እጅ ለበርካታ ጉዳዮች ይዘረጋል። ለመስጠት ይዘረጋል፤ ለመቀበል ይዘረጋል። ለመማታት ይዘረጋል፤ ለመከላከልም ይዘረጋል። ቆርሶ ለመጉረስ እንደሚዘረጋው ሁሉ ለማጉረስም ይዘረጋል። ባጭሩ ያለ እጅ መኖር አይቻልም ባይባልም መኖሩ ከባድ መሆኑን ግን መናገር ይቻላል።
እጅ ከላይ ካልናቸው በዘለለ ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ ስራዎችን የሚያከናውን ቢሆንም፤ በዘይቤያዊ አገባቡ፣ አገላለፁ፣ አገልግሎቱና ኪናዊ ፋይዳው የሚያክለው የለም። ከ”ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ” ጀምሮ እስከ “የሰላም እጆች”ን መዘርጋት ድረስ ያሉት ከፈጠራ ስራዎች (በተለይ በስነ-ቃል) እስከ ታሪክና ፖለቲካ፤ የእለት ተእለት ኑሮና ህይወት ውስጥ በመዝለቅ የሚሰጡት አገልግሎት ላቅ ያለ ነው። ወደ ተነሳንበት “የሰላም እጆች” እንመለስ፤ በተለይ ከሁለት ተፃራሪ ኃይላት አኳያ እንመልከተው።
“የሰላም እጆች” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር የሚገለፅበት መንገዱም ሆነ ዘዴው፤ ወይም ብልሀቱና አይነቱ ብዙ ነው። ከሁለት ተፃራሪ ኃይላት አኳያ ሲታይ አንዱ ወደ አንዱ በ”ይቅርታ”ም ይሁን በ”ሁሉንም እንተወው” አዝማሚያ፤ ወይም ከ”መፀፀት”ም ይሁን አለያም “ለህዝብ ጥቅም ሲባል” … ወይም ከእነዚህ በአንዱም ይሁን ወይም በሌላ እዚህ ባልጠቀስናቸው ምክንያቶች ሽማግሌ ሊልክ ይችላል። ይህ የተቀደሰ ሀሳብ ነውና በባለ ጤናማ አእምሮዎች ዘንድ ፅድቅ ነው። በምድርም ሆነ በሰማይ አያስኮንንምና ተግባሩ በሁሉም ዘንድ ይበረታታል።
ሌላው “የሰላም እጆች” እና የመዘርጋታቸው መገለጫ ወይም ማሳያ፣ ለምሳሌ ከጦርነት አኳያ፣ ተኩስ ማቆም አንዱና በብዙዎች ብዙም የማይደፈረው፤ ምናልባትም እንደ ሽንፈት የሚቆጠረው፣ ከውሳኔዎች ሁሉ ከፍተኛውን፣ ከወታደራዊም ባለፈ የፖለቲካ ውሳኔን የሚጠይቀው የ”ተኩስ አቁም” (Ceasefire) ውሳኔና አንድምታው ነው።
የ”ተኩስ አቁም” ውሳኔና አሰራሩ፤ ወይም አጠቃላይ አላማው ንፁሀንን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ እሱም በሁለት ተዋጊ ሀይላት መቆራቆስ ምክንያት ህዝብ እንዳይጎዳ፣ ተፈጥሮ እንዳይዛባ፣ የአካባቢ ፀጥታ፣ ደህንነትና ሰላም እንዳይደፈርስ፣ ማህበራዊ ኑሮ እንዳይመሰቃቀል፣ የሰዎች አብሮነት (አብሮ የመኖር ታሪካዊና ባህላዊ እሴት) እንዳይበላሽ፤ በሰው ልጆች፣ በተለይም በአንድ አካባቢ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የእርስ በእርስ ጥላቻና ያልተፈለገ የጎሪጥ መተያየት እንዳይመጣና ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፀም ወዘተርፈ ለማድረግ ነው። ይህ ነው የ”ተኩስ አቁም” አጠቃላይ አላማ።
የ”ተኩስ አቁም” ውሳኔና ተኩሱ (ውጊያው) የሚቆምበት ጊዜ ጦርነቱ የመጨረሻ እልዕባት አገኘ ማለት አይደለም። ሆኖም አያውቅም። በአንፃሩ ሁለቱ ተገዳዳይ አካላት ከመገዳደል ተግባራቸው ለጊዜውም ቢሆን አረፍ እንዲሉና የጥሞና ጊዜን አግኝተው እንዲመክሩ፤ እንዲያስቡበት፤ ከነበረው ሰብአዊ ቀውስ፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ዲፕሎማሲያዊ ክስረት፣ ፖለቲካዊ ግሽበትና ዝቅጠት ወዘተ ውስጥ በመውጣት ወደ ሰላማዊና ለሁለቱም ወገኖች ህዝብና አገር ተጠቃሚነት ሲባል ነው – እንዲሁም ለአለም ሰላም!!!
ይህ የ”ተኩስ አቁም” ውሳኔና “የጥሞና ጊዜ” እንደ አንድ ወርቃማ እድል ሊቆጠር የሚገባውና በዚሁ ወርቃማ እድል ለመጠቀም በሁለቱ ተገዳዳይ ኃይሎች መካከል ፉክክር የሚታይበት እንዲሆን በብዙዎች ይጠበቃል። የ”ተኩስ አቁም” እርምጃው እነዚህ ኃይሎች ያጡትን አንድ ትልቅ የመነጋገሪያ፣ የመተራረሚያ፣ የመግባቢያ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን መፈተሽያ … እድል ወይም መድረክ የሚፈጥርላቸው ከመሆኑ አኳያ እድሉን “በስለት የማይገኝ” የሚሉት በርካቶች ሲሆኑ፤ በተለይ “በአፍሪካ እማይታሰብ” የሚሉትም ቁጥራቸው የዛኑ ያህል ከፍተኛ ነው።
እርግጥ ነው ወደ ተኩስ አይገባ እንጂ ኋላ ኋላ፣ ሄዶ ሄዶ ማጣፊያው ማጠሩ አይቀርም። ይህንን ደግሞ የአለም ታሪክ ለአለም ህዝብ በሚገባ አስተምሮ አልፏል፤ ሆኖም በዕድሉ የሚጠቀሙ አካላት ችግራቸውን በቀላሉ አስወግደው ለህዝባቸውና ለሀገራቸው መልካም ታሪክ ማኖር ሲችሉ ከዚህ በተቃራኒ የሚሄዱት ግን ህዝብንም፤ ሀገርንም ለመከራ ዳርገው ዘላለም የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አይድኑም፡፡
ማንም እንደሚያውቀው፣ ብዙ ጊዜ በንግግርም ሆነ ጽሑፍ መሀል ጣል ሲደረግ እንደሚታየው የሰላም ጥቅም የሚታወቀው ሰላም ሲታጣ፤ ማለትም በጦርነት ወቅት ነው። የሰው ጥቅሙ የሚታወቀው “ሰው የጠፋ እለት” እንደሚሆነው ሁሉ የ”ተኩስ አቁም”ም ጥቅሙ የሚታወቀው በተኩሱ ጊዜ ወይም ተኩሱ ሳይቆም የቀረ እንደሆነ ነው። ይህ የሰው ልጅ ሁሉ ብቻ ሳይሆን የእንስሳትና አራዊቱ፣ የዱርና ገደሉ፣ የአእዋፋትና አበቦች ሁሉ ጥቅም ነውና የ”ተኩስ አቁም” በቀላሉ ሊታይና ጀርባ ሊሰጠው የሚገባ ውሳኔ አይደለም።
በዚህም ምክንያት በታደሉትና አስተውሎት ባላቸው አገራት ተኩስ አቁም ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ከአንደኛውም ይሁን ከማንኛውም ወገን ለመጣ የተኩስ አቁም ውሳኔ ምላሹ ተኩስ ማቆም ነው። ከዛ ውጪ ያለ ውሳኔ ያለአዋቂነት ውጤትና ያልተፈለገን ዋጋ የሚያስከፍል እንጂ ከታሪክ እንደተረዳነው የበሳል ፖለቲከኛ የወደፈት የተሻለ አቅጣጫ አመላካች ሆኖ አያውቅም።
ከላይ እንዳልነው፣ ተኩስ አቁም ያህልን ውሳኔ ተኩስ ባለማቆም ማስተናገድ ማለት ወይ ስለ ተኩስ አቁም ምንነት አለመረዳት ነው፤ ወይም እብሪት ነው፣ አለያም ለአገርና ለወገን ደንታቢስነት ነው። ደንታቢስነት ደግሞ የበሳል አመራር ሰጪነት፣ የበሳል ፖለቲከኛነት፣ አስተዋይነት ማሳያ አይደለም። ማሳያ ይሆናል ከተባለም ከጠቀስናቸው በተፃራሪው ነው የሚሆነውና ዘግይቶም ቢሆን ትርፉ ኪሳራ ነው።
ለህዝብና አገር ጥቅምና ህልውና ሲባል የ”ተኩስ አቁም” ውሳኔ ላይ መድረስና “የጥሞና ጊዜ” መስጠት (መሰጣጠት) አንዱ የፖለቲካ ውሳኔ አካል በመሆን ሲሰራበት የተኖረ የተለመደና ህጋዊ አሰራር ነው። ሆደ ሰፊነትና ለሀገርና ለህዝብ ማሰብም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም ሲደረግ መኖር ብቻ ሳይሆን ብዙ አገራትና ህዝቦች ተጠቃሚ ሲሆኑበት ኖረዋል።
ታዲያ ይህ የተለመደ አሰራርና የተጠቃሚነት ጉዳይ “ለምን እዚህ እኛ ጋር ሲደርስ አልሳካ አለ?” ወይም ክብር ተነፈገው የሚል ጥያቄ ቢነሳና የሚመለከታቸው አጥንተው ቢነግሩን ጥሩ መሆኑን ከወዲሁ እያሳሰብን፤ አሁን በአገራችን ያለውን ሁኔታ አስመልክተን፣ የተኩስ ማቆሙን ውሳኔና ተቀባይነት ማጣቱን አንስተን፤ የሚመለከታቸውን ወገኖች፣ በተለይም “አልቀበልም” ያለው አካል ለህዝብ ቆሜያለሁ ማለቱ የስላቅ መሆኑን መረዳት አያዳግተንም፡፡
“አፈር ነህና ወዳፈር ትመለሳለህ” እንዲል መጽሐፉ (አንድ ቀን ህዝብ መሆን አይቀርምና) ከህዝብ አካል የወጣ ወደ ህዝብ መመለሱ ስለማይቀር፤ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይታጠፉ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም ስራ እንስራ ስንል የጦርነት መሀይምነታችንን ድንበር ጥሰን ነው።
ከተኩስ ማቆም ሕይወት ይገኛል፤ ከተኩስ አለማቆም ህይወት ይታጣል። ታዲያ የቱ ነው ትክክል?? የቱስ ነው ሰብአዊነትና የህዝብ ተቆርቋሪነት? የቱስ ነው በሳል ፖለቲከኛነት? የቱስ ነው ዘመናዊነት? በተለይ በተለይ የትኛው ተግባር ነው የዲሞክራትነት፣ ህዝባዊነት፣ ህዝበኝነት፣ ኢትዮጵያዊነት መገለጫው???
አሁንም ለስንተኛ ጊዜ እንድገመው፤ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይታጠፉ ለህዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል የግል ዝናንና ጥቅምን፣ የስልጣን መሻትንና የብሽሽቅን ፖለቲካን፣ አገር ማፍረሱንና ማውደሙን ትተን ተኩስ የማቆሙን እርምጃ የጋራ ማድረግ ተገቢ ነው። እውነትም መስዋእትነታችን ለአገርና ለህዝብ ከሆነ አገርና ህዝብ የሚፈልጉት የተኩስን መቆም እንጂ የተኩሱን እየሞቀና እየተስፋፋ መሄድ አይደለምና ለህዝብና አገር ፍላጎት እንገዛ። ያለበለዚያ በህዝብና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ የማታ ማታ ተወቃሽና ተጠያቂ መሆን አይቀርም፡፡
ግርማ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013