በኢትዮጵያ አትሌቲክስና ኦሊምፒክ ታሪክ በየዘመኑ በርካታ ጀግኖች ተፈጥረው በስፖርቱ ዘመን የማይሽራቸው ታሪኮችን አበርክተው አልፈዋል። የኢትዮጵያ ስምና ዝናዋን በዓለም አደባባይ የሚያገነኑ አትሌቶች የሚነጥፉባት አገር አይደለችም። ጀግና አትሌቶች ሲፈጠሩባት ኖረዋል እየተፈጠሩባትም ነው። ወደፊትም እንደሚፈጠሩባት ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ ባለፈው ቅዳሜ በተጀመረው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የቀድሞ ጀግኖች አትሌቶቿን ሳይሆን አዲሱንና ጠንካራውን የኦሊምፒክ ትውልድ ይዛ እንደምትቀርብ አረጋግጣለች። በተለያዩ ርቀቶች አዲስና ጠንካራ የኦሊምፒክ ትውልዷ ለማስተዋወቅ የተሰናዳችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ርቀቶች ካለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች በተሻለ ጠንካራ አትሌቶች ያፈራች ሲሆን የተሻለ ውጤትም እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል። በተለይም ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የረጅም ርቀት ውድድሮች አብዛኞቹ አትሌቶች ላለፉት ዓመታት ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ሳይወጡ በመም ውድድሮች ብቻ ብቃታቸውን ሲያጎለብቱ መቆየታቸው ወደ ዘንድሮው ኦሊምፒክ በትኩስ ጉልበት እንዲያቀኑ ማድረጉ በራሱ ትልቅ እድል ከመሆኑ ባሻገር ስብስቡ ወርቃማ ትውልድ የሚሆንበት አጋጣሚ ጠባብ እንደማይሆን ታምኖበታል። ከነዚህ አዳዲስ የወርቅ ሜዳሊያ ተስፋዎች መካከል በአምስትና አስር ሺ ሜትር አራት አትሌቶች በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በስፖርቱ ተንታኞች በተለየ መልኩ ትኩረት አግኝተዋል።
ሰለሞን ባረጋ-10ሺ ሜትር
አትሌት ሰለሞን ባረጋ እኤአ በ2016 ፖላንድ ባይዳጎሽ ላይ ከሃያ አመት በታች የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር 13:21:21 ሰአት በማስመዝገብ ሲያሸንፍ ነበር የወደፊት ወርቃማ ኦሊምፒያን እንደሚሆን በርካቶች ተስፋ የጣሉበት። ይህም በ2017 የለንደን የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ገና በአስራ ሰባት አመቱ በእድሜም ይሁን በልምድ ከሚበልጡት ታላላቅ አትሌቶች ጋር አገሩን ወክሎ እንዲሳተፍ አድርጎታል። በዚህ ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአመታት በእንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ የተነጠቁትን የአምስት ሺ ሜትር ድል በሙክታር ኢድሪስ አማካኝነት መልሰው በእጃቸው ሲያስገቡ ሰለሞን በቡድን ስራ ትልቁን ሚና በመጫወት አድናቆት ሊቸረው በቅቷል። ውድድሩንም በ13:35:34 ሰአት አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። በተመሳሳይ አመት አልጄሪያ ላይ በአፍሪካ ከሃያ አመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና አምስት ሺ ሜትርን 13:51:43 በሆነ ሰአት በማሸነፍ ለአገሩ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግቧል። በዚሁ አመት ኬንያ ናይሮቢ ላይ በተካሄደው የአለም ከአስራ ስምንት አመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሶስት ሺ ሜትር 7:47:16 ሰአት አስመዝግቦ ወርቅ በማጥለቅ የበለጠ ተስፋ የሚጣልበት አትሌት መሆኑን አስመስክሯል
በ2018 ሰለሞን በእንግሊዝ በርሚንግሃም በተካሄደው የአለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሶስት ሺ ሜትር አገሩን ወክሎ በመሳተፍ 8:15:59 በሆነ ሰአት የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል። ይህም ከእድሜውና ልምዱ አኳያ ከታላላቆቹ ጋር ተፋልሞ ያስመዘገበው እንደመሆኑ ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገ ሌላ አጋጣሚ ነበር። በዚሁ አመት በናይጄሪያ አሳባ በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር 13:52:27 ሰአት በማስመዝገብ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀበት ውድድርም ሳይጠቀስ አይታለፍም። ሰለሞን እድሜው እየጨመረ በአለም አቀፍ ውድድሮችም ያለው ልምድ እየጎለበተ በመጣበት የ2019 ውድድር አመት ዛሬ ላይ በኦሊምፒክ ለታላቅ ድል ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዱ ሊሆን የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል። ይህም በኳታር መዲና ዶሃ በተካሄደው የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር ሙክታር ኢድሪስ ዳግም በርቀቱ በነገሰበት መድረክ ሰለሞን በአስደናቂ ብቃት ርቀቱን 12:59:70 በሆነ ሰአት አጠናቆ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበበት ነው።
በግል ውድድሮች በርካታ ስኬቶችን በአለም አቀፍ መድረኮች ማሳካት የቻለው ሰለሞን 2019 ላይ በኖርዌይ ኦስሎ የሶስት ሺ ሜትር ከቤት ውጪ ውድድር የግሉን ምርጥ ሰአት በ7:32:17 አስመዝግቧል። በተመሳሳይ አመትም በሁለት ማይል ርቀት ዩጂን ላይ የአለም ወጣቶች ምርጥ ሰአት የሆነውን 8:08:69 ማስመዝገብ ችሏል። በ2018 መባቻ ላይም በአምስት ሺ ሜትር የአለም ከሃያ አመት በታች ክብረወሰን የሆነውን 12:43:02 ሰአት ቤልጂየም ብራስልስ ማስመዝገቡ ይታወቃል። 2019 ለዶሃ የአለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባደረጉት የሄንግሎው ማጣሪያ ውድድር ሰለሞን በአስር ሺ ሜትር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ 26:49:46 ሰአት በማስመዝገብ በርቀቱ አገሩን እንዲወክል ቢመረጥም በአለም ቻምፒዮናው በርቀቱ ሳይወዳደር ቀርቷል። ከቤት ውጪ ውድድሮች ላይም ባለፈው የውድድር አመት ፈረንሳይ ሌቪን ላይ በሶስት ሺ ሜትር 7:26:10 የሆነ የራሱን ምርጥ ሰአት እንዳስመዘገበ ይታወቃል። ሰለሞን ገና በአስራ ስድስት አመቱ አምስት ሺ ሜትርን 13:21 በሆነ ሰአት ሮጦ የርቀቱን ከሃያ አመት በታች የአለም ክብረወሰን በእጁ ሲያስገባ የአለምን የአትሌቲክስ ቤተሰብ አስደንግጦ ነበር። ሩጫ ባህሉ ያልሆነው የወጣበት ማህበረሰብም በዚህ ስኬቱ ተነቃነቀ። በርካታ ወጣቶችም አሁን ላይ ሰለሞንን እያዩ ወደ ሩጫው አለም ለመሳብ በቅተዋል።
ዛሬ ላይ በኦሊምፒክ ለታላቅ ስኬት ከታጩ የአለማችን ከዋክብት አትሌቶች አንዱ ለመሆን የቻለው ሰለሞን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቃቱን እያሻሻለ በተለያዩ ርቀቶች በተለይም በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ቁንጮ ከሆኑ አትሌቶች አንዱ ሆኗል። በየጊዜው የአሯሯጥ ስልቱን እየቀየረ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አለም አቀፍ ውድድሮችን ያሸነፈው ሰለሞን እንደ ቀነኒሳ የአጨራረስ ብቃቱን በማሳመር ቀጣዩ ቀነኒሳ እስከመባል ደርሷል። በ2018 የውድድር ዓመት የአምስት ሺ ሜትር አጠቃላይ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ መሆን የቻለው ሰለሞን ባረጋ በርቀቱ ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ክብረወሰንን 12፡ 43፡02 በሆነ ሰዓት ከመጨበጡ ባሻገር እኤአ 2005 ላይ ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ ካስመዘገበው ሰዓት ወዲህ ፈጣን ሰዓት ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል። ይህም በረጅም ርቀት በተለይም በአምስት ሺ ሜትር ኢትዮጵያ ከነ ቀነኒሳ በቀለ ወዲህ ማግኘት ያልቻለችውን ሁነኛ ተተኪ አትሌት በቅርቡ ልታገኝ እንደምትችል ፍንጭ የሰጠ መሆኑን የስፖርቱ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
ለተሰንበት ግደይ-10ሺ ሜትር
ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ለተሰንበት ግደይ ባለፈው የ2019 የዶሃ አለም ቻምፒዮና የአስር ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን በረጅም ርቀት ውድድሮች ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው ባለተሰጥኦ የአለማችን አትሌቶች አንዷ ናት። እኤአ በ2015ና 2017 ከሃያ አመት በታች የአለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮን የሆነችው ለተሰንበት የአለም አትሌቲክስ ውድድሮች በኮቪድ-19 ተቋርጠው ከወራት በፊት ሲጀመሩ የተለየች ኮከብ ሆና ብቅ ብላለች። ኢትዮጵያ ባለፉት ኦሊምፒኮች የ10ሺ ሜትር ድልን በተለያዩ አትሌቶች ያሳካች ቢሆንም የረጅም ርቀት ንግስቷ ጥሩነሽ ዲባባ ከውድድር መራቅና ጀግናዋ አትሌት አልማዝ አያና በወሊድ ምክንያት ለዚህ ኦሊምፒክ ባለመድረሷ የተለመደው ድል ስጋት ላይ ወድቆ ነበር። ከወራት በፊት የተለየና አለምን ያስደነቀ ብቃት ይዛ ብቅ ያለችው ለተሰንበት ኢትዮጵያ በርቀቱ ተተኪ አትሌት እንደማይነጥፍባት ከማሳየቱ ባሻገር በዘንድሮው ኦሊምፒክ ያላትን የወርቅ ተስፋ አለምልሟል። ለተሰንበት በአለም አትሌቲክስ ያላትን ደረጃ ከፍ ባደረገችበት የዘንድሮ ውድድር አመት ለማመን የሚከብዱ ስኬቶችን መጎናፀፏ ቶኪዮ ልታያቸው ከሚችሉ አዳዲስ ወርቃማ ኦሊምፒያን አንዷ ብትሆን አያስገርምም። ባለፈው ታህሳስ በቫሌንሲያ በተካሄደ ውድድር ለአስራ ሁለት አመታት በኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የቆየውን የአለም የአምስት ሺ ሜትር ክብረወሰን በ14:06:62 ማሻሻል የቻለችው ለተሰንበት የኢትዮጵያ የሶስት ሺ ሜትር ክብረወሰን 8:20:27 በሆነ ሰአት በእጇ ይገኛል።
በዘንድሮው የውድድር አመት ለታላቅ ስኬት ከበቁ አትሌቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው የ23 አመቷ ለተሰንበት የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን በ10ሺ ሜትር ማሸነፍ ብትችልም በቶኪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ አዲስ ኮከብ ሆና ብቅ ትላለች ብሎ የገመተ አልነበረም። ሆኖም በሄንግሎው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር የሰራችው ተአምር ያልተጠበቀና ተፎካካሪዎቿን ጭምር ያስደነገጠ ነበር። ለተንሰበት ኔዘርላንድ፤ ሄንግሎ ውስጥ የተካሄደውን ውድድር በ29 ዲቂቃ ከ1.03 ሰከንድ በመግባት የርቀቱን የአለም ክብረወሰን በእጇ አስገብታለች። ለተሰንበት ይህን ክብረወሰን ከማሻሻሏ 48 ሰአት ቀደም ብሎ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት የርቀቱን ክብረወሰን ከአልማዝ አያና እጅ መውሰዷ አይዘነጋም። ለተንሰንበት በዚህ የውድድር አመት የዓለማችን የ5 ሺና 10 ሺ ሜትር ክብረ ወሰን ይዛለች። ሁለቱን ክብረወሰኖች በመያዝም የኖርዌይ አትሌት ከሆነችው ኢንግሪድ ክሪስቲያንሰን በመቀጠል በዓለም ሁለተኛዋ አትሌት ሆናለች። ይህም ታላቅ ስኬት በቶኪዮ የኢትዮጵያ አዳዲስ የወርቅ ተስፋዎች አንዷ እንድትሆን አሳጭቷታል።
ጉዳፍ ፀጋይ- 5ሺ ሜትር
ኢትዮጵያውያን በሚጓጉለትና በሚጠብቁት 5 ሺ ሜትርም ጥሩነሽ ዲባባ፣መሰረት ደፋርና አልማዝ አያናን የመሳሰሉ ወርቃማ ኦሊምፒያንን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ማሰለፍ ያልቻለችው ኢትዮጵያ አዲስ ወርቃማ ኦሊምፒያን ለማስተዋወቅ ተሰናድታለች። በዘንድሮው የውድድር አመት አስደናቂ ብቃት ማሳየት የቻለችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 5ሺ ሜትርን 14:13.32 በሆነ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ማሸነፏ ኢትዮጵያ አዲስና ስኬታማ ትውልድ ማፍራቷን ያረጋገጠ ነው። ጉዳፍ ከወራት በፊት የ1500 ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን ከማስመዝገቧ ባሻገር በ5ሺ ሜትር ልምድ ሳይኖራት የኢትዮጵያን ቻምፒዮና ማሸነፏ ይታወቃል። ጉዳፍ ማጣሪያውን ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰዓት በርቀቱ ታሪክ አምስተኛዋ ፈጣን አትሌትም አድርጓታል። ብዙ ጊዜ ከመካከለኛ ርቀት የተነሱ አትሌቶች ወደ ረጅም ርቀት ሲገቡ ስኬታማ እንደመሆናቸው ጉዳፍ በትክክለኛው ወቅት ትክክለኛውን የውድድር መስክ እንደመረጠች በርካቶች ይስማማሉ። ይህም የአዲሱ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ትውልድ ብዙ እንዲወራለት ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው።
ጉዳፍ ፀጋይ ደስታ ለስፖርቱ ቤተሰብ ስሟ አዲስ አይደለም። ባለፉት ጥቂት አመታት ኢትዮጵያን ወክላ በስፋት በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች በተለይም በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር በአለም አቀፍ መድረኮች መሳተፍ ችላለች። ከመሳተፍ አልፎም የተለያዩ ውጤቶችን አስመዝግባለች። ጉዳፍ ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ በ2014 የአለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ነበር። ከሁለት አመት በኋላም በተመሳሳይ ቻምፒዮና ተሳትፋ የነሐስ ሜዳሊያ በማጥለቅ በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የድል ጉዞዋን አሟሽታለች። ባለፈው 2019 በኳታር ዶሃ ተካሂዶ በነበረው ትልቁ የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ በማሸነፍ አገሯን አኩርታለች። በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የአለም የስፖርት ውድድሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ተቋርጠው ከቆዩበት ዘንድሮ ሲያንሰራሩ ቀድሞ ከነበራቸው አቋም በተለየ መልኩ ወደ ውድድር መድረክ ብቅ ካሉ አትሌቶች አንዷ ጉዳፍ ስለመሆኗ ጥርጥር የለውም። ለዚህም ባለፉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ማሳያ ናቸው።
ካለፈው የካቲት አንስቶ የዓለም አትሌቲክስ የ2021 የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው የቤት ውስጥ ውድድሮች ሲካሄዱ ድንቅ አቋሟን ማሳየት የጀመረችው ጉዳፍ፣ በፈረንሳይ ሌቪን ተካሂዶ በነበረው የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ውድድር የርቀቱን የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን 3፡53፡09 በሆነ ሰዓት በማሻሻል ደረጃዋን ከፍ አድርጋ በኦሊምፒክ ለውጤት ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች። ከዚያም በኋላ ጉዳፍ የዓለም ክብረወሰኑን ባስመዘገበች በአምስት ቀናት ልዩነት በዚያው በፈረንሳይ የብር ደረጃ በተሰጠው የቤት ውስጥ የዙር ውድድር በስምንት መቶ ሜትር ተካፍላ 1፡57፡52 የሆነ የዓለም የርቀቱ መሪ ሰዓት ማስመዝገቧ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ አይን ውስጥ እንድትገባ አንዱ ምክንያት ሆኗል። ጉዳፍ በስምንት መቶ ሜትር ያስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት የኢትዮጵያ የርቀቱ አዲስ የቤት ውስጥ ክብረወሰን ከመሆኑ ባሻገር በርቀቱ ከምንጊዜውም ፈጣን ሰዓቶች በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። በአፍሪካ ደረጃም ከሞዛምቢካዊቷ አትሌት ማሪያ ሞቶላ 1፡57፡06 ቀጥሎ ሁለተኛው የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ያሻሻለችው የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰን እኤአ 2014 ላይ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት የርቀቱ ኮከብ በገንዘቤ ዲባባ 3:55:09 ሰአት ተይዞ የቆየ ነበር።
ከወራት በፊት በፖርቹጋል በተካሄደ የፌርናንዳ ሪቤይሮ ጎልድ የአስር ሺ ሜትር ውድድር በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ የውድድሩን ዓመት ፈጣን ሰዓት 29፡39፡42 በሆነ ሰዓት ማስመዝገቧ ከምንም በላይ ትኩረት እንዲቸራት አድርጓል። ይህም ሰዓት አትሌት አልማዝ አያና በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ካስመዘገበችውና የዓለም ክብረ ወሰን ከሆነው 29 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ45 ማይክሮ ሰከንድ በመቀጠል በኢትዮጵያ የርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑን ጉዳፍን የኦሊምፒክ ተስፋ ቢያደርጋት አይገርምም። ለኦሊምፒክ ኢትዮጵያን እንድትወክል ያሳጫትም በተለያዩ ርቀቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስመዘገበች የመጣችው ስኬት ነው። ከወር በፊትም በአዲስ አበባ ስቴድየም በተካሄደው ሃምሳኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በአምስት ሺ ሜትር ያስመዘገበችው ውጤት አትሌቷ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት ውድድሮች ያላትን ትልቅ አቅም ያሳየ ነበር። ጉዳፍ ለረጅም ጊዜ ከምትታወቅበት የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ወጥታ ባለፈው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር 14፡49.06 የሆነ ሰዓት አስመዝግባ በቀዳሚነት ውድድሯን ፈጽማለች። የገባችበት ሰዓትም በ2009ዓ.ም ከተመዘገበው ክብረወሰን በአንድ ደቂቃ የፈጠነ ነበር። የጉዳፍ ልዩ የአትሌቲክስ ብቃትና ተሰጥኦ ባለፉት ጥቂት ወራት የበለጠ ጎልቶ ቢወጣም በአስቸጋሪ ሁኔታና የአየር ንብረት ውስጥ እንኳን ልዩነት መፍጠር የሚችል አቅም እንዳላት በርካታ ማሳያዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ለመካተት አዲስ አበባ ላይ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሮጣ ያስመዘገበችው ሰዓት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ጉዳፍ አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትርን በኢትዮጵያ የአየር ንብረት 4:02.4 በሆነ ሰዓት የሮጠች የመጀመሪያዋ አትሌት ናት። ከባህር ጠለል በላይ በ2355 ሜትር ከፍታ አዲስ አበባ ላይ ይህን ሰዓት ያስመዘገበችው ጉዳፍ በወቅቱ ብዙ ትኩረት ባይሰጣትም ሳይደነቅ የሚታለፍ ስኬት አይደለም።
ጌትነት ዋለ- 5ሺ ሜትር
የ3ሺ ሜትር መሰናክል የኢትዮጵያ ባለክብረወሰን የሆነው ወጣት አትሌት ጌትነት ዋለ ከተለመደው ርቀት ወጥቶ ካለፈው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ወዲህ በ5ሺ ሜትር እየደመቀ ነው። በኢትዮጵያ ቻምፒዮና በርቀቱ ማሸነፍ የቻለው ጌትነት የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ ያደረገውን ርቀት ወደ ጎን ትቶ በአዲስ መልክ መከሰቱ በሄንግሎውም ማጣሪያ ስኬታማ አድርጎታል። 12:53.28 በሆነም ሰዓት ቀዳሚ ሆኖም ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ለመወከል በቅቷል። ከ3ሺ ሜትር መሰናክል ተነስታ በ5ሺ ሜትር የስኬት ጫፍ ላይ እንደደረሰችው አልማዝ አያናም ተመሳሳይ ታሪክ ሊሰራ የሚችል አዲስ ኦሊምፒያን እንደሚሆንም ታምኖበታል።
በ2017 የአለም ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር መሰናክል ተሳትፎ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ጌትነት በ2016 ከ20 አመት በታች የአለም ቻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። 2019 ዶሃ ዳይመንድ ሊግ ላይ በርቀቱ 8:05:21 የሆነ የራሱን ፈጣን ሰአት ያስመዘገበ ሲሆን 2018 ፊንላንድ ቴምፕሪ ላይ ከ20 አመት በታች የአለም ቻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፉ ይታወቃል። ጌትነት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብዙም ስኬታማ ባልሆኑበት የ3ሺ ሜትር መሰናክል የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ ከመሆን አልፎ በርካታ ስኬቶችን ቢጎናፀፍም ከዘንድሮው አመት ጀምሮ ፊቱን ወደ 5ሺ ሜትር በማዞር ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ብቃት አሳይቷል። ጌትነት ወደ 5ሺ ሜትር ከመሸጋገሩ በፊት በፈረንሳይ ሌቪን በ3ሺ ሜትር 7:24:98 የሆነ ፈጣን ሰአት በቤት ውስጥ ውድድር ያስመዘገበ ሲሆን ይህ ሰአቱ ከታሪካዊው ኬንያዊ አትሌት ዳንኤል ኮመን ቀጥሎ በታሪክ ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ነው። ባለፈው ሚያዝያ የኢትዮጵያ ቻምፒዮና በአዲስ አበባ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ በ5ሺ ሜትር የተሳተፈው ጌትነት ውድድሩን በአስደናቂ ብቃት አሸንፏል። የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር በሄንግሎ ሲካሄድም በ5ሺ ሜትር 12:53:28 ሰአት በማስመዝገብ ተመሳሳይ ብቃት ደግሞ ሲያሸንፍ ቶኪዮ ላይ ለድል ከሚጠበቁ አዳዲስ ኦሊምፒያኖች ተርታ ራሱን ማሰለፍ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013