የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሣፓርት ኦርጋናይሽን ኢትዮጵያ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በፓርኪንሰን ታማሚ በሆኑት በወይዘሮ ክብሯ ከበደ የተመሠረተ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ500 ሕሙማን በላይ በማገዝ ላይ ይገኛል፤ የሚሰጣቸውም ዋና ዋና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው። ለሕሙማን ለአስታማሚ ቤተሠብ ሥልጠና መስጠት፤ የንግግር ሕክምና፤ የቤት ለቤት ድጋፍ፤ ከበጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነፃ የአይን እና የፊዚዮቴራፒ ሕክምና፤ የመድሀኒት እገዛ ማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እና የመሳሰሉት ምርኩዝ እና ዊልቸር ድጋፍ ያደርጋል።
የድርጅቱ ሥራዎች በአቅም ውስንነት ምክንያት አዲስ አበባ ላይ ብቻ መወሰን ዋናው ምክንያት የቦታ ችግር (ሕሙማንን በአንድ ቦታ አሰባስቦ ለማገዝ መቸገር) መሆኑን ወይዘሮ ሕይወት ተረፈ የፓርኪንሰን ሕሙማን መርጃ ማህበር ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ይናገራሉ። ወይዘሮ ሕይወት ሰዎች ስለፓርኪንሰን ሕመም ተረድተው ራሣቸውን ከአባባሽ ሁኔታ እንዲጠብቁ ይኼ መልዕክት ይድረስልኝ ብለዋል።
ፓርኪንሰን የእንቅስቃሴ ሕመም ነው። እንቅስቃሴን የሚቆጣጠሩት በአንጎል ውስጥ ያሉ የነርቭ ሴሎችን የሚነካ በሽታ ነው። ፓርኪንሰን ባላቸው ሰዎች ላይ ዶፓሚን የሚያመነጩ የነርቭ ሴሎች መጥፋት ይከሰታል። የፓርኪንሰን ምልክቶች ቀስ በቀስ እየታዩ ቀስ በቀስ እየተባባሱ ይሄዳሉ።
የፓርኪንሰን ሕመም ለመመርመር አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም የተለየ የላብራቶሪ ምርመራ የለውም። ነገር ግን በነርቭ ሕክምና በሠለጠነ ባለሙያ ምዘና ላይ የሚመረኮዝ ምርመራ ሁልጊዜ ያስፈልጋል። የፓርኪንሰን የመጀመሪያ ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የነርቭ ሕክምና ባለሙያ ጋር መታየት አስፈላጊ ነው። የነርቭ ሐኪም ሕመምተኛው በሚያሣየው አካላዊ ለውጦችን በመመልከት ምርመራ ያካሂዳል።
የፓርኪንሰን ሕመም ምልክቶቹ በእረፍት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የሰውነት በተለይም የእጅ መንቀጥቀጥ፣ የጡንቻ ጥንካሬ (ግትርነት) የመንቀሳቀስ ፍጥነት መቀነስ ናቸው። የመብላትና የመዋጥ ችግሮች ከመጠን በላይ ምራቅ አፍ ውስጥ መከማቸት የንግግር ለውጦች መውደቅ በእግር ሲጓዙ የተቀነሰ የእጅ መወዛወዝ ሲራመዱ የመዞር ችግር ሚዛን አለመጠበቅ ምልክቶቹ ናቸው።
የፓርኪንሰን ሕመም ለእያንዳንዱ ሰው የተለያዩ ምልክቶች አሉት፣ ግን በጣም የተለመዱት ምልክቶች እነዚህ ሁሉ ከእንቅስቃሴ ጋር የተዛመዱ ምልክቶች ተብለው ይጠራሉ።
ሌሎች ከእንቅስቃሴ ጋር የተዛመዱ ምልክቶች ብዙ የፓርኪንሰን ሕመም ያለባቸው ሰዎችም ከእንቅስቃሴ ጋር የማይዛመዱ ሌሎች ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ለምሣሌ ሕመም፣ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ድካም፣ መርሣት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የሆድ ድርቀት፣ ማሽተት አለመቻል እንዲሁም የሽንት ፊኛ ችግሮች ናቸው።
የፓርኪንሰን ሕመም በምን ምክንያት እንደሚመጣ በርግጠኝነት አይታወቅም። ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ደረጃ የሚያጠቃ ሕመም ነው። የበሽታው ጥናት እንደሚያሣየው ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ፤ ከእነዚህም ተጋላጭ ዘረመል እና የአካባቢ ሁኔታ (ለፀረ አረም ኬሚካሎች በተደጋጋሚ መጋለጥ፣ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ ተደጋጋሚ ጉዳት…) መጣመር ሕመሙ እንዲከሰት ያደርጋል። በአብዛኛው ግን ፓርኪንሰን ሕመም በዘር የሚተላለፍ አይደለም።
ተመራማሪዎች እስካሁን ድረስ የፓርኪንሰንን ሕመም ለመፈወስ ወይም ዕድገቱን ለመቀነስ የሚያስችል መንገድ ማግኘት አልቻሉም። ሆኖም የየዕለት እንቅስቃሴን ለማሻሻል በመድኃኒት ምልክቶችን መቆጣጠር ይቻላል።
ከእንቅስቃሴ ጋር ለተዛመዱ የሕመም ምልክቶች የተለያዩ መድሃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። በዋነኝነት ሊቮዶፓ/ካርቢዶፓ የሚባል መድሃኒት ይታዘዛል። እያንዳንዱ ሰው ለመድኃኒቱ የተለያየ ምላሽ ይሰጣል። የሚቀጥለው የመድኃኒት መውሰጃ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ምልክቶች እንደገና ሊታዩ ወይም ሊባባሱ ይችላሉ። ቅባት ያለው ምግብ (እንደ ሥጋ /ዓሣ/ እንቁላል/ ወተት) ተመግበው መድኃኒት ሲወስዱ የምግቡና የመድኃቱ ሰዓት በ1 ወይንም በ2 ሰዓት መራራቅ ይኖርበታል። በመጀመሪያ ከሐኪምዎ ጋር ሣይነጋገሩ የመድኃኒቶችን መጠን፣ ጊዜ ወይም ድግግሞሽ አይለውጡ።
የፓርኪንሰን ሕክምና ከመድሀኒት በተጨማሪ የፊዚዮቴራፒ ሕክምናን፣ የንግግር ሕክምናን፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የአመጋገብ ድጋፍን ያጠቃልላል።
ለፓርኪንሰን ሕመምተኛ የተለየ ምግብ የለም። ነገር ግን የተመጣጠነ ጤናማ አመጋገብ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። የተለመዱ ካርቦሃይድሬት ምግቦች ዳቦ፣ ድንች፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ብስኩት እና ኬኮች ናቸው። የተለመዱ ፕሮቲኖች ሥጋ፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ ጥራጥሬዎች፣ እንቁላል እና ዓሣ ናቸው። ፍራፍሬ እና አትክልቶች የሆድ ድርቀትን ይከላከላሉ። በየቀኑ ከ8 እስከ 10 ኩባያ ፈሣሾችን መጠጣት አስፈላጊ ነው። የምግብ ሠዓትን አለመዝለልና ለመብላት በቂ ጊዜ መስጠት ይመከራል።
ሕመምተኞች መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎችን ለማጠንከር እና ብዙውን ጊዜ ግትርነት የሚያስከትለውን ሕመም ለማስታገስ ይረዳል፤ የኃይል ደረጃን ለማሣደግ፣ ድካምን ለመቀነስ እና ጥሩ ጤንነትን ለማሻሻል ይረዳል። እንደ መዋኘት፣ በእግር መጓዝ፣ ብስክሌት መንዳት እና አትክልት መንከባከብን ይሞክሩ። ለአጭር ሰዓት በሣምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የተሻለ ነው። እስከቻሉ ድረስ የተለመዱትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎን መቀጠል ሁኔታዎችን ያሻሽላል ይሉናል። ማህበረሰቡም ራሱን ከበሽታ ከመጠበቅም ባለፈ ለሕሙማኑ ድጋፍ ማድረግ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013