አቶ ሰለሞን አብዲ የተባሉ የዕድሜ ባለፀጋ አርሶ አደር በተደጋጋሚ የሚናገሩት አንድ አባባል አላቸው ፡፡
“የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል”
አባባሉን እንደማንኛውም ተራ የወሬ ንግግር ከመስማት ባሻገር ትርጉም ሰጥቼው አላውቅም ::ወይም ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ጥያቄ በማቅረብ ትርጉሙን ለመረዳት ፍላጎት እና ተነሳሽነት ኖሮኝ አያውቅም ::ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ የገባኝ ከ2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ ነው ::በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንደ አገር ምርጫ የሚደረግበት ዓመት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው ፡፡
በ2012 ዓ.ም ለሚደረገው ምርጫ ሂደቱን በኃላፊነት እና በባለቤትነት የሚመራው ህጋዊ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጅምሩ ፊሽካ ሳይነፋ እና ጊዜውም ሳይደርስ በራሳቸው ጉልበት እና ፍላጎት ብቻ የምርጫውን ቅስቀሳ በአንድም በሌላም መንገድ፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የጀመሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ነበሩ:: ክፋቱም ሆነ ህገ-ወጥነቱ ጊዜው ሳይደርስ፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሳይፈቅድ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ መጀመራቸው ብቻ አልነበረም፡፡የምርጫው መደረግ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ::በምርጫውም እኛ ካላሸነፍን አገር ትፈርሳለች ደም ይፈሳል የሚለው ሟርታቸው እጅግ አሰቃቂና አስፈሪ ነበር ፡፡
ሟርቱ ካስፈራቸው እና በእጅጉ ካሳቀቃቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበርኩ:: ለመሳቀቄ ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ:: እንኳን በሟርት የተጀመረው የምረጡኝ ቅስቀሳ አይደለም በሰላም እና በግልፅነት ተደረጉ የተባሉ የአፍሪካ ብዙ ምርጫዎች የተጠናቀቁት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውንና ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይወት በመገበር ነው ::ስኬታማ የተባለው የ1997 ምርጫ የተደመደመው የብዙዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ ሺዎችን ወደ ወህኒ በማውረድ እና ሺዎችን ደግሞ ከአገር በማሰደድ ነው ፡፡
ሶስት ጊዜ በኬንያ የተካሄዱት ምርጫዎች ሶስቱም የተጠናቀቁት የሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ እና ንብረት በማውደም ነው:: በዘመነ ኮረና የተደረገው የቅርብ ጊዜ የኡጋንዳ ምርጫ የተጠናቀቀው ህይወት በመቅጠፍ ነው:: ብቻ ምን አደከማችሁ የርግማን ይሁን የምርቃት ባይታወቅም ከደቡብ አፍሪካው የነፃነት አባት ማንዴላ የስልጣን ዘመን በስተቀር አፍሪካ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ በሰላምና በደስታ የተጠናቀቀበት ጊዜ የለም ::ይህ የሆነበት ምክንያት ስልጣን የሀብት ማጋበሻ ብቸኛው አማራጭ
ስለሆነ ነው:: ሁለትም መሸነፍን በፀጋ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነ ግለሰብም ይሁን ቡድን ባለመኖሩ ነው፡፡ ስለሆነም የቦረንትቻ ልማድ ያለበት ይመስል የአፍሪካ ምርጫ የሚጠናቀቀው ደም በማፋሰስ እና ሕይወት በመገበር ነው ፡፡
ወደተነሳንበት መሰረታዊ ጉዳይ ልመለስና “ያዘነ ቢኖር ይፀልይ”፣ “የተደሰተ ቢኖር ያመስግን” የሚለውን የመፅሐፍ ቅዱስ መርሕ ከልብ ስለማምን እያስፈራኝ የነበረውን ስሜት ተሸክሜ ፈጣሪን በፀሎት ለመጠየቅ ሞረትና ጅሩ ወረዳ ቡሳዬ ቀበሌ ውስጥ ወደሚገኘው ቡሳዬ አቦ ለመድረስ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ከአዲስ አበባ ላምበረት መናኸሪያ ተነስቼ በመጓዝ ከምሽቱ 12፡50 ደነባ ከተማ ከምትገኘው እናቴ ቤት ደረስኩ፡፡ በደረስኩበት ቅፅበት እናቴ ያቀረበችልኝ እራት እየበላሁ የ1 ሰዓት ዜና ለማየት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከፈትኩ፡፡ በውል የማላስታውሰው ዜና አንባቢ አርዕሰተ ዜና ብሎ አስደንጋጭ መርዶ ተናገረ:: በአንድ ጃፓናዊ ዜጋ አማካይነት ኮረና ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን:: መርዶው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ፣ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው ነበር ፡፡
እግዚአብሔር የማንንም ልባዊ ልመናና ፀሎት ችላ አይልም:: ከፈጣሪ ጋር ለመገናኘትም የግድ ዓለም በቃኝ ብሎ መናኝ መሆን አያስፈልግም:: ሁሉም ነገር ለበጎ ነው እንደሚለው መፅሐፍ የኮረና ወረርሽኝ መምጣት ለኢትዮጵያ በጎ አስተዋፆኦ አበረከተ:: በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫው ተራዘመ:: ኮረናም በራሳችን ግዴለሽነት ከፈጠርነው ችግር በስተቀር እንደ ሌላው ዓለም የከፋ ቀውስ አላስከተለብንም::
የኮሮናው ስጋት በዚህ መልኩ ሲታለፍ ምርጫ ይሉት ነገር ደግሞ አሳሰበኝ፡፡ ብዙዎችም ምርጫው ለኢትዮጵያ ቀውስ ይዞ ይመጣል የሚል መርዶ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ምርጫውን ፈሩት፤ይዞ የሚመጣውንም መዓት በመፍራት ከወዲሁ ተሸማቀቁ፡፡ ብዙ መርዶ የተነገረለት ምርጫም ተከናወነ፡፡ያለ አንዳች ኮሽታም አስደናቂ በሆነ የህዝብ ማዕበል ታጅቦ በስኬት ተጠናቀቀ::የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በጋራ አሸነፉ ፡፡
ይህን አስደናቂ፣ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ድል ለማድነቅም ሆነ ለመዘገብ አንድም ምዕራባዊ አልተገኘም:: ከዚህ ይልቅ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ይከሰታል የተባለውን ሟርት ፈፅሞ መጠበቅ አይደለም ባልጠረጠሩት መንገድ ሲከሽፍ በእጅጉ ተደናገጡ ፡፡
ፕላን ኤ ሲከሽፍ ወደ ፕላን ቢ ተሸጋገሩ:: ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ አትሞሉም የሚል ዘመቻ በሱዳን፣ በግብፅ፣ በአረብ ሊግ፣ በአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ የተባበረ ኃይል ተጀመረ:: ዓለም አቀፍ ጫናው በረታ:: በተለይም አሜሪካ ያለችውን ሀሳብ ያልተቀበለ አገርና መሪ እጣፈንታው ምን እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ አይቷል:: የሳዳምና የጋዳፊን፣የኢራቅንና የሊቢያን እጣፋንታ ማስታወስ በቂ ነው ::ሁኔታው ጫና ብቻ ሳይሆን አስፈሪም ነበር:: ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ተወሰደ:: በርካታ ኢትዮጵያውያን ማዕቀብ እንዳይጣል ፈሩ:: ከብዙዎች እልህ አስጨራሽ የሚድያና ሰላማዊ ሰልፍ ትግል ጋር የሚደመር ተግባር የሚፈፅሙ የቁርጥ ቀን ልጆች ኢትዮጵያ አጥታ አታውቅም:: በአድዋ ጦርነት ወቅት ጣይቱና ሚኒልክ ሁለተኛው አድዋ በሆነው ህዳሴ ግድብ ዘመን ደግሞ ዶክተር ኢንጅነር ሽለሺ በቀለን ::ባደረጉት ገዥ ንግግር እና የኢትዮጵያ ሐቅ ተደምረው የተፈራውና የተጠበቀው ሳይሆን ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት ተመልሶ እንዲታይ የፀጥታው ምክር ቤት ወሰነ ፡፡
2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጣምራ ድል ዘመን ሆኖ ሊያልፍ እና በታሪክ ሲዘከር ሊኖር ወራቶች
ቀርተውታል፡፡ሆኖም አሁን በሰሜኑ ክፍል የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ እየከተተ ያለውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለዘለቄታው በመደምሰስ ድሉን እጥፍ ድርብ ማድረግ ይገባል፡፡ለዚህም ኢትዮጵያውያን ወገባቸውን ጠበቅ ማድረግ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም