በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተለይም በወጣቶች ዘንድ በስፋት እየተዘወተረ የሚገኘው የቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ። እኤአ በ1973 ስፖርቱ በኢትዮጵያ እንዲጀመር መሰረት ከጣሉ ሰባት ሰዎች አንዱ የሆኑት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ ካሃን ከረጅም ዓመት በኋላ ከሚኖሩበት ካናዳ አገር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ባለፈው ቅዳሜ በአቢሲኒያ ቴኳንዶ ማህበር በሶል ቴኳንዶ ክለብ ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የስፖርቱ ባለሙያዎች አጭር ስልጠናና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። ግራንድ ማስተር (ዘጠነኛ ዳን) ተብሎ በሚታወቀው ደረጃ በመድረስ በአፍሪካ ብቸኛው የሆኑት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ በልምድ ልውውጡ ወቅት እንደተናገሩት የቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ በጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በስፖርቱ ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ ያሳለፉት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ፣ ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ስፖርቱ በእሳቸው ዘመን ከነበረው ጊዜ አኳያ እጅግ የሚያስደስት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደጠበቃቸው ተናግረዋል። የቴኳንዶ ስፖርት በእሳቸው ዘመን በነበረው ስርዓት እንደ ልብ ለማዘውተር የማይቻልና ፍቃድ የማግኘትም እድል እንዳልነበረ ያስታወሱ ሲሆን፣ በወቅቱ ለስፖርቱ ጥሩ አመለካከት ባለመኖሩ እንዳጋጣሚ ወደ ውጭ አገር ሄደው ሳይመለሱ ቀርተዋል። አሁን ግን ስፖርቱን በርካታ ወጣቶች እያዘወተሩት እሳቸው በቀደዱት መንገድ አስደሳች ደረጃ ላይ ሆኖ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
‹‹የሌሎች አፍሪካ አገራትን በጥልቀት ባላውቅም እንደ ኢትዮጵያ ይህ ስፖርት በወጣቱ ዘንድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሚገኝ መናገር እችላለሁ›› ያሉት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት ስፖርቱን በስፋት ለማዘውተር በርካታ አማራጮች ቢኖሩም እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በፅናት እንደማይሰራበት ያስረዳሉ። ስፖርቱን በሚያዘወትሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የቴክኒክ ጥራት ላይ ጥቂት የሚታረሙ ነገሮች ቢኖሩ እንጂ ያላቸው ብቃትና አቅም ከሌሎች አገራት እንደማያንስ በድፍረት እንደሚመሰክሩም አብራርተዋል።
የቴኳንዶ ስፖርት በዓለም ላይ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ወርልድ ቴኳንዶ በሚል ተከፍሎ ይታወቃል። ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ የሚያዘወትሩትና ለትልቅ ደረጃ የበቁት በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ነው። ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በኢትዮጵያ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አዘውታሪዎች ያሉት ሲሆን በዚሁ ስፖርት ሦስት ፌዴሬሽኖችም እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ሦስት ፌዴሬሽኖች የሚያዘወትሩት ስፖርትና አላማ አንድ ሆኖ ሳለ አንድ ሆነው አለመንቀሳቀሳቸው ለበርካቶች ጥያቄ ይነሳበታል። እነዚህን ሦስት ፌዴሬሽኖች ወደ አንድ ለማምጣት ከስፖርቱ ጀርባ ብዙ ነገሮች እንዳሉ የገለፁት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ግን እምነታቸውን ገልፀዋል። ሦስቱን ፌዴሬሽኖች አንድ ለማድረግ ጊዜ ቢፈልግም አላማቸውም ይሁን ፍልስፍናቸው አንድ እንደመሆኑ አንድ ወጥ ፌዴሬሽን መሆን ባይችሉ እንኳን ተባብረው ቢሰሩና ልምድ ቢለዋወጡ ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚችሉ ይናገራሉ። በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በርካታ ስፖርተኞች ኢትዮጵያን እንዲወክሉም የፌዴሬሽኖቹ በጋራ መስራትና መተባበር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በልምድ ልውውጡ ወቅት ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ኤልያስ እስጢፋኖስ እንደተናገረውም፣ በስፖርቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱት ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ ከራሳቸው ሰፊ ልምድ በመነሳት ስፖርቱ በኢትዮጵያ እንዴት እንደተጀመረ፣ አሁን ያለበትን ደረጃና ወደ ፊት በምን መልኩ መቀጠል እንደሚችል ወጣቶች ግንዛቤ አግኝተዋል። ቴክኒክን በተመለከተ አጭር ስልጠናና የልምድ ልውውጥም ማድረግ ተችሏል። ኢንስትራክተር ኤልያስ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ባለሙያ ቢሆንም በወርልድ ቴኳንዶ ሰለሞን ቱፋ እየተካሄደ ባለው የቶኮዮ 2020 ኦሊምፒክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ የስፖርቱ የመጨረሻ መዳረሻ የት ድረስ እንደሆነ ማሳየቱን ይናገራል። ይህም በቴኳንዶ ስፖርት ውስጥ ያሉ በርካታ ወጣቶችን የሚያበረታታ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ስፖርቱ እንዲሳቡ በማድረግ ረገድ የጎላ ጥቅም እንደሚኖረው አስረድቷል። መንግሥትም ለማርሻል አርት ስፖርቶች ትኩረት እንዲሰጥ ያስችለዋል ብሏል። በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አራተኛ ዳን ያለው አሰልጣኝና ተወዳዳሪ የሆነው ሳቦም ሚሊዮን ቸርነት በስልጠናውና በልምድ ልውውጡ ከሐዋሳ በመምጣት የተካፈለ ሲሆን፣ ከግራንድ ማስተር ሚኒሊክ የቀሰመው ልምድ ወደ ፊት እንደ አገር በስፖርቱ ትልቅ ለውጥና ውጤት ለማምጣት የሚረዳ መሆኑን ተናግሯል። ስፖርቱን ሁሉም ባለድርሻ አካላት መደገፍ ከቻሉም እንደ ሰለሞን ቱፋ አገርን የሚያስጠሩ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚቻልም ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ካራቴ ስፖርት ረጅም ዓመት ካገለገሉና አንጋፋ ባለሙያ ከሆኑት መካከል የሚጠቀሰው ማስተር ሰለሞን ከበደ፣ በኢትዮጵያ ማርሻል አርት ስፖርቶች ታሪክ ትልቅ የሆኑ እንደ ግራንድ ማስተር ሚኒሊክ አይነት ባለሙያዎችን ወጣቶች እንዲያውቁና ልምድ እንዲቀስሙ በመደረጉ የተሰማውን ደስታ ይገልፃል። በእነሱ ዘመን ስፖርቱ ተደብቆ ከማዘውተርና በርካታ ፈተናዎችን ከማለፍ ተሻግሮ በዚህ ወቅት ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ አበረታች መሆኑን የሚናገረው ማስተር ሰለሞን፣ ሰለሞን ቱፋ በአሰልጣኙና በራሱ ጥረት ለኦሊምፒክ መብቃቱን ተከትሎ ሌሎች ወጣቶችንም በማርሻል አርት ስፖርቶች በብዛት በማፍራትና ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማብቃት መንግሥት ለስፖርቱ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው አስረድቷል። የማርሻል አርት ስፖርት ከህፃናት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ጎልማሶች ድረስ በርካታ ማህበረሰብ ያቀፈና ተዘውታሪ እንደመሆኑ በርካቶችን በስነምግባር በማነፅ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ መንግሥት በበጀት ጭምር ሊደግፈው እንደሚገባም አክሏል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013