የሩቅ ምሥራቋ አገር ጃፓን በበርካታ የዓለም ሕዝቦች ዘንድ በሔሮሺማና ናጋሳኪ የኒውኩሌር ቦንብ ጥቃት ሠለባ በመሆኗ በሥፋት ትታወሣለች። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የተለየ ታሪክና ትውስታ ያላት ከተማ ናት። ከደም አፋሳሹ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ኪሣራና እልቂት አገግማ ወደ ልማት ፊቷን ያዞረችው ጃፓን በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የጠለሸ ገፅታዋን ለመቀየርና ለተቀሪው ዓለም በጎ ጎኗን ለማሣየት እኤአ 1964 በመዲናዋ ያዘጋጀችው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሮላታል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከአሥራ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ቶኪዮ ያስተናገደችው ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ጃፓን ጦርነቱ በከተሞቿ ላይ ካስከተለው ድቀትና የኢኮኖሚ ኪሣራ በአስገራሚ ፍጥነት አገግማ በብልፅግና ጎዳና ላይ መጓዟን ያሳየችበት ነበር። የፈራረሱ ከተሞቿን በጥቂት ዓመታት ዳግም ገንብታ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ለማሳየት የኦሊምፒኩ የማራቶን ውድድር ትልቅ አጋጣሚ ነበር።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የማራቶን የምንጊዜም ጀግና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድሩ ላይ ተሣታፊ መሆኑ ጃፓን ከጦርነቱ በኋላ የመዲናዋ ቶኪዮን ዕድገትና የጎዳናዎቿን ውበት ምን ያህል እንዳዘመነች ለተቀሪው ዓለም ለማሣየት ረድቷታል። አበበ ቢቂላ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ አራት ዓመታት ቀደም ብሎ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆኑ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ይህ ተዓምራዊ አትሌት ምን ዓይነት ታሪክ እንደሚሰራ ለመመልከት የዓለም ሕዝብ ትኩረት ወደ ሩቅ ምሥራቋ አገር ሆኗል። በዚህ ላይ የኦሊምፒክ ውድድሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በሣተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት የተላለፉበት አጋጣሚ መፈጠሩ ለጃፓን መልካም ዜና ነበር። ይህም ኦሊምፒኩን ስቴድየም ተገኝቶ በቀጥታ ለመመልከት ከሦስት ነጥብ ሃያ ሁለት ሚሊየን በላይ የስቴድየም መግቢያ ትኬቶች እንዲሸጡ አድርጓል። ከስምንት መቶ ሚሊየን ያላነሰ የዓለም ሕዝብም ውድድሩን በቴሌቪዥን መስኮት ሊመለከተው ችሏል።
ጃፓን ያንን ታሪካዊ ኦሊምፒክ ደግሣ ብዙ ካተረፈች ሃምሣ ሰባት ዓመታት በኋላ ዳግም በመዲናዋ ቶኪዮ ታላቁን የስፖርት መድረክ በ2020 የማሠናዳት ዕድል ገጥሟታል። በርግጥ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታሰበው ይህ ኦሊምፒክ ለጃፓን እንዳለፈው ሁሉ ነገሮች እግር በእግር አልሆኑም።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጀምሮ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ካለፈው ዓመት በአሥራ ስድስት ወራት ለመራዘም ከመገደዱ ባለፈ ጃፓንን እንዳለፈው ኦሊምፒክ ትርፋማ ከማድረግ ይልቅ ለኪሣራ ዳርጓታል። ያም ሆኖ ጃፓን እስከ መሠረዝ የደረሠ አደጋ የተደቀነበትን እልህና ገንዘብ አስጨራሽ ዝግጅት ፈተናዎች አልፋ በታሪክ ውድ የሆነውን ኦሊምፒክ ከትናንት በስቲያ በይፋ ጀምራለች። ኢትዮጵያን በዚህ ታላቅ መድረክ የሚወክለው ልዑካን ቡድንም ከሣምንት በፊት በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሸኛኘት ተደርጎለታል። ልዑካን ቡድኑ ተከፋፍሎም ወደ ቶኪዮ ማቅናቱን ተያይዞታል። የዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ከሃምሣ ሰባት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወክሎ የተወዳደረው ልዑካን ቡድን በተለይም የማራቶን ባለ ድሉ አበበ ቢቂላ በወቅቱ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ድሉ ድረስ የነበረውን ውጣ ውረድ የሚያስታውስ ይሆናል።
ወደ 1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚጓዘው ቡድን በቢሾፍቱ ከተማ አየር ሃይል በትብብር በሰጠው ካምፕ በተለየ መልኩ ሲዘጋጅ ቢቆይም ወደ ኦሊምፒኩ ለመጓዝ ምክንያት የሆነው የሮም ኦሊምፒክ ባለድሉ አበበ ቢቂላን ችግሮች ይፈታተኑት ነበር። በዚሁ ዝግጅት ወቅት አበበ ወድቆ በእጁ ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር።
ይህን ዜና የሠሙ የውጪ አገራት መገናኛ ብዙሃንም ወሬውን ተቀባበሉት። አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንደማይወዳደርም ፃፉ። ይሁን እንጂ አበበ ቀላል ጉዳት እንደደረሰበት ፊት ለፊት ወጥቶ አስተባበለ። የኦሊምፒክ ጉዞው መዳረሻ ላይ ግን ሌላ ከባድ ችግር ገጠመው። አሠልጣኙ ኦኔ ኔስካነን በአበበ ላይ የተለየ ነገር ማስተዋል ከጀመሩ ሠነባብተዋል። አበበ ልምምድ ጀምሮ ያቋርጣል፣ ሲቀመጥና ሲነሳ ወንበር ይደገፍም ነበር፣ ከመኝታውም እንደ ቀድሞው ቀልጠፍ ብሎ መነሣት አልሆነለትም፣ ይባስ ብሎም ውድድር እያቋረጠ እስከ መውጣት ደረሠ።
ይህንን ያስተዋሉት ቡድን መሪው ይድነቃቸው ተሠማና ስዊድናዊው አሠልጣኝ ኦኔ ኔስካነን አበበ ቢቂላ ሕክምና መሄድ እንዳለበት ተሥማምተው ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ወሰዱት። የጤና ምርመራው ውጤት ግን ብዙዎችን ያስደነገጠ ሆነ። አበበ ትርፍ አንጀት እንዳለበትና በአስቸኳይ የቀዶ ሕክምና ካላደረገ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ መነገሩ ትልቅ ሥጋት ፈጠረ። ይህ ጉዳይ በሚስጥር ቢያዝም እያደር ገሃድ መውጣት ጀመረ። ይድነቃቸውና ኔስካነን በጉዳዩ ላይ መከሩ።
አበበም ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ ተሥማማ። የሕክምና ክፍሉና ሌሎች ወገኖች ግን ሦስት ሣምንት ለቀረው ውድድር አበበ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንደሌለበት አቋም ያዙ። ይድነቃቸውና ኔስካነን ግን በራሣቸው ሃላፊነት ወስደው ቀዶ ጥገናው እንዲደረግ ወሠኑ። በሁለቱ ሰዎች ላይ ‹‹ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የምታገኘውን ወርቅ አሥነጠቁ›› በሚል ክስና ወቀሣ ተሰነዘረባቸው። አበበ በሆስፒታል ተኝቶ የሚያሣይ ፎቶ ግራፍ በመውጣቱም የዓለም መገናኛ ብዙሃን አበበ በውድድሩ እንደማይሣተፍ መዘገብ ጀመሩ።
በአዲስ አበባ የነበሩ የዜና ወኪሎች አበበ ከቡድኑ ጋር በዝግጅት ላይ ስለሌለ በውድድሩ እንደማይሣተፍ ማረጋገጫ አገኙ። በጉዞው መጨረሻ አበበ ከቡድኑ ጋር ቢጓዝም ሕመም ላይ ስለነበረ ጋቢ ለብሶ የተሻለ ሕክምና ለማድረግ እንጂ በውድድሩ ላይ ይሣተፋል የሚል እምነት አልነበረም። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተጓዙት 16 ስዎች ሲሆኑ፣ ለዝግጅት የወጣው 80 ሺህ ብር ብቻ ነው። ማራቶን የሚካሄደው በውድድሩ መዝጊያ ዕለት በመሆኑ አበበ ከሕመሙ ለማገገም በቂ ጊዜ አገኘ።
አበበ በውድድሩ መሣተፉ እንደታወቀ ብዙዎችን አሥገረመ። ቀዶ ሕክምና አድርጎ ቁስሉ ሣይጠግ መወዳደሩ ማሸነፍ ካለመቻሉ ሌላ በጤናው ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያመጣ ተዘገበ። የጤና ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አበበን ለውድድር ማቅረባቸው በሕይወቱ ላይ እንደፈረዱ ሆኖ ተነገረ።
በዚህ መሃል ደግሞ አንድ ሰው ብቅ አለ። ሰውየው አሴክ የተባለ የስፖርት ጫማ አምራች ድርጅት ባለቤት ናቸው። ድርጅቱ ግን የሚታወቅ አልነበረም። ይህ ድርጅት ለአበበ ጫማ ሠርቶ እንደሚያቀርብ ነገራቸው። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ግን ለጫማ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንደሌላቸው ገለፁ። ባለቤቱ ግን በነፃ መሮጫ ጫማውን እንደሚያቀርብ ተናገረ። ነፃ መሆኑን የሠሙት የኛ ሰዎች ‹‹እንደዚያማ ከሆነ ልኩን ውሠድና ሠርተህ ስጠን›› አሉት።
ብዙ መላ ምት ሲሰጥበት የነበረውና ከሕመሙ በቅጡ ያላገገመው አበበ ውድድሩን ማሸነፉ ተዓምር ሆነ። ሕመምተኛው ሰው ጤነኞቹን ማሸነፉ ብቻ ሣይሆን የዓለም ክብረወሰን ማሻሻሉ ‹‹ይኼ ሌላ ፍጡር እንጂ ሰው አይደለም›› እስኪባል ተደነቀ። የጤና ባለሙያዎቹም ያዩትን ነገር ማመን ከብዷቸው መጀመሪያም ቢሆን አልታመም ወደሚል ድምዳሜ ደርሰው ቀዶ ጥገና ማድረጉን እስከመጠራጠር ደረሱ።
የቶኪዮውን ኦሊምፒክ ለየት የሚያደርገው አፍሪካውያን የነፃነት አየር መተንፈስ በጀመሩበት ወቅት ላይ መደረጉ ነው። ብዙ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ወጥተው በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሣተፉበት፣ ለመወዳደር ብቻ ሣይሆን ወደ ነፃነት ሜዳ የመጡበትም መድረክና ዓለምን የተቀላቀሉበት ሥፍራ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
አፍሪካውያን በኦሊምፒክ መድረክ የመጀመ ሪያቸው በመሆኑ የጥቁር ኩራትና ተምሣሌት በሚሉት አበበ ቢቂላ የይቻላል መንፈስ ተቀርፀው ነበር። ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያቸው ኦሊምፒክ በመሆኑ በማራቶን ውድድር እንደ አበበ ቢቂላ በባዶ እግር የሮጡበት አጋጣሚም በታሪክ ይታወሣል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአበበ ቢቂላ ሌላ ማሞ ወልዴ በአሥር ሺህ ሜትር ወርቅ ማምጣት የሚችልበት ዕድል በቀላል የቴክኒክ ስህተት ሣይሳካ መቅረቱ የሚያስቆጭ ነበር። ነገር ግን ትልቅ ትምህርት ተገኝቶበታል። በፍፃሜው ውድድር የተጠበቁት የአሜሪካና የአውስትራሊያ አትሌቶች ነበሩ። ማሞ ስለተፈጠረው ነገር ሲናገር በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገር ‹‹እንደማሸንፋቸው ርግጠኛ ነበርኩ፣ እስከ መጨረሻ ዙር አብረን ነበርን፣ ሁለቱ ከእኔ ፊት ነበሩ፣ የቱኒዚያው ጋሙዲ ከእኔ ቀጥሎ ነው፣ ከእኔ ፊት የነበሩት ሁለቱም ትንፋሽ ጨርሰዋል፣ የመጨረሻ መቶ ሜትር ላይ ደርሰን አምልጬ ለመሄድ ተዘጋጀሁ፣ አሜሪካዊው አትሌት የመጨረሻው መቶ ሜትር መታጠፊያ ላይ እየተጠመዘዝኩ አውስትራሊያዊው አትሌት በክርኑ ደቆስ አድርጎ ወደ ኋላ እንድቀር በማድረግ አምልጦ ለመውጣት ነበር የተዘጋጀው፣ እኔ ደግሞ በሁለቱ መሃል በተፈጠረው ክፍተት አምልጬ ለመሄድ ስል ለእነሱ የተሠነዘረው ክርን እኔን መቶኝ ተደናቅፌ ወደኩኝ፣ ያን ጊዜ ሁሉንም አጣሁ፣ ከኋላ የነበረው ቱኒዚያዊ አትሌት የነሐስ ሜዳሊያውን ወሰደ፣ ከውድድሩ በኋላ ከአበበ ጋር ስነጋገር ስህተት መሥራቴን አወኩኝ፣ እኔ መሄድ የነበረብኝ በሦስተኛው መስመር ነበር›› ብሏል። በአሥር ሺህ ሜትር የማሞ ስህተት ለኢትዮጵያውያን ማስተማሪያ የሆነው የቶኪዮው ኦሊምፒክ ሆኖ ከዚያ በኋላ በርቀቱ ቅርፅ ማስያዝ የተቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተጠናቀቀ በኋላ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሱ በፊት ጃፓኖች ማወቅ የፈለጉት የአበበን የአሸናፊነት ሚስጥር ነው። ሕመምተኛ ሆኖ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር የሮጠበትን ሚስጥር። በዚህ የተነሣ በጃፓን ሥርዓተ ትምህርት በሞራል ትምህርት ውስጥ አበበ ቢቂላን የሚመለከት ምዕራፍ እንዲካተት አደረጉ። ይህም ማኛውንም ነገር ከግብ ለማድረስ ፅናት ማስፈለጉን ለዚህም አበበን ምሣሌ ማድረጋቸው ነው። በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ማሸነፉ፣ በቶኪዮ ከሕመሙ ሣያገግም ጤነኞቹን ማሸነፉ ተምሣሌት መሆኑን ‹ፅናት› ካለ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ጃፓኖች ዛሬም ድረስ ያስተምሩበታል።
ከውድድሩ በኋላ አበበን የሚመለከቱ ሁለት ነገሮች ተከስተዋል። አበበ ሕመምተኛ በመሆኑ ጋቢ ለብሶ ነበር ወደ ጃፓን የተጓዘው። በወቅቱ በአገራችን አንድ ሰው ከታመመ ጋቢ መልበሱ የተለመደ ነው። ጃፓናውያንም ከውድድሩ በኋላ ለማስታወሻነት ጋቢውን አስቀርተውታል። ለዚህም ምክንያት ነበራቸው፣ እነሱ ቱሪዝምን በአግባቡ ስለሚጠቀሙበትና አበበም በውድድሩ መነጋገሪያ ስለነበረ ቱሪስቶች ጋቢውን ለብሰው ፎቶ ግራፍ እንዲነሱ ያደርጉበታል።
ሌላው አስገራሚ ነገር አበበ የጣት ቀለበቱ ባረፈበት ሆቴል መጥፋቱ ነበር። ቀለበቱ ከሮም ድል በኋላ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተበረከተለት ነበር። የቀለበቱ መጥፋት በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ተነገረ። በቀለበቱ ላይ የተፃፈው ‹‹ሮም 1960›› የሚልና የንጉሱ ፊርማ ያረፈበት መሆኑ በመገለፁ ለፈላጊዎቹ ብዙም አላስቸገረም። አበበ የወቅቱ ዝነኛና የእነሱም እንግዳ በመሆኑ ጃፓናውያን ወርቁን አፈላልገው መገኘቱን አበሠሩት።
የቶኪዮ ልዑካን ቡድን ወደ አገሩ ሲመለስ በአበበ ቢቂላ ድል አዲስ አበባ በአቀባበሉ ደምቃ ነበር። የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ (የአበበ ክፍል) ዝነኛ ሙዚቀኞች ጥላሁን ገሠሠና እሣቱ ተሠማ ‹‹በጣም ደስብሎናል ምኞታችን ሞላ፣ አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ›› በሚል ያዜሙት ለአቀባበሉ ትልቅ ድምቀት ሠጥቶታል።
የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን የተካሄደው ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም ነበር። ሕዝቡ ድሉን በራዲዮ ዜና ሠማ እንጂ ምንም ያየው ነገር አልነበረም። ነገር ግን ሚያዝያ 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭት የጀመረበት ጊዜ በመሆኑ በጃፓን ኤምባሲ ትብብር አበበ ሲሮጥና ሲያሸንፍ የታየበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
ቶኪዮ አበበን ምን ጊዜም አትረሣውም። ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በኮሮና ቫይረስ ሥጋት የተራዘመው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የአዘጋጅነት ዕድሉን ለማግኘት ጃፓን አበበ ቢቂላን ‹ዳግም አበበን ለማግኘት› በሚል ለቅስቀሳ ተጠቅማበታለች። የአገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በትምህርት ቤት ሩጫ ተሣታፊ በነበሩበት ወቅት የአበበ አድናቂና በአበበ ቅፅል ሥም የሚሮጡ እንደነበሩም ከራሣቸው አንደበት ተሠምቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራትና አምስት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜም የአበበን ቤተሠቦች ጎብኝተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013