በህዝብ አመጽ ተገፍቶ በመማጸኛ ከተማው መቐሌ የመሸገው የዛሬው አሸባሪ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ ሆኖ ሀገራችንን ለማፍረስና ለመበተን እንደ ልማዱ ተልዕኮ ተቀብሎ በሰብዓዊ ማዕበል ህጻናትን በሀሺሽ እያሳበደ ነፍሰ ጡር ሴቶችን አረጋውያንን አካል ጉዳተኞችን መነኮሳትንና የሀይማኖት አባቶችን በመማገድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን ያለ የሌለ ኃይሉን በዋግ ኽምራ በአበር ገሌ በወሎ በራያ በጎንደር በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም በአፋር ክልል ትንኮሳና ጦርነት የከፈተ ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው ክህደትና ጭፍጨፋ የፈጸመ ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ያለ ፤ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን እንዲወሩ ተንበርክኮ የሚማጸን ፤ የአሜሪካንንና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ጫና የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚለማመን፤ ሀገርን በሀሰተኛ መረጃ የሚያጠለሽ ፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ የባሕር በር አልባ ያደረገ ፤ ከዛድባሬ ወራሪ ጎን የተሰለፈ ፤ ሀገርን ለ27 ዓመታት በመዝረፍ እርቃን ያስቀረ ፤ ኢትዮጵያን አምርሮ የሚጠላ አረም ነው፡፡
የዚህ አሸባሪ ቡድን ጸያፍ ታሪኮች ብዙ ናቸው። ሀዲው የዛሬ ዓመት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተሽጧል እያለ ሲያናፋ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሊት ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል ። ሁለተኛው የውሃ ሙሊት ደግሞ ባለፈው ሀምሌ 12 ቀን 2013 ዓም 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ ተጠናቋል። ሟርተኛውና አሸባሪው ህወሓት ተሽጧል ያለው ይህ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ሁለት ሶስት ወራት በሁለቱ ተርባይኖች ብቻ 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል። የግድቡ ግንባታና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል ።
በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሰራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ለኢትዮጵያውያን እራትና መብራት ሊሆን ጫፍ ደርሷል ። የግብጽን የሱዳንን የአሜሪካና የምዕራባውያንን የአረብ ሊግን አለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናን በጥበብና በማስተዋል በመቋቋም እና ግብጽ የግድቡን ጉዳይ የዓለም የደህንነትና የሰላም ስጋት አድርጋ ለማሳየት መጀመሪያ ራሷ በኋላ በአረብ ሊግ አይዞሽ ባይነት ቱኒዚያን በመጠቀም ጉዳዩን ከአፍሪካ ሕብረት በማውጣት ወደ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳነት ለማሳደግ ያደረገችው ጥረት ሀገራችን በጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ዲስፕሊንና በጥበብ በተመራ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሀገራትን ከጎኗ በማሰለፍ የተደገሰላት ደባ እንዲከሽፍ ከማድረጓ ባሻገር የግድቡ ጉዳይ የተፋሰሱ ሀገራትና የአፍሪካ ሕብረት እንጂ የመንግስታቱ ድርጅት አለመሆኑን ማረጋገጥ ችላለች።
ድርድሩም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመልሷል። ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈው የነበሩ ምዕራባውያን እርማቸውን እንዲያወጡ አድርጋለች። ሆኖም ዛሬም ሆነ ጥንት ግብጽ አልተኛችልንም። አባይን ከመነሻው ለመቆጣጠር ከ11 ጊዜ በላይ ልትወረን ልታስገብረንና ቅኝ ልትገዛን ሞክራ እንዳልተሳካላት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። በዲፕሎማሲው መድረክ ብትረታም በሱዳን አማካኝነት የውክልና ጦርነት ከፍታ መሬታችንን አስወርራለች ። ሀገርን ለከዱ ጡት ነካሾች የገንዘብ የጦር መሳሪያ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ለየለት ቀውስና ትርምስ ለመክተት ቀን ከሌት እየሰራች ነው ። ይህን የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያንም በአንድነት ሀገራቸውን ከውስጥ ተላላኪዎችና ከውጭ ጥቃት ለመከላከል ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት ተነስተዋል። ሕዝቡም የሀገሩን ሕልውና ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ ስንቅ በማዘጋጀት ገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
ግድቡ በአሁኑ ሰዓት ከ18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውሃ በመያዝ ራሱን መከላከል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ግብጽ ለዘመናት ኢትዮጵያ ሰላም ሆና አንድነቷ የሚጠናከርና ልማቷም የሚፋጠን ከሆነ አባይን ጨምሮ ገና የውሃ ሀብቷን ታለማለች በሚል በስጋት ላይ ያነጣጠረ ስጋት ከውስጥ ተላላኪዎቿ ጋር በመሆን ኤርትራን አስገንጥላለች ። በወንዝ በጎጥ የተከፋፈለች ደካማ ሀገር እንድትሆን ሌት ተቀን ሰርታለች። በተወሰነ ደረጃም ተሳክቶላታል። ዛሬም አሸባሪውን ህወሓት ሸኔንና ሌሎች ቅጥረኛ ምንደኞችን ተጠቅማ ከውስጥ እየወጋችን ነው። ሆኖም የግብጽና የተላላኪዎቿ የቀን ቅዠት በጀግኖች ልጆቿ ይመክናል። እየመከነም ይገኛል።
አይደለም ዛሬ ሁለተኛ ግድባችንን ሞልተንና ያለአንዳች ኮሽታ ብሔራዊ ምርጫ አካሂደንና በሚያስገርም ሁኔታ በአንድነት በቆምንበት፤ ከአንድ ዓመት በፊት በሴራ ፖለቲካ ፣ በተላላኪውና በባንዳው የትህነግ ገዢ ቡድንና ተባባሪዎች ደባ በእየለቱ ቅርጹንና ይዘቱ እየቀያየረ በሚቀፈቀፍ ቀውስ መሀል ሆነን አንደኛውን የውሃ ሙሊት አካሂደናል። ከዚህ በኋላ የሚቀሩን ሙሊቶችም ያለ ምንም ስጋት ይከናወናሉ። በዚህም ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ በብልፅግና ለመድገም መስፈንጠሪያ ሰሌዳ (ስፕሪንግ ቦርድ ) በመሆን በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ ( ፍላግ ሺፕ )ፕሮጀክት ባለቤት መሆን ተችሏል፡፡ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ እንዳሉት በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልምና ፡፡ ስንዴ እየለመኑ ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች ፤ በነጻነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ብሎ መመጻደቅን ሙሉ አያደርገውምና ፡፡
መቼም አሸባሪው ትህነግ ለዘረፋና ለስልጣን ሲል የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠትና በሌብነት ጥርሱን የነቀለበት ስለሆነ እሱ እንደሚያደርገው ግድቦ ተሽጧል ቢል የሚያስገርም አይደለም። እሱ ሽጦት ስለነበረ አይደል ለአጠቃላይ ክሽፈት አንድ ሐሙስ ቀርቶት እያለ የለውጥ ኃይሉ ደርሶ የታደገው። በርሀብ ለተጎዱ ትግራዋይ ተልኮ እንደነበረው ስንዴ ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ሽጦት የነበረውስ እሱ ራሱ ህወሓት ነው። እንጨት ሽጣ ከልጆቿ ጉሮሮ ቀምታ መቀነቷን ፈታ የሰጠችውን ገንዘብ ከመስረቅ በላይ ግድቡን መሸጥ ምን አለ። ተራ የመጠጥ ውሃ ኤሌክትሮ ሜካኒካል እንኳ በቅጡ ገጥሞ ለማያውቅ በብልሹ አሰራርና በሙስና ለተዘፈቀ ተቋም ያለ ጨረታ ከመስጠት በላይ ግድቡን ከመሸጥ በላይ ምን አለ። ያው ሁላችን እንደምናውቀው የትህነግ እፉኝት ቡድን ለፖለቲካዊ ጥቅምና ስልጣን ሲል ወላጅ እናቱንም ሆነ ሀገሩን እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ከመሸጥ አይመለስም ፡፡ ለትህነግ ፖለቲካ ማለት ብሔራዊ ጥቅምን አሲዞ መገበያየት፣ የንግድ ውል መፈጣጠም (Transactional ) ነው። በዚህ የልቡና ውቅር ( ማይንድሴት ) ነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተሽጧል የሚለው፡፡ በፈጸመው ግፍና ክህደት በሰራው ስህተት በተናገረው ውሸት ወዘተረፈ ጸጸት የማያውቅና ያልፈጠረበት ሆኖ እንጂ ዛሬ ላይ በጸጸት ጸጉሩን በነጨ። እሱ እቴ ይገረማችሁ ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ ቁልቁለቱን ተያይዞታል ።
ውሎ ሳያድር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ሽጦ በቀጣናው ጅኦፖለቲካዊ ስፍራዋ መናኛ መሆኑን ሲገነዘብና ለአገዛዙም አደጋ መደቀኑን ሲረዳ የፈፀመውን ታሪካዊ ስህተት ለማጣፋትና ለማወራረድ ሀገራችን የአሜሪካና የምዕራባውያን የቀጣናው ዓለም አቀፍ የጸረ ሽብር አጋራ እንድትሆን እጇን የፊጢኝ አስሮ አስረክቧል፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት አምባገነናዊ አገዛዙ በአሜሪካ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በምዕራባውያን ዘንድ ሞገስን ከማግኘት ባሻገር በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ብድርና እርዳታ በመቀላወጥ የአገዛዙን እድሜ ማራዘም ችሏል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በ” አሜሪካ ትቅደም ! “ መሰረት ላይ በመቀረጹ እና ትራምፕ ከዓለም አቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻ ግዕብታዊ ማፈግፈግ በማድረጉ የተነሳ እንዲሁም ፊቱን ወደ አሜሪካ የውስጥ ጉዳይ በማዞሩ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም ሆነ ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም ፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ኃላፊነት መጥቶ ፖለቲካዊ ምህዳሩን ከፈት ከፈት በማድረጉ ፤ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረሙና ከ20 ዓመታት በኋላ እርቅን በማውረዱ ፤ በአረንጓዴ አሻራ ከአስር ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ በሰጠው አመራር ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትርም በሰላም የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው ሀገራችን በዓለም አቀፉ መድረክ እንደገና እንድታንሰራር አስችሏል፡፡ መልሶ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና በተላላኪዎቻቸው ሀሰተኛ መረጃና ሴራ ቢጠለሽም ። ሆኖም ሁለተኛው የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሊት የቀጣናውን ጅኦፖለቲክስ እንደ አዲስ በይኖታል። የግብጽን የውሃ ዲፕሎማሲና ፖለቲካም ከንቱ አድርጎታል ። ለዚህ ነው ዛሬ አሸባሪውን ህወሓት ተጠቅማ ሀገራችንን ለመበቀል ሌት ተቀን እየሰራች ያለችው። ሱዳንን ግፊ የምትለው። ከ40 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ከሳኡዲ አረቢያ መብታቸው ተገፎና ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዶ እንዲወጡ ያሴረችው ።
እንደ መቋጫ
እንደለመደው ሀገርን ለመሸጥ ተስማምቶ በግብጽ የእጅ አዙር የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ፤ በምዕራባውያንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲሁም እንዳሻቸው በሚጠመዝዟቸው ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባዮች ወከባ አፈር ልሶ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት ፤ አንድ ጊዜ ተሽጧል ሌላ ጊዜ ለፖለቲካዊ ጥቅም ተለውጧል እያለ የውሸት መአት ሲነዛበት የኖረው የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከአንድም ሁለት ጊዜ ውሃ በመያዝ ወደ 16 ቢሊዮን ብር ከድሀው ጓዳቸው ያዋጡለትን ዜጎች ልብ በመግዛት ለሌላ ዙር ድጋፍ አነሳስቷቸዋል ። ሀገራችን ላለፉት 30 ዓመታት አጥታው የነበረውን የቀጣናውን ጅኦፖለቲካም መልሳ እንድትረከበው አስችሏል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ !
አሜን ፡፡
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013