ከዓለም ታሪክ ተሞክሮ በማየት የጦርነት ዘመቻዎችን ከዓላማቸው አንጻር በተለያዩ አውዶች ከፍለን ልናያቸው እንችላለን። ለምሳሌ በመካከለኛው አውሮፓ የነበሩ ጦርነቶች በአብዛኛው ግዛትን በማስፋፋት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን መውሰድ ነበር። በ20ኛው ክፍለ ዘመን በቬትናም ፣ በቻይና ፣ የመሳሰሉት ሃገራት የተካሄዱት ጦርነቶች ደግሞ በውጭ ጣልቃ ገቦች ምክንያት በተፈጠረ ስጋት የሃገረ መንግሥታቸውን ህልውና የማስጠበቅ እልህ አስጨራሽ ግብግብ ነበር።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የጠራው ዘመቻም የውጭ ጣልቃ ገቦች ትህነግን የመሰለ አሸባሪ ቡድን በመጠቀም የሚያደርጉትን የጥፋት ሩጫ በማኮላሸት ሃገርን ከአጥፊዎች ለመከላከል የተደረገ የሃገርን ህልውና የማስቀጠል ዘመቻ ነው። በዚህም ዘመቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሃገሩ ህልውና በመቆም የአባቶቹን ታሪክ እንዲደግም በመንግሥት ጥሪ ቀርቦለታል። ጥሪውን ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች እና ወገኖች የተሰጡ ምላሾች የዓድዋን ጦርነት ያስታወሱ ናቸው። ከእነዚህ ምላሾች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ማየቱ ተገቢ ነው።
በ2013 ዓ.ም በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ ስመኘው ምንህነው ይባላል። ተማሪ ስመኘው ከዚህ በፊት ለሁለት ዓመታት የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር በመሆን የተመረጠ ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር በማሸነፍ ከትምህርት ሚኒስቴር የሜዳሊያ እና የብር ሽልማት ተበርክቶለታል። በትምህርቱ ይሄን ይህል ስኬታማ የሆነው ተማሪ ስመኘው አሸባሪው ህወሓት በሃገር ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ተከትሎ መንግሥት ያቀረበውን የህልውና ጥሪ ለመቀላቀል ዝግጁ መሆኑን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታው ተናግሯል። ተማሪው እንደሚለውም ትምህርት፤ ሥራም፤ ዕድገትም የሚኖረው ሀገር ስትኖር ነውና አሸባሪውን ህውሓት ለመደምሰስ ለዘመቻው ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሃውልቴ ግዛው ትባላለች ። ተማሪ ሃውልቴ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ካሉ ሴቶች አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ናት። ተማሪዋ ሃገሪቱ የተጋረጡባትን ችግሮች ለመካፈል እስከ ግንባር በመሄድ ለመዋጋት እንደምትፈልግ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራላች ።
ከዚህ በፊት ተማሪዎች በከፍተኛ ነጥብ ሲመረቁ ለዚያውም የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ ወደፊት የተደላደለ ኑሮ ለመኖር በማሰብ የተሻለ የትምህርት ዕድል ወይም ሥራ ለማግኘት ሲጓጉ ነበር የሚታዩት፤ ዛሬ ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ሀገር የሚያፈርስ አገር ጠል ቡድን ሲመጣ ግን ህይወትን ማሻሻልም ሆነ ነፃ የትምህርት ዕድል ማፈላለግ ቅንጦት ነው። ይህንንም የተረዱት የደብረ ማርቆስ የዋንጫ ተሸላሚ ተማሪዎች የሃገር ከሥራም ሆነ ከአዳዲስ የትምህርት ዕድሎች ይልቅ የገርን ህልውና አስቀድመዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ አሁን በመንግሥት የተጠራው ሃገርን እናድን የህልውና ጥሪ ምን ያህል አንገብጋቢ መሆኑንም ሁላችንም እንድንገነዘብ የሚያደርገን ነው።
ሌላው በመንግሥት ለህልውና ትግሉ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሀገርን በውትድርና ያገለገሉ ነገር ግን በተለያዩ ምክንቶች ከመከላከያ የተገለሉ አካለት ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል የአቶ ተመስገን ወርቄ ቤተሰብ አንዱ ነው። የአቶ ተመስገን ቤተሰብ ሃገር ችግር በተጋረጠባት ጊዜ ለሃገር አለሁ በሚል የሚታወቅ ቤሰብ ነው። በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት ሃገር በተደፈረች ጊዜ የአቶ ተመስገን ቤተሰብ ከቤተሰቡ ግማሹን ወደጦር ግንባር አሰማርቶ የሀገሩን ህልውና አስቀጥሏል። ይህም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ታይቷል። ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የቤተሰቡ አባላት እንደተናገሩትም አሁንም አሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት የሚደረገውንም የክተት ጥሪ ተከትሎ ቤተሰቡ ዘመቻውን ተቀላቅሏል።
የአቶ ተመስገን ቤተሰብ የሆኑት ወታደር አበበ ተመስገን እና ወታደር አሻግሬ ተመስገን ወንድማማቾች ሲሆኑ ነፃናት በየነ ደግሞ የአጎታቸው ልጅ ነው። ሁሉም በ1990ው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተሳትፈዋል። ነፃነት በየነ በቅፅል ስሙ ኮከቤ ይባላል። በጾረና ግንባር በነበረ ውጊያ በ1991 ዓ.ም ሲሰዋ ሁለቱ ወንድማማቾች ግን እስከአሁን በህይወት አሉ።
የአበበ ተመስገን የውትድርና ህይወት በሦስት ምዕራፎች የተከፈሉ ናቸው። አንደኛው 1988 እስከ 1990 በ32ኛው ክፍለ ጦር እና ከ1990 እስከ 1991 ዓ.ም ደግሞ በጾረና ግንባር በአሁኑ አራተኛ በቀድሞው 52ኛ ሜካናይዝድ መድፍ ብርጌድ በተዋጊነት ለእናት ሃገሩ አገልግሏል። ሌላኛው እና ሁለተኛ ህይወቱ ደግሞ ከ1991- 1993 በሹፍርና እና መረጃ ክፍል በመሥራት ያገለገለ ሲሆን፤ ከ1993- 1997 ግን ሙሉ በሙሉ የመረጃ ጉዳዮችን ብቻ ሲሠራ ቆይቷል።
ነገርግን በ1997 ዓ.ም ምርጫውን ተከትሎ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። በወቅቱ መንግሥትም ሆነ ያሸብር በነበረው የህወሓት የበላይ ሹማምንቶች ኢትዮጵያን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ ተልእኮ አንግበው ሲሠሩ ነበር፤ ይህንንም ተልዕኳቸውን ለማሳካት አበበን ተባባሪ ለማድረግ ይሞክራሉ። ከትብብርም ባለፈ ይህንን ዕኩይ ተግባር እንዲፈጽም ለአበበ ትዕዛዝ ይሰጠዋል። ነገር ግን አበበ የተሰጠውን ተልኮ ወደ ጎን በመተው ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጎን ተሰለፈ።
ይሁን አንጂ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን የጥፋት ጠርስ ውስጥ ሊያመልጥ አልቻለም። ብዙም ሳይቆይ ታሰረ ፣ ተደበደበ ምድር ላይ ይፈጸማሉ የሚባሉ ግፎች ሁሉ ተፈጸሙበት። በስሙ በቦሌ ክፍለከተማ የነበረው ቤትም ተነጠቀ። ብዙ መከራና ስቃይም ደረሰበት። በመጨረሻም ታሰረ።
ከእስር እንደተፈታም በወልቃይት እና በራያ ጉዳይ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለአማራ ዘብ እንቆማለን ብሎ ወደ ጫካ የገባውን አዴሃን የተባለውን ድርጅት በኤርትራ በርሃ ተቀላቀለ። ከኢትዮጵያም ወደ ኤርትራ ሰዎችን እየመለመለ ማመለላስ የተሰጠው ግዳጅ በመሆኑ ወጣቶችን እየመለመለ ወደ ኤርትራ ማጓጓዙን ያዘ። ነገር ግን አንድ ቀን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ወደ ትጥቅ ትግሉ ለመገባት የተዘጋጁ ወጣቶችን ለመውሰድ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በአሸባሪው ህወሓት ሆድ አደር የደህንነት ሰዎች በ2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ዋለ። እስከ 2010 ዓ.ም ታሰረ። በተለይም የቂሊንጦ እስርቤት ከተቃጠለ በኋላ ወደ ሸዋሮቢት እስር ቤት ተዘዋወረ። በሸዋሮቢትም መፈጠረን የሚያስጠላ ግርፋትና ስቃይ ደረሰበት።
ሌላኛው የአቶ ተመስገን ቤተሰብ የሆነው አሻግሬ ተመስገን ነው። አሻግሬ ተመስገን ገና በ18 ዓመቱ በኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት የእናት ሃገሩን ጥሪ ተከትሎ መከላከያን ተቀላቀለ። በጦርነቱም በ23ኛ ፓራኩማንዶ በመመደብ መጀመሪያ በቡሬ ግንባር በኋላም በጾረና ግንባር ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸመ ወታደር ነው። በኋላም የአጋዚ ክፍለ ጦርን ተቀላቅሎ የቤተመንግሥት ጠባቂ በመሆን ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግሏል። ይሁንና በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ማጭበርበርን እና ስርቆትን የህይወቱ አንድ አካል ያደረገው አሸባሪው ህወሓት ልማዱ አገርሽቶበት የምርጫ ድምፅም ሰረቀ። ይህን ተከትሎ የአዲስ አበባ ተማሪዎች አመፅ አስነሱ። የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ደርቅ እንዲሉ ምንም ማፋር ያልፈጠረበት የሽብር ቡድን ብሰርቅስ ምን አገባችሁ በሚል ትዕቢት ተወጥሮ ወጣቶችን በአደባባይ ረሸነ።
በባዶ እጃቸው የወጡ ወጣቶችን አጋዚ ኮማንዶ በማሰማራት ግፍ ፈጸመባቸው። ይህንን አሰቃቂ ተግባር ለመፈጸም ህሊናው ያልፈቀደለት ወታደር አሻግሬ ተመስገን እስክሪቢቶ በያዙ ተማሪዎች አልተኩስም አለ። እንዲተኩስ ቢገደድም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህም በከፍተኛ ደረጃ ጥርስ ተነከሰበት።
ሁኔታው ያልተመቸው ወታደር አሻግሬ ተመስገነን ለትህነግ ቡድን ምንም ሳያሳውቅ ወደ ትውልድ ሃገሩ እብስ ይላል። የገዳዩ ህወሓት ባለሟሎችም ኮማንዶው የሄደበትን አጣርው ይደርሱበታል። በዚህም በሌሊት የአሻግሬ ተመስገንን ቤተሰብ ቤት ከበው ያደራሉ። ሀገር ሰላም ብለው ያደሩት የተመስገን ቤተሰቦች በጠዋት ቤታቸውን ሲከፍቱ አካባቢያቸው በወታደር ተከቧል። በተለይም በሩን የከፈተችው ነፍሰጡሯ የአሻግሬ ተመስገን እህት ባየችው ነገር ተደናግጣ እራሷን ስታ ወደቀች። በሆዷ የነበረው ፅንሰም ወረደ። በዚህም የኮማንዶው እህት እስከመጨረሻው ማርገዝ እንደማትችልና እና ዓይኗን በአይኗ ለማየት እንዳልታደለች ከሃኪሞች ተነገራት።
አሻግሬ ተመስገንም ተይዞ ጨለማ እስር ቤት ተጣለ፤ለሁለት ዓመትም ማቀቀ። በሁኔታው አንጀቱ እያረረ ቀን እስኪያልፍ በእንጉርጉሮ ለማሳለፍ ተገደደ። በ1999 ዓ.ም ከተፈታበት ጀምሮ እስከአሁን ማለትም መንግሥት የህልውናውን ዘመቻ እስከጠራበት ጊዜ በጸጉር ማስተካከል ሙያ እየሠራ ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የህልውና ጥሪውን ተከትለው እነ አሻግሬ ተመስገን ክተቱን ተቀላቅለዋል።
የተለያዩ አካላት የመንግሥትን ጥሪ ተከትለው ለግዳጅ መዘጋጀታቸው የህልውና ዘመቻው ምን ያህል ኢትዮጵያ እንደ ሃገረ መንግሥት የመቀጠል ጉዳይ የሚያሳይ ማንቂያ ደወል ነው።
መንግሥት ከጠራው የህልውና ጥሪ ጋር ተያይዞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የህልውና ትግሉን ለማሸነፍ አንድ ነገር ልብ ሊል ይገባል ባይ ነኝ። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የአሸባሪው ህወሓት ያህል የኢትዮጵያን ህልውና ለውጭ ኃይላት አሳልፎ የሰጠ ስለሌለ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የህልውና ዘመቻውን እየተቀላቀሉ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ገና ሲፈጠር እና ጫካ ሲገባ እንዲሁም በስልጣንም በነበረበት ጊዜ እና አሁን በሽፍትነቱ እየፈጸመው ያለው ተግባር ኢትዮጵያ እንደሃገር የመቀጠሏን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ለመክተት ያለመ ነው። የአሁኑ ይባስ እንዲሉ ለራሱ ለትግራይ ሕዝብ መከታ የሆነውን መከላከያን ከጀርባው ወጋ። መከላከያንም አዳክሞ ለውጭ ወራሪ ኃይል አሳልፎ ለመስጠትም ቀን ከሌሊት እየሠራ ይገኛል።
የብሄርተኝነት ጫፍ በመርገጥም የትግራይ ህዝብን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር እንዲራራቅ የጥላቻ መርዝ በመርጨት ህዝቡ ለመከላከያ ደጀን እንዳይሆን አድርጓል። በዚህም ምክንያት መንግሥት የትግራይን ህዝብ በማክበር የጥሞና ጊዜ በመስጠት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ትግራይን ለቆ ወጥቷል።
ነገር ግን መንግሥት ያለምንም ውጊያ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲባል ክልሉን ለቆ መውጣቱን የአሸባሪው እርዝራዦች በእነርሱ ኃይል የተገኝ ድል በማስመሰል ከተደበቁበት የቀበሮ ጉድጓድ አፈር ልሰው በመነሳት የትግራይ ህዝብን ተነስ የምናወራርደው ሂሳብ አለን እያለ እየቀሰቀሰ ይገኛል። ኢትዮጵያንም ለማፈራረስ እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀመበት ይገናል።
ስለሆንም የሀገር ህልውና ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪ ነው። ከገባንበት የውክልና ጦርነት ለመውጣት እና ሃገራችንን ከዚህ የውክልና ጥፋት ለማዳን ከመቼውም ጊዜ በላይ አብረን የምንቆምበት ጊዜ ላይ ስለምንገኝ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን ከጠፋት ኃይሎች ማዳን አለብን። ወደ ግንባር እንትመም መልዕክቴ ነው !!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013