፖች፣ ምግቦችና መሰል ምርቶች ከሆኑና በሰዎች ውጫዊና ውሰጣዊ ጤንነት ላይ ተጽዕኖ ካሳደሩ ተጠያቂነቱ በህግ አግባብ ጭምር የሚፈታ ይሆናል፡፡
በሀገራችን የማስታወቂያ ገበያውን የተቆጣጠሩ ተመሳሳይ ምርቶች በተለያዩ የአቀራረብ ስልቶች ለተጠቃሚዎች ሲደርሱ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሕፃናትና የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያዎች፣ የሳሙናና መሰል ምርቶች፣ የሜካፕና መሰል መዋቢያዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ተቀራራቢ ምርቶች በተለያዩ አማራጮችና የአቀራረብ ጥበቦች እየቀረቡ ይገኛል፡፡
በየጊዜው ይህን መሰሉን የማስታወቂያ ፍሰት ከሚያስተውሉ ተመልካቾች መካከልም ጥያቄዎች አሉን የሚሉ አንባብያን ለዝግጅት ክፍላችን ሃሳባቸውን አድርሰዋል፡፡ ጠያቂዎቻችን ምላሽ የሚሹት በሕፃናት ምግቦችና በየጊዜው በሚቀርቡ የማስታወቂያ ይዘቶች ዙሪያ ነው፡፡ ጠያቂዎቹ እንዲመለስላቸው የሚሹትም የሕፃናት ምግቦችና የማስታወቂያ ይዘቶች እሰከምን መጓዝ እንደሚኖርባቸው ነው፡፡
አንባብያን ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የሰጡን አቶ ሙሉጌታ ፍቅሬ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ አስመጪና አከፋፋይ ኢንስፒክሽን ቡድን መሪ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ አገላለጽ ማንኛውም ምግብ የሆነ ማስታወቂያ ሲተዋወቅ በባለስልጣኑ ደንብና መመሪያ መሰረት ነው፡፡
ማንኛውም የማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅትም ይሁን ግለሰብ በባለስልጣኑ የተቀመጡትን ደንብና መመሪያዎች የማክበር ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ እንደ ቡድን መሪው አባባልም የማስታወቂያው ይዘት በተለይም የሕፃናት ምግብን የሚመለከት ከሆነ የሚመለከተው የባለስልጣኑ ክፍል በተለየ አትኩሮት የሚከታተለው ይሆናል፡፡
አቶ ሙሉጌታ እንደሚያረጋግጡት በተቀመጠው ህግ መሰረት የጨቅላ ሕፃናትን ምግቦች ማስተዋወቅ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ ከዜሮ እስከ ስድስት ወራት ዕድሜ ለሚገኙ ጨቅላ ሕፃናት ይገባቸዋል የሚባል ምግብን ማስተዋቀወቅ የማይቻልባቸው መነሻዎችም ይታወቃሉ፡፡
አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት ለዚህ የሚጠቀሰው ዋንኛ ምክንያት ከምንም በላይ ለሕፃናቱ የሚጠቅመው የእናት ጡት ወተት የመሆኑ አውነት ነው፡፡ አብዛኞቹ እንደሚያምኑበትም ተገቢውና አስፈላጊው ጉዳይ የእናት ጡት ወተትን ጠቀሜታ ማስተዋወቁ ይሆናል፡፡
እናቶች ልጆቻቸው ስድስትወራት እስኪሞላቸው በተገቢው ሁኔታ ጡት ማጥባት ይኖርባቸዋል፡፡ ያለምንም ተጨማሪ ምግቦች ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት ያለባቸው እናቶች አሳማኝ የሚባልና በሀኪም የተከለከለ በሽታ እስከሌላቸው ድረሰ ሂደቱን ተግባራዊ ሊያደርጉት ግድ ይላል፡፡
ይህ ዓይነቱ ተፈጥሯዊ ጠቀሜታ በተቸረበት የጨቅላ ሕፃናትን ምግብ በማስታወቂያ ማስነገሩ እንደማይመከር የሚጠቅሱት ቡድን መሪው ይህም በህግ አግባብ የተከለከለ ስለመሆኑ የባለስልጣኑን አሠራር ዋቢ አድርገው ይናገራሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሀገራችን በተለያዩ የማስታወቂያ ማስነገሪያዎች የሚስተዋሉ የሕፃናት ምግቦችና ወተቶችን አስመልክቶ አንባብያን ስላነሱት ጥያቄ አቶ ሙሉጌታ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት የጨቅለ ሕፃናትን ምግቦች አስመልክቶ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የሚሰራጩ የማስታወቂያ ይዘቶች በህግ አግባብ ተቀባይነት የላቸውም። ከጨቅላ ሕፃናት ምግቦች ባለፈ የሌሎች ሕፃናት ምግቦችም ቢሆን በባለስልጣኑ ከተቀመጡ የአሠራር መመሪያዎች ውጪ በማስታወቂያ መነገር አይኖርባቸውም፡፡
አቶ ሙሉጌታ ከጨቅላ ሕፃናት ምግቦች ውጪ የሚገኙ የምግብ ይዘቶቹ በማስታወቂያ ሲነገሩ የተጋነኑ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደማይገባቸውም ይናገራሉ። ምግብን ልክ እንደ መድሀኒት አድርጎ ማስተዋወቁ ትርጉሙን እንደሚያዛባው የሚጠቁሙት ቡድን መሪው መልዕክቶቹ ሲተላለፉ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ጭምር ያሳስባሉ፡፡
ህጉን ጥሰው በሚገኙ አካላት ላይ የሚወሰዱ ህጋዊ ዕርምጃዎች ስለመኖራቸው የሚገልጹት አቶ ሙሉጌታ በቅድሚያ በባለስልጣኑ የተሰጠ ፈቃድ ያለቸውን በአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች በመጠየቅ ከማስጠንቀቂያ እስከ ፈቃድ ስረዛ የሚያደርስ ቅጣት ተፈጻሚ እንደሚደረግ ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ መልኩም ጉዳዩን በህግ ለማየት በባለስልጣኑ የህግ ክፍል በኩል አግባብ በሚባል መልኩ እንደሚዳኝ የሚናገሩት ቡድን መሪው ማንኛውም የምግብ ማስታወቂያዎችን አስነጋሪ ድርጅት ምርቱን ከማስተዋወቁ በፊት በባለስልጣኑ መስሪያቤት በዘርፉ የተቀመጡ መመሪያዎችን ማወቅና መጠየቅ ግድ እንደሚለው ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013