እስኪ ስንቶቻችን ነን ልባችን ያልሞተ? ገና ድሮ ልጅ እያለን እናደርጋቸዋለን ብለን ያቀድናቸው ውጥኖች አሁንም ልባችን ውስጥ የሚርመሰመሱ? አንዳንዶቻችን ተምረን ለአገር ለወገን አለኝታ መከታ ለመሆን ስናስብ በአንጻሩ ደግሞ አንዳንዶች ከውጥናቸው ጀምሮ ለአገርና ለወገን ጸር የሆነ አስተሳሰባቸውን ለማሳካት ገና በጠዋቱ የሚታትሩ አይጠፉም።
ውዶቼ! ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ከባህር ማዶ የመጣ በጣም የቅርብ ወዳጄ ያወጋኝን እውነተኛ ታሪክ ላጫውታችሁ ወደደኩ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ነው አሉ። አሜሪካ ብዙ የፊሊፒን ዜጎችን በስደተኝነት ተቀብላ ታስተናግዳለች። በወቅቱ አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ወደ ስደተኞቹ መኖሪያ ዘንድ ሄዶ ቃለ መጠይቅ ያደርጋል። ቃለ መጠይቅ ካደረጋቸው ስደተኞች መካከል ሁለቱ ጓደኛሞች የ17 እና የ20 ዓመት ወጣቶች ነበሩ።
ጋዜጠኛው የ20 ዓመቱን ወጣት ‹‹ዓላማህ ምንድ ነው?›› በማለት ሲጠይቀው ‹‹የኔ ዓላማ ቶሎ ቶሎ ብዬ ሰርቼ፣ ገንዘቤን አጠራቅሜ፣ ወደ አገሬ ተመልሼ፣ የራሴን ቢዝነስ ከፍቼ፣ ምን የመሰለችዋን ልጃገረድ አግብቼ እፎይ ብዬ በሰላም ለመኖር ነው።›› ብሎ ይመልሳል። ‹‹አንተስ?›› ብሎ ጋዜጠኛው የ17 ዓመቱን አፍላ ወጣት ሲጠይቀው ›› የኔ ዓላማ እንደ ጓደኛዬ ነው። ከሱ የተለየ ዓላማ የለኝም።›› በማለት ይመልሳል።
ይህም ቃለ ምልልስ የሁለቱን ውጣቶች ፎቶ አትሞ በወቅቱ ጋዜጣ ላይ ይወጣል። ታዲያ ይህ ከሆነ ከ45 ዓመት ገደማ በኋላ፤ አንድ የሳንፍራንሲስኮ የምርመራ ዘገባ ጋዜጣ ዘጋቢ ቤተመዘክር በመሄድ የድሮ ጋዜጦችን ሲያገላብጥ፤ ያ ጊዜ! ከ45 ዓመት በፊት የተደረገ ቃለ ምልልስ ልቡን ያነሳሳዋል።
ከዚያም ጋዜጣውን ኮፒ አድርጎ ፊሊፒኖች በብዛት ወደ ሚኖሩበት ከተማ ይሄድና፤ የድሮዎቹን ስደተኛ ወጣቶች ፎቶና ስማቸውን ከጋዜጣው ላይ እያሳየ ማጠያየቅ ይጀምራል። ይኸውላችሁ! ከስንት ልፋትና ድካም በኋላ የ20ና የ17 ዓመት ወጣቶች የነበሩትን የስልሳ አምስት እና የስልሳ ሁለት ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ሆነው አገኛቸው።
ጋዜጠኛው እነርሱን የፈለገበትን ምክንያት ለሁለቱ ካብራራ በኋላ፤ ለስልሳ አምስት የእድሜ ባለጸጋ እንዲህ በማለት ጥያቄውን ይጀምራል። ‹‹ጌታዬ! የዛሬ 45 ዓመት በፊት በጋዜጠኛ ተጠይቀው ሲመልሱ ቶሎ ቶሎ ሰርተው፣ ገንዘብ አጠራቅመው፣ ሀገርዎ ገብተው፣ ቆንጆ ልጃገረድ አግብተው በሰላም የመኖር ዓላማ እንደነበረዎት ተናግረው ነበር።››
‹‹አዎ! እውነት ነው ብያለሁ።›› አሉ የስልሳ አምስት የእድሜ ባለጸጋ። ‹‹ታዲያ ዓላማዎን ምን አስቀየረዎት?››ጠያቂ ጋዜጠኛው። ‹‹ዓላማህን ምን አስቀየረህ ነው ያልከኝ? በቁጣ ‹‹ማን አባቱ ነው ዓላማውን ቀይሯል ያለህ!›› ብለው እርፍ አሉ።
መቼም ልብ አይሞትምና ስንቶቻችን ነን እንደኝህ የእድሜ ባለጸጋ መልካም ዓላማና ውጥናችንን በልባችን ይዘን ያረጀን? በአንጻሩ ደግሞ ከጽንሰት እስከ ምንኩስና እድሜያቸው ከሰዋዊ ስነ ምግባር ያፈነገጠና ሰይጣን የሚጸየፋቸውን እኩይ ዓላማና ተልዕኮ አንግበው ለህዝብ ጸር ለአገር ጠላት የሆኑ እንደ አሸባሪው ሕወሓት አይነት የእፍኝት ልጆች አሉና መልካም ዕራያችን በመልካም ጥረታችን ዛሬ ባይሳካ ነገ ይሳካልና እምብዛም አንዘን።
በክፋት ተጠንስሶ በክፋት ያደገው አሸባሪው ሕወሓት ውንብድናና ቅጥፈት የባህሪ ገንዘቡ ነው። አንገት የሚያስደፋ እኩይ ስራ እየሰራ እንደመልዓክ ልታይ ማለት መገለጫው ከሆነ ውሎ አድሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ ጠንካራ አገረ መንግስት እንዲገነባ ከማስቻል ይልቅ፤ ደካማ እና እርስ በእርስ የሚጠራጠር ህዝብ እንዲፈጠር የሴራ ፖለቲካውን ከውልደቱ እስከ ምንኩስና እድሜው ሲሸርብ የኖረ፤ ከአገር ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያጋብሱ የዘረፋ ቡድኖችን መረብ ዘርግቶ በልማት ስም ሲምል ሲገዘት የኖረ የጃጀ ቡድን ነው።
ይህ ቡድን በልማት ስም ኢፍትሃዊነት እንዲንሰራፋ በማድረጉ የህዝብ ቁጣ ቀስ በቀስ ገንፍሎ በመውጣቱና ውንብድናው የገባው ሰው ቁጥር ከመንግስት ውስጥም ከውጭም እየበዛ በመምጣቱ በህዝቡ ግፊትና በውስጥ ትግል ይህ ጁንታ ቡድን ከስልጣን እንዲወገድ ሆኗል።
ነገር ግን ከስልጣን ሲወገድ እየሸፋፈነ አገርና ህዝብ ሲያሞኝ የኖረው ዘራፊነቱ፣ ጨቋኝነቱ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቱና ገዳይነቱ አደባባይ ላይ ተዘርግፎ ዓለም ካወቀውና ጸሃይ ከሞቀው በኋላ ይህ ቡድን ከጥፋቱ ተምሮ ህዝብና አገር ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ወደ እብሪተኝነት ነበር የሄደው።
በህዝብ ግፊት ወደ ፊት ከመጣው የለውጥ ኃይል ጋር ከመስራት ይልቅ ከግንባሩ ተነጥሎ ከማዕከል ሸሽቶ መቀሌ መሽጎ አካሄዱን ማብጠልጠል፤ የኔ መንገድ የሚለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ሞት የሚል ግትርነት ውስጥ ነበር የገባው። ይህም አልበቃው ብሎት አንዳንድ የፌዴራሊስት ኃይሎችን ዳግም ለማሞኘት እነዚህን አካላት ስብስቦ “እኔ መልዓክ ነኝ። የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ህልውና ከኔ ጋር የተያያዘ ነው። እኔ ከሌለው የብሄር መብት ልማት ወዘተ… የለም” የሚል ዲስኩር ውስጥ ገባ። ነገር ግን ጁንታው እንዳሰበው ሳይሳካለት በፌዴራሊስት ኃይሎች አክ ትፍ ተባለ።
ይህም አልሆን ሲለው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ብሂል በየአካባቢው የግጭት ድግስ በመጠንሰስ ህዝቡ በለውጡ አመራር ተስፋ እንዲቆርጥ ያልፈነቀሉት የሴራ ድንጋይ የለም። የግጭት ድግሶቹ በዋናነት ሁለት ዓላማ የነበራቸው ሲሆን፤ ከተቻለ በግርግር ወደ ስልጣን ዳግም መመለስ ካልሆነም ወትሮውንም ምንም ደንታው ያልሆነችውን አገር መበታተንና ህዝብ ማጫረስ ነበር።
ይህ ሁሉ ድርጊታቸው በትእግስት ታልፎ አገርና ህዝብ ወደ ሚጠቅመው ንግግርና መግባባት እንሂድ እየተባለ ባለበት ወቅትም አሻፈረኝ ብሎ ወደ ጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ውስጥ መግባታቸው፤ ከማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዝና ከጋራ አካሄድ ማፈንገጥ መጀመራቸውም ይታወሳል። ይህም አልበቃ ብሏቸው የአገሪቱ ዋልታ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊታችን ከጀርባው ወግቶ ትጥቁን በቁጥጥራቸው ስር አድርጎ በኃይል ማዕከላዊ መንግስቱን አስወግዶ ወደ ስልጣን የመመለስ ቅዠታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አለም በአንድ አፍ “እብደት” ያለውን አስነዋሪ ተግባር ፈጸሙ።
በዚህ እብደታቸውም በልጅነቷ የዘለለችውን ገደል በስተርጅናዋ ለመዝለል እንደሞከረችው ዝንጀሮ ተሰባብረው ገደል ገቡ። በስተርጅና ተራ ሽፍታ ሆነው በገቡበት ዋሻ ውስጥ ተለቅመው ለስር ከመዳረግ ባለፈ በሰላም እጃችንን አንሰጥም ብለው ሲንፈራገጡ እርምጃ የተወሰደባቸውም አልጠፉም። ተከብረው ቤተክርስቲያን በሚስሙበት ወይም ሶላት በሚያደርሱበት እድሜያቸው ታሪካቸው በውርደት ተደመደመ። በነሱ መዘዝም ብዙ ወጣት ሜዳ ላይ ወደቀ፣ የትግራይ ህዝብ ሰላሙ እርቆት በርሃብና በችግር አለንጋ እየተገረፈ ይገኛል።
ከመንበረ ዙፋኑ ተዋርዶ ተራ ሽፍታ ሆኖ በየዋሻና ገደሉ አፈር ልሶ የተነሳው የጁንታው ርዝራዦች ወደ ደፈጣ ውጊያ በመግባት በተራዘመ ጦርነት የትግራይን ህዝብ አሳርና መከራውን በማብዛት ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳና በተራዘመ ጦርነት የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል በማዳከም ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል።
ነገር ግን መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ አሁን ላይ ክልሉን ለቆ ወጥቷል።‹‹ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት›› እንደሚባለው መንግስት ያለምንም ውጊያ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲባል ክልሉን ለቆ መውጣቱን የአሸባሪው እርዝራዦች በእነርሱ ኃይል የተገኘ ድል በማስመሰል ከተደበቁበት የቀበሮ ጉድጓድ አፈር ልሰው በመነሳት የትግራይ ህዝብን ተነስ የምናወራርደው ሂሳብ አለን እያለ እየቀሰቀሰ ይገኛል።
የአሸባሪው ርዝራዦች ከሞት አፋፍ የተረፈችው ነፍሱ በደሏ እንዲሻር ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው በበደል ላይ በደል ለመፈጸም አልዘገየችም። ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ከቀድሞ ተግባሩ ይልቅ ወደ ባሰ የከፋ ድርጊቱ መሻገሩን ከሰሞኑ አይተናል። እያየንም ነው።
መንግሥት የተኩስ አቁም እርምጃ በመውሰድ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት መከላከያ ሠራዊትን ከክልሉ ባወጣበት ቅጽበት መንግሥትን በማሸነፍ መቀሌ መቆጣጠሩን በጀሌዎቹ በኩል አስተጋብቷል። አፍታ እንኳን ሳይቆይ የተንኳሽነቱ ባህሪው አለቅ ብሎት ወደ አዋሳኙ አማራና አፋር ክልሎች ህጻናትን በአደንዛዥ እጽ እያሳበደና ቄስ መነኩሴ በጦርነቱ ከፊት እያሰለፈ በግልጽ በዓለም እንዲታይለት በማድረግ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ወደለየለት አረመኔያዊ ድርጊት ገብቷል።
እንደ አበደ ውሻ ያንንም ያንንም የሚናቸፈው ይህ አሸባሪ ቡድን ከ10 ዓመት እምቦቃቅላ ህፃናት እስከ 70 ዓመት አዛውንት ድረስ በጦር ሜዳ እያሰለፈ የሚገኘው የጥፋት ኃይሉ አንድም የአቅሙን ውስንነት በሌላ በኩል ደግሞ የክፋት ጥግን የሚያሳይ ነው።
በበታችነት ስሜት ወደ በረሀ የወረደው የሕወሃት የማፊያው ቡድን በ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ከደርግ መንግስት ጋር በነበረው ፍልሚያ ከተሰው የትግራይ ታጋዮች በላይ የማፊያው ቡድን በበታችነት ስሜት በሴራ የረሸናቸው ወደ 60 ሺህ የሚደርሱ የትግራይ እናቶች የማህጸን ፍሬ ታጋዮችን የት እንዳደረሳቸው መልስ ሳይሰጥ፤ ዛሬ ላይ ደግሞ ከህጻን እስከአዛውንት ጦርሜዳ በመማገድ ትግራይን ምድረ በዳ ሊያደርግ አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ይገኛል።
ምን ይሄ ብቻ! ከተደበቀበት ሆኖ የትግራይ ህዝብ ተርቧል፤ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ይድረስልኝ እያለ ሲወተውት የቆየው ጁንታው፤ ‹‹አንቺ ታመጪው አንቺው ታሮጪው›› እንዲሉ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ እርዳታ እንኳን ለህዝቡ እንዳይደርስ ለማድረግ የተከዜን ድልድይ በማፈራረስ እኩይ ተግባር ፈጽሟል፤ ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ መከራና ሰቆቃ እያበዛ ቀጥሏል።
ከስድስት አስርታት ዓመት በፊት ታዋቂ ዳንሰኛ የነበሩት ፓት ሮኒ ዘጠነኛ ዓመት የልደት ባላቸውን ሲያከብሩ ከጠሯቸው የጥንት ወዳጆቻቸው መካከል አንዱ፤ በጣም የምታምር የልጅ ልጁን ይዞ መጣ። “ሆሆሆ”….! አሉ ጌታ ሮኒ አፋቸውን ከፍተው ልጅቷን በመደነቅ እያዩ፣ ምን አለበት አሁን ሰላሳ ዓመቴ ቢሆን …… እሺ ግዴለም ሰባ።” መቼም ምኞት አይከለከል አሉ ይባላል።
አዎ! ምኞት መቼም አይከለከልምና ጁንታው በኢትዮጵያ ህዝብ እርዳታ እሽኮኮ ተብሎ አራት ኪሎ ቤተመንግስት መግባቱንና መሸኘቱን ዘንግቶት፤ ዳግም ወደ ቤተ መንግስት ለመመለስ አልያም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በምንኩስና እድሜው ጦር ሜዳ መግባቱ ከምኞት ወይም ከህልም ቅዠት የዘለለ አይሆንም።
ገና ከምስረታው አገር ክዶ የተነሳው ቁሞ ቀሩ ጁንታው ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ እያለ ሲፎክር እንዳልነበር መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በ15 ቀን ውስጥ ብትንትኑ ወጥቶ በየ ቀበሮ ጉድጓዱ አፈር ለብሶ ድረሱልኝ እያለ በየቀኑ ሲያላዝን እንዳልነበር አሁን ላይ መንግስት ለክልሉ ሰላም ሲል ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ይገኛል።
ልብ አይሞት እንዲሉ አበው ጁንታው የአገሪቱን 70 በመቶ መካናይዝድ ጦር ተሸክሞ አንዳች ነገር መፍጠር ሳይችል እጁን ተቆልምሞ ያከማቸውን የጦር መሳሪያ ተቀምቶ የቀረው ኃይል እንደቁራ መጮህ ብቻ እንደሆነ እያወቀ፤ አመድ ሁኛለሁና ተያይዘን አመድ እንሁን በሚል ስሌት በምንኩስና ዘመኑ ተራ ሽፍታ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ይገኛል።
በመሆኑም ጁንታው አቧራ ሆኖ ኢትዮጵያንም አቧራ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለጦርነት ያልደረሱ እምቦቃቅላ ህጻናትን እና አረጋዊያንን ጭምር በማሰለፍ ትውልድ እየፈጀና አለም አቀፍ የጦር ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል። አይዞህ የሚሉትን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ጭምር ደጀን በማድረግ የኢትዮጵያን መፍረስ በመመኘት ላይ ይገኛል። የጁንታው አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ ሲናገር “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን” ሲል ያለሃፍረት ሲናገር ተደምጧል። የትግራይ ሚዲያ ሃውስ ለፋፊ ካታሊን በበኩሉ “የኢትዮጵያን መፍረስ ቆሜ መመልከቴ እርካታ ይሰጠኛል” ሲል ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥላቻ ተናግሯል።
ስለዚህ አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ መነሳቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአግባቡ ተረድቶ ይሄን የጁንታ ርዝራዥ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዳግም ላይነሳ ግብዓተ መሬት ለማስገባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እላለሁ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013