አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ ተነስቷል። እራሱም አቧራ ሆኖ ኢትዮጵያንም አቧራ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለጦርነት ያልደረሱ እምቦቃቅላ ህጻናትን እና አረጋውያንን ጭምር በማሰለፍ ትውልድ እየፈጀም ይገኛል። አይዞህ የሚሉትን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ጭምር ደጀን በማድረግ የኢትዮጵያን መፍረስ በመመኘት ላይ ይገኛል። የጁንታው አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ ሲናገር ‹‹አትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን›› ሲል ያለ ሃፍረት ሲናገር ተደምጧል። የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ለፋፊ ስታሊን በበኩሉ ‹የኢትዮጵያን መፍረስ ቆሜ መመልከቴ እርካታ ይሰጠኛል › ሲል ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥላቻ ተናግሯል። ስለዚህም አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ መነሳቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአግባቡ ሊረዳ ይገባል።
ለኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ በትግራይ ላይ ክልል ይገኝ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት አስወጥቷል። መንግስት ሰራዊቱን ያስወጣው ትህነግ ለሀገሪቱ ስጋት ከመሆን መውጣቱን፣ ሀገሪቱ በትግራይ ክልል ካለው የጸጥታ ስጋት በላይ የሚያሳስባት ሌላ ሀገራዊ ጉዳይ ያላት በመሆኑ ነው። ጉዳዩን የትግራይ ህዝብም ቆም ብሎ እንዲመለከተው በሚል ነበር።
እርምጃው ጁንታው በሚፈበርከው የሀሰት መረጃ በመመስረት በክልሉ አለ በሚሉት ግጭት የትግራይ አርሶ አደር የመኸር የግብርና ስራውን ማካሄድ ተቸግሯል ፤ ይህ በዚህ ከቀጠለ በትግራይ ረሀብ አይቀሬ ነው ፤ ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረቡ ስራ በሚፈለገው ልክ እየተፈጸመ አይደለም ሲሉ ለቆዩ አንዳንድ የምእራባውያን ሀገሮች መንግስታት፣ አለም አቀፍ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን በዚህ በኩል አጀንዳ እንዲያጡ የሚያደርግም ይሆናል ተብሎ ታስቦ ነበር ።
በትህነግ የተሳሳተ መረጃ ላይ በመመስረት ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ የከተቱ እና ይበልጥ ለመክተት ሲዘገጃጁ የነበሩ መንግስታት፣ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች አካላትም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም፣ ለሰብአዊ ተግባር ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ያስገነዘበ እርምጃም ይሆናል ተብሎም ታስቦ ነበር። ሆኖም ግን ምዕራባውያንና አሸባሪው ህወሃት ዋነኛ ተልዕኳቸው ሀገር ማፍረስ ነውና በኢትዮጵያ መንግስት የሚወሰዱ በጎ ርምጃዎችን አይናቸውን ከፍተው ለመመልከት አልፈለጉም፡ ይሁን እንጂ የተኩስ አቁሙ በሀገር ውስጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በዜጎች ዘንድ ብዥታ የፈጠረበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት በተከታታይ የሰጣቸው መግለጫዎችንና ማብራሪያዎችን ተከትሎ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ድጋፍና አድናቆት ተችሮታል። ምሁራንም ማስተዋል የተሞላበት ሲሉ እርምጃውን ገልጸውታል። በመላ አለም የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራም ልክ በሀገር ውስጥ እንዳለው ዜጋ ለአጭር ጊዜ ብዥታ ቢፈጠርበትም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲና ሚሲዮኖች በወሰዱት የብዥታ ማጥራት ዘመቻ ዲያስፖራውም በእርምጃው ላይ መግባባት ላይ ደርሷል።
ምዕራባውያን ግን አሁንም የአሸባሪውን ህወሃት ድርጊት እያዩ እንዳላዩ ከማለፍም ባሻገር መንግስት ላይ ጫና የሚፈጥሩ መግለጫዎችን አሁንም ከማውጣት አልተቆጠቡም አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን ለጦርነት አሰልፎ ውጊያ መግጠሙን በግልጽ እየተመለከቱ ድርጊቱን ለማውገዝ አልደፈሩም። የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይገባ ተኩስ በመክፈት ጭምር ሲያስተጓጉል አሁንም ባልሰማ ባላየ አልፈውታል። የተኩስ አቁም ውሳኔውን ተላልፎ ህወሃት ንጹሃንን ሲገድልና ሲያፈናቅል የተናገሩት ነገር የለም።
በአጠቃላይ የአሸባሪው ህወሃትና ምዕራባውያኑ ትስስር አሜሪካንን ጨምሮ አፍጥጦ የመጣ የህልውና አደጋ ነው። ከሀገራት የተናጥል ተጽዕኖ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ጭምር በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ማድረጉ አስገራሚ ነገር ነው። በርካታ አለም አቀፋዊ ችግሮችና ቀውሶች ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ጉዳይ ዋነኛ ትኩረት መሆኑ ብዙዎችን እያስገረመ ነው።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያውን ይፋዊ ውይይት ባደረገበት ወቅት እንዳመለከቱት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመወጣት ከበቂ በላይ አቅም እንዳለው ግንዛቤ በመያዝ ከአጋሮቻችን ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነን ሲሉ የኢትዮጵያን አቋም አረጋግጠዋል።
የዚህ ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያደርገው የተኩስ አቁም ስምምነት ገንቢ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪም አቅርበው፣ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል። ይህም ለእርምጃው ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም አሁንም ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ከማድረግ አልተቆጠቡም።
በተለይም የምዕራባውያኑ ዝምታ የልብ ልብ የሰጠው ትህነግ ግን አሁንም ጸረ ሰላም አቋሙን ቀጥሎበታል። ለተኩስ አቁሙ አሁንም ድረስ ዋጋ አልሰጠውም። መቀሌ የገባው አሸንፎ መሆኑ እንደሆነ አርጎ እንደለመደው እየቦተለከ ነው።
እንደ ከዚህ ቀደሙ ክፉ ልምዱ በትግራይ ምድር ሰው ሰራሽ ረሀብ መስራት ይጠቅማል ብሎ አሁንም መስራቱን አጥብቆ ቀጥሎበታል፣ በክልሉ ሰብአዊ ቀውስ ሲፈጠር ተጠቃሚ እንደሚሆን ስለሚያስብ ለእዚህ ይረዳሉ ያላቸውን የጥፋት እርምጃዎች እየወሰደ ነው። ያለበቂ ስልጠና በለብ ለብ እያመጣ የሚያሰማራቸውን ህጻናት እያስፈጀ ሬሳቸውን ለፖለቲካ ቁማር እያዋለው ይገኛል።
የፌዴራል መንግስትና የመከላከያ ደጋፊ የነበራችሁ ባላቸው የክልሉ ነዋሪዎች ላይ እርምጃ እየወሰደባቸው ነው። ከአማራ ክልል ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለ አያለ ነው፤ በቅርቡም በኮረም በኩል ተኩስ መክፈቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።
መንግስት የትግራይ ህዝብ ሊያደርግ የሚችለው ካለ እንዲሞክር እድሉን ሰጥቷል። ቡድኑ ግን ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ክልሉም ከተሞቹ ተለቀውለትም መንግስትን ከመኮነን፣ ከማስፈራራት አልታቀበም። የትግራይን ህዝብ ከገባበት ማጥ እንዴት ላውጣ ማለት ሲገባው አሁንም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው።
ቡድኑ እሱን ከሀገርና ከህዝብ በላይ አድርጎ ስለሚቆጥር እና ዋነኛ ተልዕኮውም ኢትዮጵያን ማፍረስ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ካልተነሱ ቡድኑን ከስሩ መንቀል አይቻልም። ስለሆነም ኢትዮጵያን ማዳን የሚፈልግ ዜጋ በሙሉ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ ሊቀላቀል ይገባል። በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በአፋር፤ በደቡብ፤ በሶማሊና በሲዳማ ክልሎች የቡድኑን እስትንፋስ ለመቁረጥ የሚደረጉ ድጋፎችና ለመዝመት የተነሱ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ የሚያበረታታ ነው። ስለሆነም የህወሃትን አሸባሪ ቡድን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ መቀላቀል ኢትዮጵያን ከሚወዱ ዜጎች ሁሉ የሚጠበቅ ነው።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013